Monday 7 March 2022

ከአምልኮተ ኢትዮጵያ ተጠበቁ!

 Please read in PDF

ብሔራዊ ቲያትር ላይ አድዋን አስመልክቶ በተዘጋጀው “ዝክረ አድዋ” መርሐ ግብር ላይ፣ “‘ከኦርቶዶክስ’ በቀር ሃይማኖት የለም!” ባዩ ዘበነ ለማ፣ “ሃይማኖቶችን አክብሮና ኢትዮጵያዊነትን አስመልኮ” መቅረቡ ይደንቃል! በትያትር ቤቱ አዳራሽ ያሉ ደግሞ፣ ጩኸታቸውና ጭብጨባቸው በትክክል “ምናባዊቷን ኢትዮጵያ” ተስላ እንጂ በእውን ሳያዩ በደንብ ይስተዋላል። ዘበነ ለማ ከተናገራቸው ንግግሮች ውስጥ እኒህ ደማቅ ትምክህቶች ጎልተው ይሰማሉ።


“… ነጮች፣ ኢትዮጲያዊን ሲመለከቱ በኢትዮጵያዊ ግንባር ላይ የእግዚአብሔር ስም አለ!”

“ማርቲን ሉተር “refermation” ጀርመን ላይ ሲጀምር፣ ጴጥሮስ የተባለ ኢትዮጵያዊ ነው ያማከረው፤ የሌለህበት የለም አንተ ቅመም ኢትዮጵያዊ …” ብዙ ጭብጨባ ይከተለዋል።

“… የግሪክ የአማልክት አምላክ ዜውስ፣ ኢትዮጵያ ሄዶ የኢትዮጵያ ሰዎች ልመና ምንም ሳይሸፍነው ሰማይ ስለሚደርስ፣ ከእነርሱ ጋር በዓመት እየሄደ ይጸልያል ይላል” … ከፍ ያለ ጭብጨባ ይከተላል።

እኒህ ንግግሮች፣ በውስጣቸው አያሌ ታሪካዊ ተፋልሶን የያዙ ናቸው።

1.   ሰው ኹሉ በእግዚአብሔር መልክና አምሳል ተፈጥሮ ሳለ፣ ኢትዮጵያዊ ምን የተለየ ነገር አለውና በግንባሩ የእግዚአብሔር ስም ታተመ? በኢትዮጵያዊ ግንባር ላይ የእግዚአብሔር ስም ከታተመ፣ በኤርትራው፣ በሶማሊያዊው፣ በማልታዊው፣ በቻይናዊው፣ በአፍጋኒስታዊው፣ በጂቡቲያዊውስ … አልታተመምን? በነጭና በጥቁር መካከል ሰዋዊ ምን የተፈጥሮ ልዩነትስ አለ? … አትታበዩ፤ በኵራትም አትናገሩ፤ በፉጨትና በጭብጨባም አትኮፈሱ!

2.   እውን ማርቲን ሉተር፣ ተሐድሶን ይዞ ሲነሳ፣ ኢትዮጵያዊ ነውን ያማከረው? ታድያ ይህ ኹሉ ጥላቻ በተሐድሶ ላይ መዝነሙ ከየት መጣ? ደቂቀ እስጢፋኖሳውያን ያሥነሱት እውነተኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ተሐድሶ ምነው በአንደበታችሁ አልመሰገን፣ ቅቡል አልኾን አለ? ይህን ምነው እስከ ዛሬ ከዘበነም ይኹን ከማኅበረ ቅዱሳን አንዱም ሲያወራ ምነው ሳንሰማው? መቼም ዘበነ በመድረክ ሞቅታ እንዳልተናገረው ተስፋ እናደርጋለን።

በእርግጥ ዘበነ፣ በኢትዮጵያዊው ጴጥሮስ(ጴጥሮስ የቱ እንደ ኾነና በምን መልኩ እንዳማከረው በግልጥ ባይናገርም) አማካይነት፣ ማርቲን ሉተር፣ ተሐድሶን በአውሮፓ ምድር አቀጣጥሎ ከኾነ፣ ለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ እንቅስቃሴ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ናት ማለት ነው። ይህን ግን ከቤተ ክርስቲያኒቱ የታሪክ ፍሰትና ትርክት አንጻር፣ ከባድና ሊታመን የሚከብድ ነው።

3.   አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፍት፤ ኢትዮጵያ በጥንት በሕገ ልቡናና በኦሪት ቀጥሎም በሕገ ወንጌል የነበረች እንጂ፣ ጣኦት አምልኮ ትከተል ነበር የሚለውን ፈጽመው ተቃዋሚ ናቸው። ዘበነ ግን የግሪክ አማልክት ጭምር ወደ ኢትዮጵያ ይተምሙ ነበር የሚለውን አንድ ጭብጥ ይዞ ብቅ ብሎአል። መልካምና ይበል የሚያሰኝ ነው። ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ኢትዮጵያን ወዳድ ሰባክያን፣ ኢትዮጵያ አሕዛባዊት አገር ናት የሚለውን ለመቀበል የሚዳዳቸው ናቸውና።

በፍጻሜ፣ ዘበነ ለማ በዚህ መንገድ መገለጡ ባይደንቀኝም፣ ጌታ ከዚህ እጅግ በላቀና እንደ ደማስቆ በተንቦገቦገ ብርሃን፣ ልቡን ለእውነተኛ ተሐድሶ እንዲያነቃቃ ጸሎትና ምልጃዬ ነው! ኢትዮጵያዊነት ከሌላው ከየትኛውም አገር ዘርና ነገድ፤ ቋንቋና ሕዝብ ፈጽሞ አይበልጥም፤ አያንስምም!

No comments:

Post a Comment