Please read in PDF
ዐውድ አንድን
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ለመረዳት ወሳኝ ነው፤ ዐውድን አለመረዳት ጠቅላላ የመጽሐፉን ዐሳብ አለመረዳት ነው፤ መንፈስ ቅዱስ ቀድሞ
የተናገረውን ያብራራልናል ይገልጥልናል እንጂ፣ አዲስ መገለጥም ኾነ ኢየሱስ ከተናገረው የተለየ የሚነግረን ምንም ነገር የለውም፤
ይህም በዐውድ ውስጥ ልንረዳው እንችላለን ማለት ነው፡፡ ከመንፈስ ቅዱስ ቀጥሎ፣ ዐውድ የቀደመው መልእክት ለዝንተ ዓለም ዘመን ዘለቅ
ኾኖ እንዲሻገር ኹነኛ አጥር ነው ማለት እንችላለን፡፡
የእምነት እንቅስቃሴ
አማኞችና መምህራን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ተማሪዎችን ለማሸማቀቅ ከሚጠቀሙባቸው መንገዶች አንዱ፣ “መገለጥ የላችኹም” የሚል በትዕቢት
የታጀለ ትምህርት ነው፤ ነገር ግን እነርሱ ራሳቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ዐውድ ውጭ ኾነው፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ለገዛ ራሳቸው ሃሳብ በማጣመም
እንዴት እንደሚተረጉሙና መገለጥ የሚሉትም የራሳቸውን ሃሳብ እንደ ኾነ የእምነቱ ቅድመ አያትና መሥራች የኾነው ኤሴክ ዊሊያም ኬንየን
የተረጐመውንና እውነተኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሃሳብ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡
ይህን የኬንየንን ሃሳብ የአገራችንም አያሌ የእምነቱ መምህራንና አማኞች ሲጠቅሱት
እንመለከተዋለን፤ መልካም ንባብ …
2ጴጥ. 1፥4፦“ስለ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት
አምልጣችሁ ከመለኮት ባሕርይ ተካፋዮች በተስፋ ቃል እንድትኾኑ፥ በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ ታላቅ የኾነ ተስፋን
ሰጠን፤”(2ጴጥ. 1፥4)። በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ላይ የቃል እምነት መምህራን “የመለኮትን ባሕርይ ከመካፈል ይልቅ ሙሉ
ለሙሉ መለኮት መኾናቸውን” ይናገራሉ። “ተካፋዮች” የሚለውን ቃል አይቀበሉትም ወይም መካፈልን አያመለክትም፣ ሙሉ ለሙሉ መኾንን
እንጂ ብለው ፈጽመው ይክዳሉ። የእምነቱ ዋና መምህር ዊሊያም ኬንየን ይህን ዐውድ ባብራራበት ክፍል ሲናገር፦
“ ... እኛ የእግዚአብሔር ባሕርይ ተካፋይ ኾነናል ማለት ነው። ስለዚህም
በእግዚአብሔር ልጅ ውስጥ ያለው ተመሳሳይ ሕይወት በእኛም ውስጥ በሙላት አለ።”[1]
ይላል። የቃሉ ዐውድ
ከእነርሱ በተቃራኒ የቆመ መኾኑን ምንም ክርክር የለውም። ከዮሐንስ ወንጌል ዐሳብ ጋር ወይም ጌታችን ኢየሱስ ከተናገረው ዐሳብ
ምንም ዐይነት ዝምድና የለውም።
ቅዱስ ጴጥሮስ እያስተማረን ያለው፣ ከክፉ ምኞት የተነሣ በዓለም ውስጥ
ካለው ዓለማዊና የጥፋት ሕይወት በማምለጥ ከመለኮታዊ ባሕርይ ተካፋዮች እንዲኾኑ፣ “በእነዚያ ክብርና በጎነት የተከበረና እጅግ
ታላቅ የኾነ ተስፋን” ሰጥቶናል በማለት ነው። ከመለኮቱ ባሕርይ ተካፋዮች እንኾን ዘንድ የጸጋን፣ የኀጢአት ይቅርታን፣ ከመንፈስ
ቅዱስ የኾነ አዲስ ሕይወትንና የእግዚአብሔር ልጅነትን ተስፋ ሰጥቶናል። ይህ ታላቅና የከበረ ነገር የተሰጠን በቅድስና እንመስለው፣
ይኸንኑ ባሕርዩን እንካፈል ዘንድ እንጂ መለኮትን እንኾን ዘንድ አይደለም። አዎን! የተሰጠንና እንድንኖርለት የሚገባን ነገር
አለ፤ ከቅድስናው ባሕርዩ እንካፈል ዘንድ የሚያስችለንን ጸጋ፣ መለኮታዊ ኃይሉን ይሰጠናል፤ (ኤፌ. 3፥20፤ ፊል. 2፥13፤
4፥13)፤ በእውነትም መንፈሳውያን እንኾን ዘንድ ከርኩሰት ኹሉ ያስመልጠናል፤ (1ተሰ. 4፥7)።
ክርስቲያኖች እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው ስለሚያድር፣ ኀጢአትን
የማድረግ ዝንባሌ አይኖራቸውም፤ (ዮሐ. 14፥17፤ 1ዮሐ. 3፥9)፣ ኀጢአተኞች ግን ኀጢአትን የሚያደርጉት በውስጣቸው ካለው የኀጢአት
ባሕርይ የተነሣ ነው። ስለዚህም ክርስቲያኖች እንዲህ ካለ እግዚአብሔር ከሚጠየፈው የኀጢአት ዝንባሌ በመራቅ ወይም በማምለጥ፣
ከእርሱ ጋር እንዲኖሩ በሰማያዊ ቅዱስ ጥሪ ይጠራሉ። ደግሞም እንድንካፈለው የተባለልን ነገር አለን፣ እርሱ፦ “ከቅድስናው
እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል” (ዕብ. 12፥10)፣ መከራውንም አብረን እንካፈል ዘንድ ይገባናል፣ (1ጴጥ. 4፥13፤
5፥1)። ስለዚህም ከዓለማዊ ርኩሰት አምልጠን የቅድስናውን ባሕርይ ተካፍለናልና እንደ እርሱ በተመሰከረለት ጽድቅ ልንመላለስ
ይገባል።
ሰው በእግዚአብሔር መልክ ተፈጥሯልና፤ አምላክ ባይኾንም በመለኮታዊ
ባሕርይ ተሳታፊ መኾን ይችላል፤ ይህም ማለት፣ ሰው መንፈስ ቅዱስን እስኪቀበል በፍጹም ጕድለት ውስጥ ይኖራል፤ ፍጹም ስላይደለም
ፍጹም የእግዚአብሔር ሰው አይደለም፤ መንፈስ ቅዱስን ሲቀበል ግን “ከመለኮት ባሕርይ ተካፋይ” ይኾናል። ይህም በቅድስና
እግዚአብሔርን መምሰልን የሚያሳይ ነው፤ (1ቆሮ. 6፥19፤ ኤፌ. 4፥24)። ደግሞስ ከዚህ ክፉ ምኞት በዓለም ካለው ጥፋት
ያመለጠና የዳነ አማኝ፣ ከአዳኙ ጌታችን ኢየሱስ መስቀል ሥራ የተነሣ፣ ከመለኮት ባሕርይ ይካፈላል እንጂ፣ እንደ ምን አምላክ
መኾን ይቻለዋል?!
የቃሉ ዐውድ በትክክል እንዲህ ሊታይ ሲገባው፣ በድፍረት ቃል ራሱ
እግዚአብሔርን ወደ መኾን ለማደጋችን ማስረጃችን ነው ብሎ መጥቀስ የራስን መሻት ከመናገር አይዘልም። ምክንያቱም እኛ መቼም
ቢኾን ሰውነታችንን ጥለን መለኮታዊ አካል ወይም ባሕርይ አንለብስም፤ በዚሁ የሰውነት አካልና ባሕርይ በሰማያትም የምንቀጥል
መኾናችንንና አካላዊ ማንነት ያለን መኾኑን ጌታችን ኢየሱስ፣ “በትንሣኤስ እንደ እግዚአብሔር መላእክት በሰማይ ይሆናሉ እንጂ
አያገቡም አይጋቡምም” (ማቴ. 22፥30) በማለት አስተምሮናል።
(የእምነት እንቅስቃሴ የዛሬዪቱ
ቤተ ክርስቲያን ፈተና ከሚለው መጽሐፍ ከገጽ 30-31 የተወሰደ)
lik bilehal
ReplyDelete