Saturday 1 May 2021

የሕማም ሰው

Please read in PDF

ነቢዩ ኢሳይያስ ስቁዩንና መከራ ተቀባዩን መሲሕ፣ “ደዌን የሚያውቅ የሕማም ሰው” ብሎ ይጠራዋል (ኢሳ. 53፥3)። መሲሑ መከራን የማይቀበልና ሕመም ተጠያፊ አይደለም፤ ይልቁን ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ መኾኑን” (ፊልጵ. 2፥8) በግልጥ ተናገረ። መሲሑ ለመታመም የፈቀደ፣ ለመድቀቅ የወደደ፣ ለመዋረድ ክብሩንና ጥቅሙን ኹሉ በፈቃዱ የተወ፣ እግዚአብሔር ነፍሱ የተደሰተችበት ጻድቅ ባሪያ ነው (ኢሳ. 53፥11)።

ይህ ለየትኛውም አይሁዳዊ ወይም “ደግ ሰው ክፉ ነገር ሊያገኘው አይገባም” ብሎ ለሚያምን ኹሉ፣ ለመቀበል የሚያዳግት እጅግ አስደንጋጭ እውነት ነው። አብዛኛው አይሁዳዊ በቅቡዕ መሲሕነት፣ መሲሑን የጠበቀው ከሮማ ባርነት ነጻ ያወጣናል፤ ይቤዠናል ይታደገናል ብሎ ነው፤ ይህ ተስፋ በሐዋርያት ልብ ሳይቀር የነበረ ነው። እነርሱ ለሕማም ሰውነት የመጣ መኾኑን ለማመን የተዘናጉ ይመስላሉ፣ “ጌታ ሆይ፥ በዚህ ወራት ለእስራኤል መንግሥትን ትመልሳለህን?” (ሐዋ. 1፥6) ብለው ሲጠይቁት፣ ልባቸውና ዐሳባቸው በአገራቸውና በምድራዊ ወገኖቻቸው ላይ ብቻ የተተከለ ነበር።

ነገር ግን መሲሑ በሰው መንገድና ዐሳብ፣ የሰውን ልጅ ሊያድን አልመጣም፤ “በስብከት ሞኝነት የሚያምኑትን ሊያድን የእግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖአልና” (1ቆሮ. 1፥21) ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ የክርስቶስ የሕማም ሰው ኾኖ ወደዚህ ምድር መምጣት፣ በእርሱ ለማያምኑና ለዓለማውያን ኹሉ እጅግ ሞኝነትና ትምህርቱም እምብዛም ተቀባይነት የሌለው ነው። ዛሬ ላይ ይህ ኢ ቅቡልነት በማያምኑና በዓለማውያን ዘንድ ብቻ ሳይኾን፣ “እናምናለን፤ መጽሐፍ ቅዱስን እናስተምራለን፣ የእግዚአብሔር መንገድና እውነት ገብቶናል” በሚሉትም ዘንድ የክርስቶስ የሕማም ሰውነት የተወደደ አይደለም።

መሲሑ ግን የሕማም ሰው ነው፤ የሕማም ብርታቱንም በተመለከትን ጊዜ እንዲህ ተብሎ ተነግሮአል፣ “እኛ ግን እንደ ተመታ በእግዚአብሔርም እንደ ተቀሠፈ እንደ ተቸገረም ቈጠርነው።” (ቊ. 4)። ልክ በእግዚአብሔር እንደ ተመታ፣ እንደ ተቀሰፈ፣ እንደ ተቸገረ ሰው አየነው። የደረሰበት ኹሉ የደረሰበት፣ ልክ አንድ ኀጢአተኛ ላይ እንደሚደርስ ቅጣትና ስቃይ ተመለከትነው። በእርግጥም በመሲሑ ላይ የኾነውና የደረሰበት እንዲህ ያለ ጽኑ ሕማም ነበር።

ሕመሙ አካላዊ ብቻ ሳይኾን፣ አእምሮአዊም ነበር። በዱላ የተመታ፣ የቈሰለና እጅጉን የደማ ብቻ አይደለም፤ ምራቅ የተተፋበትና የተናቀ፣ ከሰው ልጆች አንዳችም ከበሬታን ያላገኘ፣ እኛም ጭምር ፊታችንን ከእርሱ በማዞር ከበሬታን የነፈግነው ነበር። መሲሑ ፈጽሞ ሥቃይ ያልተለየው እጅግ ታማሚ ነበር። በእርግጥ ሕመሙ ሰውን በመውደዱ የኾነ ነውና፣ ብዙ ልጆችን ወደ አባቱ ያቀርብ ዘንድም በጽኑ ሕመም ታምሞ በመታመን አፈቀረን።

ክርስቶስ ስለ መዳናችን የታመመ እውነተኛ አፍቃሪ ነው። ስለ መዳናችን የትኛውንም ዝቅታ ዝቅ በማለት፣ እንደ ሰው ዐሳብና አሠራር እጅግ ሞኝነትና ጥበብ የማይመስልን መንገድ በመከተል፣ በእርሱ የሚታመኑትን የታደገ፣ የአዲሲቱ የእግዚአብሔር እስራኤል ቅዱስ ታዳጊ ነው። አፍቃሪ በእርግጥ ብዙ ጊዜ ታማሚ ነው፤ በእውነት ከልብ እጅግ ያፈቅራልና፣ ተፈቃሪ ብዙ ጊዜ ፍቅሩን አይረዳለትምና።

እንኪያስ ተወዳጆች ሆይ! እንዲህ በጽኑ ሕመምና ሥቃይ ባልተለየው ሰውነት ፍጹም የወደዳችሁን የሕማም ሰው አያችኹትን? አስተዋላችኹትን? እርሱ ስለ ኹላችን የታመመ፣ ጽኑ የቆሰለ፣ የደቀቀ፣ የተሰበረ … መድኃኒታችንና ቤዛችን ነው። እንግዲህ ፍቅሩን በመግፋት ዳግም አታሳምሙት፤ አፍቃሪያችሁን ችላ በማለት አትበድሉት፤ ዘወትር ከእናንተ ጋር መኾን ይሻልና በፍቅር ተከትሎ እንዳዳናችሁ፣ እናንተም በፍቅር እንድትከተሉት፣ እርሱ እናንተን ወዶ ባፈቀረበትና ዋጋ በከፈለበት፣ በሕማሙ፣ በመስቀሉ ርኅራኄ እለምናችኋለሁ።

ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመጥፋት ከሚወዱ ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን። (ኤፌ. 6፥21)።


3 comments:

  1. አንተን ብሎ ስለ ኢየሱስ ተናጋሪ

    ReplyDelete
  2. ጌታ አብዝቶ ይባርክ ዘመንህ እንዲው እንዳማረ በመልካም ይለቅ !

    ReplyDelete