Saturday 2 July 2022

በአሜሪካ ለ50 ዓመታት የቆየው የውርጃ ሕግ መሻሩ!

 Please read in PDF

እግዚአብሔር በማናቸውም መንገድ የሰው ልጅ እንዲገደል አይፈልግም። ከታላላቆቹ ሕጎች መካከል አንዱ፣ “አትግደል” የሚለው ሕግ ነው። የሰው ልጆች ደግሞ በተቃራኒው፣ የሰውን ልጅ ለተለያዩ የገቢ ምንጭነትና የዓመጽ ሥራ በብርቱ ጭካኔ ከሚገድሉበት መንገድ አንዱና ዋነኛው፣ ውርጃ ከፊቶቹ ተርታ ይመደባል። ውርጃ በግልጽ በመጽሐፍ ቅዱስ ቢከለከልም፣ ተፈጥሮን የሚቃረን ቢኾንም እጅግ በሚዘገንን መልኩ አያሌ የውርጃ ተግባራት እንዲተገበሩ ብዙ ብሮች ይፈሱበታል፤ ሰዎች ተግባሩን እንዲፈጽሙ በሕግ ጭምር ከለላ ይደረግላቸዋል። ይህን በማድረግ ከሚታወቁት መካከል ግንባር ቀደሟ አሜሪካ አንዷ ናት። እናም ለ50 ዓመታት በሕግ ከለላ ሰጥታ ትፈጽም የነበረውን የውርጃ ሕግ፣ የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች ሽረውታል።

ይህ ውሳኔ የሴታዊነት (Feminism) አስተሳሰብ የሚደግፉትን ብዙዎችን ከማስቈጣቱም ባሻገር፣ ግብረ ሰዶማውያንን ውሳኔው እጅግ አበሳጭቶአቸዋል። ለዚህ ውሳኔ መወሰን ምክንያቱ ደግሞ፣ በፍርድ ቤቱ ውስጥ የተሾሙት ዳኞች ክርስቲያኖችና የውርጃ ተቃዋሚዎች መኾናቸውን ብዙ ዓለም ዓቀፍ ሚዲያዎች አስተጋብተው ዘግበውታል።

እንግዲህ፣ የአሜሪካው ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ አሜሪካ ለሃምሳ ዓመታት ያህል ትገለገል የነበረበትን የውርጃ ሕግ መሻሩ፣ ጠንካራ አማኞችና በመልካም ሞራል የዳበረ ሥነ ምግባር ያላቸው ዳኞችና ሕግ አውጪዎች ሥፍራውን የመያዝ ዕድል ቢኖራቸው ወይም በተመሳሳይ መንገድ እንዲህ ያለውን ተግባር የሚጸየፉ ሰዎችን “እንዲፈጠሩ” ብናበረታታና በብዙ ብንጥር፣ እንደ ገብረ ሰዶማዊነትና ውርጃ ያሉ ሕጎችንና መብቶችንም ጭምር የሚሽሩ “የሰላም ሰዎች” ይነሳሉ ብለን እናምናለን። ደግሞም እግዚአብሔር ሉዓላዊ ጌታ እንደ መኾኑ፣ ከወሰኑ ሳያልፍ ዓመጽን እንዴት እንደሚቆጣጠር ከምናስተውልባቸው መንገዶች አንዱም ጭምር ነውና በዚህ ጌታን እጅግ አድርገን እናከብራለን።



በተለይም ደግሞ እንደ ባላደራ፣ ምድራችንን የደም ምድር ከሚያደርጋት ክፉ ዓመጽ ከውርጃ ራሳችንን ጠብቀን፤ ሌሎችም እንዲርቁ የሚጠበቅብንን ኹሉ ማድረግ ይገባናል። እንዲህ ያሉ መልካም ውሳኔዎችን ስንሰማም፣ ዓመጽ ምንም ያገነገነና የበረታ ቢመስልም፣ በፍጻሜው ግን ሊረታና ሊሸነፍ እንደሚችል ጥቂት ማሳያ እንደኾነ ማስተዋል እንችላለን። እግዚአብሔር ምድራችንን መልካም በኾኑ ዜናዎች እንዲያበስርልን ዘወትር እየማለድን በጸሎት ከመትጋት ልንታክት  አይገባንም። ጌታ ኢየሱስ በምድራችን ከፍ ያለውን ዓመጽ ይገስጽልን፤ በጎውንና መልካሙን ዜና ያሰማን፤ አሜን።

 

1 comment:

  1. እግዚአብሔር አዳኝ አምላክ ነው። ማዳኑን ሥራ ለቅዱሳን ሰጣቸው። ያዕቆብ ወንድም ይሁዳ ቁጥር 22 አንዳንዶችንም ከእሳት ነጥቃችሁ አድኑ። የምለው የጌታ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ቃል ሐዋርያው የተናገረውን መካድ የክርስቲያን ጠባይ አይደለም። ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ ፍጥረታቱ ሁሉ በደሙ ከሐጢአታችን አንጽቶናል። ይህን ስራ ማንም ልያደርገው አይችልም። ነገር ግን ሰዎች ከሐጢአት መንገድ መመለስ አንዱ የማዳን ሥራ ነው። ሐጢአት መስራት በራሱ ሞት ነውና። ከዚህ ከሐጢአት ሞት ሰዎችን በመመለስ በህይወት እንድኖሩ ማድረግ ለቅዱሳን ሰዎች የተሰጠ ስልጣን ነዉ። ስለሰው ሐጢአት መጸለይ የማዳን ስራ ነው። ሰዎች ወደቅድስና ሕይወት እንድመለሱ ማድረግን የማዳን ስራ ነው። ነገር ግን የአዳምን በደል በሞቱ ያጠፋው ጌታችን አባታችን ኢየሱስ ከርስቶስ ብቻ በመስቀል ዲያቢሎስን ድል በመድረግ አዳነን። ለአንደና ለመጨረሻ በእርሱ ተፈጸመ። ዛሬ ግን እርሱ በየቀኑ አይሞትልንም እኛ ሞቱን ስለበዳለችን እንደሆነ እንመሰክራለን። በጌታ የምያምኑ ቅዱሳን ሰዎች ለሌሎችን ሐጢአት ይጸልያሉ ከሐጢአት ሞት በጸሎት ያድናሉ። ሐዋርያዉ ጰዉሎስም እንኳን እንድህ በማለት ተናግሮዋል 'ወንድሞቼ ሆይ ስለእኛ ጸልዩ" ማለት ተናግሮ ነበር ወደ 1ኛ ተሰሎም 5 ፡ 25

    ReplyDelete