Wednesday, 30 October 2019

“ሂዱና … ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።” (ማቴ. 28÷19)

Please read in PDF
   የቤተ ክርስቲያን የመጀመርያና የመጨረሻው ዋነኛ ራዕይና ተልዕኮ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል ለፍጥረት ሁሉ ማድረስና ደቀ መዛሙርት አድርጎ ወደመንግስቱ መሰብሰብ ነው። ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር የመንግሥት ወንጌል ከማገልገል በቀር ሌላ ምንም ተልዕኮ፤ የምትዋደቅለትም ዓላማ የላትም። በስደት ዘመን ሰማዕታት፤በሰላም ዘመን መምህራንና መጋቢዎችን፣ ድንቅ አማኞችን ቤተ ክርስቲያን ያፈራችው በእውነተኛው ዘር በክርስቶስ ህያውና ቅዱስ ዘር በሆነው ቃሉ ነው።
      ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በዘመነ ሥጋዌው ባገለገለበት አገልግሎቱና በሕይወት ለእኛ ፍለጋውን ከተወልን ዋና አብነቱ ወደተለያየ ቦታዎች እየሄደ ማገልገሉም ነው። በጌርጌሴኖን በመቃብሩ ስፍራ ፍለጋ መሄዱን ስናይ፣ ከኢየሩሳሌም ብዙ ኪሎ ሜትር ወደሚርቁት ጢሮስና ሲዶና ድረስ አንዲት ሴት ፍለጋ መጓዙን ስንመለከት፣ ወደተናቁትና ወደተገለሉት ሳምራውያን መንደር ተገኝቶ ሳምራውያንን መጎብኘቱ፣ አምስት መመላለሻ ወዳሉባት ቤተ ሳይዳ ሰው የሌላቸውን ብዙ ህመምተኞች ተገኝቶ ማየቱ፣ በቢታንያ በለቅሶ ቤት እያለቀሰ እንባን ማበሱና ማጽናናቱ፣ በገበያው ሥፍራ በባህር ዳርቻና በተራራማው ሐገሮች እየተገኘ ማስተማሩ፣ መምከሩና የፍቅር ሕግ መመስረቱ፣ ነውራቸው በአደባባይ ከታወቁና ከተገለሉ መጠቋቆሚያ ከሆኑት ሰዎችና ኃጢአተኞች ሌዊና ዘኬዎስ በቤታቸው ተገኝቶ የመዳንን ወንጌል ለእናንተም ያለ፤ የመግደሎም ሴት ማርያም፣ ባለሽቱዋ ማርያም፣ አስራ ሁለት ዓመት ደም የሚፈሳትን ሴት እጅ ዘርግቶ የተቀበለና በአድራሻቸውም በመሔድ ፈልጎ የተገናኛቸውና ወደበረቱም የመለሳቸው ነው።
      ጌታ ሊፈልግ የመጣው ከሰማያት ብቻ አይደለም፤ ከቅድስት ድንግል ከተወሰደ በኋላም ሁሉንም አዳማዊና ሔዋናዊ ፍጡር በአድራሻው ሲፈልግ አይተናል። ደመና እየጠቀሰ፣ የእሳት ሰረገላ እያዘጋጀ ያለምንም ድካም ግን አልነበረም። ከኀጢአተኞች ጋር “የኃጢአተኞችና የቀራጮች ወዳጅ” ተብሎ ስድብን ጠግቦ፣ ከተገፉት ጋር እርሱም ከሚኖርበት መቅደሱ ተገፍቶ፣ በጠራራ ፀሐይ የሰውን መዳን ናፍቆ እጅግ ደክሞ ነው።
      የጌታን ፍለጋ ተከትሎ ክርስቶስን በሕይወቱ የመሰለው ብርቱው ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስም የጤናውና የርቀቱ ነገር ሳያሰጋው የክርስቶስን የመንግሥት ወንጌል ለመመስከርና የማትፈርሰዋን ህያው ቤተ ክርስቲያን ሊመሰርት ከአስር ሺህ ማይልስ በላይ በእግሮቹ እንደተጓዘ የመጽሐፍ ቅዱስ የታሪክ ጸሐፍት ዘግበዋል። አስተውሉ! የሮማ ጎዳናዎች የተዋቡና ደልቃቃ አውቶሞቢሎችንና ያማሩ መኪኖችን ማፍሰስ አልጀመሩም። ጉዞዎች ሁሉ በእግርና አድካሚ በሆኑ መርከቦችና ጀልባዎች ነበር። ቅዱስ ጳውሎስ ሙሉውን ዘመን በሚያስብል መልኩ ወንጌልን የሰበከው በመሔድና ብዙ ዋጋን በመክፈል ነው።
      ቃሉ አንድ ቦታ በመርጋት ወንጌሉን እንድናገለግል አላዘዘንም። ምቹ ነገርም በመጠበቅ ወንጌሉ አልተገለገለም። ተቀምጬ፣ ተሰናድቼና ተዘጋጅቼ እጠብቃችኋለሁ የምትል ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ያልተማረች ደካማ ቤተ ክርስቲያን ናት። ልፋትን በመጥላት፣ ድካምን በመሸሽ፣ ተደላድላ ዙፋን ላይ ተቀምጣ፣ ባማረ ካባና ላንቃ ተሞሽራ፣ በተዋቡ ህንጻዎች ውስጥ ተደላድላ “ኑልኝ” የምትል ቤተ ክርስቲያን የተቀማጠለችና የሞተች ቤተ ክርስቲያን ናት።
      የዛሬዎቹ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት የተደላደሉ የጉዞ መስመሮች፣በሕግ የተረጋገጡ ሃሳብን የመግለጥ መብቶች ኖረው፣በስሙ የመዘዋወር ክልከላዎች ሳይኖሩብን … ምቹ አውደ ምህረቶች፣ ቅንጡ ቀሚሶች፣ ድካም አቅላይ ያማሩ ድምጽ ማጉያዎች ይዘን ተቀምጠን “ሂዱ” መባልን መርሳታችን ያሳዝናል። ዛሬ በገበያ፣ በየሆስፒታሎቹ፣ በየወህኒ ቤቶቹ፣ በጎዳና ነዋሪዎቹ … መካከል ለሪፖርትና ለፈንድ ማሰባሰቢያ በዘለለ ተግታ የምታገለግል  ቤተ ክርስቲያን ማግኘት እጅግ ይጨንቃል።
    የማይንቀሳቀስና የማይወርድ ውኃ ከመሽተት አልፎ ትላትል ያፈራል። ቤተ ክርስቲያን እንደ ጌታ ቃል መሄድ፣ መንቀሳቀስና መጓዝ ካልቻለች የተኛውን ማንቃትና የቆመውን ጉዞውን እንዲቀጥል ማድረግ አትችልም። ሐዋርያቱ ወንጌሉን ይዘው በተጓዙበትና ያለመታከት በሄዱበት ዘመን ቤተክርስቲያን ታፈራ፣ ነብሳት ትጨምር፣ የተኛውን ሙት መንፈስ ታነቃ ወደሕይወትም ትመራ ነበር። ብዙ ድካሞች ቢኖሩባትም በንስሐ እየታደሰች በደሙ ተጋርዳ ለነገስታቱ ፍርሐት፣ ለአላውያን ተግሳጽና ለመናፍቃኑ የማስደንገጥ ቃል ነበራት።
  የዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ከመሔድ ይልቅ ቁጭ ብላ የተቀማጠለች ይመስላል። ስለግብፅ ቤተ ክርስቲያን የሰማሁት ነገር ይደንቀኛል። አንድ ሰው ከቤተ ክርስቲያን ቢቀር ቄሱ ፈጥኖ ወደቤቱ ይሄዳል፤ ባይመጣ ጳጳሱ ፈጥኖ ይሄዳል፤ ከዚያ በኋላ ግን ፓትርያርኩ ይመጣል ብሎ ስለሚያፍር ፈጥኖ ወደህብረቱ ይመጣል። ቤተ ክርስቲያን ባትመጣ ኖሮ ምናልባት ይህ ሰው እስከወዲያኛው ሊቀር ይችላል። ወደእኛ ስንመጣ ምን ያህል የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ለሚቀርና ለማይመጣ አማኛቸው ተጨንቀው ፍለጋ እንደሚወጡ ስናስብ የምናየው እውነት የፈጠጠ ነው። አስራት ለመሰብሰብ የሚፈጥኑ እግሮች አማኝ ፍለጋ አለመሔዳቸው ስንፍናችንን ይበልጥ ያጐላዋል።
     ከመነካከስ እስከመበላላት የደረስነው፣ነውረኝነታችን ሸቶ የከረፋው፣ ከእኛ ጠፍቶ በዓለማውያንና በአህዛብ ፊት ፍርድ ቤት ፍትህ ፍለጋ የተቅበዘበዝነው፣ ኃጢአታችንን ሌሎች የገለጡት … ለቅዱሱ ሥራ ሂዱ ተብለን መቀመጣችን … ደቀመዛሙርት አብዙ ተብለን ባለው ቁጥር መመካታችንና ለሌሎች መዳን ከመትጋት ድካምና ልፋትን መጥላታችን ነው። ሂዱ ተብሏልና ቤተ ክርስቲያን ላለመኑትና በሩቁ ላሉትም የመንግስቱን ወንጌል ለመስበክ እግሮችሽን አፍጥኚ።
    ጌታ መንፈስ ቅዱስ ጸጋውን ያብዛልን።አሜን።
ኅዳር 2008 ዓ.ም ተጻፈ!

2 comments: