Saturday 19 October 2019

በልብ መጠበቅ

Please read in PDF

ነገርን በልብ ስለ መጠበቅ በመጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ምዕራፍ ኹለት ጊዜ የተነገረላት እናት የኢየሱስ እናት ቅድስት ማርያም ናት። ቅድስት ድንግል ማርያምን በተመለከተ ከኹለት ልዩ ልዩ አካላት የሚሰነዘሩትን ነገሮች በጥሙና ለሰማ ሰው ዲያብሎስ ሐሳቡ የተሳካለት ይመስላል። (አንዱ ቤት ከአምላክ እንድትስተካከል አድርጎ፣ ሌላው ቤት ደግሞ ፈጽሞ እንድትጠላ በማድረግ)። ኹለቱም ወገኖች ከመጽሐፍ ቅዱስ አድራሻ ለመራቃቸው እማኙና የመጀመርያው ማስረጃ ያው ታላቁ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። (ስለነዚህ ወገኖች ሌላ የብዕር ቀጠሮ ልያዝና በቀጥታ ወደ ዛሬው ዐሳቤ ላቅና)።

    ነገርን በልብ መጠበቅ የእግዚአብሔርን የሥራ ጊዜ ማክበር ነው። አለጊዜው የሚገለጥ ማናቸውም ነገር ሁሉ ከማትረፍ ይልቅ ያከስራል። ቅድስት ድንግል ነገርን በልብ ትጠብቅ የነበረው ብዙ ነገሮች መከናወናቸውን እያየች ነው። ታላላቆቹ የሩቅ ምስራቅ ጠቢባን ነገሥታት አለቅነትና ሥልጣን በጫንቃው ላይ ላለ፣ ለተወለደው ሕፃን ወድቀው ሲሰግዱ፣ በልዩ መገለጥ እኒያ መንጋቸውን በሌሊት ይጠብቁ የነበሩት እረኞች “መንጋችንን ማን ይጠብቅልናል?” ሳይሉ፣ እስከ ቤተ-ልሔም  በራእይ ተረድተው እንደ መጡና ምስጋናን ከመላዕክቱ ጋር እንደዘመሩ፣ ሰማያውያን እሳታውያን መላዕክት በብርሐን ጎርፍ ተመስለው ምስጋናን በምድሪቱ ሲያዘንሙ፣ እንዲህ ያለው ጌታ ማደርያው በረት አጃቢው ግዕዛን እንሰሳት ሲሆኑ፣ የእስራኤልን መጽናናት ጠባቂው ትጉሁ ጻድቅ ስምዖን የተናገረውን ድንቅ ትንቢት፣ አሴራዊቷ የፋኑኤል ልጅ ሐና ቀርባ ያመሰገነችን ምስጋና በመቅደስ ተገኝቶ ሲሰማና ሲጠይቅ በመልሱና በማስተዋሉ ሊቃውንትን ፀጥ ሲያሰኝ፣ ሊቀ ሊቃውንት፣ ርዕሰ መምህራን፣ የትንቢት መከተቻ፣ መጋቤ ብሉይ ወሐዲስ፣ መዝገበ ጥበብ … "ትንሹን" ሕፃን ጌታን በሥጋ የወለደች እናት በዐይኗ አይታለች። ነገር ግን "እናቱም ይህን ነገር ሁሉ በልብዋ ትጠብቀው ነበር።" ይላል ታላቁ መጽሐፍ።
    የኢየሱስ እናት ያጌጠችበት ትልቅ ልብስ፣ የተዋበችበት ልዩ መጎናጸፊያ፣ ያማረችበት ውብ ደምግባት … ዝግ ባለ በመጠበቅ ሕይወት ነው። የታየው ሁሉ ሲናፈቅ የነበረ ልዩ መገለጥ ነው። ነገር ግን ትጠብቅ ነበር … መከር የተወደደ ወቅት ነው ነገር ግን የእርሻ፣ የማለስለስ፣ የዘር፣ የአረም፣ የአጨዳ፣ የውቅያ … ጊዜ ሊከበር ይገባል። አለጊዜው ከሆነ ነገር በጊዜው ያልሆነ ነገር ይሻላል።
    የኾነውን ሁሉ ነገር ከመናገር የተቆጠበች፣ በልብዋ ተመስጣ በቃል ከሚገለጠው በላይ አሰምታ የተናገረች ይህች እናት የተሰጣት ጸጋ ጆሮ ላለው የሚሰማ፣ ዝምታዋም በውስጡ ከእልፍ ቃላት ይልቅ የሚጮህ ነው።
   ዛሬ "ማርያምን እንወዳታለን" የሚሉ ወገኖች "ስል አንደበትን" ማን እንዳሰለጠናቸው ከየት እንዳመጡት ቢነግሩን መልካም ነበር። የቅድስት ድንግል "በልብ መጠበቅ" ኮንፊዩሸስ እንዳለው "… ከአስር ሺህ ቃላት "በላይ የተብራራ ነው። እንደ ዝምታ እንደ መጠበቅም ያለ ታላቅ የድል መንገድ የለም። እንኳን ለስድብ፣ ለአሽሙር … ለመልካም ዝም ማለትን የኢየሱስ እናት ታስተምረናለች።
  አዲስ መከራ አፈኛ ያደረጋችሁ፣ "እንወዳታለን" እያላችሁ ለትውልዱ "የክህደትና የስድብ ምርቅ የምትፈተፍቱ ሆይ ዝምታዋ … ይውቀሳቸሁ!!! "…ማርያም ግን ይህን ነገር ኹሉ በልብዋ እያሰበች ትጠብቀው ነበር።"
  በልብ ማሰላሰል፣ ቃሉን ማጉተምተም፣ በጸሎት ማሰብን ጌታ ለኹላችን ያብዛ። ጌታዬ መድኃኒቴ ሆይ ክብር ሁሉ ላንተ ይጠቅለል። አሜን።

ነሐሴ 2008 ዓ.ም ተጻፈ!

2 comments:

  1. እንደ ዝምታ እንደ መጠበቅም ያለ ታላቅ የድል መንገድ የለም። tebarek abeni!

    ReplyDelete
  2. Tebarke beyesus seme

    ReplyDelete