Please read in PDF
2.
ለመስረቅ፦ ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ወደ በጐች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው፤” በማለት ሲናገር ሾላኮቹ ራሳቸውን በማመሳሰልና በመደበቅ የተካኑ መኾናቸውን
እየነገረንም ጭምር ነው፤ (ዮሐ. 10፥1)። ሌባ በባሕርይው ተደብቆ ወይም ሾልኮ እንጂ በግልጽ መግባትን አያውቅም። ይህንም የሚያደርገው
ተቀዳሚ ዐላማው የእርሱ ያልኾነውን ነገር፣ ለራሱ ጥቅምና ፍላጎት ለመስረቅና ለመውሰድ ነው።
ብዙ ጊዜ ለመሹለክ እንዲያመቸው አገባቡ በሌሊት ነው (ኢዮብ 24፥14፤ 1ተሰ. 5፥2)፤ ዘወትርም በመስኮት እንጂ በበር
የማይገባ አደገኛ ነው (ኢዮ. 2፥9)፤ በብሉይ ኪዳን፣ “ማንም ሰው ከእስራኤል ልጆች ከወንድሞቹ አንዱን ሰርቆ እንደ ባሪያ ሲያደርግበት ወይም ሲሸጠው ቢገኝ፥ ያ
ሌባ ይሙት፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታስወግዳለህ።” (ዘዳ. 24፥7) ተብሎ እንደ ተጻፈ፣ ሌብነት ይህን ያህል በቀደመው
ኪዳን ጥዩፍና ርኩስ ተግባር ነው። ባለቤቱ በሌለበት፣ ሳይፈቅድም የራስ ያልኾነ ማናቸውንም ነገር ለራስ መብትና ጥቅም መጠቀም እርሱ
ሌብነት ነው።
የራሳቸው ያልኾነን ነገር ለመውሰድና ለመስረቅ፣ ሌቦቹ ወይም ሾላኮቹ የሚመጡት
ድንገት ወይም ሳይታሰብ፣ ባለቤቱ በማያውቅበት መንገድና ሰዓት ነው፤ (1ተሰ. 5፥4፤ 2ጴጥ. 3፥10)። ሾላኮቹ ሌቦች ሊሰርቁ
የሚመጡት ተራ ቍስን አይደለም፤ ለክርስቶስ የሚገባውን ክቡሩን የሰው ልጅ እንጂ፤ የብሉይ ኪዳን የሐሰት ነቢያት ያገኛቸው ወቀሳ
በሐሰተኝነት በጐችን ለክፉዎች አሳልፈው በመስጠታቸው ነው፤ የበጐችን ነገር ለራሳቸው መብትና ጥቅም ሙሉ ለሙሉ ማዋላቸው ነው፤ “ጕበኞቹ ዕውሮች ናቸው፥ ሁሉ ያለ እውቀት ናቸው፤ ሁሉም ዲዳ የሆኑ ውሾች ናቸው ይጮኹም ዘንድ አይችሉም፤ … መብል ወዳጆች ከቶ የማይጠግቡ ውሾች ናቸው፥ እነርሱም ያስተውሉ ዘንድ የማይችሉ እረኞች ናቸው፤” (ኢሳ. 56፥10-11)።
ሌባ በማናቸውም ሰዓት እንደሚመጣ (ራእ. 3፥3)፣ ሾላኮቹና የሰዎችን ነፍስ
የሚነጥቁ መናፍቃንና የሐሰት መምህራንም የሚመጡት እንዲሁ ነው፤ ሌቦ የሚመጡበትን ሰዓት ብናውቅ አስቀድመን ተጠንቅቀን በጠበቅናቸው
ነበር፤ (ሉቃ. 12፥39)። ነገር ግን የሚመጡበትን ሰዓት አናውቅምና እጅግ መጠንቀቅ ይገባናል፣ መንገዳቸው ስብከት፣ ትምህርት፣
መዝሙር፣ ባልንጀራ … ሊኾን ይላል፤ በዚህ ወጥመዳቸው ነፍሳችንን ከነጠቁ በኋላ ያለርኅራኄ ባሪያቸው ስለሚያደርጉን ከእነርሱ መጠበቅ
ይገባል።
ከሌባና ከሾላካ ጋር የሚተባበር እርሱ ነፍሱን የሚጠላ ነው፤ ነፍስን ከሚሰርቁና
ፈጽመው ሊያርዱ ከሚያደቡ ጋር የሚሠሩማ እንዴት ይበልጥ ነፍሳቸውን የሚጠሉ አይኾኑ? (ምሳ. 29፥24)። መጽሐፍ ቅዱስን ለመስማት
አለመውደድ፣ የኢየሱስን ሕይወት ለመኖር አለመሻት፣ ቅዱስ መጽሐፍ ለሚለው ብቻ ለመገዛት አለመፍቀድ … በሞት ሸለቆ ውስጥ ለመረማመድ
ማሰብ ነው።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተቃራኒው ግን እርሱ በፊት ለፊት እንጂ በጓሮ በር
አይገባም፣ ደግሞም የሚራራ፣ በፍቅርና በእውነት የሚያስበን፣ እንደ ፈቃዱም የሚያስፈልገንን የሚያደርግልን፣ ሕይወት እንዲኾልንና
እንዲበዛልን የመጣ ተፈቃሪና አፍቃሪ ውድ እረኛችን ነው። ሾላኮቹ ግን ዘወትር ዓላማቸው ከኢየሱስ በተቃራኒ፣ “ሆዳቸው አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው” (ፊልጵ. 3፥19)።
ጌታችን ኢየሱስ ከእኛ ምንም ሳይጠብቅ እንደ ምሕረቱ ባለጠግነት ራሱን አሳልፎ
ሰጠን፤ ወደደን፣ በሚይዝና በማይጥል ሕያው ፍቅር ወደደን፤ ምሕረትና ባለጠግነቱን አፈሰሰልን፤ ሌቦቹ ግን ኹል ጊዜ ይህን ሕያውና
ቅዱስ እውነት ሊሰርቁብን ይመጣሉና ከእነዚህ ፈቀቅ ማለት መንፈሳዊ ግዴታ አለብን። የተሰቀለውን ኢየሱስ፣ በክብር ትንሣኤ ያረገውን
ጌታና መድኃኒት፣ አምላክና ቤዛ ሳያፍሩበት እየመሰከሩ የማይመጡ ሁሉ እኒህ ሾላካ ሌቦች፤ ለራሳቸው ክብርና ጥቅም የሚክለፈለፉ ናቸው፤
ኢየሱስ ግን በተገለጠ ሕይወትና ትምህርት እነሆ ዘመናትን አልፎና አሳልፎ አለ፤ ስሙ ይባረክ፤ አሜን።
3.
ለማረድና ለመግደል፦ ጌታችን
ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ እርሱ ሌባ ወንበዴም ነው፤” በማለት ከተናገረ በኋላ፣ ሌባው የሚመጣበትን ምክንያትና ዓላማ ሲናገር ደግሞ፣
“ሌባው ሊሰርቅና ሊያርድ ሊያጠፋም እንጂ ስለ ሌላ አይመጣም፤” በማለት
በግልጥ ይናገራል፤ (ዮሐ. 10፥1፤ 10)። መስረቅና ማረድ፣ ማጥፋትም የሾላካው ሌባ ዓይነተኛ ጠባይ ነው። የራሱ ገንዘብ አይደለምና
ለሰረቀው ለየትኛውም ንብረትና ሃብት አንዳች አይሳሳም።
ይህ የሾላኮቹን እጅግ ከፍ ያለ ጭካኔያቸውን፣ ከክፉ አውሬ ያልተናነሰ እኩይ ጠባያቸውን አመልካች ነው። እነርሱ አራጆችና
ገዳዮች፣ ነፍሳችንን አጥፊ እንጂ እኛን ያዳነንና ከጥፋት ያስመለጠንን የጌታችን ኢየሱስ ሕይወትና ትምህርት ፈጽሞ የሌላቸው፣ ለምድ
ለባሽ ተኩላና ቀበሮዎች ናቸው፤ ነገር ግን በተከታዮቻቸው ፊት እጅግ አዛኝና ሩኅሩኅ ኾነው ይታያሉ፤ ይህን ተግባርም በዒላማ በተከታዮቻቸውና
በሚደግፏቸው ፊት ያደርጋ። የሐሰተኛ መምህራን ተከታዮች አጥብቀው ለመምህራኖቻቸው ፍጹም የሚሟገቱበት ምክንያቱ ይኸው ነው።
የሾላኮቹ ደቀ መዛሙርት እነርሱ ለመምህራኖቻቸው
ሲቀኑ ትክክል፣ እኛ ለኢየሱስ ስንቀና ስህተት፣ እነርሱ እኛን እስከ ግል ሕይወታችን መጥተው ሲሳደቡ እውነተኞች፣ እኛን ግን በመርዝ
የተለወሰ ምርቅ ትምህርታቸውንና በካባና ላንቃ የተሽሞነሞነ ዝንባሌያቸውን እንደ ቃሉ ስንተችና ስንሔስ ግን “የወንድሞች ከሳሽ፣
ጠላት፣ ሐራጥቃ” ታርጋችን አድርገው መለጠፍን እንኳ ዘወር ብለው መመዘን እስኪሳናቸው ድረስ የሚታወሩት ከዚህ የተነሣ ነው። እስከ
መጨረሻውም ከኢየሱስ በላይ ለሾላካና አራጅ መምህራኖቻቸው እጅግ ታማኝ ናቸው።
ነገር ግን አራጅነት መለያቸው፣ ገዳይነት ኹነኛ ጠባያቸው፣ ማጥፋት ደግሞ የመጨረሻ
ግባቸው እንደ ኾነ ፈጽሞ ልንዘነጋ አይገባንም። ይህንም የሚያደርጉት ደግሞ ለራሳቸው ክብርና ጥቅም ብቻ እንጂ ኢየሱስን ለማክበር
ወይም ለኢየሱስ ክብርን ለማምጣት አይደለም። ልክ የብሉይ ኪዳን የሐሰት ነቢያት የበጐችን ጠጉር ለልብሳቸው፣ ሥጋቸውን ደግሞ ለሆዳቸው
እንደሚያደርጉ እኒህም ያው ናቸው። “ራሳቸውን ለሚያሰማሩ ለእስራኤል እረኞች ወዮላቸው! እረኞች በጎችን ያሰማሩ ዘንድ አይገባቸውምን? ጮማውን ትበላላችሁ ጠጕሩንም ትለብሳላችሁ፥ የወፈሩትን ታርዳላችሁ፤ በጎቹን ግን አታሰማሩም።” እንዲል፣ ሐሰተኞች መምህራን እንዲህ ናቸው፤ እውነተኛ አማኞች፣ የኢየሱስ በጎች ሆይ! ወደ እረኛችሁ ከማያመለክቱ፣
ከአባቱ ጋር ከማያወዳጇችሁ፣ ከመንፈሱም ጋር ከማያጣብቋችሁ አባይና ሾላካ አገልጋዮችን እንደ ቃሉ እየመረመራችሁ ራቁ፤ ተጠበቁም፤
ለእናንተ ግን ኢየሱስን መውደድ፣ አባቱን ማፍቀር፣ መንፈሱን መጣበቅ ይብዛላችሁ፤ አሜን።
ይቀጥላል …
ተባረክ አቤኑ
ReplyDelete