Thursday 2 June 2022

ዕርገት - ወደ ሄደው ጌታ እንሄዳለን!

 Please read in PDF

የክርስቶስ ኢየሱስ ስቅለትና ሞቱ፣ የኀጢአታችን ዕዳ ፍጹም መከፈሉንና ቤዛችን እኛን ወክሎ መከራ መቀበሉን ያበሥራል፤ ትንሣኤው ደግሞ የዕዳችን ክፍያ ፍጹም መጠናቀቁንና መረጋገጡን የሚያመለክት ታላቅ ደስታችን ነው። ሞቱ ያለ ትንሣኤው ከንቱ ነበረ፤ ትንሣኤው ግን ሞቱን ጽድቃችን አደረገው፤ ከትንሣኤው ኃይልና ሕይወት የተነሣም የጸደቅንና የተቀደስን መኾናችንን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክሩልናል፤ “እርሱ[ክርስቶስ] ስለ ኀጢአታችን እንዲሞት ዐልፎ ተሰጠ፤ እኛን ጻድቅ አድርጎ ለማቅረብም ከሞት ተነሣ” እንዲል፤ (ሮሜ 4፥25)።

ከሙታን የተነሣው ጌታችን ኢየሱስ ወደ ሰማያት፤ ወደሚታወቅ ሥፍራ አርጐአል። ዕርገቱንም የተመለከቱ ምስክሮች መኖራቸውን፣ “እስከ ቢታንያም[ደቀ መዛሙርቱን] አወጣቸው እጆቹንም አንሥቶ ባረካቸው። ሲባርካቸውም ከእነርሱ ተለየ ወደ ሰማይም ዐረገ።” (ሉቃ. 24፥50-51)፤ “እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው። እርሱም ሲሄድ ወደ ሰማይ ትኵር ብለው ሲመለከቱ ሳሉ፥ እነሆ፥ ነጫጭ ልብስ የለበሱ ሁለት ሰዎች በአጠገባቸው ቆሙ፤ ደግሞም፦ የገሊላ ሰዎች ሆይ፥ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ ስለ ምን ቆማችኋል? ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው።” (የሐ. ሥ. 1፥9-11) በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይመሰክራል።

እንግዲህ፣ እንዲህ ማለት እንችላለን፣

·        ጌታችን ኢየሱስ የሄደው ወደሚታወቅና እኛም ልንሄድበት ወይም እርሱ ራሱ ወደራሱ ሊወስደን ወዳለው ስፍራ ሄዶአል፤ “ሄጄም ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ፣ እኔ ባለሁበት እናንተም ከእኔ ጋር እንድትኾኑ ልወስዳችሁ ዳግመኛ እመጣለሁ” (ዮሐ. 14፥3) እንዲል። ጌታችን ኢየሱስ ይመጣል፤ አዎን ይመጣል፤ የሚመጣው ደግሞ በእርሱ የምናምነውን የማናፍርበትን ብቻ ሊወስደን ነው። በእርግጥ ከሙታን በተነሣው ጌታችን፣ እኛም ከኀጢአት ሙትነት በመንቃት ለእርሱ እንኖር ዘንድ ነው። በዚህ ምድር የእርሱን ትምህርት የተከተሉ፣ ሕይወቱን የኖሩት ደግሞ ወደ እርሱ ይሄዱ ዘንድ ታላቅ ኪዳናዊ ተስፋ አላቸው!

·        ጌታችን በሰማያት በአባቱ በግርማው ቀኝ ተቀምጦአል። የዕብራውያን ጸሐፊ እንደ ተናገረው፣ “ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤” (ዕብ. 1፥3)። በብሉይ ኪዳን ሊቀ ካህናቱ፣ ደሙን ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይዞ ከገባ በኋላ፣ እግዚአብሔር ሕዝቡን በምሕረት መማሩን ለማሳየት ከቅድስተ ቅዱሳኑ ወጥቶ በአደባባዩ ላይ ይቆማል። ሊቀ ካህናቱ ለሕዝቡ ዕረፍት በመምጣቱ ከቅድስተ ቅዱሳኑ ወጥቶ በአደባባዩ ይታያል፤ ደግሞም ያርፋል። ጌታችንም በግርማው ቀኝ ስለ መጽደቃችን ተቀመጠ፤ ደግሞም ሥልጣን በሰማይና በምድር ተሰጠው፤ (ማቴ. 28፥19)።

·        ማረጉና በግርማው ቀጥ መቀመጡ፣ መዳናችን ፍጹም መጠናቀቁንም ያመለክታል። ጌታችን ከሙታን መካከል ተነሥቶ በማረግ፣ በሰማያት ግርማው ቀኝ መቀመጡ የመዳናችን ነገር ፍጹም መጠናቀቁንም ያመለክታል። ደግሞም ጠላታችንም ድል መነሣቱንና ጌታችንም በጠላታችንና በመላለሙ ላይ ሥልጣን መቀበሉንም ያሳያል፤ “እርሱም መላእክትና ሥልጣናት ኃይላትም ከተገዙለት በኋላ ወደ ሰማይ ሄዶ በእግዚአብሔር ቀኝ አለ።” (1ጴጥ. 3፥22) እንዲል።

አዎን፤ ጌታችን ወደ ሰማያት አርጐአል፤ በአባቱም ቀኝ ተቀምጦአል፤ ተቀመጠ ማለት ግን አንዳች ላይሠራ ዝም ብሎ ተቀምጦአል ማለት አይደለም፤ እርሱ ዛሬም ለቤተ ክርስቲያን ሌላ አጽናኝና ራስ፤ ጌታዋም ነው፤ ደግሞም፣ “የብዙዎችን ኃጢአት ሊሸከም አንድ ጊዜ ከተሰዋ በኋላ፥ ያድናቸው ዘንድ ለሚጠባበቁት ሁለተኛ ጊዜ ያለ ኃጢአት ይታይላቸዋል። (ዕብ. 9፥28)። እናም ይህ ጻድቅና ቅዱስ መሲሕ፤ እርሱ ወዳለበት ሊወስደን ዳግመኛ ይመጣል፤ እርሱ መሄዱና ማረጉ ጥቅማችን እንደ ኾነ፣ እንዲሁ መምጣቱና እኛን መውሰዱም እጅግ የምናፍቀው ነው! የሄድኸው ጌታችን ሆይ ቶሎ ናልን፤ አማኞች ሆይ፤ “ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፥ የማትነቃነቁም፥ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።” (1ቆሮ. 15፥58)።

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።

No comments:

Post a Comment