ኢትዮጵያ ቅድስት አገር እንደ
ኾነች ለማሳመን፣ ከሚጠቀሱት ጥቅሶች መካከል አንዱ ይህ ጥቅስ ነው። ብዙዎችም በዚህ ጥቅስ በጣም ደስ ይላቸዋል፤ እንዲያውም
አንዳንዶች ይህን ጥቅስ በመጥቀስ፣ “ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋ ነበር” ብለው ሲሞግቱ
እንሰማቸዋለን። ነገር ግን ጥቅሱ እውን ሰዎች የሚሉትን ይናገራል ወይ? ክፍሉን ብንመረምር ተቃራኒውን ኾኖ እናገኘዋለን።
መግቢያ
መዝሙር 68ን ርዕስ እንስጠው
ብንል፣ “ያህዌ የምስኪኖች አባት ነው” ወይም “ያህዌ መለኮታዊ ጦረኛ ኾኖ እንዲመጣ የቀረበ ጸሎት” ነው ብለን መናገር
እንችላለን። በክፍሉ ውስጥ እስራኤል ሰላም እንድትኾን፣ በእስራኤል ላይ የሚነሣሱ ጦረኞች ኹሉ በመለኮታዊ ጦር እንዲጠቁና
እንዲሸነፉ የቀረበን ጸሎት በውስጡ እንመለከታለን። ለዚህም እግዚአብሔር በሰማይ ካለው “ከተቀደሰው ማደሪያው” ሰዎችን ኹሉ
ያያል። የእርሱ ዐይኖችም መብታቸው በኃያላንና በቅንጡ ባለጠጎች በተረገጠ ምስኪኖችና ጭቁኖች ላይ ናቸው። እናም እንዲህ ላሉት
ጭቁኖችና፣ መብታቸውና ክብራቸው ለተረገጡ ሰዎች እግዚአብሔር ተሟጋች፣ ዋስ ጠበቃ፣ ታዳጊና አባት መኾኑን መዝሙረኛው ይዘምራል።
ምስክርነቱ!
እግዚአብሔር ታዳጊና አባት ለመኾኑ
የቀረበው ማስረጃ፣ “አቤቱ፥ በሕዝብም ፊት በወጣህ ጊዜ፥ በምድረ በዳም ባለፍህ ጊዜ፥ ምድር ተናወጠች፥”
(መዝ. 68፥7) የሚል ነው። ኪዳናዊው አምላክ ለእስራኤል በምድረ በዳው ጉዞ ከፊት የወጣና የተንከባከበ ጻድቅ አምላክ ነው፤
(ዘጸ. 10፥23፤ 13፥22፤ 14፥19)። እግዚአብሔር እጅግ የተጨቆኑትን ሕዝቡን አባት ኾኖ ከቸርነቱ ለድኾች የሚያስፈልጋቸውን
ኹሉ ሰጠ። ይህም ታላቅ ምስክር ነው። “አቤቱ፥ የሞገስን ዝናብ ለርስትህ
አዘነብህ፥ በደከመም ጊዜ አንተ አጸናኸው።” እንዲል፣ መጠበቅና መንከባከብ ይችልበታል።
ይህ ብቻ ሳይኾን፣ እግዚአብሔር
ለሕዝቡ ተዋጊና ድል ነሺ አምላክም ነው። “የሠራዊት ነገሥታት ፈጥነው
ይሸሻሉ፤ በቤትም የምትኖር ምርኮን ተካፈለች።” እንዲል (ቍ. 12)። መለኮታዊው ድልም፣ “በሰልሞን ላይ እንደ ዘነበ በረዶ” ታላቅና ቁልል ነው። እንደሚበታተንም
በረዶ እግዚአብሔር የሕዝቦቹን ጠላቶች ፈጽሞ ይበታትናቸዋል።
ምስጋና!
ለተዋጋላቸው ጌታ ደግሞ ቸርነት የበዛላቸው
ሕዝቡ፣“እግዚአብሔር አምላክ ቡሩክ ነው እግዚአብሔር በየዕለቱ ቡሩክ ነው የመድኃኒታችን
አምላክ ይረዳናል።” (ቍ. 19) የሚል ታላቅ የውዳሴና የድልን ዝማሬን ዘመሩለት። ለአሸናፊው ጌታ የቀረበ
ምስጋና “አምላኬና ንጉሤ” በሚል ሙገሳ ያሸበረቀ ነው። እግዚአብሔርና ሕዝቡም ከጦርነትና ከሰልፍ ስፍራ በድል አድራጊነትና በእልልታ
ወደ “ቤተ መቅደሱ” መመለሱን እንመለከታለን።
የ“ማሳረጊያው”
ጸሎት
እግዚአብሔር ለሕዝቡ ድልን አምጥቶአል፤
ለዚህም ሕዝቡ ምስጋናና እጅ መንሻን ለአምላኩ አምጥቶአል፤ (ቍ. 28-29)። በተጨማሪም ደግሞም ሕዝቡ ሌላ ጸሎትን አቅርቦአል፤
ጸሎቱም ለእግዚአብሔር ያልተገዙ ሕዝቦች እንዲመቱ የቀረበ ጸሎት ነው። እኒህ ለእግዚአብሔር ያልገዙት ሕዝቦች በኹለት ምሳሌዎች ተገልጠዋል።
1.
“በሸንበቆ መካከል በሚኖሩ አራዊት” (ቍ. 30)፦ ይህ በምሳሌነት የእስራኤል ጠላቶች ሁከተኞች
መኾናቸውን ነው። በዚህ ምሳሌነት የተጠቀሰችው ግብጽ ናት። እርስዋ፣ “በወንዞች መካከል የምትተኛና፦ ወንዙ የእኔ ነው ለራሴም ሠርቼዋለሁ የምትል” ናትና
(ሕዝ. 29፥3)፣
2.
“ጥጆች መካከል ያለውንም የኮርማ መንጋ” (ቍ. 30)፦ ይህ በምሳሌነት የሚያመለክተው ደግሞ
የእስራኤል ጠላቶች ጨካኞች መኾናቸውን ነው። ይኸውም ምሳሌ ግብጽን ወይም ፈርዖንን የሚረዱ ሌሎች አገራትን የሚያመለክት ምሳሌ ነው።
በዚህ በኩል ግብጽ ዐመጸኛ ነገሥታትን ወክላ ቆማለች፤ በዚያው ትይዩ ደግሞ ኢትዮጵያም ከግብጽ ጋር ቆማ እንመለከታለን።
“ሰልፍን[ጦርነትን] የሚወድዱትን አሕዛብ”፣ እጆቻቸውን ዘርግተው ለእግዚአብሔር
እንደ ተንበረከኩ” እና እንደ ተበታተኑ እንዲኹ፣ ለግብጽ አጋር ኾነው የእስራኤልን ሰላም የማይሹ ኹሉ በፍጻሜአቸው ለእግዚአብሔር
እጃቸውን ዘርግተው ይሸነፋሉ። ከእነዚህም አንዷ ደግሞ ኢትዮጵያ ናት። የእግዚአብሔር አገዛዝ በሚወዱት ሕዝቡ በእስራኤል ላይ ነውና፣
“እግዚአብሔር በቅዱሳኑ ላይ ድንቅ ነው፤ የእስራኤል አምላክ እርሱ ኃይልን
ብርታትንም ለሕዝቡ ይሰጣል፤ እግዚአብሔርም ይመስገን።” አሜን፤ ዛሬም ጦር ወዳድዋና በጥጆች[አቅም
በሌላቸው ሕፃናት] መካከል በኮርማነት የምትፋንነውና በጭካኔዋ ወደር ያልተገኘላት ኢትዮጵያ፣ ወደ እግዚአብሔር እጆችዋን ትዘረጋ
ዘንድ ምልጃና መቃተት አለን!
“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን”
(ኤፌ. 6፥24)።
No comments:
Post a Comment