Please read in PDF
መግቢያ
ቅዱስ ጳውሎስ ዘርዝሮ ካልጨረሳቸው(ገላ.
5፥19-21) እና ተዘርዝረው ከማያልቁት የሥጋ ሥራዎች አንዱ ንቀት ወይም ሰዎችን መናቅ ነው፤ የሥጋ ሥራዎችን እንዘርዝራቸው
ብንል ዳርቻው ኹሉ እንደማይበቃቸው እናውቃለን፤ ነገር ግን ክርስቶስ ኢየሱስ በመስቀሉ ኃይል እኒህንና ሌሎችንም ኃይላት ደካማ
በሚመስል መንገድ ሰብሮና በመስቀሉ ጠርቆ አስወግዶአቸዋል። አለቅነት፣ ሥልጣን፣ ኃይል፣ ጌትነት ኹሉ በክርስቶስ ጌትነትና ኃይል
ተሽሮአል፤ (ኤፌ. 1፥20-21፤ 3፥10፤ ፊልጵ. 2፥9)። ክርስቶስ በመስቀል ሞቱ የተወደደና ቅዱስ ሕይወት እንኖር ዘንድ
በደሙ ፉጨት ጠርቶናል።
ነገር ግን ብዙዎቻችን ዘንድ የተጠራንለትን ጥሪና ጌታ የሚያስከብርና
ለእርሱም ክብርን በሚያመጣ ሕይወት ስንመላለስ አንታይም። ሕይወታችን በተለያዩ የሥጋ ሥራዎች ነቅዟል፤ በሥጋ ሥራ ሕይወቱ
የደከረተ “ሰው፣ ማኅበረ ሰብ፣ ክርስቲያንና ቤተ ክርስቲያን” ማየት ብርቅ አይደለም፤ በተለይም ደግሞ አኹን ባለንበት ወቅት
ከክርስትናው ዓለም ባሻገር ካለው ዓለም ጋር እኛንም ያመሳሰለን ነውር ቢኖር፣ አንዱ መናቅ ወይም መናናቅ እንደ ኾነ ይሰማኛል፤
እናም ንቀትን በተመለከተ ጥቂት በዚህ የጡመራ መድረክ ማውራትና ከቃለ እግዚአብሔር አንጻር መነጋገርን ፈለግኹ፤ አንዳች መረዳት
እንደምታገኙበት ተስፋ አደርጋለሁ።
ንቀት ምንድር ነው?
“ንቀት” የሚለውን ቃል የደስታ ተክለ ወልድ መዝገበ ቃላት እንዲህ
ተርጉመውታል፤ “ናቀ፣ አኰሰሰ አቀለለ አዋረደ ጠላ፣ ክብርን መውደድን አሳጣ (ዘኊል. ፲፭፥፴፩፤ ኢሳ. ፳፫፥፱)፤ ናቂ፣ የናቀ
የሚንቅ፤ አኰሳሽ። (ሰው ናቂ) ትቢተኛ ኵራተኛ። … መናቅ፣ ማቃለል፣ ማኰሰስ፣ መጥላት … ንቀት፣ ሌላውን መናቅ … (አስ.
፩፥፲፰፤ ኢዮብ ፲፪፥፳፩)[1]
በማለት። በአንድ ሌላ ትርጉም ደግሞ እንዲህ ተጠቅሶአል፤ “ዋዘ፣ ተሣለቀ፣ ተላገጠ፣ ማንቋሸሽ፣ እንደ ወራዳ ተግባር መቁጠር”።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዕይታን በተመለከተ ደግሞ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ
ቃላት እንዲህ በማለት ይፈታዋል፤ “ንቀት በምክንያት ወይም አለ ምክንያት ሰውን ዝቅ አድርጎ መመልከት፥ ማዋረድ።”[2] እንግዲህ
ንቀት ወይም ሰውን መናቅ እጅግ አደገኛ የመንፈሳዊ ወይም የስብእና ንቅዘት ውጤት መኾኑን ማስተዋል አይቸግርም። ሰውን
በአለባበሱ፣ በብሔሩ፣ በኑሮው፣ በመልኩ፣ በአገሩ፣ በዕውቀቱ፣ … መናቅም መኾን መቀበል በማኅበረ ሰባችን ወይም አንዳንዴ በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ መመልከት እንግዳ ተግባር
አይደለም።
የመጀመሪያው የንቀት አስተማሪ
ሰይጣን የክፋት መጀመሪያ ነው፤ የኃጢአት ምንጭ በእርሱ ዘንድ ነው፤
ለኃጢአት “ከመጀመሪያ” ተብሎ የተነገረለት ዲያብሎስ ነው፤ (ዮሐ. 8፥44)። በፍጥረት መጀመሪያ የሰው ልጅን ለመጣል የመጣበት
መንገድ ቀላል ግን እጅግ አደገኛ ነበር፤ በበኵር ቋንቋ የተጻፈውን[3]
መጽሐፍ ቅዱስና የዘፍጥረት ጸሐፊ የፍጥረትን ነገር በተለይም የሰው ልጅ ከተፈጠረ በኋላ ያለውን ሂደት ያሰፈረበትን መንገድ
ስንመለከት፣ እግዚአብሔርን “ያህዌ ኤሎሂም” በሚለው ስም በመጥራት ነው። ነገር ግን ሰይጣን ወይም አሳቹ መጥቶ ከሴቲቱ ጋር ሲያወራ፣ ኾን ብሎ
“ያህዌ” የሚለውን ስም በመተው፣ ኤሎሂም በሚለው ስም ብቻ ሲያነጋግራት እንመለከታለን።
በመጽሐፍ ቅዱስ ኤሎሂም የሚለው ስም “ … ጣዖታትን
(ዘፀአ. 18፥11፤ መዝ. 95፥3፤ 96፥5)፣ መላእክትን (መዝ. 8፥5) እና ሰዎችን ሊያመለክት ይችላል፤ (ዘፀአ. 7፥1፤
21፥6፤ 22፥8፤ መዝ. 82፥1-6፤ ዮሐ. 10፥34-35)። ኤልና ኤሎሂም እንደ ዓውዱ በአምላክ ወይም በአማልክት ሊተረጎሙ
ይችላሉ። ብዙ ጊዜ ግን ትክክለኛ ትርጉም የሚኾነው እግዚአብሔርን የሚያመለክት ነው።”[4] እንግዲህ
ሰይጣን ያህዌ የሚለውን ስም ኾን ብሎ የሚተወው[5]፣
በንቀት መንፈስና ሴቲቱም እግዚአብሔር አምላክን በመናቅ እንደ እኩያዋ በመቊጠር እንድትበድልና እንድትወድቅ አሸምቆ ያዘጋጀው
ወጥመድ ነው።
እናም በንቀት ንግግር ወደ እርሷ በመጣ ጊዜ፣ ሴቲቱ ተዘናጋች እንጂ
አላስተዋለችም፤ ስለሚጠቀምባቸው ቃላትና ስለ ንግግሩ ሳታስተውል፣ ይዞ ለመጣው ዐሳብ የተመቻቸች ኾነች። እናም በተደጋጋሚ ያህዌ
የሚለውን ስም ሲተው “ለምን?” ብላ ባለመጠየቅና ባለማስተዋል፣ በአንድነት ከእርሱ ጋር በደለች። በተጨማሪም ስሙን ብቻ ሳይኾን
ዘፍ. 3፥2 ላይ ሴቲቱ ሕጉን ስትናገር፣ ሰይጣን ግን ኾን ብሎ አኹንም ሕጉን በመተው [በመናቅ]፣ ሴቲቱን ወደ ራሱ መንገድ
የሚስብበትን አማራጭ መንገድ ይከተላል፤ ይኸውም በእግዚአብሔር ክልከላ ላይ በማተኰር። ስሙን ናቀ፤ ከዚያም ተከትሎ ሕጉን ናቀ፤
ሴቲቱ በዚህ ኹሉ መንገድ ውስጥ አላስተዋለችም።
ሰይጣን እንዲህ ያለ አስቀያሚ መንገድን በመጠቀም፣ የንቀትን ዐሳብ
ወደ ሰዎች ልጆች አሰረጸ፤ ያህዌን ለማዋረድ በማሰብና ሕጉንም ጭምር ባለማክበር ወይም በመናቅ የስህተትን አሠራር አመጣ። እንግዲህ
ስለ ንቀት ስናወራ፣ ስለ ሰይጣንና የእርሱን መንገድ በመከተል እግዚአብሔርንና ፍጥረቱን ስለሚንቁ ኹሉ እየተናገርን እንደ ኾነ
ማስተዋል እንወዳለን። ወዳጆቼ ሰዎችን ትንቃላችኹን? መናቃችሁንስ ኃጢአት እንደ ኾነ አስተውላችሁ ታውቃላችኹን? የንቀትን
ተግባር በመፈጸማችኹስ የዲያብሎስ የግብር ልጆች እንደ ኾናችሁ ታውቆአችኋልን? … ጌታ ኢየሱስ በነገር ኹሉ ማስተዋልን ይስጠን፤
አሜን።
ይቀጥላል …
[1] ደስታ ተክለ ወልድ፤ ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት፤ 1962 ዓ.ም፤ አዲስ
አበባ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ቤት፤ ገጽ 871 እና 872
[2] የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፤
የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 6ኛ
ዕትም፤ 142
[4] ቄስ ኮሊን
ማንሰል፤ ትምህርተ እግዚአብሔር፤ 1995
ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ንግድ ማተሚያ ድርጅት። ገጽ 174 እና አቤንኤዘር ተክሉ (ዲያቆን)፤ የእምነት እንቅስቃሴ የዛሬዪቱ ቤተ ክርስቲያን ፈተና፤ አዲስ አበባ፤ 2011 ዓ.ም፤ ማተሚያ ቤቱ
ያልተጠቀሰ፤ ገጽ 113።
[5] የአይሁድ ራቢዎች ሰይጣን “ያህዌ”
የሚለውን ስም፣ የእግዚአብሔርን ምሕረት አልተለማመደምና መጥራትም ኾነ መጠቀም አይችልም ብለው ያምናሉ። ነገር ግን ለዘወትር ክፋትና
ኃጢአት በሰይጣን ዝንባሌ ውስጥ ኹሉ እንዳለ ልንዘነጋ አይገባም፤ (A.B Devidson; OT Theology; pp. 300-303.)
በጣም አስተማሪ ነው ተባርክ እግዚአብሔር ፀጋዉን ያቢዛልህ አሜን!!!
ReplyDeleteበጣም በጣም የተወደድክ ወንድማችን በአንተ ትምህርት ምን ያክል እንደተጠቀምኩ በቃል መግለጽ አልችልም !
ReplyDeleteእግዚአብሄር ይባርክ ፀጋውን ይጨምርል የሚገርም መረዳት ነው ቃላት የለኝም ብቻ ተባረክ
ReplyDeleteዘመንህ ይለምልም
ReplyDeleteምላስ ከታናጋህ ጋር ይጣበቅ ብስብስ ይበል አንተ ክፉ ቅዱሳን አባቶቻችንን የያ አይንህ ጨለማ ይሁን ቅዱስት ሃገራችንን ለማርከስ በየ አደራሹ ስትጮህ ስትጨፍር ፍርዱ የዘገየው አምላክ ስለ ድንግል ስለ ቅድስት ማርያም ክብር ሲል በአደባባይ ያዋርድህ !! ቤተ ክርስቲያን ላይ ስለ አሰባችሁት ሴራ እና ስለ ግብረ ሰዶማዊነት አላማችሁ የእቶን እሳት በላያችሁ ላይ ይልቀቅባችሁ የእራማው መላክ ቅዱስ ገብርኤል !!
ReplyDelete