Saturday 15 May 2021

መድሎተ ስሑት ወይስ “መድሎተ ጽድቅ”?! (ክፍል ፰)

 Please read in PDF

 ካለፈው የቀጠለ …

 እምነት፦ ሰው፣ በእግዚአብሔር ላይ ያለውን መደገፍ ከሚገልጥበት መንገድ አንዱና ተቀዳሚው እምነት ነው። እግዚአብሔር ለዘላለም እርሱም፤ ቃሉም ታማኝ ነው (2ጢሞ. 2፥13፤ ቲቶ 3፥8)። አማኝ እግዚአብሔር በተናገረው ቃሎቹ ላይ ፍጹም መደገፉ እርሱ እምነት ነው። እኛ በእግዚአብሔር ላይ ጥገኞች ነን፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር የፍጥረቱ አካል አይደለም፤ ይልቅ ፍጥረቱን ብቻውን ፈጥሮአልና እርሱ ከፍጥረቱ እጅግ የተለየና ምጡቅ ነው። ፍጥረት በእርሱ ይደገፋል፣ የእርሱን መግቦት ይጠባበቃል፤ እግዚአብሔር ግን በፍጥረቱ ፈጽሞ አይደገፍም።



ፍጥረት በእግዚአብሔር የሚደገፍና መግቦቱን የሚጠባበቅ በመኾኑም፣ “እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ኹሉንም ለኹሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም።” (ሐዋ. 17፥25)። ከፍጥረት እጅግ ምጡቅ ቢኾንም፣ ነገር ግን ፈጽሞ ከፍጥረቱ የተለየና ዓለሙን ፈጥሮ የተወ አይደለም። ፍጥረቱን ይመግባል፣ ይንከባከባል፣ ይጠብቃል። በተለይም አማኞች በእግዚአብሔር፤ በተናገራቸው በተስፋ ቃሎቹ ላይ ፍጹም በመደገፋቸው፣ እውነተኛ አማኞች መኾናቸው በዚህ ይታወቃል።

“የክርስትና ሃይማኖት በሰው ነፍስ ውስጥ የሚተከለው፥ ሰው የሃይማኖት ዘር የኾነውን የወንጌልን ቃል በእምነት ሲቀበል ነው።”[1] “እንዲሁም ለተሰጠው ተስፋ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ይሆንልኛል ይደረግልኛል … አሜን ወአሜን ብሎ ያለ ማወላወል በሙሉ ልብ እግዚአብሔርንና ቃሉን በተአምኖ ሲቀበል ነው።”[2] ስለዚህም ስለ እምነት ስናወራ እግዚአብሔርን ራሱን ወይም ቃሉን ማመንና ተስፋ ማድረግን ያመለክታል።

ከዚኹ ጋር በተያያዥነት ደግሞ፣ “የክርስቶስን ማንነት በትክክል ማወቅና ማመን የክርስቲያን ሃይማኖት መሠረት ብቻ ሳይኾን ከሌሎችም ሃይማኖት የምንለይበት መመዘኛና መለኪያ ነው።”[3] ራሱ የ“መድሎተ ጽድቅ” ጸሐፊም እንደሚለው፣ “… እግዚአብሔር በቅዱሳት መጻሕፍት እንዲሁም በሥጋዌው[በኢየሱስ ክርስቶስ] የገለጸውን የእውነት ትምህርት (ሃይማኖት) ሳይቆነጻጽሉና ሳያጎድሉ በምልአት መቀበልና ማመን ነው።”[4] ነገር ግን ጸሐፊውም ለዚህ ታላቅ እውነት ሲታመንና ሲገዛ አንመለከተውም።

እንኪያስ፣ አንድ ሰው “በልጁ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፤ በልጁ የማያምን ግን የእግዚአብሔር ቍጣ በእርሱ ላይ ይኖራል እንጂ ሕይወትን አያይም።” (ዮሐ. 3፥36) የሚለውን ቃል ሰምቶ ቢያምን፣ በጌታ ጎን ከተሰቀሉት መካከል እንደ ዳነው አንዱ ወንበዴ፣ ወዲያው ይድናል። መጽሐፍ የዘላለም ሕይወት ምን እንደ ኾነ ሲናገር፣ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የኾንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።” (ዮሐ. 17፥13) ብሎአልና።

ሰዎች፣ ስለ እምነት እኒህን ሦስት ነገሮችን ማስተዋል ይገባቸዋል። ይኸውም፣

1.   ሰዎች ስለ እግዚአብሔር ሊያውቁ፤ ሊረዱም ይችላሉ። የመላለሙን ፍጥረት አልያም ተአምራትን አይተው ወይም ደግሞ፣ እንደ አጋንንት ባለ እምነት ሰዎች ስለ እግዚአብሔር ዕውቀት ሊኖራቸው ይችላል (ያዕ. 2፥19)። እኒህ ሰዎች አስደናቂ ነገርን ሊናገሩ ይችላሉ፤ ለምሳሌ፦

“አምላኬ ሆይ፥ በመካነ ደይን(ገሃነመ እሳት) መቃጠልን ፈርቼ አንተን እያመለክሁ ብገኝ፥ በገሃነም አቃጥለኝ፤

በገነት ምኞት ተጠምጄ አንተን ያመለክሁ ቢመስለኝ፥

ከደጃፉ አታድርሰኝ፤

ነገር ግን አንተን በመፈለግ ብቻ እያመለክሁ ብገኝ፥

ዘላለማዊውን ውበትህን አየው ዘንድ እርዳኝ።”

የልመናው መልእክት በጣም ጥልቅ ነው። ምንስ እንከን ይወጣለታል? ኾኖም፥ ሳያገኙት ማረፍ የለማ። በክርስቶስ በኩል ቅሩብ የኾነውን አምላክ ሳያውቁ እረፍት የማይገኝበት የሕይወት በረሓ ውስጥ ነፍስ በመዛል በትር ትደቈሳለች።”[5]

2.   ክርስቶስን በማመን የምንድንበት እምነት አለ፤ ይህ ክርስቶስ እንደ ሞተና እንደ ተነሣ በሙሉ ልብ ማመን፣ ለዚህም እውነት ኹለንተናችንን ማስገዛት (ሮሜ 1፥16-17፤ 6፥17-18፤ ዕብ. 10፥22)። ይህም የመዳን እምነት በስጦታነት የሚገኘውም ከራሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፤ “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም፥” (ዮሐ. 6፥44)፤[6]በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጽድቅ ካገኘነው ጋር የተካከለ የክብር እምነትን ላገኙ፤” (2ጴጥ. 1፥1-12) እንዲል። (እንዲሁም በተጨማሪ ኤፌ. 2፥8-9 እና 2ተሰ. 2፥13 ይመልከቱ)።

ይህ የመዳን እውነተኛ እምነት የንስሐ እምነትም ያለው ነው (ሐዋ. 2፥37፤ ማቴ. 3፥2)። ይኸውም በክርስቶስ በኩል ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ  የሚደረግን እውነተኛ ጸጸትና ኑዛዜያዊ መንገድን የሚያመለክት ታላቅ የመዳን እምነት ነው። ዘወትር መዘንጋት የሌለብን ነገር፣ እግዚአብሔር እንዲሁ በነጻ የዘላለምን ሕይወት በክርስቶስ ኢየሱስ ሰጥቶናል። ምክንያቱም መክበር በከንቱ ወይም እንዲያው የኾነው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ካሳ ድኅነት በመገኘቱ ነው።[7] ይህን የነጻ ስጦታ እንድንቀበልም የእምነትን አቅም የሚሰጠንም እርሱ ነው። ክርስቶስን በማመን የሚገኘው የመዳን ጸጋ (ሮሜ 3፥22፡ 24-25፡ 28) የሚገኘውና የሚሰጠን በጸጋው መንገድ ብቻ ነው (ዮሐ. 1፥16)፤ ይህን ማመን ይገባል።

መጽሐፍ ቅዱስ አንዳች ማብራራት በማያሻው መንገድ መዳናችን ሙሉ ለሙሉ በእግዚአብሔር የተሠራና እኛም በእምነት ብቻ መቀበል እንዳለብን እንዲህ በማለት አጽንቶ ይናገራል።

“አብርሃም በሥራ ጸድቆ ቢኾን ኖሮ፣ የሚመካበት ነበረው፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር መመካት አይችልም።” (ሮሜ 4፥2)

ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ። ነገር ግን፦ የሚመካ በእግዚአብሔር ይመካ ተብሎ እንደ ተጻፈው ይኾን ዘንድ፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጥበብና ጽድቅ ቅድስናም ቤዛነትም በተደረገልን በክርስቶስ ኢየሱስ የኾናችሁ ከእርሱ ነው።” (1ቆሮ. 1፥29-30)

3.   ክርስቶስን አምነን ደግሞ በሕይወት ዘመናችን ኹሉ በመታዘዝ የምንኖርለትና የመንፈስ ፍሬ የሚኾን እምነትም አለ። ይህ እምነት ያድጋል፤ ይበዛል፤ (ማር. 9፥24፤ ሮሜ 4፥19-21፤ ያዕ. 2፥22-24)። ያመነው ሰው ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ ክርስቶስን በማመን ዳግመኛ የተወለደ በመኾኑ፣ “እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካም ሥራ እንዲሠራ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠረ የእግዚአብሔር እጅ ሥራ ነውና።” (ኤፌ. 2፥8-10)።

ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ያለውን እምነት ከመንፈስ ፍሬዎች አንዱ እንደ ኾነ ይነግረናል (ገላ. 5፥19)። ይህም እምነት እንደ ሌሎች የመንፈስ ፍሬዎች የሚያድግ፣ አእላፍ ፍሬዎችን የሚያፈራ፣ ከታላቁ ከእግዚአብሔር ጸጋና ስጦታ የተነሣ ብዙ መንፈሳዊ ሥራዎችንም የምንሠራበት ነው። አማኞች፣ እንደ አጋንንት ያይደለ የሚያውቁትን አምላክ ይታዘዙታል፤ ይገዙለታል፤ ያከብሩታል፤ ያመልኩታልም።

የ“መድሎተ ጽድቅ ጸሐፊ” የእምነት ትርጕም ስህተቱ

“እምነት እንጂ እምነት ብቻ አያድንም[8]፣ እንዲሁም መዳን በአንድ ቅጽበት፣ ያውም ምሥጢራትን ኹሉ ሳያካትት፣ እንዲሁ በእምነት ብቻ ይፈጸማል ማለት ስህተት ነው፤ … ሰው ያለ እምነት፣ ያለ ምሥጢራት “ሰው በምግባሩ በሚያደርገው ጥረት፣ ሰባቱን አጽዋማት በመጾም፣ ምጽዋት በመመጽወት” ብቻ ይጸድቃል አንልም።”[9] “መጽሐፍ ቅዱስ “በእምነት ብቻ” ስለ መዳን አንድም ቦታ አይናገርም። … ” እንዲሁም፣ እጅግ ድፍረት በተሞላበት ንግግር፣ “… ይህን የመዳን ጸጋ በአማናዊ መንገድ የሚያገኝባቸውንና የራሱ የሚያደርግባቸውን ምስጢራት - ጥምቀት፣ ሜሮን እና ቅዱስ ቁርባን ሲፈጽም ነው።”[10] በማለት፣ እግዚአብሔር እንዲያው በጸጋው በክርስቶስ በኩል የሰጠውን የመዳን ስጦታ አምኖ ቢቀበል፣ ብቻውን በቂ እንዳልኾነና እንዲህ ብሎ መናገር ለኀጢአት ነጻነት እንደ መስጠት ነው ብሎ ሲናገር እንሰማዋለን።

በዚህ አባባሉ ውስጥ ግልጥ ስህተቶች አሉ፤ እኒህንም ለይተን ማውጣት እንችላለን፦

·        ሰው በጸጋው እንዲያው በማመኑ ይድናል ማለት፣ በኀጢአት ይጨማለቃል ማለት አይደለም፣

·        በጸጋ መዳን ማለት፣ የጽድቅ ሥራን እንድንጥል አያደርግም፤

·        የምንፈጽማቸው የጥምቀትና የጌታ እራት ተግባራት፣ የመንፈስ ቅዱስ በአማኙ ሕይወት ውስጥ የሚሠራውን እንደ ዳግመኛ መወለድ ያሉትን ታላላቅ የእምነት ተግባራትን በፍጹም ተክተው ይሠራሉ ማለት አይደለም።

ከጌታ ጋር ከተሰቀሉት አንዱ በእምነት ጸድቋል (ሉቃ. 23፥43)፤ የብዙዎች አባት አብርሃም ገና ሳይገረዝ፣ እምነቱ ጽድቅ ኾኖ ተቈጥሮለታል (ሮሜ 4፥9)፤ “ሳይገረዝም በነበረው እምነት ያገኘው የጽድቅ ማኅተም የኾነ የመገረዝን ምልክት ተቀበለ፤” እንዲል (ቊ. 11) ግዝረት የጥምቀት ምልክት ከኾነ፣ አብርሃም ደግሞ ሳይገረዝ ከጸደቀ፣ እንኪያስ በእግዚአብሔር የማመን እምነት ከግዝረት፤ ከውኃ ጥምቀትም ይበልጣል። ይኹንና ስለ ማመናችንና ወደ ቤተ ክርስቲያን አንድነት ስለ መጨመራችን ምስክር ይኾነን ዘንድ እነሆ፤ እየመሰከርን እንጠመቃለን።

ስንጠቀልል፦

·        ሰው በራሱ ሥራ እንደሚድን የሚታመንም ከኾነ፣ የክርስቶስን ሥራ ፈጽሞ ያናንቃል፤ ያዋርዳልም። ልክ ቅዱስ ጳውሎስ “ክርስቶስም ካልተነሣ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት፤” (1ቆሮ. 15፥14) እንዲል፣

·        እግዚአብሔር መዳንን፣ በእምነት ሠርቶና መንገዱን አዘጋጅቶ ሳለ፣ ነገር ግን እኔ በሥራዬ ነው የምድነው ማለት፣ ይህ እግዚአብሔርን አለማመን፤ አለመታመን፤ መንገዱንም ኹሉ መንቀፍ ነው።

·        ሰው መልካም ሥራን በራሱ ማድረግ አይችልም፤ ምክንያቱም ሰው፣ “ከኀጢአት የተነሣ ከፍጥረቱ የቊጣ ልጅ ነበርና” (ኤፌ. 2፥2)። ስለዚህ ሰው ጽድቅን ይሠራ ዘንድ፣ ከሞተና ከተበላሸው ከራሱ ማንነት መንጻትና መዳን ይገባዋል። መልካም ሥራ የሚሠራው፣ ከዳነበትና በክርስቶስ ከጸደቀበት ማንነቱ የተነሣ ብቻ ነውና።

·        ሰው በራሱ ሥራ የሚደገፍና የሚታመን ከኾነ፣ ይህ ፈጽሞ እርግማንና ከንቱነት ነው።

“ነገር ግን ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ እንዳይሆን አውቀን፥ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በሕግ ሥራ ስለማይጸድቅ፥ እኛ ራሳችን በሕግ ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ እምነት እንጸድቅ ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነናል።” (ገላ. 2፥16)። አሜን።

ይቀጥላል …

 



[1] የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 9ኛ እትም፤ ገጽ 178

[2] ሊቀ ጉባኤ አበራ በቀለ፤ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት፤ ገጽ 20

[3] ዝኒ ከማኹ ገጽ 22

[4] ገጽ 124

[5] ሰሎሞን አበበ ገብረ መድኅን፤ የተቈረሱ ነፍሶች፤ 2009 ዓ.ም፤ ዐዲስ አበባ፤ አሳታሚው ያልተገለጸ፤ ገጽ 70

[6] የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሊቃውንት ይህን የወንጌል ቃል ሲተረጕሙት በግልጥ እንዲህ ብለው ተርጕመዋል።  “የላከኝ አባቴ በሀብት ስቦ በረድኤት አቅርቦ ካልሰጠኝ በኔ ማመን የሚቻለው የለም።” (ወንጌል አንድምታ፤ 1997 ዓ.ም፤ ገጽ 409) ሊቀ ጉባኤ አበራም፣ “ወደ ክርስቶስ የሚመጣም ኾነ የሚያምን ኹሉ በቅድሚያ “ከእግዚአብሔር አብ የሰማ የተማረም” በጸጋውም የተጠራ መኾን አለበት” ብለው ተረድተውታል፤ ትምህርተ ሃይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት፤ ገጽ 176)

[7] የቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት አንድምታ፤ 1988 ዓ.ም፤  ገጽ 43

[8] ገጽ 183

[9] ገጽ 184-185

[10] ገጽ 215

9 comments:

  1. GOD bless you for sharing Abiny. May the SPIRIT be your guide and strength for days to come!!!!!!!!!

    ReplyDelete
  2. ለረከሰ አላማሕ ስtiል ብዙ ባtiራመድ መልካም ነው መጀመሪያ የራስሕን ስም አስteካክል ለምስር ወጥ ስtiል በየፖስtu የምለጥፈው የእስከዛሬው ኑፋቄሕ አይበቃሕም ፤ ቆይ አንድ ጥያቄ ልጠይቅሕ "ጸሎte ሐይማኖtiን" ሳtiማር ነው እንዴ ዲቁና የteቀበልከው ?

    ReplyDelete
  3. አንተ ደንቆሮ ምናምንቴ ዝም ብለህ አርባ ስምንት ስዓት ለፍርፋሪህ ስትል 365 ቀናት ሙሉ ታቀረሻለህ? ድሮስ ከደንቆሮ ፓስተር ምን ይጠበቃል።

    ReplyDelete
  4. አንተ ደንቆሮ ምናምንቴ ዝም ብለህ አርባ ስምንት ስዓት ለፍርፋሪህ ስትል 365 ቀናት ሙሉ ታቀረሻለህ? ድሮስ ከደንቆሮ ፓስተር ምን ይጠበቃል።

    ReplyDelete
  5. ቀላዋጭ ምን አገባህ ታዲያ!

    ReplyDelete
  6. ወሬ ብቻ

    ReplyDelete
  7. አንተ ሰው ምንድነው ችግርህ?የእአምሮ መቃወስ ደርሶብሃል እግዜር ከመዳኒቱ ያገናኝህ እአምሮን ፈትሽ

    ReplyDelete
  8. ወዳጄ ማነስ መውረድ ይባላል!!! ሃሳብ የማመንጨት አቅም ማጣት። ሌላ ምን ይባላል!!!

    ReplyDelete