Saturday, 18 June 2022

“... ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፤ ” (ዳን. 10፥13)

Please read in PDF

ይህን ቃል የተናገረው ነቢዩ ዳንኤል አይደለም፤ ከመላእክት መካከል ዕርዳታ ይፈልግ ከነበረ መልአክ መካከል አንዱ ወይም መልአኩ ገብርኤል ነው። የተናገረው ደግሞ ለነቢዩ ዳንኤል ነው። እንዴት?

ነቢዩ ዳንኤል በምዕ. 10፥1 በተመለከተው ታላቅ የጦርነት ራእይ እጅግ አዝኖ አለቀሰ። እናም እንደ አንድ ታላቅ መንፈሳዊ አገልጋይ፣ ያየውን ነገር በእግዚአብሔር ፊት ለማቅረብ፣ ባየው ራእይ ላይ የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደ ኾነ ለማወቅ፣ ራሱን ከምግብና ከመጠጥ በመከልከል ሦስት ሳምንታት እስኪፈጸሙ ጾምን ጾመ።

ዳንኤል ባየው ራእይ እጅግ ተንቀጥቅጦአል፣ ጉልበት አልቀረለትም፣ መልኩም ገርጥቶአል፣ ኀይሉንም አጥቶአል። ከእርሱ ጋር የነበሩት ሰዎች በመሸሻቸውም ራእዩን የተመለከተው ብቻውን ነው። በብርቱ ፍርሃት ውስጥም ሳለ፣ አንድ እጅ ዳስሳው ታጽናናው፤ ታበረታታው ጀመር። የሚያበረታውና የሚያጽናናው እጅ ሲናገርም እንዲህ አለ፣
“ዳንኤል ሆይ፤ አትፍራ፣ ማስተዋልን ለማግኘትና በአምላክህም ፊት ራስህን ለማዋረድ ከወሰንህበት ከመጀመሪያው ቀን አንሥቶ ቃልህ ተሰምቶአል፤ እኔም የቃልህን መልስ ይዤ መጥቻለሁ። ነገር ግን የፋርስ መንግሥት አለቃ ሃያ አንድ ቀን ተቋቋመኝ፤ ከዋነኞቹ አለቆች አንዱ የሆነው ሚካኤል ሊረዳኝ መጣ፤ እኔም በዚያ ከፋርስ ንጉሥ ጋር ተውሁት።" (ዳን. 10፥12-13)።

የዳንኤል ጸሎት የተመለሰው ወዲያውኑ ነበር። የጸሎትም መልስ ይዞ የመጣው እጅ(መልአክ) ወዲያውኑ መልሱን ለዳንኤል ሊነግረው አልቻለም። ምክንያቱም በፋርስ መንግሥት ላይ አለቃ የነበረው ክፉ መንፈስ ወይም ሰይጣን መልአኩ ወደ ዳንኤል እንዳይደርስ አዘግይቶት ነበር። በእርግጥ በቀደመው ፍርድ ውስጥ፣ ሰይጣን ወይም እባቡ ሰኮና ነካሽ ወይም ሰኮና ቀጥቃጭ ነው ተብሎአል፤ (ዘፍ. 3፥15) ደግሞም፣ በተደጋጋሚ የሚያዘገይ መኾኑ ተጠቅሶአል፤ “ወደ እናንተ ለመምጣት ፈልገን ነበር፤ በተለይም እኔ ጳውሎስ ብዙ ጊዜ ሞክሬ ነበር፤ ነገር ግን ሰይጣን አዘገየኝ።” (1ተሰ. 2፥18) እንዲል።

ከዚህ ባሻገር ሰይጣን ዘወትር በማያቋርጥ ውጊያ ውስጥ ቢኾንም፣ እግዚአብሔር ደግሞ እጅግ አስደናቂ በኾነ መንገድ ልጆቹን ከጠላት ውጊያና ቅሰጣ የሚያድን አምላክ ነው።

እንግዲህ መልአኩ ለሦስት ሳምንታት ያህል ወደ ዳንኤል መድረስ ባለመቻሉ፣ ቅዱስ ሚካኤል በፋርስ አለቃ ክፉ መንፈስ  ወደ ተከለከለው ወይም ወደ ተቋቋመው መልአክ ሊራዳ መጣ። እናም ረዳው፣ ወደ ዳንኤልም እንዲሄድ መንገዱን አደላደለ፣ ተርጓሚው መልአክም ወደ ዳንኤል ደረሰ። በደረሰም ጊዜ የገጠመውን ኸሉ ለነቢዩ ዳንኤል አወራለት።

ዳንኤል በጸሎቱ ትጋት የፋርስን መንፈስ አለቃ አሸነፈ። ዳንኤል የጸለየበትም ነገር ቢዘገይ፣ በያዘው ጾምና ጸሎት ግን ጸና፤ እጅግም ታግሦ ቆመ። ጌታችን፣ “ሳይታክቱም ዘወትር ሊጸልዩ እንዲገባቸው” (ሉቃ. 18፥1) እንዳስተማረ። ለእኛም ይህ ታላቅ ትምህርት ነው፤ በታላቅ ውጊያ ውስጥ ጸንቶ መቆም!

ሚካኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ፣ በመንገድ ተቃዋሚ የገጠመውን መልአክ ረዳው። መላእክት ከእግዚአብሔር ተልከው ሰዎችን ማዳናቸው አይደንቅም። አንዱ ዓላማቸው ሲላኩ ማዳንና መርዳት ነውና። ነገር ግን መልአክ መልአክን መርዳቱ፣ "መላእክት እሳታውያንና ነፋሳውያን" ስለ ኾኑ ፍጹማን ናቸው ብሎ ለሚያምን ማኅበረ ሰብ፣ መልአክ ራሱ ሌላ ረጅ መልአክ አስፈልጎታል ብንል አለማመናቸው ይደንቀናል። ለዚህ ነው ብዙዎች ለመልአኩ የተነገረውን ለዳንኤል እንደ ተነገረ አድርገው የሚያቀርቡትና ያንኑ ቃልም ለራሳቸውም የሚጠቅሱት።

እግዚአብሔር ግን፦

·        በእርሱ የታመኑትንና የጸኑትን ከማናቸውም ተቃዋሚ ኀይል ያድናቸዋል፣

·        የጸሎታቸውንም መልስ ይመልሳል፣

·        ሰይጣን የቱንም ያህል መልስ ቢያዘገይ እግዚአብሔር ግን መልሱን ከነብድራቱ ሙሉ አድርጎ ይመልሳል።

እናም በፍጡር አዳኝነት አትታመኑ፤ ይልቅ ለሰውም ለመላእክቱም ረዳት መልአክ በሚልከው እግዚአብሔር ፍጹም ታመኑ።

 


No comments:

Post a Comment