Please read in PDF
ተፈጸመ።
ምን እንድርግ?
በባለፉት ጊዜያት እጅግ መልካም ነገሮችን በማንሣት በዚህ ርእስ ሥር ስናጠና
ቆይተናል፤ ሾላኮችን ጠባያቸውንና ኹለንተናዊ ባሕርያቸውን አንስተንም ተመልክተናል፤ ከዚህ በመቀጠል ደግሞ እኛ ምን ማድረግ እንደሚገባን
በማንሣት የእግዚአብሔርን ቃል እንጫወታለን።
1.
ወደ ቃሉ
እንመለስ፦ የሾላኮቹ ያላሳለሰ ተግባራቸው እኛን ከቃሉ መነጣጠል ነው፤ ወደ ቃሉ ልንመለስና ዘወር የምንልባቸውን ማናቸውንም
ምክንያቶችና መንገዶችን ጨርሰው ነው የሚዘጉት። ብንመለስ እንኳ ለገዛ ራሳቸው እንዲመች አድርገው ቃሉን ያጣምማሉ እንጂ በትክክል
እንድንመለስ አያደርጉም፤ አይፈልጉምም።
ስለዚህም እውነተኛ መመለስና እውነተኛ ንስሐ ወደ ራሱ ወደ እግዚአብሔር መመለስ ነውና ወደ ቃሉ ለመመለስ ጨካኝ መኾን
አለብን፤ እግዚአብሔር ደግሞ በቅዱስ ቃሉ ውስጥ ፈቃዱን ገልጦ እናገኘዋለን። ወደ ቃሉ መመለስ ወደ ሕይወትና ወደ ዘላለም እውነት
መመለስ ነው። ነገር ግን ሾላኮችን ማድመጥና እነርሱንም መከተል ከሕይወትም ከእውነትም እስከ ፍጻሜው ይለያየናል። ወደ ቃሉ በትክክል
መመለስ ከሾላኮች ፈጽሞ ያቆራርጠናል። ቅዱስ ቃሉ ከሾላኮች የሚሸሽግ አምባ ነው!
2.
ኢየሱስ ብቻ
ዋናችን ይኹን፦ ሾላኮች ትምህርቶቻቸውና ውጫዊ ነገራቸው አማላይ፣ ሳቢና ጆሮ አሳካኪ ናቸው። ውስጣዊ ነገራቸው
ግን ባዶና ክህደት ነው፤ በውስጣቸው የታጨቁት ዓመጻና ክፋት፣ ማጥመድና ለገዛ ረባቸው መጠቀም ብቻ ነው። ስለዚህም ይህን አሟጥጠው
ለመጠቀም እንዲረዳቸው ራሳቸውን ጭምር ዋና አድርገው በማቅረብ ይታወቃሉ።
ጌታችን ኢየሱስን ዋና አለማድረግ ለየትኛውም ክፉ ወጥመድ አሳልፎ ሳይሰጥ አይቀርም። የዘላለም
ዋናችን ክርስቶስ ኢየሱስ ከኾነ፣ ከእርሱ በቀር ሌላ ማየት አይኾንልንም፤ ነገር ግን እርሱ ዋናችን ካልኾነ ሾልከው የሚገቡ የጠላት
አሠራሮች አያሌ ናቸው ብለን ደፍረን መናገር እንችላለን። ኢየሱስን ዋና ማድረግ ከብዙ ስህተትና ዕድፈት ይጠብቃል።
ሰማዕታትና አባቶች ኢየሱስ ዋናቸው ስለ ነበረ የትኛውንም የመንግሥት ማባበልና ማስፈራራት፣ እንዲሁም ሽንገላን ፈጽሞ
አልተቀበሉም፤ ሾላኮች እንኳ ገብተው ሊያባብሉአቸው ቢሞክሩም ፈጽመው አልሰሙአቸውም፤ ምክንያቱም የተሰቀለው ኢየሱስ ዋናቸው ነበርና፤
ዛሬም ቢኾን በዙርያችን ካሉት አገልጋዮች፣ አማንያን፣ ወንድሞችና እህቶች በላይና እጅግ አልቀን ኢየሱስን ዋናችን ማድረግ ተቀዳሚ
ተግባራችን ካልኾነ በገዛ በቅርብ ወገናችን መታለላችን አይቀርም።
ከመካከላችን ለሚነሡት ሾላካ መናፍቃን መፍትሔው ኢየሱስን ዋና አድርጎ ዘወትር ማድመጥና መከተል፤ እርሱን ብቻ መታዘዝ
ነው!
3.
እንቃወም፦ ሾላኮች
ራሳቸውን የሚሰውሩት በጨለማ ውስጥ ነው፤ ጨለማ ደግሞ ተምሳሌትነቱ ኃጢአትና ክፋት ነው፤ በተለይም ጨለማን የሚለብሱት ለአደገኛ
የክፋት ሥራ ነውና እንዲህ ያለውን መንገድ መቃወምና ማጋለጥ ይገባል። መጽሐፍ እንዲህ እንደሚል፦ “ፍሬም ከሌለው
ከጨለማ ሥራ ጋር አትተባበሩ፥ ይልቁን ግለጡት እንጂ፥” (ኤፌ. 5፥11)።
በሌላ ስፍራም፣ “… በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት
ለሚኖር አብና ወልድ አሉት። ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤ ሰላም የሚለው
ሰው በክፉ ሥራው ይካፈላልና።” (2ዮሐ. 9-11) ተብሎ ተጽፎአል፤ የጨለማ ሥራ በተለይም የኢየሱስ ክርስቶስን ዋና መኾን፣ አዳኝና
ቤዛነቱን የሚቃወም ትምህርትን መታገስና ችላ ብሎ ማለፍ፣ ይኽንን ተግባር ከሚሠሩ ሰዎች ጋር እኩል የመተባበር ያህል ነው።
ስለዚህም ክፋት ተገልጦ በታየ ጊዜ አለመቃወምና ችላ ማለት የተገለጠውን ክፋት፣
“እኔም አለሁበት” የማለት ያህል ያስተባብራል፤ ጳውሎስ ቆሮንቶሳውያንን በዚህ ጉዳይ እንደ ወቀሳቸው መዘንጋት የለብንም፤ የተገለጠ
ነውርን በተለይም የሾላኮችን ሾላካነት በዝምታ ማለፍ ተላላነት ነው፤ ሰዎች እንዲህ ባለ ነውር ሲያዙ በፍቅርና በርኅራኄ መምከርና
መውቀስ ተገቢ ነው፤ በጸሎትም መርዳት ይገባል፤ ተረባርቦ ለመመለስ መትጋት ሊቀድምም ይገባል፤ ይህን ኹሉ ባይቀበሉ ግን የጨለማውን
ሥራ መግለጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊና የተገባም ነው።
4.
እንጸልይ፦ ቤተ ክርስቲያን
ዘወትር አለመጸለይዋ ኃጢአት ነው፤ በማናቸውም የሕይወት መንገዷ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ነገሯን ከማከናወኗና ከማድረጓ በፊት መጸለይን
መተው የለባትም። ብዙ ነገሮች ዛሬ መልክ አልባና አቅም አልባ የኾኑት የጸሎት አቅማቸው እጅግ አናሳ ስለኾነ ነው።
ሾላኮች የዚህ ሕይወት ተቃራኒ ናቸው፤ ተድላና መለዳለድ
እንጂ በትጋት በእግዚአብሔር ፊት የሚቆሙና የሚጸኑ አይደሉም፤ አማኞች ግን በእግዚአብሔር ፊት በትጋት ሲቆሙ ሥራቸውን ኹሉ የታመኑበት
አምላክና አባት በእውነትና በቅድስና እንደሚሠራ እናምናለን። በትጋት ጸልዩ፤ ጌታ ሾላኮችን ከመካከላችን እንዲያጠራና ቤተ ክርስቲያን
በቅድስና እንድትቆም ሳታቋርጡ ጸልዩ።
No comments:
Post a Comment