Monday 12 August 2019

ሾላኮቹ (ክፍል ፩)

Please read in PDF
   መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ቃል ሐራጥቃ[1] የኾኑ መናፍቃንን ጠባያቸውን ሊገልጥ በሚችል መንገድ፣ ሾላኮች ወይም ወደ ቤቶች ሾልከው የሚገቡ በማለት ይጠራቸዋል፤ (ገላ. 2፥4፤ 2ጢሞ. 3፥6፤ ይሁ. 4)። ቅዱስ ጳውሎስ ወደ እግዚአብሔር አደባባይና ወደ አማኞች የሚገቡት እንደ ሰላይ ነው ይለናል፤ ጌታችን ኢየሱስ ደግሞ ከአማኞች ጋር ልዩነት የሌላቸው እስኪመስሉ ድረስ “እንደ ተኩላ” (ማቴ. 7፥15) ነው ይለናል፤ ሰላይ መመሳሰልን ገንዘብ ያደርጋል፤ ተኩላም ኹለ ነገሩ ከበግ ጋር አንድ ዓይነት መኾንን ይመርጣል፤ ይህን ተፈጥሮአዊ ተመሳስሎታቸውን የሚጠቀሙት ግን የሚፈልጉትን ለማግኘት ወይም በጭካኔያቸው ለመንጠቅና በግን በሕይወቱ ቦጫጭቀው ለመብላት ነው።

   ጌታችን ኢየሱስ በሌላ ስፍራ፣ “ወደ በጎች በረት በበሩ የማይገባ በሌላ መንገድ ግን የሚወጣ” (ዮሐ. 10፥1) በማለት ሾላካነታቸውን ይገልጥልናል። እውነተኛ እረኛ ኹል ጊዜ በበሩ እንጂ በሌላ በር አይገባም፤ ጌታ ኢየሱስ እውነተኛ እረኛ ነው፣ እውነተኛ እረኛ ስለኾነም፣ ሕይወቱም ትምህርቱም ፊት ለፊትና ግልጽ ነው፤ የሚገባው በበሩ ነው፣ በጐቹን ለማሠማራትና ለመጥራት የሚወጣውም በበሩ ብቻ ነው፣ ጌታችን ኢየሱስ መዳፋችንን በግልጥ ከምናየው በላይ እጅግ በጣም ግልጽ የኾነ ማንነት ያለው ነው።
   ግልጥ ሕይወትና ትምህርት ስላለውም በጐቹን ድምጹን አሰምቶ ይጠራቸዋል፤ እነርሱም ድምጹን ለይተው ያውቁታልና ይመልሱለታል። ሾላኮቹ ከመዳን በፊት ወዳለው ሕይወት ወይም ደግሞ መዳናቸውን በቀጥታም ይኹን በተዘዋወሪ በማስጣል እነርሱን ብቻ እንዲተባበሩ ለማድረግ፣ ወደ ገላትያ አማኞች ሾልከው እንደ ገቡት እንዲሁ ከማድረግ ቸል የሚሉ አይደሉም።
   ኹል ጊዜም ቃላተ እግዚአብሔርን ተተግነው የሚመጡና ለእግዚአብሔር ቀናተኞች መስለው ሰለሚገለጡ ሾላኮችን አስቀድሞ መለየትና ማወቅ አዳጋች ነው። ሾልከው ሲገቡም እጅግ የሚመሳሰሉ ናቸው፤ አንዳንዴ እንዲያውም ከእውነተኞቹ ደቀ መዛሙርት ይልቅ በብዙዎች ዘንድ ይታመናሉ፣ ብዙ ተከታዮች አሏቸው፣ “አጋንንትን ሊያወጡ”ና ታላላቅ ተአምራትን ሊያደርጉ ይችላሉ፤ ለዚህም ነው፣ ለማሳሳት እንዲመቻቸው ሾላኮቹ ክርስቶስና መጽሐፍ ቅዱስን ተተግነው ትምህርቶቻቸውን የሚያዘጋጁትና የሚያስተምሩት። የትኛውም የስህተትና የኑፋቄ ትምህርት ለሚያስተምረው አንድ ትምህርቱ ቢያንስ አንድ ማስደገፊያ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ አለው።
 ሐራጥቃውያን በተለይም መጽሐፍ ቅዱስን ከተነገረበት ዐውድ ውጭ መተርጎምና ማስተማር[መጽሐፉ የለም ያለውን አለ፣ አለ ያለውን ደግሞ የለም ወይም አዎ ያለውን አይደለ፣ አይደለም ያለውን ደግሞ አዎ በማለት] የተካኑበት ዋና “ሙያቸው” ነው፤ ተከታዮቻቸውም ንግግሮቻቸውን በማድነቅና በማጋፈር እንጂ የሰሙትን በቅዱሳት መጻሕፍት እውነት በመመዘን አይከተሏቸውም። የሾላኮች ደቀ መዛሙርት ከኢየሱስ ይልቅ ለመምህራኖቻቸው ሲሟገቱ በዚህ ይታወቃሉ። ስለዚህም ጌታ ኢየሱስ እንደሚል ዕውር፣ ዕውራንን እንደሚመራ ያለ አስፈሪ ፍጻሜ ያገኛቸዋል፤ (ማቴ. 15፥14፤ ሉቃ. 6፥39)።
   በኦሮሚኛ እንሽላሊት “Lootu” ተብሎ ይጠራል፤ ትርጉሙም “ሾላካ” ማለት ነው፤ እንደምናውቀው እንሽላሊት የማይሾልክበት ቀዳዳ የለም፤ ጠቢቡ ሰለሞን “በእጅ የሚያዘው ደካማ መሳዩ እንሽላሊት፣ በነገሥታት ግቢ እንደሚኖር” (ምሳ. 30፥28) ይነግረናል፤ በሾላካነቱ በብዙ በሚጠበቀው በነገሥታት ግቢና የትም መገኘት ይላል፤ አዎን! ሾላኮቹ በመካከላችን ተቀምጠው ደቀ መዛሙርትን ከኋላቸው እንደሚስቡ ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም፤ (ሐዋ. 20፥28)።
ለምን ግን ሾልከው ይገባሉ?
1.      ማበላሸት፦ ጠቢቡ ሰሎሞን ሾልከው ወደ ወይኑ ቦታ የሚገቡ፣ የተተከለ ፍራፍሬ ወይም የወይኑን ቦታ እንዳያጠፉት ቀበሮዎችን፣ ጥቃቅኑን ቀበሮዎች አጥምዳችሁ ያዙልን ይላል፤ (መኃ. 2፥15)። ቀበሮ በጠባዩ ለምለሙን ስፍራ ያደርቃል፤ ወናም ያደርጋል፤ መኖሪያውም በፍርስራሽ ውስጥ በባድማ ምድረ በዳ ነው (ኢሳ. 35፥7፤ ሕዝ. 13፥4፤ ሚል. 1፥3)፣ ምግቡ ጥንብ እንደ መኾኑ መጠን መልካሙን የወይን ስፍራ በማበላሸት ይታወቃል። በመጽሐፍ ቅዱስ ቀበሮ የተንኮለኛና የደካማ ሰው ጠባይ ኾኖ ተጠቅሶአል፤ (ሉቃ. 13፥32፤ ነህ. 4፥3)።[2]
    እንግዲህ ሐራጥቃውያኑ ሾላኮች፣ እንደ ቀበሮ መልካም የወንጌል ቃልና የኢየሱስ ሕይወት ስለማይጥማቸው፣ በተንኮላቸው የራሳቸውን ነገር አሾልከው ማስገባት ይፈልጋሉ። ጥንብን ለመብላት ምንም ማደንና መድከም እንደማያስፈልገው እንዲሁ የቀበሮ ጠባይ ያላቸው ሐራጥቃውያን የኾኑ መናፍቃንም፣ ጌታ ኢየሱስ እንዳስተማረን ሰፊው መንገድ እንጂ ጠባቡ መንገድ ፈጽሞ አይመቻቸውም። ጠባቡ መንገድ ኢየሱስን ብቻ መስማትና መታዘዝ ይፈልጋል (ማቴ. 7፥13-14)፤ እንዲህ መኖር የሚፈልጉ ደግሞ እጅግ በጣም ጥቂቶች፣ ለኢየሱስ ብቻ የጨከኑ፣ በሰፊው ተመላላሽ የኾኑ ብዙኀንን የተውና ለዓለም ሙሉ ለሙሉ ጀርባቸውን የሰጡ ብቻ ናቸው።
  ሾላኮቹ ግን አበላሽ ናቸውና ጠባቡን የመስቀልና ኢየሱስን ብቻ የመስማት መንገድ መከተልን አይወዱም፤ እኛ ግን ከመበላሸት ተርፈን፣ ከመጥፋት ድነን፣ ከሾላኮቹ አምልጠን ሕይወትን መውረስ የምንፈልግ ከኾንን ኢየሱስን በትክክል ልንሰማው፣ የሾላኮቹን ተንኮለኝነትና አበላሽነት በማወቅ ከእነርሱ ልንጠበቅ ይገባናል። ሾላኮቹ ሰዎችን በሰፊው መንገድ ያጓጉዛሉ፣ ተጓዦቹም መንገዱ ቀሎአቸው ይጓዙበታል፤ “በክርሰቶስ ነጻ ወጥታችኋል” በሚል ሰበብ፣ ከመብላት፣ ከመጠጣት፣ ከመዝናናት፣ ከመልበስ፣ ከዳንኪራ፣ ከመዝፈን፣ ከሃብት ማግኘት፣ ከክብርና ከዝና፣ ከመደላደል፣ ከመቀማጠል፣ ከ“ታገኛለህ”፣ ከ“ያልፍልሃል”፣ ከ“ትጥሳለህ”፣ ከ“ትጠረምሳለህ” … በዘለለ በትምህርታቸው ውስጥ ማስጠንቀቂያ፣ ንስሐና የኃጢአት ኑዛዜ የለም፤ ኢየሱስን መፍራትና በኹለንተና ለእርሱ መገዛት የሚሉ ትምህርቶች የሉም።
   ከሚያበላሿችሁ ሾላኮች ተጠበቁ፤ የኢየሱስ ሕይወትና ትምህርት ከማይጥማቸው ቃርሚያ በመልቀም ዘመናቸውን በብልና በዝገት ከሚያበላሹ ሐራጥቃ መናፍቃን ራቁ፤ ዐላማቸው እናንተን ማበላሸት እንጂ እናንተን መርዳት፣ ኢየሱስን አብዝታችሁ እንድትወዱ መምከር፣ ቃሉን በመናፈቅ እንድታነቡና ተግታችሁ እንድትጸልዩ አይደለምና መንገዳቸው ሰፊ ከኾኑት ሽሹ፤ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ዘወትር ወደምትጓዙበት ጠባቡ የጽድቅ መንገድ ተመለሱና በጽናት ተመላለሱ፤ የእግዚአብሔር ጸጋና የኢየሱስ ጽድቅ፣ የመንፈስ ቅዱስም ብርሃን ወደ ሕይወትና መዳን ይምራችሁ፤ ያጽናችሁ፤ አሜን።
ይቀጥላል …



[1] ሐራጥቃ ማለት፣ “መናፍቅ ጠዋየ ሃይማኖት ባህሉና ትርጓሜው ከመጽሐፍ ከንባብ የማይገጥም፤ መጻሕፍት እወ ያሉትን አልቦ፣ አልቦ ያሉትን እወ የሚል፤ የርሱን ሃሳብ ብቻ የሚከተል፤ የጨዋ የወታደር ዐይነት፤ ነገሩ ከጨዋ የሚስማማ ከሊቃውንት የማይስማማ፤ እንደ አርዮስ እንደ ንስጥሮስ … ” ብለው ይተረጉሙታል ታዋቂው ሊቅ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ (ገጽ ፬፻፷፪)
[2] የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ገጽ 90

No comments:

Post a Comment