Sunday 20 March 2022

የጌታ ያልኾኑ የጌታ ነበርን ባዮች!

 Please read in PDF

የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ፣ “ተሐድሶ ወይም ሐድሶ” የአንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንቅስቃሴ፣ በመኾኑ እንጂ፣ የአንድ ወይም የተለዩ አካላት መጠሪያ በመኾኑ አያምንም። አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፦ “ሐድሶ ማለት ማደስ፤ መለወጥ፤ ሐዲስ ማድረግ፤ ማጥናት ማበርታት፤ መሥራት መጠገን፤ ያሮጌ የሰባራ።” በማለት ተርጉመው፣ “ሐዳሲ ወይም ሐዳስያን ማለት ደግሞ፣ የሚያድስ የሚጠግን፤ ወጌሻ፤ ገንቢ፤ ዐናጢ” ብለው፣ ውጤቱን ደግሞ፣ “ተሐደሰ፤ ታደሰ፣ ተለወጠ፤ ዐዲስ ኾነ” በማለት በግልጥ የተረጐሙትን ትርጒም ታሳቢ በማድረግ፣ “ሐዳሲ ወይም ሐዳስያን” የሚለውን ቃል ይጠቀማል።

ሐዳሲነት፣ ጤናማ ትምህርትና ሕይወት ይፈልጋል!

እስራኤል፣ በኀጢአትዋ በባቢሎን ምድር እንደ ጨው ተበትና፣ በብርቱ ውድቀት ውስጥ በነበረችባቸው ወራት፣ ታላላቅ ሐዳስያንን እግዚአብሔር አሥነሳላት። ሐዳስያኑም አስቀድመው ያደረጉት ነገር ቢኖር፣ ቅዱስ ቃሉንና የእግዚአብሔርን ሕግ በመፈለግ ተጉ። ሕዝቡ ያለበትን ውርደትና ንቀት፤ መገፋቱንና መተዉን ተመለከቱ፤ እናም ስለ ራሳቸውና ስለ ሕዝባቸው በተደጋጋሚ፣ “አያሌ ቀንም ያዝኑ፤ በሰማይም አምላክ ፊት ይጾሙና ይጸልዩ ነበር፥” (ነህ. 1፥3)። እውነተኛ ሐዳስያን አስቀድሞ ቃሉንና የእግዚአብሔርን ፊት በመፈለግ እጅግ ይተጋሉ። ፈልገውም ባገኙት ጊዜ፣ በሕዝብ ኹሉ ጆሮ ያነብቡታል። “ወንዶችና ሴቶች የሚያስተውሉም ሲሰሙ፥ ከማለዳ ጀምሮ እስከ ቀትር ድረስ[ዕዝራ] አነበበው የሕዝቡም ሁሉ ጆሮ የሕጉን መጽሐፍ ለመስማት ያደምጥ ነበር።” (ነህ. 8፥3) እንዲል።

ሐዳስያን እውነተኞች ከኾኑ፣ ተሐድስያኑም ምላሻቸውና በሕይወታቸው ላይ የሚወስኑት ውሳኔ ጤናማና ትክክለኛ ነው። ሕዝቡም እንዲህ አሉ፤ “ስለ ክፉ ሥራችንና ስለ ታላቁ በደላችን ካገኘን ነገር ሁሉ በኋላ፥ አንተ አምላካችን እንደ ኃጢአታችን ብዛት አልቀሠፍኸንም ነገር ግን ቅሬታን ሰጠኸን። … አምላካችንን በድለናል፤ የምድርን አሕዛብ እንግዶች ሴቶችን አግብተናል፤ አሁን ግን ስለዚህ ነገር ገና ለእስራኤል ተስፋ አለ” (ዕዝ. 9፥13፤ 10፥2) ብለው፣ እውነተኛ ተሐድሶ የተሐድስያንን ልብ በመለወጥ፣ ኃጢአታቸውን በግልጥ ያሳያል፤ ከዚያም ወደ ንስሐ ይመራቸዋል። ቃሉ ሲገለጥ የእግዚአብሔር ክብር ይገለጣል፤ የሰው ኀጢአተኝነትም ይታያል፤ ሰዎችም ንስሐ ለመግባት ይደፍራሉ! አማናዊ ሐድሶ ወደ ቅዱስ ቃሉና ሕይወት የሚመልስ ሲኾን፣ እውነተኛ ሐዳሲም ዘወትር ቃሉን ይዞ የሚቆም ነው!

ዛሬ ላይ፣ “ተሐድሶ ነበርን ወደ እናታችን ተመልሰናል” የሚሉቱ አብዛኛዎቹ፣ ሐዳሲም፤ ሐዳስያንም አልነበሩም። እርግጥ ነው፣ “ይዘምሩ” ነበረ፣ ነገር ግን ዝማሬው የእነርሱና የሕይወታቸው ፍሬ አልነበረም፤ ባማሩና በተዋቡ አገላለጦች ወንጌል “ይመሰክሩ” ነበረ፤ ነገር ግን ከሕይወታቸው ያልተዋሐደ ነበረ።

በሥጋ ወፍሮ በነፍስ መክሳት!

ለእስራኤል እንዲህ ተብሎ እንደ ተነገረ፣ “የለመኑትንም ሰጣቸው፤ ለነፍሳቸው ግን ክሳትን ላከ።” (መዝ. 106፥15)። “ወደ እናት ኦርቶዶክስ ተመልሰናል” የሚሉ አካላት፣ የተመለሱት የአንድ ባለጠጋ ሎሌ ለመኾን እንጂ፣ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ አይደለም፤ በእርግጥ ሰውየው፣ ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ተመልሶ፣ “መጋቢ አእላፍ” የሚል ማዕረግ ተሰጥቶታል። በእርግጥም ለ“ተመልሰናል” ባዮቹ፣ ወርሐዊ ደሞዛቸውን እስከ ብር ሰባ ሺህ  በመክፈል፣ ለሥጋቸው መወፈሪያ ሳይቆጥብ በ“መግቦት” ይከፍላቸዋል። ነፍሳቸው ግን በማኅበራዊ ሚድያ እንደምንመለከተው ነው።

በእርግጥም የአብዛኛዎቹ ሕልማቸው ትልቅ ደመወዝ፣ የተሻለ ምድራዊ ኑሮ ነበር፤ ሰውየው ይህን ደካማ ጐናቸውን በሚገባ ስላጠና፣ “ከተሐድሶ ተመልሰናል በሉ” የሚል፣ ደማቅና ጕልህ ማስታወቂያ እንዲሠሩ ተጠቀመባቸው። እነርሱም ጠቀሙት። እና በኢየሱስ አፍሮ፣ ማርያምን ለመስበክና ፍጡራንን ለማስመለክ፣ ለፍጡራንም ለመዘመር፣ በሰው እጅ ለተሠራና በተገለጠ ኪዳን ለተሻረ ታቦት ለመስገድና ለማሰገድ … የበለጠ ምን የከፋ የነፍስ ክሳት አለ? እናም፣ ከሰው ተወዳጅነት ለማግኘት እያለቀሱ በዝማሬና በስብከት፣ "ኢየሱስ፤ ኢየሱስ" የሚሉ፣ በእልፍኝ ግን ልባቸው የሸፈተ ብዙዎች ገና አሉና፣ ሌሎችም "ተመልሰናል" ቢሉ አንደነግጥም!

ሐዳሲ ለመኾን በማናቸውም መንገድ፣ ከሥጋ አምሮትና ከነፍስ ክሳት ነፍስን በብርቱ መጠበቅ ያሻል። ፊተኛው እስራኤል፣ ስለ ሥጋ አምሮት እግዚአብሔርን ተፈታተኑ፤ እርሱም የሥጋ አምሮታቸውን ሰጥቶ፣ በነፍሳቸው ግን ክሳትን ሰደደ። ዛሬም ሐዳስያን ሳይኾኑ፣ ነን ያሉትን፣ የፈለጉትን የሥጋ አምሮታቸውን ማለትም፣ በሰው ዘንድ መወደድን፣ ቅይጥ አምልኮን፣ ብዙ ገንዘብን፣ አቦ አቦ መባልን፣ ልቅ ኑሮን … ሰጣቸውና ቅድስናን፣ ለኢየሱስ ብቻ መኖርን፣ ለቅዱሳት መጻሕፍት ሥልጣን መታዘዝን፣ አምልኮ ፍጡራንን መጠየፍን … ወሰደባቸው! ቢያውቁስ፣ ኢየሱስን አጊኝተው በምድር ኹሉ ፊት እንደ ጉድፍና ከንቱ ቢጣሉ፣ ቢናቁ፣ ቢተቹ … ሕይወትና የነፍስ መስባት በኾነላቸው ነበር። የእግዚአብሔር እስራኤል ሆይ፤ በሥጋ ሰብቶና ወፍሮ፤ ደንድኖ፣ በነፍስ መክሳት፤ መሞገግ አይኹንባችሁ! አሜን።

ማጠቃለያ

እግዚአብሔር ጻድቅ ነው፤ በፍርዱ አይሳሳትም፤ ዛሬም እውነተኛ ሐዳስያን አሉት፤ ዋላይና ወላዋይ፤ መልቲና ሸንጋይ የእግዚአብሔር ልጆች፤ የመንግሥቱ ሠራተኞች ባሕርይ አይደለም። የእግዚአብሔርን መንግሥት የሚሹና የሚያገለግሉ፣ ብርቱዎችና ራሳቸውን ከክርስቶስ ጋር በመስቀል ሰቅለው፣ ለእርሱ ብቻ የሚኖሩ ናቸው። “ከመጥምቁ ዮሐንስ ጀምሮ እስከ አኹን ድረስ መንግሥተ ሰማያት በብዙ ትገፋለች፤ የሚያገኟትም ብርቱዎች ናቸው” (ማቴ. 11፥2) ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ መንግሥተ ሰማያትን የሚያገኟት ለመንፈሳዊ ነገር የጨከኑ፣ እጅግ ብርቱ የኾኑ፣ ኀጢአትንና ኀጢአተኝነትን የተጠየፉ እንጂ፣ በጮሌ ጠባይ፣ በቀበሮ ማንነት፣ ለገንዘብ ለሃጭ በሚያዝረበርብ ባሕርይ ለተካኑ አይደለም። “ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።

No comments:

Post a Comment