Saturday 26 March 2022

የካውንስሉ የማይቀር መንገዳገድ!

 Please read in PDF

ቅዱስ ቃሉ፣ “በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ትጉ።” (ኤፌ. 4፥3) እንዲል፣ ቤተ ክርስቲያን ከምንም ነገር ይልቅ መጠንቀቅ ያለባት ለመንፈስ አንድነትዋ ነው። መሲሑ በሊቀ ካህናትነት በጸለየውም ጸሎትም፣ “ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው።” (ዮሐ. 17፥11) የሚል ነው። ሰይጣን፣ ቤተ ክርስቲያንን ከሚፈትንበትና ድል ከሚያደርግበት አንዱና ዋናው መንገዱ፣ መለያየት፣ መከፋፈል፣ ክፉ የልዩነትን ዘር በመዝራት ነው። “አንድ ቤተሰብ እርስ በእርሱ ከተለያየ ጸንቶ መኖር አይችልም” እንዲል (ማር. 3፥25)።

የቤተ ክርስቲያን አንድነት፣ ተራ አንድነት አይደለም። በምድራችን ላይ አያሌ አንድ ያልኾኑ አንድነቶች አሉ። ለቤተ ክርስቲያን ግን የተባለላት አንድነት፣ “የመንፈስ አንድነት” ነው። አዎን፤ የክርስቲያኖች አንድነት የተመሠረተው፣ በሥላሴ ዘንድ ባለው “የመንፈስ አንድነት” ነው። በአብና በወልድ መካከል እንዳለ አንድነት፣ የክርስቲያኖችም አንድነት እንዲያ ሊኾን ይገባዋል። አብ ወልድን ይወደዋል፤ ወልድም አብን እንዲሁ። ክርስቲያኖችም ከሥላሴ ባዩት ፍቅር አማካይነት ሊዋደዱ ይገባቸዋል። የመንፈስ አንድነት መሠረቱ፣ ፍቅር ነው፤ ጌታችን ኢየሱስ፣ “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ፥ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ።” (ዮሐ. 13፥34) ብሎ አስተምሮናል።

ጤናማ ያልኾነ አመሠራረት

በአዋጅ ቍጥር 1208/2012 የተቋቋመውና “የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል” በሚል ስያሜ የተሰየመው፣ ከአመሠራረቱ ጀምሮ “በጎ” ነገር ያልነበረው ነው ማለት ይቻላል። ለዚህም ምክንያቶች አሉኝ፤

1.   በግና ተኵላን በአንድ ያቃኘ ጉባኤ ነበርና፤ “ክርስቶስን ያሰየጠኑ”፣ የሥላሴን ትምህርት በአደባባይ የካዱና ክርስቶስን ቤዛና አምላክ ብለው የሚያምኑ በአንድ ጉባኤ ተሰይመው ነበርና፣

2.   በአዋጁ መግቢያና አስፈላጊነቱን በሚናገርበት ክፍል እንዲህ የሚል ሐረግ አለ፤ “ … የኢትዮጵያ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናትና የአብያተ ክርስቲያናት ህብረቶች ያቋቋሙትን ሀገር አቀፍ ተቋም የሕግ ሰውነት መስጠት አስፈላጊ በመኾኑ” ይላል። ነገር ግን በተደጋጋሚ ሲጮኽና ሲለፈፍ እንደ ነበረው፣ መሥራቾቹ መንግሥትና የመንግሥት አጋፋሪዎች እንጂ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት እንዳልነበሩ አውቅ ነበር። በአዋጁ ውስጥ ተካትቶ ሲቀርብ ግን ገርሞኝም፤ ደንቆኝም ነበር።

3.   የካውንስሉ “በግና ተኩላን አስማምቶ” መያዙና መቋቋሙ፣ ለሌሎችም ክርስቲያናዊ ኅብረቶች ምሳሌነቱ እጅግ አደገኛና የሚመርዝ ነበር።

በኅብረቱ ጉዞ ውስጥ፣ የወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት መሪ ጉባኤያቸውን ረግጠው መውጣታቸውና በተቃራኒው ደግሞ የካውንስሉ መሪ የነበሩት የመንግሥት ኹነኛ ሹም መኾናቸው ልዩነቱን ይበልጥ አጕልቶ ያሳያል። የቁልቁለቱንም መንገድ ከዚሁ “መጀመሩን” ያመለክታል።

የካውንስሉ የቁልቁለት መንገድ

ካውንስሉ ውስጥ “ንቃቃት መፈጠሩንና ሊፈርስ እየተንገዳገደ” እንዳለ፣ በምሥረታው ወቅት “በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ከተመረጡትና አኹንም የመንግሥት ባለሥልጣን ከኾኑ” አንድ ሰው፣ ወሬው በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ተለቅቆአል። በርግጥ ካውንስሉ የቁልቁለቱን መንገድ የጀመረው፣ ከመንግሥት ጋር ተሻርኮ፣ ለጸሎትና ለአምልኮ አንድ ጉባኤ ላይ የማይገናኙ አካላትን ያቧደነ ቀን ነው። ከዚህም በከፋ ኹኔታ የካውንስሉ ስውር ዓላማ፣ ከወንጌላውያን ወገን የነበረ ሰው፣ “ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን መገዳደር” እንደ ኾነ፣ ባለፈው ወር “Youtube” ላይ ቃለ መጠይቁ ሲንቀለቀል ነበር።

እንግዲህ ካውንስሉ ከመጀመሪያውም በጎ አልነበረም ማለት ነው። እንደ እኔ እምነት፣ “አገልጋዮቹ” በካውንስሉ ምሥረታ አስባብ፣ በቤተ መንግሥት ግብዣ ላይ መገኘታቸው በራሱ ትክክል ነው አልልም። ቤተ ክርስቲያንና ቤተ መንግሥት ከጥንትም ዘመድና አጋር አይደሉምና። ፊልፕ ያንሲ፣ በአንድ ወቅት ቢል ክሊንተን የአሜሪካ ሰባኪያንን ሰብስበው ያወሩበትን እውነታ ሲናገሩ እንዲህ ይላሉ፤

“ከባህረ ሰላጤው ጦርነት በኋላ፣ ከዋይት ሀውስ ጥሪ ቀረበልኝ። ጉዳዩ ፕረዘዳንት ቢል ክሊንተን በወንጌላውያን ክርስቲኖያች ዘንድ ያላቸው ተቀባይነት መመናመኑ ስላሳሰባቸው ዐሥራ ሁለት ያህል አገልጋዮችን ለቁርስ ጠርተው፣ የምንለውን ለመስማት ነበር ያስጠሩን። እዚያ ተቀምጬ ሳለ፣ ‘ኢየሱስ በእኔ ቦታ ቢኾን ኖሮ ምን ብሎ ይመልስ ነበር?’ የሚለው ጥያቄ በአእምሮዬ ይመላለስ ነበር፤ ከዚያም ኢየሱስ ከአድራጊ ፈጣሪ የፖለቲካ መሪዎች ጋር ፊት ለፊት የተገጣጠመው አንድ ጊዜ ብቻ ሲኾን፣ ያም እጆቹ ታብተው፣ ጀርባውም ተተልትሎና ደም ተቋጥሮበት እንደ ነበር ታወሰኝ። ከዚያ ዘመን ጀምሮ፣ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት እጅግም ፍቅር ሆነው አያውቁም።”

ካውንስሉ ይህን ታላቅ እውነት ነው የሻረው። አኹንም እንዲህ እንላለን፤

1.   ቤተ ክርስቲያን ኅብረትዋን መመሥረት ያለባት፣ በኢየሱስ ትምህርትና ሕይወት ላይ ብቻ ነው። ማናቸውም ምክንያትና ሰበብ[“መንፈሳዊ” ነው ቢባልም እንኳ]፣ ከኢየሱስ ትምህርትና ሕይወት የሚለየን ከኾነ እርሱ ከሰይጣን ነው። የመንፈስ አንድነት ከሌለበት ጉባኤ፣ ለዘወትር ቤተ ክርስቲያን ራስዋን መከልከል ካልቻለች፣ ራስዋን ጭምር ጭካኔያቸው ወደር ለማይገኝላቸው ተኵላዎች አሳልፋ መስጠትዋ አይቀሬ ነው። እናም የካውንስሉ መንገዳገድ ብዙም አይደንቅም፣ ቀድሞም በጽናት ለመቆም የሚያበቃ፣ የኢየሱስ ሕይወትና ትምህርት አልነበረውና።

2.   በካውንስሉ ውስጥ የነበሩና ከቀድሞም ወንጌሉን በትክክል ይሰብኩ የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት፣ ከተኩላዎቹ ጋር ያሳለፉበትን ጊዜ በንስሐ በማደስ የመንፈስ አንድነታቸውን አጽንተው መያዝና ወደፊት መገስገስ ይገባቸዋል።

3.   ለዚህም በታሪክና በትውልድ ፊት ተጠያቂ ላለመኾንና የበጎች እረኛ አለቃ በኾነው በጌታችን ኢየሱስ ፊት አንገታቸውን እንዳይደፉ፣ ቅይጡን ኅብረት አፍርሰው፣ እውነተኛና በጌታ ኢየሱስ ትምህርትና ሕይወት ላይ የጸናውን ኅብረት ይዘው መቆም  ይገባቸዋል። “ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።

1 comment:

  1. ይህች ብሎግ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤተክርስቲያን እየተባባሱ የመጡ አማጻዎችን፣ክህደቶችና የስሐተት ትምህርቶችን፣በማጋለጥ ማስጠንቀቂያዎችንና ትምህርቶችን ለመስጠት የተዘጋጀች ናት።"" BUY THE TRUTH DON"T SELL IT ""

    ReplyDelete