Saturday 8 May 2021

ግንቦት ልደታና የሕይወት ትዝታዬ!

 Please read in PDF

የዛሬ አሥራ ሰባት ዓመት ገደማ፣ ነፍሴ ከግንቦት አንድ አምላኪያን እጅ ያመለጠችበት ቀን ነው። በዚያን ቀን፣ በአርሲ ነጌሌ ሶጊዶ ማርያም ቤተ ክርስቲያን በዓለ ንግሡ ላይ ላገለግል ተጠርቼ በዚያ ነበርኩ። “የተሸሸገ ጣዖት” በሚል ርዕስ፣ የያዕቆብ ሚስት ራሔል ጣዖትን መሸሸጓንና በዚህም የደረሰባትን በማንሳት አንስቼ አገለገልሁ፤ እኛም ይህን ማድረግ እንደሌለብን ብርቱ ማስጠንቀቂያ በማኖር ጭምር። ነገር ግን በዚያን ቀን ሳስተምር፣ ከታቦቱ ጎን ትምህርቴን ቆሞ ይሰማ የነበረ፣ የገጠር ከተማይቱ ጠንቋይ ደም በሰረበ ዓይኖቹ ይመለከተኝ ኖሯል።

ስብከቱን ጨርሼ ስወርድ ቀሳውስቱን፣ ጠንቋዩ ሰውዬ አንቈራጠጣቸው፤ ማን እንደ ኾነ ስጠይቅ ጠንቋይ እንደ ኾነ ነገሩኝ። ወዲያው ታቦታቱን የተሸከሙት ቀሳውስት፣ ለበአሉ ደም ወደ ፈሰሰበት ቦታ አቀኑ፤ ደሙን ተራመዱ፤ ከዚያም ኹሉ ነገር፣ በጠንቋዩ አጋፋሪነት ተከናወነ። የእኔ የጣዖትን ነገር ነቅፎ ማስተማር ጠንቋዩን አላስደሰተውም፤ እናም የምመለስበት ቀን ጠብቀው በመንገድ ላይ እኔን የሚያጠቁ ሰዎች ተዘጋጁ፤ ነገር ግን እጅግ ፈጣን ሯጭ ነበርኩና [“ሚሽነሪ” አገልጋዮች ለካ ስፖርት የሚሠሩትና ሩጫ የሚለማመዱት እንዲህ ባለ ቁርጥ ቀን በረው ለማምለጥም ጭምር ነው?]፣ በበረራ ነፍሴን ከእጃቸው በእግዚአብሔር ረድኤት አስመለጥኹ። በዚያን ቀን እንዳገለግልና ጣዖትን በመቃወም እንዳስተምር አስበውበት የጋበዙኝ ወንድሞች ለማና አበራ ነበሩ፤ (ዛሬ የት ኾነው ይኾን?)።

በግንቦት አንድ ቀን በማርያም ስም ወደ ወንዝ ተወርዶ ለባዕድ አምልኮ ማረድ፣ የተቀቀለና የተቆላ እህል መድፋት፣ የበሰለ ቂጣ መወርወር፣ ቅቤ ዛፎችን መቀባት፣ አድባራት ሥር መሰብሰብ፣ መለማመንና አማልክትን መማጠን እጅግ የተለመደ ተግባር ነው። ድርጊቱ እጅግ የባዕድ አማልክት ልምምድ ያለበት ቢኾንም፣ አንዳንዶች የማርያምን ልደት የማርያም ወላጆች በሊባኖስ ዱር ውስጥ እንዳከበሩ፣ እኛም ከቤት ወጣ ብለን በዓሏን እናከብራለን ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ ከፍጹም የባዕድ አምልኮ ልምምድ ጋር በማያያዝ ሲያከብሩ ይስተዋላል። የማርያምን ልደት በሚያከብሩ በአንዳንዶች ዘንድ ታቦታት ባዕድ አምልኮ ወደሚፈጸምባቸው ወንዞች የሚወርዱበት ጊዜም እጅግ ብዙ ነው።

ምንም እንኳ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን “ክርስቶስን ብቻ ነው የማመልከው” ብትልም፣ እንዲህ ያሉ ግልጥ ባዕድ አምልኮአዊ ልምምዶችን በአደባባይ ስታወግዝና ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ መኾናቸውን ስትኮንን አይስተዋልም። ግንቦት አንድ ቀን፣ የሚከናወነው ኹሉም ተግባራት ከባዕድ አምልኮ ጋር ፍጹም ቁርኝት ያለው ነው። ይህን ሃይማኖታዊ ሽፋን መስጠት፣ ባዕድ አምልኮን በግልጥ የመደገፍ ያህል እንጂ ፈጽሞ እውነት ነው ሊያስብለው አይችልም። ባዕድ አምልኮ በእግዚአብሔር ፊት ጽዩፍና እጅግ አስነዋሪ ተግባር ነውና። እንዲህ ዓይነት ልምምድ ያላቸውን እግዚአብሔር እጅግ ይጠየፋል። ከእርሱ ውጭ ሊታመን፣ ሊለመን፣ ሊማጠን የሚገባ መለኮታዊ ኀይል በላይ በሰማይ፤ በታች በምድር ፈጽሞ የለምና።

እንዲሁም፣ የክርስቶስን መስቀል የሚጋርድ የትኛውም ትምህርት፣ ልምምድ፣ ማኅበራዊ እሴት እርሱ የክርስቶስ መስቀል ጠላት (ፊልጵ. 3፥18)፣ እንግዳ ትምህርት (2ቆሮ. 10-13)፣ አዲስ ወይም ልዩ ወንጌል (ገላ. 1፥8)፣ በጌታ ትምህርት ደግሞ እንክርዳድ (ማቴ. 13፥25) ተብሎ ተጠርቶአል። “በግንቦት አንድ፣ እኛ ማርያምን እናከብርበታለን እንጂ ጣዖት አናመልክም” የሚል ማመካኛ ወይም ማሳበቢያ ፈጽሞ አያስፈልግም። ምክንያቱም በዕለቱ የሚከናወነው ተግባር ኹሉ መስቀሉን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤውን የሚናኝና የሚመሰክር አንዳች ነገር የለውምና።

ጌታ በመስቀል ላይ የሠራው የመስቀሉ ሥራ ሕይወታችን ነው፤ የክርስቶስ ትንሣኤ የደመቅንበት ሞገሳዊ ጌጣችን ነው፤ ከእርሱ ትምህርትና ሕይወት ውጭ ሌላ ትምህርት፣ ሌላ ልምምድ የለንም፤ ከክርስቶስ በቀር የምንሰብከው ሌላ ርዕስና አጀንዳም ፈጽሞ የለንም። እና በአጭር ቃል ግንቦት አንድ ማርያምን የማክበር ተብሎ ሽፋን ቢሰጠውም፤ ባይሰጠውም፣ ፍጻሜው  ከክርስቶስ ወንጌል ውጭ የኾነ ትምህርትና ልምምድ መኾኑን መዘንጋት አይገባም፤ በምትወዱትና በምታከብሩት ነገር በኩል የሚመጣ፣ የትኛውንም ባዕድ ንግግርና ትምህርት ከመከተል ራሳችሁን ጠብቁ።

 ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመጥፋት ከሚወዱ ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን። (ኤፌ. 6፥24)

3 comments:

  1. “አውሬው...እግዚአብሔርንም ለመሳደብ ስሙንና ማደሪያውንም በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ።”
    — ራእይ 13፥6
    ወዳጄ ሆይ ሰው ብትሆን ይሻልሀል,, !!!

    ReplyDelete
  2. ምን ዙሪያ ጥምጥም ትሄዳለህ በምን ልንቀፍ ነው ኦርቶዶክስ ተዋህዶ

    ReplyDelete
  3. አንተን ከመንገር ድንጋይ ማናገር ይቀላል ሆዳሙ ፓስተር አቤኔዘር ተኩላው

    ReplyDelete