Wednesday 15 June 2022

መዳንም በሌላ በማንም የለም!

 Please read in PDF

·        ዛሬ በኢየሱስ ስም መስበክ ወይም ኢየሱስ ያድናል ማለት መናፍቅ አሰኝቶ ያስወግዛል!

·        ገድለ ተክለ ሃይማኖት ደግሞ፣ የተክለ ሃይማኖትን ስም የጠራ ይድናል ይላል!

 “መዳንም በሌላ በማንም የለም እንድንበት ዘንድ የተሰጠን ከሰማይ በታች ሌላ የለም” (የሐ.ሥ 12፥4)

ይህን ቃል የተናገረው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ነው። የተናገረውም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ በቅዱስ ድፍረት ውስጥ ኾኖ ነው። ይህን ቃል ለመናገር ያበቃው ደግሞ፣ ሲወለድ ጀምሮ ሽባ የነበረውን ሰው ከፈወሰ በኋላ ለተነሣው ሙግት ምላሽ ነው። ሰውዬው ለመሥራት ለመሮጥ፣ ለመቅደም፣ ለመታገል የማይችል ምስኪን ሰው ሆኖ፣ በወላጆቹ ላይ ወድቆ የሚኖር ሰው ነበር። ጥዋትና ማታ በቤተ መቅደስ በር ላይ እያመጡ ይጥሉታል፣ ከሕዝብ ምጽዋት እየለመነ የዕለት እንጀራውን ያገኛል። ከዚህ ሕይወት የሚያወጣው ሌላ እድል አያገኝም፣ ተስፋው በሙሉ በሰው ስጦታ ላይ የተመሠረተ ነው። አንድ ቀን በትክክል ቆሜ እራመዳለሁ ብሎ አስቦ አያውቅም፣ የሚያስበው በቀን ምን ያህል ምጽዋት እንደሚያገኝና ኑሮውን እንደሚገፋ ብቻ ነው። በዚህ ሁኔታ ከ40 ዓመት በላይ አሳልፎአል።

ሐዋርያት ጴጥሮስና ዮሐንስ ወደ ቤተመቅደስ ለጸሎት ሲሄዱ ይህን ሽባ አገኙት፣ እርሱ ለማንኛውም ሰው እንደሚያደርገው ምጽዋት ለመናቸው፤ እነርሱ ግን፣ “ብርና ወርቅ የለንም ነገር ግን ያለንን እንሰጥሃለን” አሉት። ሰውየው “ምን ይሰጡኝ ይኾን?” ብሎ መጠባበቅ ጀመረ፤ ጴጥሮስ ግን “በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነስና ተመላለስ” አለው። ለ40 ዓመት ያህል ሽባ የነበረ ሰው፣ ተነስቶ ዘለለ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሮጦ ገባና እግዚአብሔርን አመስገነ። ይህን ያደረገው የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው።  

ጌታችን ኢየሱስ፣ ሐዋርያቱን “ብርና ወርቅ አትያዙ” ብሎ አስተምሮአቸው ነበር፣ ምክንያቱም እነርሱ የያዙት ከብርና ከወርቅ እጅግ የሚበልጥ ነውና። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “አንዳች የሌለን ስንኾን ኹሉ የእኛ ነው” ብሏል፤ (2ቆሮ. 6፥11)። ክርስቶስን የያዘ ሰው፣ ከወርቅና ከአልማዝ ይልቅ የከበረ ሀብት ያለው ነው። እኛም ማንም ሀብትን አፍርቻለሁ ከሚል ማንኛውም ሰው ይልቅ ሀብታሞች ነን ብለን የምናምነው፣ በክርስቶስ የተሰጠንን ሁሉ በመቍጠር ነው። በዚህም ዓለም በሚመጣውም ዓለም በክርስቶስ አንዳች አይጎድልብንም ብለን እንወራረዳለን። በዚህ ዓለም ባይሰጠንም እንኳ እንወደዋለን። እኛ ሀብትን ማካበት ዓላማ አድርገን አናገለግልም፤ ቃሉ ግን “ባለጠጐች ደኸዩ ተራቡም እግዚአብሔርን የሚፈልጉት ግን ከመልካም ነገር አይጎድሉም” (መዝ. 33፥10) “እግዚአብሔር በቅንነት የሚሄዱትን ከመልካም ነገር አያሳጣቸውም” ይላል፤ (መዝ. 84፥11)።  

እንግዲህ የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም እሥራትን ሽባነትን እንቆቅልሽን ሁሉ የሚፈታ ስም ነው። ለክርስቲያኖች ከጌታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ስም በላይ ሌላ ሀብት የላቸውም። በተለይም ኢየሱስ የሚለው ስም ምድር አንቀጥቅጥ ስም ነው። በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያለ ፍጥረት ሁሉ የሚንበረከክበት ስም ነው። ሰይጣን ይህ ስም እንዳይጠራ በብርቱ ይታገላል። ክርስቲያኖች ግን ስሙን በሥፍራ ሁሉ ለመጥራት ማፈር የለባቸውም። ከኢየሱስ ስም በላይ ለእግዚአብሔር ክብር የሚጠራ ሌላ ስም የለምና። ቃሉ እንዲህ ይላል፣ “በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ኾነ ይመሰክር ዘንድ ነው” (ፊልጵ. 2፥9-11)።

ስሙ “ኢየሱስ፣ እንዲባል እግዚአብሔር አስቀድሞ የወሰነው በስሙ ውስጥ ምሥጢር ስላለ ነው። “ልጅም ትወልጃለሽ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ” (ሉቃ. 1፥31)። የማዳኑ ኃይል ያለው በስሙ ነው። ድል መንሣትም ማሸነፍ የሚቻለውም በስሙ ነው። “እነዚያ በሠረገላ እነዚያም በፈረስ ይታመናሉ እኛ ግን በአምላካችን በእግዚአብሔር ስም ከፍ ከፍ እንላለን” (መዝ. 19፥7)። “በወደደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን” ይላል፤ (ሮሜ 8፥39)፡፡

ንስሐና የኃጢአት ሥርየት የሚገኘውም በስሙ ነው። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ በስሙ የኃጢአቱን ሥርየት እንዲቀበል ነቢያት ሁሉ ይመሰክሩለታል”፤ (የሐ.ሥ. 10፥43)።

የልባችን ሰላም የሚጠበቀውም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። “አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና ሐሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል” (ፊልጵ 4፥7)።

ሰማያዊና ምድራዊ በረከት የሚሞላብን በስሙ ነው። “አምላኬ እንደባለጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል” (ፊልጵ. 4፥19)። 

አጋንንትን የምናወጣው የጠላትን ኃይል ሁሉ የምንቋቋመውም በስሙ ነው። “የሚያምኑትንም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ” (ማር. 16፥17)። “ጳውሎስ ግን ተቸገረና ዘወር ብሎ መንፈሱን ከእርስዋ እንድትወጣ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አዝሃለሁ አለው በዚያም ሰዓት ወጣ” (የሐ.ሥ. 16፥18)።

አብ መንፈስ ቅዱስን የሚሰጠን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኋችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል” (የሐ.ሥ. 14፥26)።

በመካከላችን ለመገኘት ቃል የገባውም በስሙ ከተሰባሰብን ነው “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰባሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እገኛለሁ” (ማቴ. 18፥20)።

በስሙ ብናበላ ብናጠጣ ዋጋችን በሰማይ ይቆየናል “የክርስቶስ ስለሆናችሁ በስሜ ቀዝቃዛ ጽዋ የሚያጠጣችሁ ሁሉ፤ ዋጋው እንዳይጠፋበት እውነት እላችኋለሁ” (ማር. 9፥41)።

ጸሎት የሚያርገውም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው። “እውነት እውነት እላችኋለሁ አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ ይሰጣችኋል” (ዮሐ. 16፥23)። አባቶች፣ "በእንተ ፍቁር ወልድከ እግዚእነ ኢየሱስ፣ "በተወደደው ባንድ ልጅህ በጌታችን ቢየሱስ ክርስቶስ” በማለት ጸሎታቸውን ያሳርጋሉ።

ይህን ሁሉ የእግዚአብሔር ቃል ስናነብ፤ መልአኩ ገብርኤል በተላከው መሠረት "ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ” ብሎ የተናገረው ያለ ምክንያት እንዳልኾነ እንገነዘባለን። ነገር ሁሉ በዚህ ስም ስለሚከናወን ነው። ሐዋርያት አባቶቻችን "በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም አድርጉት” በማለት አስተምረዋል፤ (ቈላ. 3፥16)።

ዛሬ ግን ጠላት የአብያተ ክርስቲያናትን በለይም የኦርቶዶክሳውያንን ተቋም በመቈጣጠሩ በኢየሱስ ስም መናገር ከባድ እየኾነ ነው። በኢየሱስ ስም መስበክ፤ በኢየሱስ ስም መጸለይ፤ በኢየሱስ ስም መዘሙር መናፍቅ አስኝቶ ያስወግዛል። የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ስትራቴጂውን ቀይሮ ቤተክርስቲያን ውስጥ በቅዱሳን ስም ተደራጅቶ ተቀምጦአል። በቅዱሳን ስም የኢየሱስን ስም ይቃወማል። እንንቃ!

ገድለ ተክለሃይማኖት፤ የተክለ ሃይማኖትን ስም የጠራ ይድናል ይላል፤ ገድለ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፤ የገብረ መንፈስ ቅዱስን ስም የጠራ ይድናል ይላል። ገድለ ክርስቶስ ሰምራ፤ የክርስቶስ ሰምራን ስም የጠራ ይድናል ይላል። ገድለ ጊዮርጊስ፤ የጊዮርጊስን ስም የጠራ ይድናል ይላል። ገድለ ላሊበላ፤ የላሊበላን ስም የጠራ ይድናል ይላል። ድርሳነ ሚካኤል፤ የሚካኤልን ስም የጠራ ይድናል ይላል። ድርሳነ ገብርኤል፤ የገብርኤልን  ስም የጠራ ይድናል ይላል። ድርሳነ ኡራኤል፤ የኡራኤልን ስም የጠራ ይድናል ይላል። ታምረ ማርያም፤ የማርያምን  ስም የጠራ ይድናል ይላል። እያንዳዱ ገድል በመጨረሻው ላይ የባለገድሉን ወይም ባለድርሳኑን ስም የጠራ ይድናል በማለት ይናገራል።

መንፈስ ቅዱስ ያደረበት የጌታችን ሐዋርያ የሃይማኖታችን መሠረት ቅዱስ ጴጥሮስ ደግሞ፣ "እንድንበት ዘንድ የሚገባ ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለም” ይላል። ጎበዝ ማንን እንስማ? ገድላትና ድርሳናት የጠላት ጽሑፎች አይደሉምን? ዛሬ ሕዝባችን በገድላትና በድርሳናት ትምህርት የታሠረ አይደለምን? ወንጌል እንዳይሰበክና ሕዝባችን ወደ እውነቱ እንዳይመጣ ከፍተኛ ትግል እየተደረገ ያለው ይህ የጠላት ሥራ እንዳይፈርስ ነው። እውነቱን ለመናገር ይህ ገለባ እሳት ነዶበታልና መቃጠሉ አይቀርም፤ እሥራት ይፈታል የአጋንንት ሥራ ይፈርሳል፤ የክርስቶስ አዳኝነት ይገለጣል፤ የሥላሴ ክብር ምድሪቱን ይከድናል። እንግዲህ ብቻውን ጌታ የኾነው የታረደው የእግዚአብሔር በግ ድል እስኪነሣ ድረስ በሰማያዊ ስፍራ ከሥጋና ደም ጋር ያይደለ ጦርነታችንን እንቀጥል።

ክብር ለታረደው በግ ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ ይሁን አሜን!

5 comments:

  1. Geta Yebarke. I am telling my friends "how those evil books are contradicted to bible." You and your fiends need to work hard, we need you guys,please save the orthodox Church other ways. If you don't do some thing, the church will lose most most of the follower, don't even think the young generation. Bible!Bible! Bible!

    ReplyDelete
  2. መዳንም በሌላ በማንም የለም። «መዳንም በሌላ በማንም የለም እንድንበት ዘንድ የተሰጠን ከሰማይ በታች ሌላ የለም» የሐዋ 12፥4 ይህ እውነተኛ የእግዚአብሔር ቃል ነው። ከእርሱ በቀር አዳኝ አምላክ የለም። ነገር ግን አምላችን ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ የአመነትን ቅደሳን የጸጋ የማዳን ስልጣን ለቅዱሳን ሰጥቶአቸዋል።መጽ መሳፍ 3፡9 የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ እግዚአብሔርም የሚያድናቸውን አዳኝ የካሌብን የታናሽ ወንድሙን የቄኔዝን ልጅ ጎቶንያልን አስነሣላቸው።መጽ መሳፍ 3፥15 የእስራኤልም ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጮኹ እግዚአብሔርም ብንያማዊውን የጌራን ልጅ ናዖድን ግራኙን ሰው አዳኝ አስነሣላቸው የእስራኤልም ልጆች በእርሱ እጅ ወደ ሞዓብ ንጉሥ ወደ ዔግሎም ግብር ላኩ። የያዕቆብ ወንድም የይሁዳ መል ቁጥር 22 እንድህ ይላል "አንዳንዶች ተካራካርዎችንም ዉቀሱ አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አደኑ" በዚህ የእግዚአብሔር ቃል ላይ የማዳን ስልጣን የተሰጠው ለቅዱሳን ነው። የእነ ሐዋርያው ጴጥሮስ ጥላ ብዙ በሽተኖችን አድኖዋል። በሐዋርያው ጳዉሎስ ልብስ በዙዎች ድነዋል። እራሱ ጌታችን እንድህ በማለት የተናገረው ቃል አለ በእኔ የሚያምን እነ የማደርገውን ያደርጋል ከእነም የበለጠ ያደርጋል በማለት ታላቅ ሥልጣንን ሰጥቶአቸዋል። ቅዱሳን የጸጋ የማዳን ስልጣን በመጽሐፍ ቅዱስ አላቸው። ቅድሰት ቤተክርስቲያነችን የጌታ አዳኝነት ታምናለች። ለቅዱሳንም የጸጋ ማዳን ስልጣን ትቀበላለች። እንደ ጌታችን ቅዱስ ቃል ትመራበታለችም። እውነቱ በሰላም

    ReplyDelete
  3. እኔ እኮ የሚገርመኝ አንድ ሰው መጻፍ ስለቻለ ብቻ ለምንድነው አይነት አስተያየት በመስጠት የእነሸዋዬን ሀሳብ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ በገገማ ፍልስፍናው የሚያጫፍረው?
    አረ ለመሆኑ የጠቀስከው የመጽሐፈ መሳፍንት 3፡9ኝን መሰረተ ሐሳብ በማስተዋል አንብበሀው ታውቃለህ? ምን አለ ከመናገር መማር ይቅደም ያሉትን የአባቶች አባባል ቆም ብለህ ብታስተውለው፡? የእግዚአብሔር ቃል የሆነው የወቅቱ የእስራኤልን ታሪክ የያዘውና አንተ ለገዛ ቅዠትህ ይጠቅመኛል ብለህ የጠቀስከው ታሪክ የሚናገረው ሌላ! አንተ የምትቃዠው ሌላ! ታዲያ ያንተን ተረት እንመን ወይስ የእግዚአብሔርን ቃል መሰረታዊ ሀሳብ እጅግ በጣም ትገርማለህ ጊዜሕን አመቻችተህ በድንቁርና ትእቢት ከመወጠር ከአንተ የተሻሉ አባቶችንና ወንድሞችን እንዲሁም እህቶችን ጠይቀህ ለመረዳት ብትሞክር ያም ባይሆን እንኩዋን የጠቀስከውን መጽሐፍ ሙሉ ምእራፉን በማስተዋል ብታነበው ከስህተትህ በከፍተኛ ጸጸት እንደምትመለስአምናለሁ። በጥቂቱ ግን ለማስተዋል እንዲረዳህ መንገድ ልስጥህ ታሪኩ እንዲህ ነው፦ ሲጀመር ዘመኑ ዘመነ ፍዳ ታሪኩም የእስራኤል ዘስጋ ታሪክ ነው እስራኤላውያን በከነዓናውያን በኬጢያውያንም በአሞራውያንም በፌርዛውያንም በኤዊያውያንም በኢያቡሳውያንም መካከል ተቀመጡ።ታዲያ በዚህ ጊዜ በፈጠሩት የጋብቻ ስህተት ላላስፈላጊ አምልኮተ ጣኦት በመዳረጋቸው ምክንያት እ/ር በመስጴጦምያ ንጉሥ በኵሰርሰቴም እጅ አሳልፎ ሰጣቸው በዚያም ለ8 አመት በደረሰባቸው መከራ ተቀጥተው ወደ አምላካቸው በመጮሃቸው ከዚያ ለቅጣት ከተሰጡበት ንጉስ እጅ የሚያድናቸው ጎቶንያል ተሰጣቸው እንጂ አንተ ሳይገባሕ እንደዘባረቅከው ነፍሳቸውን የሚታደግና ወደዘለአለም ሕይወት የሚያደርሳቸው ጎቶንያል አይደለም የተሰጣቸው። ወንድሜ ተስፋ እየነገረህ ያለው ስለዘለአለማዊ ድህነትህ እንጂ (ከሞተስጋበኍላስለአለውና) ለዚያ ስለሚያበቃህ እንጂ አንተ እንደምትለው በሰራዊት ሀይል ስለሚፈጸመው ምድራዊ መዳን ብቻ አይደለም።ልብ ይስጥህ ልብ ይስጠን።

    ReplyDelete
  4. የማቴዎስ ወንጌል
    10፥40 እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል።

    ወገን እናስተውል! ይህንን ቃል የተናገረው ጌታችን መድኋኒታች ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፥
    መዳን በሌላ በማንም የለም፡ እውነት ነው ቃሉ የታመነ ነው። ግን ምን ማለት ነው? ቤ/ንም በዚህ ቃል ታምናለች። ጸሃፊው ጌታን እና ቅዱሳንን እያወዳዳረ ነው በጣም ይገርማል ትልቅ ስህተት ነው። ቅዱሳን ይህ ቃል የተሰጣቸው እርሱን ተጠግተው ነው። ቃሉን ሰምተው የተሰጣቸው ልዩ ስጦታ ነው። እንደውም እርሱን ለመቀበል የመጀመሪያው መስፈርት አድርጎታል። ምን ይዋጥህ?? ምቀኛ!! አርፈህ ቃሉን አስተውል። የክርቶስን ማዳን ማንም አይተካዉም፣ የሚተካውማ ብኖር ወደዚህ ምድርምን አስመጣው??? በኦሪቱ ብዙ መስዋት ተሰውቷል፡ ብዙ ነብያትም ነበሩ፡ አልቻሉም ምክኛቱም አዳማዊ ህትያት በደማቸው ስለነበር፡ አካላዊ ቃል፣ በሱ ፈቃድ ባባቱ ፈቃድ እንዲሁም በባሕሪ ህየወቱ በመንፈስ ቅዱስ ፈቃድ ወደዚህ ምድር መጣ። እኛን ሊያድን። አዳነን ነጻም አወጣን።ስለዚህ ይህ ድህነት በማንም አልነበረም ወደፊትም አይኖርም። ባጭሩ

    ReplyDelete
  5. You are hopeless rather. What do you mean? Had been he has taught about Teklehaimanot Gedil you would be the first to aknowledge this guy, but because he puts the pure gospel" mencahat jemerk". It is the evil spirit inside you bro. Prary, God will set you free.

    ReplyDelete