Sunday 3 March 2019

“እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነውን?” (ኢሳ. 58፥3)

    እስራኤል በግልጥ ነውር ተይዛለች፤ በነውር የተያዘችው እስራኤል በሠራችው ኀጢአት ንስሐ መግባትና ራስዋን በጾም ክዳ ወደ አምላኳ ያህዌ ኤሎሂም መምጣት ሲገባት፣ እርሷ ግን ሃሰተኛ አምልኮ በማቅረብ፣ አምላኳን በሃሰተኛ አምልኮ ለመደለል፤ ለማታለል ፈለገች። በሰው አተያይ አምላክ የሚያይ መስሏት ኢየሩሳሌም ተታለለች፤ በታይታዊ የግብዝነት ሕይወት ትጾማለች ግን ጾሟ በእግዚአብሔር ፊት የተወደደ አልነበረም፤ ሰውነቷን ታዋርዳለች ግን ውርደቷን በክብር የሚለውጥላት አንዳች የለም፤ ምክንያቱም ፈቃድዋን እንጂ የያህዌን ፈቃድ አትፈጽምምና።


“ስለ ምን ጾምን፥ አንተም አልተመለከትኸንም? ሰውነታችንንስ ስለ ምን አዋረድን፥ አንተም አላወቅህም? ይላሉ። እነሆ፥ በጾማችሁ ቀን ፈቃዳችሁን ታደርጋላችሁ፥ ሠራተኞቻችሁንም ሁሉ ታስጨንቃላችሁ። እነሆ፥ ለጥልና ለክርክር ትጾማላችሁ በግፍ ጡጫም ትማታላችሁ፤ ድምፃችሁንም ወደ ላይ ታሰሙ ዘንድ ዛሬ እንደምትጾሙት አትጾሙም።” (ቁ. 3-4)

  ነቢዩ የእስራኤልን ኀጢአት በመመልከት በትክክል ንስሐ እንድትገባ ቢናገራትም፣ በእውነተኛ ንስሐ ከመመለስና በእስራኤል ቅዱስ ፊት ራስዋን ከማዋረድ ይልቅ ሰዋዊ ብልሃትን መጠቀምን መረጠች፤ ይህን እጅግ ወራዳ መንገድን እየመረጠች፣ በዚሁ መንገድ ደግሞ እግዚአብሔር አምላክ እንዲሰማት ትወድድ፤ ትፈልግም ነበር፤ እግዚአብሔርን የሃሳቧ አስፈጻሚ ሎሌ ለማድረግ፣ ልክ እንደ እርሷ እንዲያስብና ከንቱ ምልልሷን እንዲቀበልላት ፈለገች። እግዚአብሔር አምላክ ማስመሰልና ሃሰተኛ አምልኮን ፈጽሞ እንደሚጠየፍ ፈጽማ አላስተዋለችም።

 እግዚአብሔርን የእግዚአብሔር የኾነውን ነገር በግድየለሽነትና በንዝህላልነት በመፈጸም ልናስደስተው ወይም ልናሸንፈው አንችልም። የእግዚአብሔር የኾነውን ነገር በምን ዐይነት የልባችን ዝንባሌ እንደምንፈጽመው እግዚአብሔር ይመዝነዋል፤ በእግዚአብሔር ዘንድ ከሚሠራው የሥራ ትልቅነት ይልቅ፣ የሚፈጸምበት ልብ ትልቁን ሥፍራ ይይዛል። “ትንንሽ” ትሁት ልቦች ትልልቅ ሥራዎችን ይሠራሉ፤ ትልልቅ እብሪተኛ ልቦች ግን ታናሺቱን ሥራ የመሥራት አቅም እንኳ አይኖራትም።

  ከመጾም በፊት ቅበላችን ንስሐ ካልኾነ፣ መጾማችን ከንቱና ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጪ ነው፤ በአገራችን የጾም ቅበላው ሥጋ መብላት፣ ዋዜማው መጠጥና ዳንኪራ ነው፤ ሥጋ ላለመብላት እንጾማለን፤ ሥጋ ለመብላት እንፈስካለን! ጌታ እግዚአብሔር ግን እንዲህ ይለናል፤ “እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ ነውን? ሰውስ ነፍሱን የሚያዋርደው እንደዚህ ባለ ቀን ነውን?”፤ አዎን! ጾም የሚጾመው ሥጋ ቤትና መጠጥ ቤት ከማጣበብ በመጀመር አይደለም። እግዚአብሔር እንዲህ ያለውን ጾም፤ ጾም አላለውም፤ አልመረጠውምም።

  ትላንት ማለዳ ላይ ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ፣ ሥጋ የሚሸጥበት የሸማቾች ሱቅ በር ላይ በኹለት ረድፍ የተሰለፈ ረጅም ሰልፍ አየሁ፤ ምንድር ነው? ብዬ ወደ ሰልፉ መጀመርያ ዐይኔን ሳቀና፣ የተኮለኮለው ሰልፍ የከብት ሥጋ ገዥ ማኅበረሰብ ነው፤ ምክንያቱም “የጾም ቅበላው ሥጋ ነውና!”፤ ሃምሳ አምስት ቀን ለመጾም አንዱን ሌሊት በሥጋ መብል እናስጨንቀዋለን፤ “ሲፈሰክ” ደግሞ በሌላ የኀጢአት ጭቃ ለመንደባለል በቀጠሮ እንከርማለን፤ በእውኑ፣ ጌታ የመረጠው ጾም ይህ ነውን?፤ በፍጹም አይደለም፤ አይኾንምም።

  ፈቃዳችንን እየፈጸምን እንድንጾም አልተባለልንም፤ ለእግዚአብሔር ሳንሸነፍ፣ ለፍቅሩ ሳንገዛ፣ ለማዳኑ ሳንንበረከክ፣ ለሞተልን ኢየሱስ ሳንዋረድ፣ ለቤዛችን ክርስቶስ እጅ ዘርግተን ሳንማረክ፣ እግዚአብሔር አብ በልጁ ምን እንዳረገልንና እንደ ሰጠን፣ ከመንፈሱ ደግሞ ሳይከፍል ጸጋውን እንዴት እንዳፈሰሰልን በትክክል ሳንረዳ ብንጾም፣ ብንጸልይ፣ ለድሃ ብንለግስ፣ ብዙ እጅግ ብዙ፣ ሺህ ጊዜ ሺህ ብንሰግድ፣ ለድሆች ሳንራራ፣ ለድሃ አደጎች ሳንፈርድ፣ የተጨቆኑትን ነጻ ሳናወጣ፣ የታረዙትን ሳናለብስ፣ ከዘረኝነታችን ሳንፈታ፣ ከብሔርተኝነታችን ሳንላቀቅ፣ ከዘፋኝነታችን እንደ ተጣባን፣ ከሴሰኝትና ከዝሙታችን በንስሐ ላንመለስበት መንገዳችንን ሳናስተካክል … ከፋሲካ በኋላ ቀጠሮ ይዘን የምንጾመው ጾም፣ በእግዚአብሔር ለመዘበት እንጂ እርሱ የወደደው ጾም አይደለም።

  እርሱ የወደደው ጾም ግን እንዲህ ያለውን ነው፣ “እኔስ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፥ የቀንበርንስ ጠፍር ትለቅቁ ዘንድ፥ የተገፉትንስ አርነት ትሰድዱ ዘንድ፥ ቀንበሩንስ ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን? ንጀራህንስ ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘምድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን? … ” በእውኑ እኛ ይህን ሳናደርግ ከጭልፋና ከገበታ ትሪ ብንጾም በእውኑ ጾመናልን? በፍጾም አልጾምንም!!!

  እግዚአብሔር አብ በልጁ ያደረገልንን በትክክል በማሰብ፣ መስቀሉን፣ ሞቱን፣ ሕማሙን፣ ችንካሩን፣ ትንሣኤውን፣ ዕርገቱን፣ ዳግመኛ መምጣቱን … በማሰብና በማመን በሕይወታችንና በሌሎችም ሕይወት ጸጋውን እንዲያበዛ፣ ከኀጢአት እንዲለየንና በኀጢአት ላይ ድልን በጸጋው እንዲያቀዳጀን … አምነን ሳንቀርብ እንዲያው ብንጾም ከንቱ የረሃብ አድማ ነው፤ ጾም፣ መታዘዛችንን፣ ፍጹም መሰጠታችንን፣ ራሳችንን ለእርሱ ብቻ ማስገዛታችንን የምንመሰክርበት አምልኮ ነው!!!

 ለመጽደቅ አንጾምም፣ በረከት ለመቀበል አንጾምም፣ ሥጋን ለማድከም አንጾምም፣ ጽድቃችን ክርስቶስ፣ በረከታችን ኢየሱስ፣ ሥጋን የምንገድልበትና የምንሰቅልበት፣ ከክርስቶስ ጋር በጽድቅ ሕይወት ለመኖር የምንነሣበት ኃይላችን መንፈስ ቅዱስ ነው፤ መሰጠታችንን፣ መገዛታችንን፣ ለእግዚአብሔር ብቻ መታዘዛችንን፣ ተዘርረን፣ ተሸንፈን፣ ተዋርደን … እርሱን ብቻ ማምለካችንን ለማሳየት እና የቸገረንንና በፍቅር ከእጁ የምንቀበለውን አንዳች ነገር ለማሳሰብ ለአምልኮ በፊቱ የምንቆምበት አንዱ መንገድ ነው፤ ጾም!!!

ተወዳጆች ሆይ! በዚህ የጾም ወራት ከወንድሞቼና እህቶቼ ጋር እንዲህ አስበናል፤ እግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናትን በወንጌል እንዲያንጽ፣ ፊታቸውን ወደ ተሰቀለው ኢየሱስ ወንጌል ዘወር እንዲያደርጉ፣ እኛም ደግሞ ለቅዱሱ ወንጌል ምስክርነት እንድንነቃቃ እና ስለአገራችን ኢትዮጵያ እንድንማልድ በጾምና ጸሎታችን አስበናል፤ እንኪያስ ወንድሞች ሆይ! ይህ እጅግ መልካም አይደለምን? እግዚአብሔርስ የመረጠው ጾም እንዲህ ያለውን አይደለምን? ጾም አምልኮ ነው፤ በአምልኮ መንፈስ ጹሙ እንጂ በልማድስ አይሁን፤ መንፈስ ቅዱስ በጸጋው ይደግፈን፤ አሜን፤ ጸጋ ይብዛላችሁ!!! አሜን።

No comments:

Post a Comment