Friday 4 October 2019

እሬቻን የማላከብርበት ክርስቲያናዊ ምክንያቴ

Please read in PDF
መግቢያ

   ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ “የፖለቲካው ጡዘት አገራዊ መልኩን በመልቀቁ፣ ብሔርና ሃይማኖት ተደጋፊ” ከመኾን ጋር ተያይዞ፣ የበአላትን ፉክክር ሃይማኖታዊ መልክ ሲያለብሱ እየተመለከትን ነው። ይህ ደግሞ ውል አልባ የኾነ መጠዛጠዝንና መገፋፋትን፣ “እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ!” የሚል ሥጋዊ መቀናናትን ሲያስከትልና ትውልድ የሚመርዙ ተግባራት “ሃይ ባይ” ማጣታቸውንም እንድንመለከት አድርጎናል። ልክ እንደ ዘመነ መሣፍንት፣ “በዚያም ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም፤ ሰውም ሁሉ በፊቱ መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር።” (መሣ. 16፥7) ተብሎ እንደ ተነገረው፣ የትኛውም ሰውና ብሔር መልካም መስሎ የታየውን ከማድረግ ከልካይ የሌለበትና እግዚአብሔር የተገፋበት የተናቀበት ዘመን ላይ ነን።


 በሌላ ስፍራም “እስራኤልም ብዙ ዘመን ያለ እውነተኛ አምላክ፥ ያለ አስተማሪም ካህን፥ ያለ ሕግም ይኖሩ ነበር።” (2ዜና. 15፥3) ተብሎ እንደ ተነገረ፣ ሃይማኖተኛ የኾነው ሕዝባችን እውነተኛውን አምላክ ከማምለክ የወጣበት ዘመናት እጅግ አያሌዎች ናቸው። የዚያን ውጤት ነው ዛሬ ኹሉም፣ የየመንገዱን አምላክ ወደ ማምለክ እንዲያዘነብል ያደረገው።
የበዓላት ታሪካዊ ዳራ በብሉይ ኪዳን
  መጽሐፍ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን የታወቁ ሰባት በዓላት እንደ ነበሩና እኒህንም በዓላት፣ እስራኤል ዘሥጋ በያህዌ ትእዛዝ ያከብሩ፣ እርሱንም ያመልኩበት ነበር፤ እኒህም በዓላት (1) የሰንበት በዓል (ዘሌ. 23፥2-3) (2) የቂጣ በዓል ወይም በዓለ ናእት ወይም እስራኤል ከግብጽ የወጡበትን መታሰቢያቸውን ለማክበር በተለምዶ የፋሲካ በዓል እየተባለ የሚጠራው (ዘጸ. 12፥1-20፤ ዘሌ. 23፥5-8) (3) የመከር በዓል (በዓለ ሠዊት)፣ ወይም ሰባቱ ሱባኤ እየተባለ የሚጠራው የምስጋና በዓል (ዘጸ. 23፥16፤ 34፥22፤ ዘኍል. 28፥26) (4) የዳስ በዓል (በዓለ መጸለት)፣ ወይም የአዝመራ ማከማቻ በዓል (ዘሌ. 23፥39-43) (5) የመለከት በዓል (ዘሌ. 23፥23-25)፤ ዘኍል. 29፥1 (6) የማስተስረያ ቀን ወይም የማስተስረያ በዓል (ዘሌ. 23፥26-32) (7) ፉሪም፣ ይህም በአስቴር ዘመን አይሁድ ከጠላት እጅ ስለ መዳናቸው ወይም ዕረፍት በማግኘታቸው የሚያከብሩት (አስ. 9፥16-28) በዓላት ናቸው።
  ከእነዚህ በዓላት አይሁድ በአገራቸው ተገኝተው ለማክበር የሚገደዱባቸው በዓላት አሉ፣ በተለይም ሦስቱን በዓላት በአገራቸው ጭምር ተገኝተው በቤተ መቅደሱ ሊያከብሩ ይገባቸዋል፤ “በዓመት ሦስት ጊዜ በዓል ታደርግልኛለህ። የቂጣውን በዓል ጠብቅ፤ በአቢብ ወር ከግብፅ ምድር ወጥታችኋልና በዚህ ወር እንዳዘዝሁህ ሰባት ቀን ቂጣ እንጀራ ትበላለህ፤ በፊቴም ባዶ እጃችሁን አትታዩ። በእርሻም የምትዘራትን የፍሬህን በኵራት የመከር በዓል፥ ዓመቱም ሳያልቅ ፍሬህን ከእርሻ ባከማቸህ ጊዜ የመክተቻውን በዓል ጠብቅ።” እንዲል (ዘጸ. 23፥14-16፤ ዘዳግ. 16፥16)።
  ያህዌ እኒህን በዓላት ለእስራኤል ዘሥጋ የሰጠው አምላካቸውን ዘወትር እንዲያስቡና ፈጽመው እንዳይዘነጉትም ጭምር ነው። ዋና ዓላማውም እርሱንና እርሱን ብቻ እንዲያመለኩትና ለእርሱ ብቻ ክብርን እንዲያመጡለት የተሰጡ ታላላቅ በዓላት ነበሩ።
የአዲስ ኪዳኑ በዓል
 በአዲስ ኪዳን ግን እኒህ የአይሁድ በዓላት በግልጥ መሻራቸውንና በሌላ መተካታቸውን መጽሐፍ ቅዱስ በአንድም በሌላም መንገድ ያስተምረናል። ለምሳሌ፦ የፋሲካ በዓል ሙሉ ለሙሉ ተሽሮ በአማናዊው ፋሲካ በክርስቶስ ኢየሱስ ተተክቷል፤ እስራኤል ከሞት ወደ ሕይወት የተሻገሩበት ፋሲካ እንደ ኾነ እጅግ በሚልቅ መለኮታዊ ዕቅድ፣ እኛ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የፈለስንበት ፋሲካችን፣ የታረደልን መስዋዕታችን ክርስቶስ ኢየሱስ ኾኖአል፤ (1ቆሮ. 5፥7፤ ራእ. 5፥9-10)፣ ከኢየሱስ በቀር ሌላ የፋሲካ በዓል አናውቅም፣ ፋሲካውም በዓሉም አንዱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እንዲሁ በዓለ ዓምሳ ወይም የመከር በዓል እየተባለ የሚጠራው በዓል ደግሞ ሙሉ ለሙሉ በመንፈስ ቅዱስ በዓል ወይም ጰንጠቆስጤ ወይም ጰራቅሊጦስ ተተክቶ እንመለከተዋለን፤ (ሐዋ. 2፥1)።
በአዲስ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት የታዘዝነው በዓላት የለንም!
  ከዚህ በዘለለ ደግሞ በአዲስ ኪዳን ከኢየሱስ በቀር የምናከብረው ሌላ በዓል ወይም ደስታ የለንም፤ እግዚአብሔር ለዘለዓለም መታረቂያና መታሰቢያ፣ መዳኛና መፈወሻ፣ መቅረቢያና መካከለኛ፣ ሕይወትና ቤዛ አድርጎ አንድያ ልጁን በመስጠት ጥላዎቹን ኹሉ፣ ምሳሌዎቹንም አስወግዶአል፤ (ዕብ. 8፥5፤ 10፥1)። ጥላና ምሳሌዎቹን ኹሉ አሳልፎ ክርስቶስ ዋናና አካሉ ኾኖ ተገልጦአል፣ ስለዚህም በሰማይም ኾነ በምድር ከክርስቶስ የሚልቅ “የሕዝብ ኹሉ የሚኾን ደስታ” ፈጽሞ የለም፤ ወደ ፊትም ከቶውንም ሊመጣ እንደማይችል እናምናለን፤ እታመናለን። በዓላችንም ደስታንም ክርስቶስ ብቻ ነውና ሌላ በዓል የለንም።
  “እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ፤ እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፥ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው። ትሕትናንና የመላእክትን አምልኮ እየወደደ፥ ባላየውም ያለ ፈቃድ እየገባ፥ በሥጋዊም አእምሮ በከንቱ እየታበየ ማንም አይፍረድባችሁ።” (ቈላ. 2፥16-18)
   የአይሁድን የበዓልና የመሥዋዕት ሕግ አኹን ማክበር አይገባም፤ በዚህ ማንም ሊከሰንና ሊፈርድብን አይችልም፤ እኒህ ጥላና ምሳሌያት አገልግሎት ክርስቶስ እስኪመጣ ድረስ የነበሩ ናቸው፤ ክርስቶስ ሲመጣ አካል ነውና ጥላውን ደመሰሳቸው። ስለዚህም ማንም “ይህን በዓል አክብሩ ወይም ከክርስቶስ ሌላም በዓል አለን” ሊል አይችልም። እርሱ ብቻ የረካንበትና ያረፍንበት በዓላችን ነው!
እሬቻን እናክብርን?
  እውነተኛ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከኾንን ማክበርም፣ በዚያ ተገኝተን ማምለክና ማናቸውንም ባህላዊ ተግባራት ማከናወን አይገባንም፤ ምክንያቱም ሰው ያለ ኢየሱስ እውነተኛና ትክክለኛ አምልኮን ከልቡ ማፍለቅና ለአብ ማቅረብ አይችልም። አምልኮ ደግሞ ከትክክለኛና በኢየሱስ ደም ከነጻ ልብ ካልቀረበ ከንቱ ነው፤ ስለዚህም እሬቻን ከዚህ በታች ባሉት ምክንያቶች ልናከብር አይገባንም፦
1.      በክርስትና አንድን ድርጊት የምንተገብረው ለኹለት ዓላማ ብቻ ነው፤ አንደኛው የምናደርገው ነገር ለእግዚአብሔር አባታችን ክብርን የሚያመጣ ከኾነና ቤተ ክርስቲያንን የሚያንጽ ወይም የሚጠቅም ከኾነ ብቻ ነው፤ (ሉቃ. 2፥14፤ ሮሜ 4፥20፤ 1ቆሮ. 10፥31፤ 2ቆሮ. 4፥15፤ 8፥19፤ ኤፌ. 1፥6)። የትኛውንም መልካም ተግባር የምናደርገው ለእግዚአብሔር ክብርን እንዲያመጣ ካላደረገ ዘወትር ከጀርባው ሰይጣን ለመኖሩ ምንም ጥርጥር የለም።
2.     ጸሎትና ልመናው፣ ምስጋናውና ስእለቱ፣ በየስምንት ዓመት የሚደረገው ጾምና ምህላው … እንዲሁም በዚያ የሚደረገው ማናቸውም አምልኮ በኢየሱስ ስም የሚፈጸምና የሚከናወን አይደለም፤ እንኪያስ ኢየሱስ ከሌለበት ስፍራ እኛ ማን ነንና እዚያ ነን?! ነው ወይስ ከኢየሱስ ይልቅ ጻድቅ ኾንን?!
3.     በአንድ አምላክ እናምናለን ቢሉንም፣ የእግዚአብሔርን ሦስትነት ግን እንደ አይሁድና እስልምና ጨርሶውኑ ይክዳሉ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ አያምኑም፣ “Waaqa gurraacha - ጥቁሩ እግዚአብሔር” ከማለት ውጭ ሌላ የአብ፣ የወልድና የመንፈስ ቅዱስን አካልነትና ሕልውና ፈጽሞ አይቀበሉም፣
4.     የአምልኮው መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ አይደለም፤ የአምልኮው መካከለኛቸውም ክርስቶስ ኢየሱስ አይደለም፣ የአምልኮአቸው ማዕከል በወንዝ ዳር መገኘትና ልምላሜን የታከከ ነው፣
5.     ኢየሱስ በሥጋ መምጣቱን፣ ቤዛነቱንና አዳኝነቱን የሚቀበል አንዳች ሰነድና ትምህርት የለውም፤ አያምኑምም!፣
6.    አንዳንዶች እንደሚሉት ባሕላዊ አምልኮ ከኾነ ከክርስትና ትምህርት ጋር ፊት ለፊት ይላተማል፤ ምክንያቱም ክርስትና ከባሕልና ከየትኛውም ፍጥረታዊ ክንውን በላይ በኾነ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የሚከናወን አምልኮ እንጂ ባሕላዊ አምልኮን ፈጽሞ ይጠየፋል፣ አይቀበልምም፣
7.     እንኳንስ ባሕላዊ ሃይማኖት፣ የብሉይ ኪዳኑ የአይሁድ እምነት እንኳ ወደ ክርስቶስ መድረስ ካልቻለ፣ ከሚያደነዝዝ ሃይማኖት በቀር ሌላ ትርጉም የለውም፤ ምክንያቱም ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት እግዚአብሔር ደጁን ወለል አድርጎ የከፈተው ሕጉን በተቀበለው በሙሴ በኩል ሳይኾን፣ ቤዛ ኾኖ ባዳነን በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል ብቻ ነውና።
ታድያ ምን እናድርግ?
   በአገራችን ወንጌል ያልደረሳቸው በብዙ ሚሊየን የሚቆጠሩ ሕዝቦች አሉ፤ “ክርስቲያን ነን” የሚሉትም ጭምር። ዛሬ ላይ እሬቻን ከሚያከብሩት አያሌ ሰዎች መካከል “በመጽሐፍ ቅዱስ እናምናለን” የሚሉ ጭምር እንዳሉበት እያስተዋልን ነው። ስለዚህም እንዲህ ማድረግ አይገባንምን?
1.      ወደ መጽሐፍ ቅዱስ በትክክል መመለስና የወንጌል ምስክርነት ልክ ለአሕዛብ መሰጠት ባለበት ልክ፣ “ክርስቲያን ነኝ” ለሚለው ማኅበረ ሰብም ማወጅ፣ መመስከር፣ በትክክል ማስተማር፣
2.     ከመጽሐፍ ቅዱስ የወጣና ያፈነገጠ ማናቸውም ትምህርትና ልምምድ ባእድ አምልኮና ስህተት መኾኑን አውቀው እንዲህ ካለው ነገር መራቅ እንዲገባቸው በእምነት ማጽናት፣ በተለይም ቤተ ክርስቲያን አባላቶቿን በአግባቡ መያዝና እውነተኛ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በማድረግ ተግታ ልትሠራ ይገባታል፣
3.     ወደ ሕያው አምላክ በትጋትና ያለ ማቋረጥ መጸለይና ማሳሰብ። ምድሪቱ ወደ ሕያው አምላክ ፊቷን እንድትመልስና የኢየሱስን ጌታነትና አዳኝነት በትክክል እንድትቀበል በእንባና በዋይታ መማለድ።

   ጌታ ኢየሱስ ሆይ ምድራችንን አስብ፤ ለክፉዎች፣ አንተን ለማያውቁ፣ ርኅራኄህን ላላዩና ላልቀመሱ ፈጽመህ አሳልፈህ አትስጠን፤ ራራልን፣ እዘንልን፣ ማረን፣ ይቅር በለን፣ ፊትህንም መልሰህ ተቀበለን፤ በውዱ ስምህ አሜን።


2 comments:

  1. አሜን! አስተማሪና መልካም መልክት ነው:: ፀጋውን ያብዛልህ::

    ReplyDelete