Tuesday 5 March 2019

ከሰማይ በመውረዱ ራሱን ባዶ ያደረገ ኢየሱስ[ዘወረደ]

Please read in PDF
  ጌታ ኢየሱስ የሰውን ሥጋ በመልበሱ፣ ከሰማየ ሰማያት ገሊላዊት ወደ ኾነችው የናዝሬት መንደር በመውረዱ፣ ከአንዲት በናዝሬት አገር ከምትኖር ድኃ ድንግል ሴት በመወለዱ፣ ኃጢአት በሚገዛው ዓለም በመመላለሱ … እጅግ ተዋርዷል። ይህን በማድረጉም በገዛ ፈቃዱ ራሱን ከራሱ ባዶ በማድረግ ለአባቱ ፈቃድ ፍጹም ታዟል።
 ጌታ ኢየሱስ ከሰማይ ወደ ምድር ወረደ ስንል፣ በአምላካዊ ማንነቱ ወይም በመንፈሱ ወዳልነበረበት ዓለም መጣ እያልን አይደለም፤ እርሱ ኹሉን የሚያውቅ (ዮሐ. 2፥24-25)፣ ኹሉን የፈጠረና የደገፈ ደግሞም፣ “ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል”፤ (ዮሐ. 1፥3፤ ቈላ. 1፥16፤ ዕብ. 1፥2-3) እንዲል፣ ኹሉ በኹሉ የኾነ፣ ጌታና የፍጥረት ኹሉ ባለቤት ነው። ምድርና መላዋ የእርሱና እርሱም ያለባት ናት፤ (መዝ. 24፥1)።
  ነገር ግን ይህ ጌታ ሰማይና ምድርን ይገዛ የነበረበትን ሥልጣኑን፣ መብቱን፣ ጥቅሙን፣ ተወ፤ ራሱን ባዶ አደረገ፤ ከሰማይ ወደ ምድር በመውረዱ ፍጹም ተዋረደ። የተዋረደው በመስቀል ላይ ዕርቃኑን ሲሰቀል ብቻ አይደለም፤ በኃጢአት የተዋረደውን የአምላኩን ቃል ባለመታዘዝ ያመጸውን የሰው ልጅ፣ እንከን አልባ በኾነ መንገድ ሥጋውን በመልበሱና ሰው በመኾኑ ነው።
  እግዚአብሔር ሰውን በመልኩ በመፍጠሩ እጅግ አክብሮታል፤ አልቆታልም፤ “እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤”፣ “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፥ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች” (ዘፍጥ. 1፥26፤ መዝ. 139፥14) እንዲል። ነገር ግን ሰው ለያህዌ ኤሎሂም ባለመታዘዙ ከእግዚአብሔር መልክና አምሳል[ክብር] ወደ ውርደት[ሰውነት ብቻ] ወረደ፤ “አዳምም ሁለት መቶ ሠላሳ ዓመት ኖረ፥ ልጅንም በምሳሌው እንደ መልኩ ወለደ” (ዘፍ. 5፥3) እንዲል ተንኮታኮተ፣ በኀጢአቱ የውርደትን ማቅ ታጠቀ፣ አይወርዱ መውረድ ከክብር ስፍራው ከገነት ወረደ፤ አዳም በምድር የሚያነሣው እስከማይገኝለት ወረደ፣ ተዋረደ።
  በኃጢአቱ የተዋረደውን አዳም በጽድቁና በቅድስናው ሊያነሣ ክርስቶስ ወደ እኛ ወረደ። የኃጢአትን መንገድ በመምረጥ አምላኩን አሳዝኖ ለወረደውና ለተዋረደው አዳም ኢየሱስ አባቱን ደስ በማሰኘት ለአዳምና ለዘሩ እውነተኛና ብቸኛ ቤዛ ይኾን ዘንድ በፈቃዱ አምላካዊ ክብሩንና መብቱን በመተው ተዋርዶ ያከብረው ዘንድ በፈቃዱ ወደደ።
  በፈቃዱ ራሱን ባዶ አድርጓልና ልጆቹ በኃጢአት ምክንያት ሊከፍሉ ያላቸውን ማናቸውንም ውርደትና ስቅየት ሊቀበል ዝግጁ ነበር፤እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ” (ፊል. 2፥6-8) እንዲል፣ በኃጢአት የሚያገኘንን የትኛውንም ውርደት ኢየሱስ በሥጋው ሕመምና ሞት ፍጹም ተቀብሏል።
  ይህንም የተቀበለው የባርያን መልክ በመያዝ ወይም በትክክል እንደ ባርያ በመታዘዝ፣ እጅግ ዝቅ ዝቅ በማለትና ምንም እንደሌለው ራሱን በመቊጠር ለአባቱ ፈቃድ ፍጹም በመታዘዝ ባዶ ኾነ። በመካከላችን ሲመላለስ እንዲህ ተመላለሰ። ታላቁ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ በትሁትና በተዋረደ መንፈስ በመካከላችን ተመላለሰ፤ ባዶ አድርጎ በመካከላችን ውሎ አደረ፤ ድንኳኑንም በጸጋና በእውነት ደኮነ።
  እናም ወረደ ስንል ተዋረደ፣ ተዋረደ ስንል ደግሞ ለእኛ ፍጹም ክብርን አመጣ፣ አከበረን፣ በብቃቱና በአዳኝነቱ አበቃን፣ አዳነን ማለታችን፤ እንዲህም ማመናችን መታመናችንም ነው። ራስህን ከራስህ እንኳ ባዶ ያደረግህልን ኢየሱስ ሆይ! እጅግ አድርገን በብዙ እንወድሃለን፤ እናከብርሃለን፤ እናመልክሃለን፤ ምክንያቱም አንተ ብቻ ነህና፣
“በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤ ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፥ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው” (ፊል. 2፥9-11)።


ጌታችን ኢየሱስ ሆይ! ይገባሃል፤ አሜን።

No comments:

Post a Comment