Friday 8 March 2019

ሰባት ዓመታት በጡመራ መድረክ (በብሎግ) አገልግሎት

   ኹሉም ነገሮቻችን በእኛ አቅም የተያዙ አይደሉም፣ መያዝም አይችሉም፤ በጌታ እግዚአብሔር ኹሉን ቻይነትና አለኝታነት ተደግፈው ያሉ እንጂ። የሕይወት እስትንፋሳችን እንኳ ተቀጥላ ያለችው፣ በእስትንፋስና በሕይወት ባለቤት በእግዚአብሔር መግቦት ብቻ ነው። ምሕረቱ ባይበዛልን፣ ቸርነቱ ባይገንልን፣ ፍቅሩ ባይትረፈረፍልን፣ ተግሳጹ ነፍሳችንን ባይመልሳት፣ ምክሩ ድካማችንን ባያበረታው፣ ማጽናናቱ ልባችንን ባይደግፈው … ገና ያኔ ገና በተዋጥን፣ የአዳኙ ወጥመድ ይዞን በጠፋን ነበር።


   ነገር ግን በመሐሪው ጉልበትና በደጉ አባት ችሎታ እስከ ዛሬ ድረስ አለን፤ መዝሙረኛው ዳዊት በመዓረግ መዝሙሩ እንደ ዘመረው፦
 “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን እስራኤል እንዲህ ይበል፦ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን ሰዎች በእኛ ላይ በተነሡ ጊዜ፥ ቍጣቸውን በላያችን በነደደ ጊዜ፥ በዚያን ጊዜ ሕያዋን ሳለን በዋጡን ነበር፤ በዚያን ጊዜ ውኃ ባሰጠመን ነበር፥ በነፍሳችንም ላይ ፈሳሽ ባለፈ ነበር፤ በዚያን ጊዜ የጐርፍ ውኃ በነፍሳችን ላይ ባለፈ ነበር። ለጥርሳቸው ንክሻ ያላደረገን እግዚአብሔር ይባረክ። ነፍሳችን እንደ ወፍ ከአዳኞች ወጥመድ አመለጠች፤ ወጥመድ ተሰበረ እኛም አመለጥን። ረድኤታችን ሰማይንና ምድርን በሠራ በእግዚአብሔር ስም ነው።” (መዝ. 124)
  በባለፉት ዘመኖቻችን ጠላታችን እያየን ቊጣው ያላነደደን፣ መቅሰፍቱ ያላገኘን፣ ውኃውና ሞገዱ ያልዋጠን፣ በነፍሳችን ላይ ብዙ ጎርፍና ስለት ቢያልፍም ያላሰጠመንና ያልሸረከተን፣ ወጥመድ ቢዘረጋም ያላጠመደንና ያልያዘን፣ ከሳሽ በስውር ሴራው ካጠመደው ወጥመድ እንደ ወፍ በርረን ያመለጥነው፣ የሐሰት መምህራን ትምህርት ፈጽሞ ያላገኘንና አሽክላቸው ጠላልፎ ያልጣለን፣ ለገዛ መልካምነታችን እንኳ ተላልፈን ያልተሰጠነው የደጉ መሐሪ ምሕረት ከልክ በላይ እንደ ጠል አረስርሶን፣ እንደ ውሽንፍር ቸርነትና መግቦቱን አጥግቦን ነው።
  አዎን! ላለፉት ሰባት የአገልግሎት ዓመታት ረድኤቴና መደገፊያዬ ሰማይንና ምድርን የሠራ የእግዚአብሔር ስም ነበረ፣ ወደ ፊትም ከእርሱ በቀር ሌላ ላላውቅ በእርሱ ጉልበት ኪዳን ገባለሁ፤ የጡመራው መድረክ ሥራም በእርሱ ጉልበት ብቻ የተሠራ ነው፤ ክብሩን፣ ሙገሳውን፣ ውደሳውን፣ ቅደሳውን፣ ቡረካውን፣ እልልታውን፣ ምስጋናውን፣ ጭብጨባውን፣ አድናቆቱን፣ መገረሙንኹሉ መውሰድ ያለበት አንድዬ ብቻ ነው፤ ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ!!!
  ያለፉት ሰባት ዓመታት የብሎግ አገልግሎት ዓመታትን ክብር ብቻውን መውሰድ ያለበት እርሱ ብቻ ነው፤ በእነዚህ ዓመታት በእኔ ኹኔታ ሊገለገል የወደደ የእስራኤል ቅዱስ ይባረክ፣ ሳይንቀኝ፣ ሳይታዘበኝ፣ ሳይታክተኝ፣ ድካሜን ኹሉ እያለፈ፣ ፊቴን በንስሐ ወደ እርሱ በመለስሁ ጊዜ በኃጢአቴ ላይ ምሕረት እያበዛ፣ ርኅራኄ እያዘነበጸጋውን በእኔ ያፈሰሰ፣ በእኔ ሊገለገል ያላፈረ፣ በእርሻው መከር ላይ እንደ ታማኝ ሠራተኛ ቈጥሮ ያሠማራኝ ጌታና አባት እግዚአብሔር፣ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ መንፈስ ቅዱስ ስሙ ይባረክ። አሜን።
  በእነዚህ ዓመታት ታናሽነቴን ሳትንቁ በጸሎት፣ ጽሑፎችን ቡስት በማድረግ፣ መጽሐፎችን ገዝቶ በመርዳት፣ በምክርና በሃሳብ፣ በተግሳጽና በቊጣ፣ በዝልፈትና በስድብ፣ በቀና ትችትና በጥላቻ ውረፋኹሉ አብራችሁኝ ለነበራችሁ፣ ላነቃችሁኝ፣ ላበረታታችሁኝ፣ ርእስላቀበላችሁኝ  ከሐሜት ይልቅ ፊት ለፊት ለወቀሳችሁኝና ለገሰጻችሁኝየጌታ ጸጋና ምሕረት እንዲበዛላችሁ በጸሎት እጅግ እቃትታለሁ።
 ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ! ቀሪ ዘመናችንን ለክብሩ ይጠቅልለው፤ ጌታ ሆይ! እዚህ ስላደረስከኝ ዘመኔን ሙሉ እባርክሃለሁ፤ አከብርሃለሁ፣ አመልክሃለሁ፣ እፈራሃለሁ፣ ተንበርክኬ እሰግድልሃለሁ፤ አሜን።

No comments:

Post a Comment