Tuesday 19 March 2019

ምኩራብ

  Please read in PDF
  አይሁድ ወደ ባቢሎን በምርኰ በወረዱ ጊዜ የቀደመው ኪዳን “የአምልኮ ማዕከል” ከኾነው ከመቅደሱ ተለያዩ፤ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነጾር በሦስተኛው ዙር የምርኰ ማጋዝ በአካል ወደ ኢየሩሳሌም በመምጣት ኢየሩሳሌም ገለበጣት፤ መቅደሷንም አፈረሰ፤ ከመቅደሱ ንዋየ ቅዱሳቱንም ዘረፈ፤ እስራኤልን ሙሉ ለሙሉ ባድማ አደረጋት።
   እናም የኪዳኑ ሕዝብ እስራኤል በምርኰ ሳሉ አምልኮ “ናፈቁ”፤ ከኢየሩሳሌም በቀር በሌላ ስፍራ [በባቢሎን ጭምር] መቅደስ መሥራት ባይቻላቸው፣ በዚያው በምርኰ ባሉበት ምድር ኾነው የሚሰባበሰቡበትንና በዋናነትም ቅዱሳት መጻሕፍትን የሚያነቡበትን፣ በንባብም የሚያመልኩበት ምኩራብ፣ በቁጥር አነስ ያሉ ሰዎችን ሊይዝ በሚችል መልኩ በሕዝቡ መካከል ሠሩ፤ እናም በምርኰ ምድር ኾነው በንባብ እግዚአብሔርን ለማምለክ፣ ሊታዘዙትም ምኩራብን ለሕዝቡ አቅራቢያ በኾነበት ስፍራ ተግተው ሠሩ።

  በኹሉም ምኩራቦች ውስጥ ብዙ ቅዱሳት መጻሕፍት በጥቅልል መልክ ተዘጋጅተው እንዲቀመጡ ተደረገ፤ በየሰንበቱም ቃሉን ማንበብም ኾነ መስማት፣ መተርጐምም በምኩራብ የሚደረግ ዋነኛ አምልኮ ሆነ። እውነት ነው! ቃሉን ማንበብና መስማት፣ እንደ ተነገረውም መታዘዝ ዋነኛ የአምልኮና የመንፈሳዊ ሕይወት መገለጫዎች ናቸው፤ ቅዱስ ቃሉን አጥርቶ የማይሰማ በትክክል አያምንም፤ እምነት ከመስማት ነውና፤ “እንግዲያስ እምነት ከመስማት ነው መስማትም በእግዚአብሔር ቃል ነው” (ሮሜ 10፥17) እንዲል፣ በትክክል ለመስማት ደግሞ በትክክል የሚያነብና በትክክል የሚተረጉም አማኝና መምህር ሊኖር ያስፈልጋል።
  ዛሬ በአብያተ ክርስቲያት ያለው ትልቁ ችግር ይህ ነው፤ ቃሉን በትክክል ማንበብና መስማት እንደ አምልኮ ካለመቈጠሩም ባሻገር፣ በጠማማ ንባብና ትርጉም ትውልድ ሲመረዝ፣ ሲስት ከልካይ ጠፍቶ የእብድ ገላጋይ በዝቷል። በትክክል የማያነብ በትክክል አይተረጎምም፤ በትክክል ከማይተረጉም ሰባኪ ደግሞ ትክክለኛ የኾነ አምልኮና ልምምድ ያለውና ጤናማ የኾነ ክርስቲያን አማኝ ማግኘት ፈጽሞ ሊታሰብ የማይችል ነው።
   ምኩራብ የቅዱሳት መጻሕፍት ንባብና መስማት “የዳበረበት” ሥፍራ ነው። ንባብና መስማት፣ በቅዱሱ መጽሐፍ በውስጡ የተጻፈውን ማድረግም አምልኮና የብጽዕና ሽልማት የሚያስገኝ መኾኑን፣ “ዘመኑ ቀርቦአልና የሚያነበው፥ የትንቢቱን ቃል የሚሰሙትና በውስጡ የተጻፈውን የሚጠብቁት ብፁዓን ናቸው” (ራእ. 1፥3) በማለት ይገልጠዋል፤ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ፣ መስማትና በውስጣቸውም የተጻፈውን ማድረግ እንደ ቅዳሴ፣ እንደ ውዳሴ፣ እንደ ዝማሬ … ልዩና ድንቅ አምልኮ ነው! ጌታችን ኢየሱስም በምኩራብ በተገኘም ጊዜ ያደረገው እንዲሁ ነው፤ (ሉቃ. 4፥16-19)
   የአምልኮ ችግርና የመንፈሳዊ ሕይወት ዝለትን ለማከምና ለማበረታታት ምኩራብ በሕዝቡ መካከል ወርዳ ተተከለች። መንፈሳዊ ሥራ ተንቀሳቅሰው ሲሠሩት እንጂ ተቀምጠው ሲጠብቁት አያረካም። የተጠራነነው ችግር ወዳለበትና በጭንቀት ውስጥ ወዳለ ማኅበረ ሰብ በመሄድ፤ የቅዱስ ቃሉን ፍቺ በማብራት፣ በማንበብና በማሰማት መፍትሔ እንድንሰጥ ነው። በእጃችን የማይለወጥ ወንጌል ኾኖ (ማር. 16፥8) የሰዎችን ሕይወት የሚለውጠውን ወንጌል ይዘን ለሰዎች ግን ከዚህ ያነሰ መፍትሔ ማቅረባችን የቤተ ክርስቲያንን፣ የአገርን፣ የማኅበረ ሰብን … ችግር ከድጥ ወደ ማጥ አፍልሰነዋል
   የክርስትና አገልግሎት የምኩራብ አገልግሎትን ይመስላል፤ ችግር ወዳለበት የሚሄድ ተንቀሳቃሽ አገልግሎት ነው። ይህ ብቻ አይደለም፤ አንድ ምኩራብ በውስጡ የሚይዘው እስከ አስር አባወራ ብቻ ነው፤ ይህም ጥቂት ሰዎችን ግን እጅግ የተሳሰሩ፣ በግል የሚዋወቁ፣ ነፍሶቻቸው የተሳሰረች ሰዎችን የሚይዝ እንዲኾን ታስቦ የተሠራ ነው ችግር ወዳለበት የማይሄድ ክርስትና ልምሾና ጉንድሽ ነው፤ እውነተኛ ክርስትና “እንግዲህ ሂዱ” (ማቴ. 28፥20) የሚለውን መሲሐዊ ትእዛዝ አክባሪና ከሕንጻና ከግንብ ወጥቶ ወደ ማኅበረ ሰቡ የሚፈስና የታዘዘውን የሚተገብር ነው!
  ምኩራብ ቃሉ ብቻ ይነበብበት፤ ይሰማበት እንደ ነበር እንዲሁ፣ ዛሬም የሰው ትምህርት ገለል ብሎ ቃሉ ብቻ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ይነበብ፤ ይሰማ፣ አማኙ ማኅበረ ሰብ እንዲታዘዘው እግዚአብሔር በልጁ ጸጋ እንዲያበዛ መንፈስ ቅዱስን መማለድ ይገባል፤ በዚህም እግዚአብሔር እጅግ ይመለካል፤ እንዲሁ ደግሞ ምኩራብ በሕዝቡ መካከል በቅርበት እንደ ነበርም ቤተ ክርስቲያን ለሕዝቡ በቅርብ ያለች “ከመንፈስ ቅዱስ የተላከች መንፈሳዊት ሐኪም ቤት” ልትኾን ይገባታል፤ ጸጋ ይብዛላችሁ፤ አሜን።



1 comment:

  1. ቤተ ክርስቲያን ለሕዝቡ በቅርብ ያለች “ከመንፈስ ቅዱስ የተላከች መንፈሳዊት ሐኪም ቤት” ልትኾን ይገባታል፤ amen des yemil melkt.

    ReplyDelete