Wednesday 8 June 2022

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፲፮)

 Please read in PDF

የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን፣ የራሱ የእግዚአብሔር ሥልጣን ነው!

“የመጽሐፉ ባለቤት ጌታ ራሱ ካልረዳ በስተቀር የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጓሜና ምስክርነት ለመረዳት አይቻልም። መጻሕፍቱ ምንም በሰው እጅ የተጻፉ ቢኾኑ በጌታ ትእዛዝ እንደ ተጻፉ እናምናለን።”[1] 

መግቢያ

ክርስትናም ኾነ የብሉይ ኪዳን እምነት የተመሠረተው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነትና ሥልጣን ላይ ነው። እግዚአብሔር ለወደቀው ዓለም፣ ተስፋ መስጠቱን ያረጋገጠበት እውነተኛ ሰነድ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። የኦሪት መጻሕፍት የመሰጠታቸው ዓላማ፣ በምድረ በዳ ለነበረችው እስራኤል የተሰጠ አስደናቂ የተስፋና የእምነት መጽሐፍ ነው። የእግዚአብሔር ኹሉን ቻይነትና ታዳጊነት እንዲደገፉበት የተጻፈ መጽሐፍ ነው። ቅዱሱ ፍጥረት፣ ውድቀቱ፣ ተስፋውና ደገፌታው ጭምር በውስጡ መጠቀሱም በዋናነት ይኸንኑ ሊያመለከት አለ።

ጠቅላላው ብሉይ ኪዳን ደግሞ፣ እግዚአብሔር እንደ ተስፋ ቃሉ የሰጠውን መሲሕ በመናፈቅ እንዲታመኑና ተግተው እንዲጠብቁ የተሰጠ ሲኾን፣ አዲሱ ኪዳን ደግሞ፣ የአብ አስተርእዮና የመጨረሻው መገለጥ የኾነውን የእግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን እንድንድን የተጻፈ አስደናቂ የዘላለም ሕይወት ምንጭ መጽሐፍ ነው።

ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን፣ በአብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ኹለት ዐይነት ምልከታ አለ። አንደኛው የካቶሊክ ሲኾን፣ ሌላኛው ደግሞ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ትምህርት ነው።

ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን የካቶሊክ ትምህርት

ካቶሊክን ጨምሮ የላቲን አብያተ ክርስቲያናት፣ ቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ቤተ ክርስቲያን ሃብት የሚቆጠሩ በመኾናቸውና በቤተ ክርስቲያን በኩል እንደ መጡ ስለሚታመን፣ ቤተ ክርስቲያን በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ብያኔ መስጠት እንደምትችል ያምናሉ። ለዚህም የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን ከትውፊት ጋር በማቆራኘት፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን የትውፊት አንዱ አካል አድርጎ በማመን፣ ቤተ ክርስቲያን በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ብያኔ መስጠት እንደምትችል ጭምር ያምናሉ።

በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያን በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ፣ አስተያየትና የተለያዩ ብያኔዎችን መስጠት እንደምትችል ብቻ ሳይኾን፣ ዶግማዊ ብያኔዎችን መስጠት እንደምትችል በታሪክ የተሰጡ ብያኔዎች እውነታውን ያረጋግጣሉ። ለምሳሌ፦

1.   በ1870 ዓመተ እግዚእ ፖፑ አንድን ውሳኔ ሲወስኑ ትክክልና ያለ ኀጢአት ይወስናሉ በማለት ወደ ቅዱሳት መጻሕፍት ተካካይ ሥልጣን አመጡአቸው። ምክንያቱንም ሲያብራሩ “የሮማው ፓፓ የቅዱስ ጴጥሮስ ቀጥተኛ ተከታይ ናቸው” የሚል ጽኑ እምነት አለ።[2] ጴጥሮስ የቤተ ክርስቲያን ራስ ነውና በማለት።[3]

ከዚህም የተነሣ ፓፓው ብቻቸውን ታላላቅ ሃይማኖታዊ ውሳኔዎችና አዋጆችን በይፋ መወሰን ወይም ማወጅ ይችላሉ፤ ይህም ሃይማኖታዊ ድንጋጌ “ዶግማ” ወይም “አንቀጸ ሃይማኖት” ተብሎ ሊጠራ ይችላል።[4]

2.   በ1950 ዓመተ እግዚዕ የማርያምን ከሙታን መካከል መነሣትና ወደ ሰማያት ማረግ ወይም በሥጋና በነፍስ ወደ ሰማይ መውጣት በፓፓው ከተወሰኑ አንቀጸ ሃይማኖቶች አንዱ ነው።[5] ይህ ውሳኔ “ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒዮስ 12ኛ የእመቤታችንን ወደ ሰማይ መውጣት አንቀጸ ሃይማኖት (ዶግማ) አወጁ።”[6]

3.   ማርያም ክርስቶስን ወልዳ ስለ ሰጠችን “እመቤታችን” ተብላ ልትጠራ ይገባታል በማለት፣[7] ይህም አስገዳጅ መጠሪያ እንደ ኾነም ወስኑ፤[8]

4.   ትውፊት ተጨማሪ አስተርዕዮ ያመጣል የሚል ጽኑ እምነት አለ። በተለይ የካቶሊክ ፖፑ የሚወስነው ውሳኔ፣ እንደ ተጨማሪ አስተርዕዮ በማየት የሚቀበሉትና እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ቃል የሚቆጠር ነው።

5.   መካነ ንስሐ ወይም ኀጢአተኞች ለንስሐ ስለሚቆዩበት ስፍራ(purgatory) ውሳኔ[9]፣ እንዲሁም የሥልጣን ተዋረድም በዲያቆን፣ በቄስና በኤጲስ ቆጶስነት መቀመጡን በውሳኔ ተደንግጎአል፣[10]

6.   በ1215 ዓ.ም በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውሳኔ፣ በቤተ ክርስቲያኑ ፖፕ የሚወሰነው ማናቸውም ውሳኔ ትክክልና ስህተት የማይገኝበት ነው፤[11]

7.   1854 ዓ.ም ድንግል ማርያም ያለ ኀጢአት መፀነስዋንና ይህም የኾነው በእግዚአብሔር ጥበቃ እንደ ኾነ ወሰኑ።[12] ከዚህም በቀር ወደ እርስዋ መጸለይ እንደሚገባም ሲወስኑ፣ በእርስዋ በኩል መሰማትን እግዚአብሔር መፍቀዱን የሚል ምክንያትም አብሮ ተጠቅሶአል፤[13]

እንግዲህ እኒህና ሌሎችም ውሳኔዎች፣ ፖፑ አንድን ውሳኔ እንደ ዶግማ እንዲወስኑ፣ በቀጥታ ራሳቸውን ከመንፈስ ቅዱስ ጋር በማስተካከል እጅግ አደገኛ መንገድ እንዲከተሉ ያደርጋቸዋል። ከዚህ የተነሣም፣ በካቶሊክና በላቲን አብያተ ክርስቲያናት “የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ” የሚል ቃል ወይም የትምህርት ይዘት ሲበዛ እንመለከታለን። አንዳንድ የኦርቶዶክስ ጸሐፍትና ሰባክያን “የቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ” ሲሉ፣ ምን ያህል በካቶሊክ አስተምህሮ ሥር መውደቃቸውን ማስተዋል ይቻላል። የመድሎተ ጽድቅ ጸሐፊም በዚህ ሚዛን ሲመዘን፣ ካቶሊካዊ ትምህርቶችን እንዴት እጅግ አሳዛኝ በኾነ መንገድ፣ ኦርቶዶክሳዊ አድርጎ ለማቅረብ እንደሚባዝን በሚቀጥሉት ጽሑፎች በስፋት እንመለከታለን።

ይቀጥላል …



[1] አበራ በቀለ (ሊቀ ጉባኤ)፤ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት፤ ገጽ 157

[2] የካቶሊክ እምነታችን ምንነት(ካቶሊክ በመኾናችን የሚሰማን ደስታ)፤ 2007 ዓ.ም አዲስ አበባ፤ አሳታሚ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ሐዋርያዊ ሥራዎች ኮሚሽን፤ ገጽ 15፤ LG 22.25, NUC 861, 891

[3] LG 19

[4] የካቶሊክ እምነታችን ምንነት(ካቶሊክ በመኾናችን የሚሰማን ደስታ)፤ ገጽ 15፤

[5] ዝኒ ከማኹ እና LG 59

[6] የካቶሊክ እምነታችን ምንነት(ካቶሊክ በመኾናችን የሚሰማን ደስታ)፤ ገጽ 64

[7] ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ለ2008 ዓ.ም. ጾመ ፍልሰታ ባስተላለፉት ቃለ ምዕዳን ውስጥ ይህን ልምምድ ሊያጸና የሚችል ወይም ተመሳሳይነት ያለው መልእክት እንዲህ ሲሉ አስተላልፈው ነበር፤ “ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ ‘እነኋት እናትህ’ ከተባለበት ሰዓት ጀምሮ እመቤታችንን ወስዶ በቤቱ አኑሮአታል፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እመቤታችን በእያንዳንዱ አማኝ ልጇ ቤት በመንፈስ እየገባች ትኖራለች።” (www. addisababa.eotc. org.et /site/en/news/343, 2008)።

ይህ የቅዱስነታቸው መልእክት፥ ከላይ በፕሮፌሰር ጌታቸው ከተጠቀሰው የማርያምን በአንድ በስሟ በታነጸ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መገኘት እጅግ ሰፋ አድርጎ ወደያንዳንዱ ኦርቶዶክሳዊ ቤት ድረስ ያወርደዋል። ነገር ግን ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያስተምረው የክርስትና ትምህርት ፈጽሞ የራቀና ከላይ በተጠቀሰው ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተሳሰብ ላይ የቆመ እንደ ኾነ መመልከት ይቻላል። ስለ ዮሐንስ “እነኋት እናትህ” ተብሎ የተነገረው ቃል፣ ለምእመናን ኹሉ እንደ ተነገረ ተደርጎ በልማድ ሲጠቀስ መስማት የተለመደ ቢኾንም፣ ቃሉ ከዮሐንስ ዐልፎ ግን ለምእመናን ኹሉ የተነገረ አይደለም።

ዮሐንስ፣ “እነኋት እናትህ” የተባለው፣ ቅድስት ማርያም ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መከራ ሲቀበል ካየችው በላይ፣ የሞትን ጽዋ ሲጐነጭ ተመልክታ፣ የበለጠ ሐዘን እንዳይከብድባት ብሎ እንደ ኾነ ከዐውደ ምንባቡ እንገነዘባለን። የአባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ ድርሰት በኾነው “ጸሎተ ሰብዓቱ ጊዜያት” ውስጥም ይህን የሚያረጋግጥ ምስክር እናገኛለን።

“ሐዘነ ማርያም እምከ ነጺረከ ለዘታፈቅሮ ሐዋርያ፣

ትቤሎ እምከ ነያ፣

ከመ ትናዝዝ ብዝኀ ብካያ …”

ትርጕም፦  “የእናትህን የማርያምን ሐዘን ተመልክተህ፣ ከልቅሶዋ ብዛት ታረጋጋ ዘንድ፣ ለምትወደው ሐዋርያ እነኋት እናትህ አልኸው።” (ጸሎተ ሰብዐቱ ጊዜያት)።

ቀደም ሲል ይህን፣ “እነሆ ልጅሽ … እነኋት እናትህ” የሚለውን ቃል፣ በዐውደ ምንባቡ መሠረት ሊቃውንት ይረዱት የነበረው በዚህ መልኩ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታዲያ ለዮሐንስ፣ ለዚያው ጊዜ ብቻ የተነገረው ይህ ቃል፣ ለምእመናን ኹሉ የተነገረ ነው የሚባለው በምን ምክንያትና በምን መሠረት ይኾን? እርሷ አኹን በዐጸደ ነፍስ ባለችበት ኹኔታ ዮሐንስ እንዳደረገው የማንም ርዳታ አያስፈልጋትምና፣ ያም ሐዘኗ በደስታ ተተክቷልና ምእመናን እርሷን ወደ ቤታቸው የሚወስዱበት ምክንያትም፣ አግባብም፣ መንገድም የለም፤ አይኖርምም። እርሷም ደግሞ በያንዳንዱ አማኝ ልጇ ቤት በመንፈስ እየገባች የምትኖርበት ምክንያትም፣ አግባብም፣ መንገድም ፈጽሞ የለም።

[8] Gaudium et spes 65, sacrosanctum Concilium 103

[9] NUC 1030 ff; LG 49

[10] NUC 1554

[11] LG 25 (Papal infallibility)

[12] Lumen gentium 56

[13] New universal Catechism 975

No comments:

Post a Comment