Wednesday 2 March 2022

ጾሙ ተሐድሶ ያስፈልገዋል!

Please read in PDF

ጾም መጽሐፍ ቅዱሳዊ አምልኮ ሲኾን፣ ክርስቲያን የኾነ ኹሉ በግልም ኾነ በማኅበር እግዚአብሔርን በእውነትና በመንፈስ ለማምለክና ወደ እርሱ ለመጸለይ፣ ይቅርታን ለመለመን፣ ስለ ተለያዩ ችግሮችና የልብ መሻቶች የእግዚአብሔርን ርዳታና ምላሽ ለማግኘት እግረ ልቡናውን ወደ እግዚአብሔር የሚያቀናበት መንገድ ነው። እግዚአብሔር የሚፈልገው በትሕትና የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ በመኾኑ፣ ክርስቲያን በጾሙ ራሱን ከኀያሉ እግዚአብሔር እጅ በታች ስለሚያዋርድ፣ እንዲህ በእውነት ተዋርዶ ለእግዚአብሔር የሚያቀርበውን አምልኮትና ጸሎትም እግዚአብሔር ስለሚቀበለው ችግሩ ይቃለላል፤ጥያቄውም ይመለሳል፤ (መዝ. 51፥17፤ 1ጴጥ. 5፥6)።

በመጽሐፍ ቅዱስ የጾሙ ምእመናን፣ ይህን የጾም ዐላማ ተከትለው በመጾማቸው የሚፈልጉትን አግኝተዋል (መሳ. 20፥26-28፤ 1ሳሙ. 7፥6-11፤ ዕዝ. 8፥21-23፤ ነህ. 1፥4፤ 9፥1-2፤ አስ. 4፥3፡16)። የገዛ ምኞታቸውን ተከትለውና ለታይታ የጾሙት ግን ከእግዚአብሔር ያገኙት አንዳች ነገር የለም (2ሳሙ. 12፥22፤ ኢሳ. 58፥3-5፤ ኤር. 14፥10-12፤ ማቴ. 6፥16)።

ጾም ከጸሎት ተለይቶ ሊከናወን አይችልም፤ምክንያቱም የሚጾመው የረኃብ አድማን የመሰለ ትዕይንትን ለማሳየት ሳይኾን ለመጸለይ ነውና። በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት (1972፣ 257) እንደ ተገለጸው ጾም፣ “በሃይማኖት ምክንያት ያለ ምግብና ያለ መጠጥ መዋል” ነው። ይሁን እንጂ የጾም ዐላማ፣ ከምግብና መጠጥ መከልከል ብቻ ሳይኾን፣ በተዋረደ ልብ ኾኖ የእግዚአብሔርን ፊት መፈለግ ነውና፣ የሚጾሙ ኹሉ ይጸልዩ ዘንድ ተገቢያቸው ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የምናገኛቸው የጾሙ ሰዎች ጸልየዋል (ሉቃ. 2፥37፤ የሐ.ሥ. 13፥3፤ 14፥23፤ ማቴ. 7፥21፤ የላይኞቹንም ጥቅሶች ይመለከቷል)። ከሞላ ጐደል የጾም ምንነትና ትክክለኛ ዐላማው ይህን ይመስላል።

ዛሬ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሚታየውን ጾም ከዚህ አንጻር ብንገመግመው በርካታ ችግሮች ይስተዋሉበታል። ሃይማኖታዊ ሥርዐትና ልምድ ሆኖ ቀርቷል ማለት ይቻላል። አብዛኞቹ ምእመናን የሚጾሙትም ይህንኑ ጸሎት አልባና ከተወሰነ ምግብ መታቀብ የኾነውን የስም ብቻ ጾም ነው።

በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በቊጥር ከሌሎቹ አብያተ ክርስቲያናት የበለጠ የጾም ወቅት መኖሩ  ይታወቃል። አፈጻጸሙ ሲታይ ግን ከስሙ በቀር መንፈሳዊ ዐላማውና ይዘቱ ተዛብቶ፣ በሥርዐት በተደነገገ የተወሰነ ወቅትና የተወሰኑ ምግቦችን (ጥሉላትን) በመተው ላይ ብቻ ተመሥርቶ፣ የተወሰነ ሰዓትን ወይም ጊዜን ብቻ መቆየት ማዕከል ያደረገ ነው።

ሌላው፣ ጾም በምእመናን ዘንድ የሚታየው እንደ ሕግ ነው። ለአዳም የተሰጠውን ትእዛዝ (ዘፍ. 2፥17) ከጾም ጋር በማያያዝ፣ ጾም ለአዳም የተሰጠ የመጀመሪያው ትእዛዝ አድርገው የሚቈጥሩና የሚያስተምሩም እንዳሉ ይታወቃል (መርሐ ጽድቅ ባህለ ሃይማኖት 1988፣ 65)። በመኾኑም የጾመ ሕጉን እንደ ጠበቀ፣ በጾም ወቅት ከተከለከሉት ምግቦች በስሕተትም ይሁን በአስገዳጅ ኹኔታ የበላ /የቀመሰ/ ግን ኀጢአት እንደሠራ ይታሰባልና፣ ወደ ንስሓ አባቱ ሄዶ፦ ጾም፣ ስግደት፣ ምጽዋትና የመሳሰለውን ተግባር በመፈጸም ለኀጢአቱ መቀጮ ይከፍላል፤ ኾኖም ይህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለውም። ከላይ እንደ ተገለጠው ጾም ለርዳታ  የእግዚአብሔርን ፊት የምንፈልግበት የትሕትና መንገድ እንጂ፣ የሚጠበቅ ሕግ፣ ሕግነቱ ሲጣስ ደግሞ የኀጢአት መቀጮ የሚከፈልበት ዋጋ አይደለም። ያልጾመ ሰው በችግሩ ጊዜ የእግዚአብሔር ርዳታና ባርኮት ይቀርበታል እንጂ “ይኰነናል” የሚል አንቀጽ በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ አልሰፈረም። ስለኾነም በዚህ መንገድ የሚጾሙ ወገኖቻችን፣ትክክለኛውን የጾም ዐላማ ተከትለው ሳይሆን ሥርዐትነቱን ለመፈጸም ሲሉ ነውና የሚጾሙት ጾማችን ለውጥ ያስፈልገዋል።

በቤተ ክርስቲያናችን የአጿጿም ሥርዐት መሠረት በጾም ወቅት ጥሉላት ምግቦችን /ሥጋን፣ እንቊላልን፣ ወተትንና የወተት ተዋፅኦዎችን ወዘተ./ መመገብ ተከልክሏል። ለዚህም መነሻ ተደርጎ የሚወሰደው፣ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰ የአንዳንድ የእግዚአብሔር ሰዎች አርኣያነት እንደሆነ ይታወቃል (መዝ. 10924፤ ዳን. 102-3)። ነገር ግን እነዚህ የእግዚአብሔር ሰዎች፣ በተለይም ነቢዩ ዳንኤል ያዝን በነበረባቸው ሦስት ሳምንታት ውስጥ ካልተመገባቸው ምግቦችና መጠጦች መካከል እኛ የማንወስደው ከፊሉን ብቻ መሆኑ፣ ቃሉን ለጾማችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት ለመስጠት ብለን ሳይሆን ለሽፋን የምንጠቅሰው ያስመስለናል። ነቢዩ፣ “ማለፊያ እንጀራ አልበላሁም፤ ሥጋና ጠጅም በአፌ አልገባም፤ ... ዘይትም አልተቀባሁም፣ በማለት ከተዘረዘሩት ምግቦች እንደ ታቀበ ብቻ ሳይሆን፣ ራሱን በእግዚአብሔር ፊት እንዴት እንዳዋረደም ገልጿል። እኛ ግን በአንድ በኩል አጿጿማችን የዳንኤልን የአጿጿም ሥርዐት የተከተለ ነው ስንል፣ በሌላ በኩል ደግሞ እርሱ ሲጾም ካልወሰዳቸው ምግቦችና መጠጦች ውስጥ የተውነው ቢኖር ሥጋን ብቻ ነው። ከጥሉላቱ ውጪ ከሚገኙት የምግብ ዐይነቶች መካከል ግን ያገኘነውን ጥሩ ጥሩ ምግብ እንመገባለን /እዚህ ላይ ጥራ ጥሬ እየበሉና ውሃ እየጠጡ የሚጾሙም እንዳሉ አይካድም/። ምናልባትም ከነዚህ ምግቦች የጥሉላቱ ምግቦች ለሰውነታችን ሊሰጡ የሚችሉትን ጥቅም በተዘዋዋሪ እናገኛለን። በመኾኑም የራቅነው /የሸሸነው/ ከጥሉላቱ ምግቦች እንጂ፣ ከእነርሱ ከሚገኘው ጥቅም ባለመሆኑ አሁንም ራሳችንን እያታለልን እንደ ሆነ ሊሰማን ይገባል።

ይህም ብቻ አይደለም፤ ቤተክርስቲያናችን ከዓመት እስከ ዓመት በሰንበቴ፣ በማኅበር፣ በዝክርና በተዝካር ስም በሚደገሰው ድግስ ውስጥ፦ ጠላ፣ አረቄ፣ ጠጅና የመሳሰለው አልኮል ነክ መጠጥ አይቀርም። ከጥቂቶች በቀር ሁሉም ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ የመጠጡ ተቋዳሽ ነው። ስለሆነም በጾም ወቅት እንኳ እንደ ዳንኤል የመጠጥን ጾምነት አይቀበልም። በአንዳንዶች ዘንድ እንዲያውም መጠጥ ጠጪነት የኦርቶዶክስነት መለያ ምልክት ተደርጎ እስከ መወሰድ የደረሰበትም ሁኔታ እንዳለ ይታወቃል። ከዚህ አንጻር በአጿጿማችን የነዳንኤልን አርኣያነት ተከትለናል ማለት እንችላለን? አንዱን ጥሎ፣ አንዱን አንጠልጥሎስ ይሆናልን?

ስለ ጾም ምንነት ትክክለኛ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ግንዛቤ በሌለበት ሁኔታ፣ ከምግብ ጋር ለተያያዘው ነገር ካልሆነ በቀር በጾም ወቅት መከናወን ላለበት መንፈሳዊው ጒዳይ ትኲረት ይሰጣል ብሎ መጠበቁ ሞኝነት ነው። የብዙ የልማድ ጿሚዎች ዋና ትኲረት በመብል ላይ ያነጣጠረ ነው። ስለሆነም ለጾሙ የሚደረገው ትልቁ ዝግጅታቸው፣ ጾሙ እንደ ነገ ሊጀመር እንደ ዛሬ በቅበላ /ጾሙን የመቀበያ ቀን ወይም ዋዜማ/ የልኳንዳ ቤቶችን ደጃፍ በማጨናነቅ ሥጋ ላይ መራኰት ነው። በጾሙ ወራት ሊያደርጉ ስለሚገባቸው የጽድቅ ሥራ የሚያስቡ ጥቂቶች ይኖሩ እንደ ሆነ አይታወቅም። በጣም የሚገርመው ደግሞ በቅበላውና በፍስኩ ጊዜ የጥሉላቱን ምግቦች አላስይዝ አላስቀምስ የሚሉት፣ ያንኑ የሥርዐት ጾም በአግባቡ የማይጾሙት ወገኖች መሆናቸው ነው። በአግባቡ አለመጾማቸው ሳያንስ፣ በሆነ አጋጣሚ ስሕተት ቢፈጠር እንኳ የጾሙ ሥርዐት ተበላሸ፤ ተጓደለ ባዮችም እነዚሁ ባዶ ቀናተኞች ናቸው። በመሠረቱ መብል ወደ እግዚአብሔር አያቀርበንም፤ ብንበላም የሚተርፈን ባንበላም  የሚጐድለን አይኖርምና (1ቆሮ. 8፡8) ጾምን በተመለከተ ከአመጋገባችን ይልቅ ለጾም ዐላማ ትኲረት መስጠቱ መንፈሳዊነት ነው።  

የጾም ነገር ሲነሣ፣ የማንን ጾም ነው የምንጾመው? የሚለው ሌላው አነጋጋሪ ጒዳይ ነው። በቤተክርስቲያናችን በዐዋጅ የተደነገጉትና ምእመናን በየዓመቱ እንዲጾሟቸው ከታዘዙት አጽዋማት ብዙዎቹ፣ የእኛ ሳይሆኑ ሌሎች በተለያየ ምክንያት የጾሟቸው ናቸው። በቤተክርስቲያን፣ በአገርና በወገን ላይ ችግር ቢደርስም ባይደርስም፣ በዓመት ውስጥ የተወሰነላቸውን ወቅት ጠብቀው የቀድሞ ታሪክን /ምናልባትም ከእኛ ጋር ትስስር የሌለውን ታሪክ ጭምር/ በማሰብ የሚጾሙት አጽዋማት ሰባት ናቸው፤ (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ታሪክ ከልደተ ክርስቶስ እስከ ፳፻ ዓ.ም. 2000፣ 32) እነርሱም፦

1.   ጾመ ነቢያት /ነቢያት በተለያየ ጊዜ ጾሙት የሚባል/፣

2.   ጾመ ነነዌ /በትንቢተ ዮናስ እንደ ተጻፈው የነነዌ ሰዎች የጾሙት/፣

3.   ጾመ ዓቢይ /ዐቢይ ጾም ወይም ጌታ የጾመው/፣

4.   ጾመ ሐዋርያት /ሐዋርያት መቼ እንደ ጾሙት ባይታወቅም ጾመውታል የሚባለው/፣

5.   ጾመ ፍልሰታ /ሐዋርያት በድንግል ማርያም ሞትና ትንሣኤ ምክንያት ጾመውታል የሚባለው/፣

6.   ጾመ ገሃድ /የክርስቶስ ልደትና ጥምቀት በዓል ረቡዕና ዐርብ ቀን የሚውል ከሆነ ለዚያ ለውጥ በዋዜማቸው የሚጾም/ እና

7.   ጾመ ድኅነት /ከበዓለ ኀምሳ በቀር ዘወትር ረቡዕና ዐርብ የሚጾመው/ ናቸው።

ከሰባቱ አጽዋማት አብዛኞቹን ስንመለከት፣ ሰዎቹ የጾሙት እግዚአብሔር ችግራቸውን እንዲያቃልል፣ ፍላጎታቸውን እንዲያሟላና ጥያቄያቸውን እንዲመልስ ነው። በምሳሌነት እንኳ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነውን የነነዌን ሰዎች ጾም ብንመለከት፣ ከእግዚአብሔር ዘንድ በጥፋታቸው ላይ የነደደው ቊጣ እንዲበርድ፣ እግዚአብሔርን በጸሎትና በምሕላ ለመለመን ሲሉ ነው የጾሙት። በመሆኑም እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ተቀብሎ ምሕረት አድርጎላቸዋል (ዮና. 3፡5-10)። እንግዲህ የእኛ፣ የነነዌን ሰዎች ጾም በየዓመቱ መጾማችን ከምን የተነሣ ይሆን? በመታሰቢያነት መጾም ቢያስፈልግ እንኳ ጾመ ነነዌ ከእኛ ይልቅ ትርጒም የሚሰጠው ከዚያው ትውልድ ለቀጠሉት ለነነዌ ነዋሪዎች ነው። ለእኛ ምናልባት ጾማቸው ትልቅ ትምህርት ሊያስተምረን ከመቻሉ በቀር ሌላ የሚተርፈን ነገር አይኖርም። በወቅቱ በእግዚአብሔር ፊት ለቀረበው የምሕረት አቤቱታ ምላሽ ተሰጥቶበት የተዘጋውን ፋይል /የነነዌን ሰዎች ጾም/ ዳግም ከፍተን የእኛ ያልሆነውን ታሪክ በየዓመቱ ከምንዘክር ይልቅ፣ ለእኛዎቹ አንገብጋቢ ችግሮች ጾም-ጸሎት ይዘን የእግዚአብሔርን ምሕረት ብንለምን እንጠቀማለን። የተለየ  ታሪክ የምንዘክርበት ጾም ቢኖር እንኳ ከእኛ ሕይወት ጋር ጥብቅ ትስስር ያለውና ትርጒም የሚሰጠን ጾም ሊሆን ይገባል። ለምሳሌ፦ ዐቢይ ጾም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እኛን ለማዳን ሰው ሆኖ የጾመውና ስለእኛ የተቀበላቸው ሕማማት የሚዘከሩበት ጾም በመሆኑ ከእኛ ሕይወት ጋር ትስስር አለው ማለት እንችላለን። ስለሆነም ይህን እያሰብንና የጾምን ዐላማ ተከትለን ብንጾመው መልካም ነው።

እነዚህ የተጠቀሱት ነጥቦች በጾማችን ውስጥ የሚታዩትን ጒድለቶች በመጠኑም ቢሆን ሊያመለክቱን ይችላሉ።እነዚህንና ሌሎች ያልተጠቀሱትን ከጾም ጋር የተያያዙትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ትምህርቶችንና ሥርዐቶችን፣ ቤተክርስቲያናችን በእግዚአብሔር ቃል መሠረት እያረመችና እያስተካከለች፣ ምእመኗን  የእግዚአብሔር ቃል የሚደግፈውን ጾም እንዲጾሙ ልታበረታታቸው ይገባል።

ምንጭ፡-  የለውጥ ያለህ!!! ገጽ 215

ይህ ጽሑፍ አባ ሰላማ በተባለው ብሎግ ወጥቶ የነበረ ነው።


2 comments:

  1. እስኪ ንገሩኝ፣ ከግሪክና ከዕብራውያነ የመጣውን መጽሐፍ ቅዱስ አይደል እንዴ የምንጠቀመው። ኢትዮጵያዊ ደራሲ አድርገናቸው ይሆን ነብያትና ወንጌላውያኑንን ? ረሳችሁት እንጂ ቅዱሳን ወንጌላውያን፡ ነብያት፡ ሃዋርያት፡ አርድእት፡ ሰማእታት ቅዱሳት አንስት በሙሉ ኢትዮጵያዊ አይደሉም። ደግሞስ በየዋህነት የጾመው የኢትዮጵያ ህዝብ ምኑ ሲጎዳና ሲጎድልበት አያችሁ፡ እስኪ እናንት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጾሞችዋ ይታደስ (ተሃድሶ ያስፈልጋታል)የምትሉ ሰዎች ከየትኞቹ ቅዱሳን በልጣችሁ ነው ለማደስ የተነሳችሁ፡ የናንት እናትና አባቶች አልጾሙትም እንዴ? የቀደመችውን ስርአት ማሰቡ ላይ ልብ አላላችሁም? ነው ወይስ ሰው በህገ ልቦና (በየዋህነት) ሲጾም አይዋጥላችሁም / ቅር ይላችኃል እንዴ? ለመሆኑ እራሳችሁን አይታችኃል? የጾመ ምን ተጎዳ? እስኪ ቀን ይምጣ ለሁላችንም የስራችን ይከፈለናል፤ በተለይ ለእናንት የህዝቡን ቀልብ የሳባችሁ ደግሞም የማስ ሚድያው ጥበብ በጃችሁ የሆናችሁ ለሰው መውደቂያም ማስተማሪያም (መነሻም) ስለሆናችሁ ተጠንቀቁ ከፍርድም ቀላልና ከባድ አለውና ወደ ልብ መመለሱ ጥሩ ሳይሆን አይቀርም።
    ቸር ይግጠመን፤
    አንድ ሃሳብ አንድ ልብ ያድርገን!
    ይልቅስ መቃወም ወንድም ወንድሙን ለፍርድ አቁሞ ሲከሰውና የአህዛብ መሳቂያ መሳለቂያ ስንሆን ነው መቃወም።

    ReplyDelete
  2. የኢኦተቤክ ከሌሎች የሃይማኖት ድርጅቶች ልዩ ሆና የተገኘችበትና እምነትና ሥርዓቷ ዕድሳት እንደሚያስፈልገው የሚመከርባት ምክንያቱ አልገባህ ይለኛል።
    - እስላም ወንድሞች ከነቢዩ መሃመድ ጀምሮ የወጣ የጾም ሥርዓትን ተከትለው እያከበሩ ስለሆነ፣ የርዕስ ጾም እንዲጀምሩ እስቲ እነሱንም ምከራቸው፤
    - ካቶሊኮችም (ከዓለም ትልቁ የክርስትና ድርጅት) እንደዚሁ በየጊዜው የሚቀያየር የጾም ደንብ የላቸውም፤ እንዲያውም ይኸ የዓቢይ ጾም ወቅት ከኛ ጋር በአብዛኛው ቀናት ይገጣጠማልና አቤቱታ ያለህ ወደዛም ሰፊ የሃይማኖት ድርጅት ማመልከቻህን አስገባ።
    - ሌሎች እህት ኦርቶዶክስ ማኀበራትም የሚጾሙት ጾም፡ በእንደዚሁ በኛው ዓይነት ሥርዓት የተዘረጋ እንጅ የሳምንትና የዓመት፣ የጾም ርዕስና ደንብ እያወጁ ዘወትር አዲስ ዓይነት ጾም የላቸውምና ጥቆማህን ጀባ በላቸው።

    ታድያ የናንተ ከየት የመጣ፣ ማንን የተከተለ ነው ይባላል? ትግላችሁ አዲስ የሃይማኖት ሥርዓት ለመዘርጋት ወይስ የኘሮቴስታንት ትምህርትን ወደ ቤተክርስቲያናችን ለማስገባት ይሆን? የትናንቱ ወቀሳ ከሌሎች በተለየንበት ጉዳይ ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ሌሎችን በምንመስልበትና የክርስትናችን መሠረታዊ ሥርዓት በሆነው ሁሉ ላይ መጣ።

    ReplyDelete