Tuesday 8 March 2022

ኢየሱስ እስኪመጣ አሥር ዓመታት በጡመራ መድረክ አገልግሎት!

 Please read in PDF

እግዚአብሔር አምላኬ በብዙ ባበዛልኝ ጸጋ ተደግፌ፣ ላለፉት አሥር ዓመታት በጡመራ መድረክ (blog) አገልግያለሁ። ቅዱስ ጳውሎስ፣ “ከተመሠረተው በቀር ማንም ሌላ መሠረት ሊመሠርት አይችልምና፥ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ማንም ግን በዚህ መሠረት ላይ በወርቅ ቢሆን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ፥ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ በእሳት ስለሚገለጥ ያ ቀን ያሳያልና፥ የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል።” (1ቆሮ. 3፥11-13) እንዲል፣ አገልግሎቴ አንድ ጊዜ በተመሠረተው መሠረት ላይ እንጂ፣ አዲስ ወይም ወይም ሌላ መሠረት በመመሥረት አልነበረም። ምክንያቱም አዲስ መሠረትን ብመሠረትና ከኢየሱስ የተለየ ወንጌልን ብመሰክር አገልግሎቴ በእሳት ሊበላ አለውና።


በእሳት የሚበላ አገልግሎትን ለማገልገል አልደከምኹም፤ በከንቱ ለሚቀር ትጋት ኀጢአትንና ኀጢአተኝነትን አልጠየፍኩም፤ በክርስቶስ ፊት “ወዳጄ፤ ባሪያዬ” የማልባልበትን አገልግሎት፣ ለማገልገል አልታተርኩም። እናም እንዴትም ይኹን የትም ሳገለግል፣ ለቅዱሱና ለማይናወጠው መሠረት በብርቱ ተጠንቅቄ ለማገልገል ራሴን ሰጥቻለሁ። ምክንያቱም መድኀኒታችን፣ “በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታንም ሊፈርድ ባለው በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፥ … ቃሉን ስበክ፥ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ፥ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም።” የሚለው ቃል እጅግ ደምቆ ይሰማኛልና (2ጢሞ. 4፥1-2)።

የምሰብከው ወንጌል መሠረቱ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ የተመሠረተ ነውና ከቶ አይናወጥም፤ አይለወጥምም። ይህን መሠረት በመናድ ወይም በመሸርሸር ወይም በመሠረቱ ላይ በመሸቀጥ፣ በመጨመርና በመቀነስ በተወዳጁ መሲሕ ፊት ማፈርና አንገትን መድፋት፣ ክብርና መወደድን፣ በመንግሥቱም ስፍራ ማጣትን አልሻም፤ ከቶውንም አልፈልግም (2ጢሞ. 2፥15፤ 1ዮሐ. 2፥28፤ ማቴ. 5፥19፤ 19፥30፤ ሮሜ 2፥7)። ይልቁን በተሰጠኝ ጸጋና በምመላስበት ታላቅ ምሕረት በመታመን፣ ለጌታዬ ኢየሱስ ራስን በመስጠት በተገለጠልኝ ልክ ላገለግለው ገና ይገባኛል።

የተጠራሁለትና እንድታመንለት የተጋበዝኩት የመዳን ወንጌል፣ በቀጥታ እውነት፤ እውነት እንደ ኾነ እንዳምንና እንድታመንለት ደግሞም በሕይወቴ መግለጥና ፍጹም መመስከርን የሚሻ ነው። እናም ለዚህ ተጠርቻለሁ፣ ከእኔ ታላቅና የቅድስና ሕይወትን ይሻል። በእኒህ አሥር ዓመታት ለዚህ ብርቱና ላልተፈለሰፈ፣ በሰዎችም ላልደረጀና በክርስቶስ ኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ላይ ጸንቶ ለቆመ እውነት መታዘዝን መርጬ፣ አሥር ዓመታት በጡመራ መድረክ አገልግያለሁ። በእነዚህ አገልግሎቶች ቀኛችሁን ለሰጣችሁኝ ኹሉ ጸጋ ሰላም ይብዛላችሁ። ደግሞም ከፊት ይልቅ እተጋ ዘንድ ጸልዩልኝ። ኢየሱስ እስኪመጣ ገና በምሕረቱ እተጋለሁ! “ጌታችንን ኢሱስ ክርስቶስን በማይጠፋ ፍቅር ለሚወዱ ኹሉ ጸጋ ይኹን፤ አሜን” (ኤፌ. 6፥24)።

No comments:

Post a Comment