Thursday 24 October 2019

ገና አልተመለከታችሁምን? (ማር. 8፥17)

Please read in PDF
ይህ ጽሑፍ በ2008 ዓ.ም አጋማሽ ላይ በአንድ ሌላ የጡመራ መድረክ ላይ በብዙዎች የተነበበ ነው! መልእክቱ ዛሬም ደማቅ ስለ ኾነ በድጋሚ እንዲቀርብ ኾኖአል!
       ቃሉን የተናገረው በወርቀ ደሙ የዋጀንና ያዳነን መድኅን አለም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ደቀ መዛሙርቱ በፈሪሳውያንና በሄሮድስ እርሾ ክፉ ኃጢአት በመዋጥ እንዳይጠፉ ባስጠነቀቃቸው ጊዜ፣ እነርሱ ግን ከማስተዋል ዘግይተው እንጀራ ባለመያዛቸው እንደ ተናገረ አስበው ተነጋገሩ። ጌታ ያየላቸው ዘላለማዊውን ዐሳብ ነው። እነርሱ ግን ገና በሥጋ አዕምሮ ነበሩና ስለ ቍሳዊውና ተበልቶ እዳሪ ስለሆነው እንጀራ አሰቡ። እርሱ ስለመንፈሳዊው ነገር ይነግራቸዋል እነርሱ ግን የሚናገራቸውን እንኳ በወግ አያስተውሉም።

      በመንፈሳዊው አለም ትልቁ ውድቀት የእግዚአብሔርን ዐሳብና ፈቃድ በራስ እውቀትና ማስተዋል ለመረዳትና ለማስተማር ማሰብ ነው። የትኛውም ሆነ ማናቸውም ዐሳብና ሥራ እንደ ጌታ ቃል እንደ ወንጌሉ ብቻ ነው መታየትና መመዘን ያለበት። የቤርያ ቅዱሳን አማኞች ማንም ቢያስተምር፣ ብዙ ተአምራትንም ቢያዩ ገና እንዳልተመለከተ ሰው ልባቸው የደነዘዘ ሳይኾን ብሩህ ኅሊና ሰፊ ልቡና ነበራቸውና የትኛውንም ትምህርትና ተአምር እንደ ጌታ ቃል እንደ መጽሐፉ ሲኾን ብቻ በሙሉ ልባቸው በመቀበል ያምናሉ፤ (ሐዋ.17÷10)።
     ይህ መመዘኛ ለኹሉም አማኝ የሚያገለግል ነው። ማንም ሊያስተምር ይችላል። ተናጋሪው የሚመዘንበት ዋናው ሚዛን ቅዱስ  ቃሉ ነው። የቱም ተአምር ሊታይ፣ ሊደረግ፣ ተገለጠ ሊባል ይችላል … ትልቁ የተአምራቱ መመዘኛ ቅዱስ የጌታ ወንጌል ነው። ከሰሞኑ የሰማነው አንድ ነገር አለ። "መስቀል ከሰማይ ወረደ" የሚል። እንግዲህ አሁን ነው ተአምሩን በጌታ ቃል ሚዛን መመዘን።
     በእውኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ዐሳብ መስቀል ሲል የተመሳቀለ እንጨትን ወይም ብረትን ወይም ወርቅን የሚጠቁም ነውን? ደግሞስ በሰማያዊው መንፈሳዊ ዓለም ላይም ይህ የምናየው ምድራዊና ቁሳዊ ነገር በዚያም የሰለጠነ ነውን? እንጨት፣ ብረት፣ ወርቅ … የሚባሉ ነገሮች በዚያ በሰማይም አሉ? በውኑ ይህን እንኳ ገና አላስተዋልንምን?
     ጌታ የመሰቀሉ ነገር ገና በማንም ልብ ባልታሰበበት ጊዜ "መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም። ነፍሱን የሚያገኝ ያጠፋታል፥ ነፍሱንም ስለ እኔ የሚያጠፋ ያገኛታል።" (ማቴ. 10፥38) ሲል፣ በእውኑ ስለየትኛው መስቀል ለመናገር ፈልጎ ይኾን? ትልቁን ጌታ መድኀኒ ዓለምን በሕይወት ብቻ የምንመስለው አይደለንም ለወንጌሉ እውነት በሞቱም እንኳ የምንተባበር ነን። ሕይወቱን ከእርሱ ጋር ለመኖር ሞቱንም ከእርሱ ጋር በመተባበር መስቀሉን (መከራና ሞቱን ችግርና ስደቱን ) ተሸክመን በመከተል ለእርሱ እንድንኾን ተጋብዘናል።
 በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ብዙ ጊዜ ዋና ዐሳብ እየሰወሩ፣ ቅዱስ ቃሉ የማይደግፈውንና የማይለውን እያጎሉ ማምጣት የተለመደ ሆኗል። ለምሳሌ፦ ቤተ ክርስቲያን የሚለውን ቃል ለሕንጻው ብቻ በመስጠት ወይም በማጉላት የመጽሐፍ ቅዱሱ ዋና ሐሳብ የሰው ሰውነትና ቅዱሱ የክርስቶስ ኅብረት ቤተ ክርስቲያን መባሉ ተድበስብሶ ተረስቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ መስቀል የሚለውም ቃል በተነሳ ቁጥር፣ ሰዎች ስለ ተመሳቀለው እንጨት እንጂ በመስቀሉ ሊተላለፍ የተፈለገው ዋናውን ዐሳብ ሥፍራም አልተሰጠው።
       ስለዚህም ለዐሳባቸው ማስፈጸሚያ ቃሉን ወደ ልባቸው ዐሳብ ሲያፈሱት እናያለን። "የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።"(1ቆሮ. 1፥18) በሚለው ቃል ውስጥ ሊነገር የተፈለገው ዋና ሐሳብ መስቀሉ አይደለም። ምክንያቱም "የ" የምትለዋ ፊደል ከፊት ታጫፍራለችና ሊነገር የተፈለገው ስለ"የመስቀሉ ቃል" ነው። ለሚጠፉ ሁልጊዜ ሞኝነት የኾነው የመስቀሉ ቃል፣ ቃለ እግዚአብሔር፣ አካላዊ ቃል፣ ፈጣሪ ቃል …  ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ለሚድኑ ግን የመስቀሉ ቃል ኃይላቸው፣ ቀኝ ክንዳቸው፣ ብርታታቸው ነው።
      በመጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በቤተ ክርስቲያን አባቶች ትምህርት የተመኩበትና ደስ የተሰኙበት መስቀል ቍሳዊው መስቀል አይደለም። ቅዱስ ቄርሎስ ዘእስክንድርያ "ከመስቀሉ በቀር በሌላ አልመካም" በማለት ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረውን ሲተረጉም እንዲህ ብሏል፣ ዳዊት "በመድኃኒቴ በእግዚአብሔር እመካለሁ" ብሎ እንደ ተናገረ መዝሙረኛውና ቅዱስ ጳውሎስ በሰው ሳይሆን በእውነተኛው አምላክ በክርስቶስ ይመካል፤ (ቄርሎስ እስትጉቡእ)። በመስቀሉ መመካት ማለት በክርስቶስ ከመመካት ጋር አንድና የማይነጣጠል ነውና፤ (ሮሜ 15፥7፤ ፊሊጵ. 3፥3)።
     ሰማያዊውን ዐሳብ ስንዘነጋ ወደ ምድራዊው ማዘንበላችን ግድ ነው። የመስቀሉ ቃል ክርስቶስ ከሆነ፣ በመስቀሉም ደም አለሙ ከዳነ (ዕብ. 10፥10፤ ሮሜ 5፥10፤ 1ጴጥ. 1፥19፤ ኤፌ. 1፥7)፣ መስቀሉም የክርስቶስን ሥራ፣ ሞትና ሕማሙንም ካመለከተ ለምን ይሆን ሰዎች ወደ ቍሳዊው ነገር ያዘነበሉት?
      የእስራኤል ልጆች በበረሐ በበደሉ ጊዜ በእባብ እንዲነደፉና እንዲሞቱ ሲታዘዝ ፈጥነው ወደ ልባቸው ተመልሰው ንስሐ በመግባታቸው እግዚአብሔር ሙሴን የነሐስ እባብ በመሥራት እንዲሰቅልና ያንን የተመለከተም እንደሚድን ነግሮ ብዙዎች ከመሞት ድነዋል (ዘኊ. 21፥4-10)። ነገር ግን የእስራኤል ልጆች ታላቁን የእግዚአብሔር ዐሳብ በመዘንጋት ያንን የነሐስ እባብ ቍስ ነገር ይዘው እስከ ሕዝቅያስ ዘመን ያመልኩት እንደ ነበር ተዘግቦልናል።
      የእግዚአብሔር ዐሳብ መርዝ ያለው እባብ ቢሰቀል የሚድን ሰው የለም ነው። ኃጢአት መርዝ ያለበት አዳማዊ ፍጡር ቢሰቀልም አያድንም። መርዝ የሌለበት እባብ ተሰቅሎ እስራኤል እንደ ዳኑ ምክንያት፣ በደል፣ ኃጢአትና ነውር ያልተገኘበት ንጹሑ ክርስቶስ ተሰቅሎ አለምን እንደሚያድን ድንቅ ምሳሌ ነበር (ዮሐ. 3፥14)። እነርሱ ግን  የዘላለሙን ሳይኾን የቅርቡን ቁስ አመለኩ። ዕጣንም አጠኑት።
    በኋለኛው ዘመን ግን ጣኦታትንና የመስገጃ ኮረብታዎችን ሐውልቶችንም የቀለጣጠመውን ታላቁን ቀናተኛ ንጉስ ሕዝቅያስን ጌታ እግዚአብሔር አስነስቶ" የእስራኤልም ልጆች እስከዚህ ዘመን ድረስ ያጥኑለት የነበረውን  ሙሴ የሠራውን የናሱን እባብ ሰባበረ ስሙንም ነሑሽታን ብሎ ጠራው።"(2ነገ. 18፥1-5) ትርጉሙም "ነሐስ ብቻ" ማለት ነው። ቍሳዊው መስቀልም ፍጻሜው ከዚህ የዘለለ አይደለም። የጌታ ዐሳቡ በመስቀሉ ቃል በክርስቶስ ዓለሙን ሁሉ ማዳንና እኛም ይህን በማመን እንድንቀርብ እንጂ እንደ ነሑሽታን እንጨቱን ብቻ በማየት እንድንቀር አይደለም። በውኑ ይህን ገና አልተመለከትንምን? ገናስ አላስተዋልንምን?
  እንድናስተውል ጌታ መንፈስ ቅዱስ ይርዳን፤ አሜን።

1 comment: