Friday 30 August 2019

የቄሳር ተላላኪ “ቀሳውስት” - ሠርግና ምላሽ



ቤተ ክርስቲያን ከመንግሥት ጋር “ተቃራኒ” በነበረችባቸው ዘመናት፣ ማለትም ነገሥታት ጸረ ክርስትና አቋም ይዘው ተነሥተው በነበሩባቸው ዘመናት፣ ቤተ ክርስቲያን ከሩቅ የሚታይ አብረቅራቂ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋን ተጐናጽፋ ነበር፤ ከአንድ መቶ ሃምሳ ዓመታት በላይ ከኔሮን ቄሣር እስከ ዲዮቅልጥያኖስ የዘለቀው ጽኑ የመከራ ዘመን ቤተ ክርስቲያን እንደ ቦኸር በዐለት ላይ ተከላት እንጂ፣ ፈጽሞ ካመነችው እውነትና ከመንፈስ አንድነቷ አላነወጣትም፤ አልከፋፈላትም፡፡ መከራ ማጥሪያዋ ብቻ ሳይኾን መጽናኛዋም ጭምር ነበር፡፡



   ቤተ ክርስቲያን በመከራው ዘመን እንደ ፈርጥ ደምቃ ታየች፤ እንደ ፀሐይ ፈካች እንጂ ፈጽሞ አልደበዘዘችም፤ የኔሮን ቄሣር እጆች ከመግደል ብዛት ደከሙ እንጂ ቤተ ክርስቲያንን አላንበረከኩም፣ የነዳክዮስ የክስ ዘመቻ ሐሰትነቱ ሲገለጥ ታፈረበት እንጂ እርሷን አላኮሰመናትም፣ የነ ማርቆስ አውሬሊያኖስ ጽንፍ የለሽ ጥላቻ ቤተ ክርስቲያንን ፊቷን አላጨማደዳትም፣ የትራይ ኢኖስ ክርስቲያኖችን ማታገያ ኮሎሴየም ግንባታና ከአውሬ ጋር ማታገል ስፍራ ቤተ ክርስቲያንን ቅንጣት ታህል አላስፈራትም፣ የዲዮቅልጥያኖስ ጥበባዊ ሴራና የማያባራ የመሰለው ፍጅቱና ማሰቃየቱ እርሱን አታከተው፣ አደከመው እንጂ ቤተ ክርስቲያንን ፈጽሞ ወደ ኋላ እንድታፈገፍግ አላደረጋትም፡፡ ነገሥታቱ አረጁ፣ አረመኔዎቹ አለፉ፣ በቤተ ክርስቲያን ሰቆቃ የሳቁ ኹሉም ረገፉ፣ የማሰቃያና የግድያ ጥበባቸው ኹሉ አለቀባቸው፣ ገዳይ እጃቸውና ልባቸው ዛለ፣ ስለታቸው ዶለዶመ፣ ጦራቸው ታጠፈ፣ ቤተ ክርስቲያን ግን ጎመራች፣ በዛች፣ አፈራች፣ በረከተች፣ ተትረፈረፈች፣ ከተወዳጁ መሲሕዋ ጋራ እየዘመረች ክፉዎቹን ቀናት ተሻገረች፡፡
   ነገር ግን ቤተ ክርስቲያን በተደጋጋሚ የወደቀችበት ፈተናዋ ከቤተ መንግሥት ጋር ስትሻረክ ነው፤ ከመከራ ዘመን ይልቅ ቤተ ክርስቲያን ውብ ቀሚሷ ተቀድዶ የታየውና ከመንፈሳዊ ጭካኔዋ ተለሳልሳ የታየችበት ዘመን ቢኖር፣ ከመንግሥት ጋር “ጋብቻና ስምም” በፈጠረችባቸው ዘመናቷ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሙሽራዋ አንድ ነው፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ! ደግሞም የምታውጀውና የምትመሰክረው አዋጅዋ አንድ የሰማይ መንግሥት አዋጅ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ሌላ ሙሽራ፣ ሌላ የመንግሥት አዋጅ የላትም፡፡
    በመከራው ዘመን የስህተት ትምህርት ወይም ቤተ ክርስቲያንን የሚከፋፍል ነገር ሳይኖር ቀርቶ አልነበረም፤ ቢኖርም ግን አቅም አልነበረውም፤ ምክንያቱም የመከራ ዘመን በመንፈሳዊ ሕይወት ለጨከኑ፣ በኢየሱስ ጉዳይ በሕይወታቸው ለማይደራደሩ ብቻ እንጂ ተልመጥማጦቹና ግብዞቹማ ጊዜውንና ዘመኑን ለመምሰል ማን ተካክሎዐቸው!!! በመከራ ዘመን ወደፊት የሚመጡትና በኢየሱስ ስም የመጣውን መከራ ለመቀበል ደስተኞች የሚኾኑት፣ የኢየሱስ መስቀልና ኑሮ በትክክል የገባቸው ብቻ ናቸውና፡፡
   ታላቁ ቆስጠንጢኖስ ሲመጣ በክርስቲያኖች ላይ የነበረውን መከራ በአዋጅ ሻረው፤ እናም ቤተ ክርስቲያን “የነጻነት ዘመንን ተጐናጸፈች”፤ ከመከራ አረፈች፡፡ ነገር ግን ገና ከማረፏ በመከራው ዘመን፣ ለሽ ብሎ የነበረው የስህተት ትምህርትና የሚከፋፍል መንፈስ ወዲያው በአርዮስ አማካይነት አቈጠቈጠ፤ በመከራው ዘመን ያልሰበከውን ስብከት አኹን የነጻነት ዘመን ሲፈነጥቅ በአደባባይ መስበክና ማስተማር ጀመረ፡፡ “አብ ወልድን፣ ወልድ ደግሞ መንፈስ ቅዱስን ፈጠረው” የሚለው የአርዮስ ኑፋቄያዊ ትምህርት መላ እስክንድርያን አናወጣት፡፡ እናም ይህ ትምህርት የመንፈስ አንድነቷን የሚያናጋ ኾነ፡፡
   እንደ ቅዱስ አትናቴዎስ ያሉ ቆራጥ አባቶች አርዮስንና ደጋፊዎቹን ፊት ለፊት ተጋፈጡ፤ ከመንበረ ፓትርያርኩ ከሠላሳ ዓመታት በላይ ለመሰደድ ምክንያት የኾነውም አርዮሳውያንን ፊት ለፊት መቃወሙ ነበር፤ መንግሥት የሰጠውና ያወጀው “የነጻነት ዘመን” እንኳ፣ ለእውነተኛ አማኝ ደቀ መዛሙርት ፈጽሞ የሚመች በረከትና ኹኔታ የለውም፡፡
   ከሰሞኑ “በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም፣ “ክልላዊ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት” ለመክፈት “በቄስ በላይ መኮንን” አስተባባሪነት መገናኛ ብዙሃን መጋበዛቸውን ሰማንም፤ አየንም፡፡ የስብሰባቸውንም ስፍራ በመሃል አዲስ አበባ በሚገኘው “የኦሮሞ ባህል ማዕከል” እንደ ኾነም ጭምር በማስታወቅ፡፡ ባልሳሳት የኦሮሞ ባህል ማዕከልን የሚያስተዳድረው መንግሥት እንደ ኾነ አይጠፋኝም፤ መንግሥትንና “ክልላዊ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት”ን ግን ምን ሊያሻርካቸው እንደ ቻለ መገመት ብዙም አድካሚ አይደለም፡፡
  ሃሳቡ እጅግ የተሰነገ ሃሳብ ነው፤ የቀረበበት መንገድ ፍትፍት ቢመስልም ውስጡ ግን ምርቅ ነው፤ ሽፋናዊ ምክንያቱ፣ “በቋንቋችን ወንጌል እንስማ፣ እንቀድስ፣ በቋንቋችን ወንጌል እንስበክ …” የሚል ሲኾን፣ ይህን አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱት ግን “ኢሬቻና ብዝሃ አማልክትን” የሚደግፉና በቦታውም ተገኝተው በሚባርኩ “ቀሳውስትና መነኮሳት”፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ “ሽማግሌዎች” ጥልቅ ጥላቻ ባላቸውና “ውድቀቷን በሚመኙ” አካላት አማካይነት መኾኑ ደግሞ ነገሩን ከእባብ ወደ ዘንዶ ያደርገዋል፡፡ 
  በገዛ ቋንቋ ወንጌልን መስማት፣ ማምለክ፣ መስበክ፣ መገልገል … ምንም ችግር የለበትም፤ ቤተ ክርስቲያንም በየዘመኗ ይህን ስታደርግ ኖራለች፣ መንፈሳዊ የውዴታ ግዴታዋም ነው፡፡  ነገር ግን ይህን ልታደርግ የምትችለው ከዘረኝነትና ከብሔርተኝነት ዘውግ ነጻ ወጥተው፣ ለመላው ዓለም ወንጌል እንዲዳረስ በሚናፍቁና በመንፈስ በሚቃጠሉ አማኝ ልጆቿ እንጂ በፖለቲካ ካቲካላና አብሾ ሰክረው፣ አንድ ብሔርና ነገድ በሚያንቆለጳጵሱ “አድሎዓዊ ወገንተኞች” አይደለም፡፡ እንዲህ ያለ ሠርግና ምላሽ ፍጻሜው ውርደትና ውድቀት እንጂ ፈጽሞ ክብርና ትንሣኤ አይኾንም፡፡ ቋንቋና ብሔር አንድ ካደረገው ይልቅ፣ የተለያየ ቋንቋ እየተናገረና የተለያየ ባህል ይዞ በወንጌል ተማርኮ ዘመን የተሻገረ ክርስትና እንዳለን ከመጽሐፍ ቅዱስ ባሻገር ሕያው ታሪክ ምስክር አለ፡፡
   እውነተኞች ከኾንን የየትኛውም ቋንቋ ተናጋሪና ባህል ተከታይ ብንኾን፣ ባለንበት ኾነን መጠየቅና ማድረግ የሚከለክለን የለም፤ እስከ ዛሬም ድረስ ቤተ ክርስቲያኒቱ “ኹሉንም በቋንቋ ስታስተምር” ነበር፤ አያሌ ድክመቶችና ስንፍናዎች ቢኖሩባትም፡፡ በተለይም እንዲህ ያለው ዘርንና ነገድን ማዕከል ያደረገ ቡድንተኝነት ለሌሎቹም አብያተ ክርስቲያናት ክፉ ምሳሌና አስነዋሪ ተግባርም ነው፡፡ በተደጋጋሚ የዚህ ጡመራ መድረክ ጸሐፊ በምዕራቡ ዓለም፣ በዘረኝነትና በብሔርተኝት፣ በሰፈርና በወንዝ የተደራጁ ዲያስፖራዎች የያዙትን መርገም ሃሳብ ይዘው መጥተው ቢረጩ ውጤቱ እጅግ መራር፣ አገርን በብዙ መከፋፈል ውስጥ ሊያስገባ እንደሚችል በተደጋጋሚ ማንሳቱን ማስታወስ ይወዳል፡፡   
   እንግዲህ የቤተ መንግሥት የፖለቲካ ግብር እየበሉ፣ ቅዱስ ቃሉን ከዐውዱ ቦጭቀው በማውጣትና ላልተነገረበት ዓላማ በማዋል፣ “ስለወንጌል ሁሉን አደርጋለሁ” ብሎ ወንጌላዊ ለመምሰል ጠቅሶ፣ ነገር ግን በሕዝቡ መካከል ክፉ እንክርዳድ የሚዘሩትን እንደ ቅዱስ ቃሉ አይደለም ከማለት ባሻገር፣ በዚህ ጉዳይ በብዙ ልንማልድ ይገባናል፡፡ በተለይም ከዚህ ጀርባ ኾነው በፖለቲካ ቀመር የሚያሤሩትን ሴረኞች እጃቸውን እንዲሰበስቡ “ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ” እንዲል፣ ተዉ፣ እረፉ፣ አትሸቅጡ ማለትን እንወዳለን፡፡ ሉዓላዊው አምላክ በዙፋኑ አለ፣ ምንም ነገር ከእርሱ ቁጥጥር ውጭ አይደለም፣ እንዲህ ሲደረግ ዝም ያለው ደካማ ስለኾነና ማስወገድ ስለማይችል አይደለም፤ ነገር ግን ከክፋታችን እንመለስ ዘንድ በብዙ ምሕረት በሩን አስፍቶ እየጠበቀን ያለን፣ ጠባቂ አባት ስለኾነ ብቻ ነው፡፡
   ቄስ በላይና ከጀርባ ያላችሁ ጳጳሳት ሆይ! ማፍረስን መምረጣችሁ፣ አንድነትን መናድ መውደዳችሁ፣ ወንጌል ታክካችሁ ለአንድ ብሔር “የወንጌል ዘብ” መቆማችሁ … የወንጌል ጠባይ፣ ከኢየሱስ ሕይወትና ትምህርት የተቀዳ አይደለምና መንገዳችሁን መርምሩ፣ የልባችሁን ቤት አስተካክሉ፣ አይበጃችሁምና አካሄዳችሁን በንስሐ አቅኑ፤ ጌታ ኢየሱስ ለሰው ኹሉ የሞተበትን የመስቀሉን ሥራ ማየት እንድትችሉ የልባችሁን ዓይኖች ያብራላችሁ፤ አሜን፡፡


2 comments:

  1. Dear friend in Christ
    I like very much your blog but now your Post has some problem.One thing we should understand clearly is that God is not the respector if any language.if someone wants to worship God with his mother tongue language.This will not make him racists.A racist is someone who protect people from worshipping God by his mother tongue language.

    ReplyDelete
  2. Dear friend in Christ
    I like very much your blog but now your Post has some problem.One thing we should understand clearly is that God is not the respector if any language.if someone wants to worship God with his mother tongue language.This will not make him racists.A racist is someone who protect people from worshipping God by his mother tongue language.

    ReplyDelete