Saturday 26 February 2022

ኑሮን በማስወደድ እንከብራለን ለሚሉቱ!

 Please read in PDF

“ችጋረኛውን የምትውጡ፥ የአገሩንም ድሀ የምታጠፉ እናንተ ሆይ፦ እህልን እንሸጥ ዘንድ መባቻው መቼ ያልፋል? የኢፍ መስፈሪያውንም እያሳነስን፥ ሰቅሉንም እያበዛን፥ በሐሰተኛም ሚዛን እያታለልን፥ ድሀውን በብር ችጋረኛውንም በአንድ ጥንድ ጫማ እንገዛ ዘንድ፥ የስንዴውን ግርድ እንሸጥ ዘንድ ስንዴውን እንድንሸምት ሰንበት መቼ ያልፋል? የምትሉ እናንተ ሆይ፥ ይህን ስሙ።” (አሞ. 8፥4-6)

ታሪካዊ ዳራ!

ነቢዩ አሞጽ ያገለገለበት ጊዜ፣ በዳግማዊ ኢዮርብዓም የኋለኛው አጋማሽ ዘመን አከባቢ ነበር። በዚህ ዘመን ደግሞ የነበረው ብልጽግና፣ በማኅበራዊ ንቅዘት የተነወረ ነበር፤ ንቅዘቱና መበስበሱም እጅግ ተስፋፍቶ ነበር። በሌላ መልክ ደግሞ፣ እስራኤል በእግዚአብሔር መመረጥዋን ተገን በማድረግ፣ ብዙ በደልን ፈጽማ ነበር። እግዚአብሔርም በአሞጽ አንደበት በርግጠኝነት መመረጥዋን ተናገሮ (3፥2) ነገር ግን መመረጥዋ ብቻውን፣ ለእውነተኛው በረከትና መትረፍረፍ ዋስትና አለመኾኑንም ሲናገር እንሰማዋለን። ምክንያቱም ለተስፋው ቃልና ለተሰጣቸው ትእዛዝ መታዘዝና መጽናት አለባቸውና፤ “አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤” (ዘጸ. 19፥5) እንዲል።


ነገር ግን፣ እስራኤል ከተነገረላት በተቃራኒ ነበረች እንጂ ፈጽሞ አልታዘዘችም። አሞጽ በትንቢቱ እንደሚናገረው፣ እጅግ አደገኛ በኾኑ ማኅበራዊ ወንጀሎች ውስጥ ተዘፍቃ ነበር። ሃይማኖታዊ ክንውኖች ለታይታና ለይስሙላ እንጂ በመታዘዝና እግዚአብሔርን ከመፍራት የመነጩ አልነበሩም። ይህን ተግባር የሚፈጽሙ ሰዎች፣ ድኾችን የሚውጡ ወይም የሚያጠፉ፣ በዝባዦች ናቸው፤ አንዳች ርኅርኄ የሌላቸው ጨካኞች ናቸው።

ከእንጦሮጦስ የጠለቀ ስግብግብነት!

ነጋዴዎቿ ንግዱ ጣዖት ስለ ኾነባቸው፣ ሰንበት ባይኖር ጭምር እጅግ ይመርጣሉ፤ “እህልን እንሸጥ ዘንድ መባቻው መች ያልፋል? የኢፍ መስፈሪያውንም እያሳነስን፥ ሰቅሉንም እያበዛን፥ በሐሰተኛም ሚዛን እያታለልን፥ ድሃውን በብር ችጋረኛውንም በአንድ ጥንድ ጫማ እንገዛ ዘንድ፥ የስንዴውን ግርድ እንሸጥ ዘንድ ስንዴውን እንድንሸምት ሰንበት መች ያልፋል? …” (ቊ. 3-4) እንዲል፣ ነጋዴዎቹ ከእንጦሮጦስ ይልቅ በከፋው ስግብግብነታቸው፣ በሐሰተኛ ሚዛን ለማግበስበስ ካሰቡት ሃብት የተነሳ፣ ሰንበትን እንኳ ቢሽሩ ደስ ባላቸው ነበር።

ከቀኑ ማጠር ባሻገር፣ ሲሸጡ ደግሞ መልካሙን ስንዴ ከግርዱ ጋር በአንድነት ቀላቅለው ነበር። በማናቸውም መንገድ ቢኾን፣ ማትረፍ ብቻ ዋና መርኀቸው ነው። ሰንበትን በመጠበቅ ደግሞ የሚያህላቸው ሌላ አካል አልነበረም። ሃይማኖታዊ መልክ አላቸው ነገር ግን እግዚአብሔርን ፈጽሞ አያውቁትም። እንዲህ ካሉ ታላላቅ ማኅበራዊ ወንጀሎች ሊከተል የሚችለውን ጥፋት መጽሐፍ ቅዱስ ያለመታከት ይናገራል፤ ቍ. 3 ሊኾን ያለውን ሲናገር እንዲህ ይላል፤ “የመቅደሱ ዝማሬ በዚያ ቀን ዋይታ ይኾናል”። እንዴት ያለ አስጨናቂ ነው?!

ለኹለት ጌታ መገዛት አይቻልም!

እግዚአብሔርን የመውደዳችን ትክክለኝነትና ፍጹምነቱ የሚታወቀው ሌላውን ባልንጀራችንን መውደዳችን ስናሳይ ነው። ጌታችን ኢየሱስ በግልጥ እንዳስተማረው፣ “ባልንጀራህን እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት።” (ማቴ. 22፥37-39)፤ ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ፣ ለባልንጀራ አለማሰብ ከእግዚአብሔር እንዳይደለ፣ “ጽድቅን የማያደርግና ወንድሙን የማይወድ ሁሉ ከእግዚአብሔር አይደለም።” (1ዮሐ. 3፥10) ተብሎ ተጽፎአል።

ጌታችን ኢየሱስ እንዳስተማረን፣ “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም።” (ማቴ. 6፥24)። ብዙዎች ለእግዚአብሔር መንግሥት፣ ለግልና ለማኅበር አምልኮ ግድ እስከማይላቸው ድረስ በአታላዩና ዋሾው የብልጥግና ገንዘብ መውደድ ታስረውና ብኵርና ክርስትናቸውን ሲያንኳስሱ እናያለን። በድኾች ቀንበር ላይ የምንጭነው ቀንበር፣ በመጨረሻው ቀን ዋጋ እንደሚያስከፍለን እንዳንዘንጋ!

እግዚአብሔርን በትክክል የምንወድድ ከኾነ፣ ባልንጀራችንን በማናቸውም መንገድ ለመውደድ አንቸገርም። እግዚአብሔርን በትክክል የማይወድድ እርሱ፣ ባልንጀራውን ባይወድድ፣ የገዛ ወገኑን ቢጎዳ፣ በገዛ ወገኖቹ ላይ የማይገባ ነገር ቢያደርግ አንዳች አንደነቅም። ነገር ግን እናምናለን የሚሉት፣ እንዲህ ባለ ክፋት መያዛቸው እጅግ ልብ ሰባሪ ነው። በዚህ ሚዛን ዓለማችንን ስንመለከት፣ በብዙ ነገር ብልሹና ከኀጢአት አንጻር በፍጥነት እየፈረሰ መኾኑን ማስተዋል አይሳነንም። ከማኅበራዊ መበስበስ አደጋዎች አንዱና አደገኛው መገለጫችን፣ በየጊዜው እየጨመረ፣ በድኾች ጫንቃ እየተጫነና አያሌዎችን እየፈተነ፣ እየዋጠ ወይም እያጠፋ የመጣው የኑሮ ውድነት ወይም ልክ አልባ ስግብግብነት ነው። ስንቶቻችን ክርስቲያን ነጋድያን ከዚህ መንገድ ነጻ ኾነን ይኾን? ከእግዚአብሔር ጋር ብቻ ባለ ጽድቅ ለመኖር የጨከንን ስንቶች እንኾን?!

“ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)

No comments:

Post a Comment