Monday 11 February 2019

ቤተ ክርስቲያን ተጐታችና ዘመነኛ ችግሮቿን አስተውላ ይኾንን!? (የመጨረሻ ክፍል)


1.10.    የዘፋኞችንና የአለማውያንን ዝናና ዕውቅና “መቀላወጥ”
      ቤተ ክርስቲያን ከአስተማሪዋ መንፈስ ቅዱስ የተማረችው አንድ ትልቅ እውነት “ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞትን በመካድ … ራስዋን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን መኖርን” ነው (ቲቶ 2፥12-14)።  “እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ እንጂ፥ በእኛ መልካም ሥነ ምግባር አለመዳናችንንም አውቀን” (ቲቶ 3፥5) መዳናችንን በመልካም ሥራ መገለጽ እንዳለበት ጸጋን አደላዳዩ መንፈስ ቅዱስ ያስተምረናል። ምክንያቱም ትክክለኛ የኾነ ሥነ ምግባር ምንጩ ትክክለኛ ትምህርት ነውና።

     ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር መንግሥት መገለጫና የመንግሥቱ ሥራ ብቻ የሚታወጅባት ዐውድ ከኾነች በውስጧ ሊያገለግሉ የሚገባቸውም አገልጋዮች እንደ ቤተ ክርስቲያን ራስ፥ ክርስቶስ ኢየሱስ “በመንፈስ ድሆች የሆኑ (ማቴ. 5፥3፤ ፊልጵ. 2፥8)፣ የሚያዝኑ (ማቴ. 5፥4፤ 9፥37)፣ የዋሆች (ማቴ. 5፥5፤ 11፥29)፣ ጽድቅን የሚራቡ (ማቴ. 5፥6፤ 21፥18፤ ዮሐ. 19፥29)፣ የሚምሩ (ማቴ. 6፥7፤ ሉቃ. 6፥36፤ ኤፌ. 2፥4 )፣ ልበ ንጹሕ (ማቴ. 5፥8፤ 23፥4፤ ዕብ. 7፥26)፣ የሚያስተራርቁ (ማቴ. 5፥9፤ 2ቆሮ. 5፥18)፣ ስለጽድቅ የሚሰደዱ (ማቴ. 5፥10 ፤ ሮሜ 8፥35-36)፣ በስሙ የሚነቀፉና የሚሰደዱ ክፉው ሁሉ በውሸት የሚነገርባቸው (ማቴ. 5፥11፤ ዕብ. 13፥12፤ 1ጴጥ. 2፥23) ሊሆኑ ይገባቸዋል እንጂ ስለዘፈናቸውና በአደባባይ የበደሉትን ሕዝብ ገና ይቅርታ ያልጠየቁና ንስሐ ያልገቡ ሊሆኑ አይገባቸውም።
   እግዚአብሔር እርሱን የሚያገለግሉትን አገልጋዮች ሰው እንደሚያይ አይቶ አይመርጥም፤ (1ሳሙ. 16፥7)፤ እግዚአብሔር እንደልቡ የሚሆንለትንና የሚመላለስለትን፤ ፈቃዱንም ሁሉ የሚያደርግለትን እንጂ (ሐዋ. 13፥22) በሁለት ሃሳብ የሚያነክሱ ዘፋኞችን አይፈልግም፤ (1ነገ. 18፥21፤ ማቴ. 6፥24)። ቤተ ክርስቲያን አለም ያከበረቻቸውንና በዘፈን ኀጢአት የመሰከረችላቸውን ለምን ሄዳ ደጅ እንደምትጠናቸው ወይም እናገልግል ሲሉ ለምን ተንገብግባ፤ አሰፍስፋ እንደምትቀበላቸው ግልጽ አይደለም።
    ከአገልግሎት በፊት መጠራት፤ ከመጠራት በኋላ ደግሞ የሕይወትና የምግባር ምስክርነት እንደሚስፈልግ የዘነጋች ወይም ቃየላዊ መሥዋዕትን የወደደች ይመስላል። በተደጋጋሚ ዘፋኞችና ሌሎች  የዘፋኝነትና የታወቀ ነውራቸውን በክርስቶስ ደም አጥርተው፤ በንስሐ የበደሉትን ሕዝብ ክሰው ሳይመለሱ  “የወንጌሉን አውደ ምህረት” ረግጠው “ለሕንጻ ማሠርያ አገልግለው” ወደቀደመ ሥፍራቸው ተመልሰዋል። በዘፈን ትውልድ እያጠመዱ ለዝሙት እያጩ ዘላለማዊውን የሥላሴ ሕንጻ ያፈርሳሉ፤ ነገር ግን ነገ ለሚፈርሰው ሕንጻ ደግሞ “በድምጻቸው” ብር ይሰበስባሉ። አይ ቤተ ክርስቲያን! የዘላለሙን እየከሰረች ለጊዜያዊው ትደክማለች! ምናለ ሕንጻው ቀርቶ አንድ የሥላሴ ሕንጻ ክርስቶስ የሞተለትን ማዳን መቻሉ፥ ከአንድ ሕንጻ እንደሚበልጥ ብናስተውል!?
   ያለድርድር ይህም ክፉ ምሳሌነታችን የንስሐ ልቅሶና ኑዛዜ ያስፈልገዋል!!! መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት እንዲል … ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ።
ሌሎችን ብዙ ችግሮችን  ማንሳት ቢቻልም፣ እኒህን ለማሳያነት ማንሳቱ በቂ ነው። እኒህ ኹሉ ግን የችግሩ ዋና ምንጮች አይደሉም፤ አሁን ላለችው ቤተ ክርስቲያን ዋናውና አንኳሩ የችግሮች አውራው ደግሜ እላለሁ፦
1.    እግዚአብሔር ብቻ አለመመለኩ ነው

   ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን ብቻ ያላመለከችበት ወይም የሚያመልኩትን ፊት የነሳችበት ዘመን ብዙ ነው። ለምሳሌ የቅርቡን ብናነሳ፦
  “ … ለገበሬው ማርክሲዝም ሌኒኒዝም በስፋት ተሰበከ። በሶሻሊስት ቲዮሪ ታንፆ ገበሬው ማርክሲስት ሆነ። መጣቱ ማቴሪያሊስት ሆኖ እግዚአብሔርን ትቶ በቁስ አካል ማመን ደረጃ ላይ ደረሰ። አንዳንድ ማርክሲስት የኾኑ ቄሶች ሁሉ ነበሩ። ከሐሙሲት (ቆላ ሐሙሲት) የአንድ ቀን መንገድ ርቃ በምትገኘው ፀባሪያ በምትባል መንደር ላይ ይኖሩ የነበሩ አንድ ሽማግሌ በያመቱ የሚዘክሩትን የሀምሳት በዓል (ከፋሲካ በኋላ) ደግሰው ሲያበሉ ለታዳሚው ድግሴን ለመጨረሻ ጊዜ ብሉ ከእንግዲህ አላዘክርም ብለው ተናግረዋል። ቲዮሪው እስከዚህ ዘልቆ ነበር።”[1]
   ምንም ልንክደው የማንችለው እውነት በደርግ ዘመን ቤተ ክርስቲያን “እግዚአብሔር የለም” የሚሉ ካህናትን፣ ሰባክያንንና ሌሎችንም በጉያዋ ይዛ ነበር፤ ይህ ብቻ ያይደለ “የፓትርያርክ አቡነ ቴዎፍሎስ መገደልን በተመለከተ መንግሥት ብቻ ሳይኾን የቤተ ክርስቲያኒቱም ሲኖዶስ እጅ አለበት” የሚለው ከባድ ጥርጣሬ መነሾው ተራ ነገር አይደለም። ያኔ “እግዚአብሔር የለም” ዛሬ ደግሞ “እግዚአብሔር ወይም እውነት አንጻራዊ ነው” የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ቤተ ክርስቲያን ምንም ማለት በሚያስደፍር መልኩ ተቃውሞ አለማሰማቷና በመቃረን ጨክና አለማስተማሯ ነው።
      የዚያኔ አውነተኛውን ወንጌልአለማስተማሯ ብቻ ሳይኾን፥ አሁንም እንኳ ያንን ያስተማረችውንና የኖረችውን ሕይወት በመቃወም ማስተማርና ንስሐ መግባት ሲገባት፥ “በአልተሳሳትኩም፤ አልሳሳትምም” እልኸኝነት መንፈስ ስትመላለስ እናያታለን። ቤተ እስራኤል በጠላት ተላልፈው የመሰጠታቸውና የመሸነፋቸው ምክንያት እንዲሁም እግዚአብሔርን እየተከተሉ የማዘናቸውን ነቢዩ ቅዱስ ሳሙኤል ሲነግራቸው “እግዚአብሔርን ብቻ አለማምለካቸው” እንደሆነ በነገራቸው ጊዜ በፍጹም መመለስ ነበር ንስሐ የገቡት። ለዛሬዋም ቤተ ክርስቲያን በቤቱ ስደተኛ ያደረገችውን ጌታ አምላክዋን ይቅርታ በመለመን ንስሐ ስትገባ ብቻ እርቅን ታገኛለች እንጂ የአሁኑ መንገዷ ፈጽሞ የትም አያደርስም።
2.   የሐዋርያትን ትምህርትና ትውፊት አለመከተላችንም ነው። (ሐዋ.2፥42)

     የሐዋርያት ትምህርት መጀመርያው የክርስቶስ ነገረ ድኅነት ፍጻሜውም በክርስቶስ ኢየሱስ የተገኘውን የዘላለም ሕይወት ለአለሙ ሁሉ የምሥራች ብሎ መስበክ ነው (ዮሐ. 20፥31)፤ ከእርሱ ወንጌል በቀር ምንም ዕዳ፣ አንዳች ሸክም እንደሌለባቸው አበክረው ተናግረዋል። ይህንን አገልግሎትና ሥራ እንዲተው ብዙ ማስጠንቀቂያ፣ ማስፈራራት፣ ዛቻ፣ ድብደባና፣ ግድያ ቢደርስባቸውም አብዝተው ከማገልገል ሊያግዳቸው ከቶውንም አልቻለም (ሐዋ. 4፥2፤ 18፤ 5፥40፤ 7፥58፤ 12፥1-3፤ 13፥50፤ 14፥2፤ 19፤ 16፥22-24፤ 17፥5፤ 32፤ 19፥9፤ 28፤ 21፥35 ፤ 22፥22 ፤ 24፥5 27 ፤ ሮሜ 1፥26 ፤ 1ቆሮ. 1፥23 ፤ ገላ. 5፥11)
    ስለጌታ ኢየሱስ ማስተማርን በተቃወሟቸውም ጊዜ ጸሎታቸው “ … አሁንም፥ ጌታ ሆይ፥ ወደ ዛቻቸው ተመልከት፤ ለመፈወስም እጅህን ስትዘረጋ በቅዱስ ብላቴናህም በኢየሱስ ስም ምልክትና ድንቅ ሲደረግ፥ ባሪያዎችህ በፍጹም ግልጥነት ቃልህን እንዲናገሩ ስጣቸው።” የሚል ነበር። (ሐዋ. 4፥29-30) ቅዱስ ጳውሎስ በቁም እስሩ ሳለ ያደርግ የነበረውም “ … የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ገልጦ ያስተምር ነበር።” (ሐዋ. 28፥31) ስለዚህም የሐዋርያት ትምህርት ስንል ለመጽሐፍ ቅዱስ ታማኝ መሆናቸውንና ያንኑ ብቻ በማስተማር መጽናታቸውን ማንሳታችን ነው፤ ደቀ መዛሙርቱ የጌታን ትምህርት ያካተተውንና  እጅግ ታማኝ የነበሩበት ትምህርታቸው “የሐዋርያት ትምህርት ወይም መሠረት” ተብሎ ተጠርቷል። (ሐዋ. 2፥42 ፤ ኤፌ. 2፥19-20)
     የቅዱስ ጳውሎስ ትልቁ ምጥና ጭንቀት በአማኞች ልብ ክርስቶስ እስኪሳል መትጋትና ስለአማኞች ማሰብ እንደሆነ ተናግሯል፤ (2ቆሮ. 11፥28፤ ገላ. 4፥19)። እንኪያስ ትልቁ የጌታችን ሐዋርያት ፤ የቤተ ክርስቲያን ኃላፊነትና ተልዕኮ የጌታን መንግሥት ወንጌል እስከኣለም ፍጻሜ መስበክና መናኘት ነው። ከዚህ ውጪ ሌላ ሥራ፣ ሌላ ኃላፊነት ፈጽሞ አይኖርም፤ (ማቴ. 28፥19)።
    ስለዚህም ሐዋርያት በትውፊታቸው፦
       ነገርን ሁሉ በጸሎት የመጀመርና የመፈጸም ወግ ፤ እንዲሁም በጸሎት የመትጋት ልማድ ነበራቸው። ጸሎትም “ከሁሉ በፊት እንዲደረግ” በመልዕክቶቻቸው ያሳስቡ ነበር። (ሐዋ. 1፥25-26፤ 2፥42፤ 46፤ 3፥1፤ 4፥24-31፤ 6፥4፤ 6፤ 9፥40፤ 12፥5፤ 13፥2፤ 14፥23፤ 1ተሰ. 5፥25፤ 1ጢሞ. 2፥1-2፤ ዕብ. 13፥18)
       መንፈሳዊ ትምህርቶችን መስማት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን እያወጡ ያነቡ ነበር፤ ስብከትም ይሰብኩ ነበር።
       በዜማና በመዝሙርም ይሰብኩ ነበር።
       ዘወትርም የጌታን እራት በመቁረስ ይተጉም ነበር፤ (ሐዋ. 2፥42፤ 46፤ 20፥7)፣
       በአንድነትም በመመገብ፤ ለሌላቸው የማካፈል፤ ገንዘባቸውንም በአንድነት የማኖርና፤ በኅብረት የመኖር ልማድም ነበራቸው፤ ( ሐዋ. 4፥32-36 ፤ ፊልጵ. 4፥14-17)፣
       ያመኑትን በውኃ ያጠምቁ ነበር፤ (ሐዋ. 2፥41፤ 8፥12፤ 38፤ 10፥48፤ 1ቆሮ. 1፥18)፣
       በየሰንበቱም በአይሁድ ምኩራብ(በጸሎት ሥፍራ) ይገኙ ፤ ይሰብኩም ነበር፤ (ሐዋ. 13፥5፤ 14፤ 44፤ 14፥1፤ 16፥13፤ 17፥2፤ 19፥8፤ 21፥26-29)፣
       ክርስቲናዊውን ኑሮ የመሩበት ሥርዓት ማለትም ወግ ነበራቸው፤ (ሐዋ.16፥4 ፤ 1ተሰ. 3፥6)
       የራሳቸው የማስተማሪያ መንገድ ነበራቸው። (1ቆሮ. 14፥27-33) ከዚሁ ጋር በተያያዘ  ሴቶች ዝግ ብለው እንዲማሩ እንጂ እንዲያስተምሩ የሚፈቅድ ትውፊት አልነበራቸውም፤ (1ቆሮ. 14፥34-36፤ 1ጢሞ. 2፥11-13)፣
       በጸሎት ሰዓት ሊሆን የሚገባ የአለባበስ ልዩወግም ነበራቸው፤ (1ቆሮ. 11፥13-16)፣
       በትውፊታቸው ሁሉም አማኞች የተማሩት ከማን እንደሆነ አውቀው በተማሩት ትምህርት እንዲጸኑ ፤ ለተማሩትም ትምህርት እንዲጠነቀቁ የማስተማር ልማድ ነበራቸው፤ (1ጢሞ. 2፥1-2፤ 3፥14-16)፣
       ስለአገልግሎታቸው የሰውን እጅ የማይጠብቁና በራሳቸው ገቢና የእጅ ሥራ ሙያ ይተዳደሩ የነበሩም ናቸው። (ሐዋ. 18፥3 ፤ 2ተሰ.3፥7)
ስለዚህም እኛም፦
o   የመጽሐፍ ቅዱስን ሉዓላዊነት(የበላይነት) ፍጹም ልናምን ይገባናል። አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ቅድመ ኬልቄዶን እንደነበሩት አበው “ኦርቶዶክስ” የሚለውን ስያሜ ከሐዋርያት ትክክለኛ አስተምህሮ ጋርና ከኒቂያ ጉባኤ ውሳኔ ጋር በማገናዘብ (በማዛመድ) ለትምህርቱ ትክክለኛነት ሰጥተው ተርጉመውታል። የዚህ እውነታው ደግሞ እንደሐዋርያት ትውፊት ለመጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ ለሙሉ ታማኝ መሆንን ያገናዝባል።
o   ከላይ ያየናቸው ሐዋርያውያን ትውፊቶች በመካከላችን በእውነት ቢኖሩ ዛሬ የምናየው ምስቅልቅሉ የወጣው መንፈሳዊነት መስመር ይዞ ውበትና መልክ ይኖረው ነበር።

ፍጻሜ ቃል
   ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል መልኩ በቤተ  ክርስቲያን ድካም ላይ ማተኮራችን ቤተ ክርስቲያን ራስዋን በመመልከት ለንስሐና በሙሽራዋ ፊት ለመናዘዝ እንድትቸኩል ለማለት እንጂ “ምንም ምን ጠንካራ ነገር የላትም” የሚል አቋም የለኝም። የቀደመችው ቤተ ክርስቲያን እንኳ በክርስቶስ ፊት ጠንካራ የመሆኗን ያህል የጸሎቷን መልስ ለመቀበል የተጠራጠረችበትም ጊዜ ነበርና (ሐዋ. 12፥12-17) በዚህ ምድር ያለች ቤተ ክርስቲያን ሙሽራዋ መጥቶ እስኪጠቀልላት ድረስ በድካም መያዟ ብዙም ግር አያሰኝም። ነገር ግን ለንስሐ በመዘግየት ከወዴት እንደወደቀች አስባ አለመመለሷ ከሁሉ የበረታ ቅጣትን ማምጣቱ አይቀርም (ራእ. 2፥16)።
  ቅዱስ አትናቴዎስ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦  “ዓለም እውነቱን ለመቃወም ከተነሳች አትናቴዎስ ደግሞ አለምን ለመቃወም ይነሳል።” በማለት። እንኪያስ! ይህን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የሚቃወመውን ማንኛውንም ኃይልና መንፈስ በክርስቶስ ኢየሱስ ስምና ሥልጣን አጽንተን እንቃወማለን፤ እናወግዛለንንም። ትልቁ መሻታችን ቤተ ክርስቲያን በቅድስናና በንጽዕና ለምልማ፤ በመንፈሳዊ ፍሬ ጎምርታ ማየት እንጂ ድካምን በማውራት ብቻ ዘመንን መቁጠር አይደለም። ይህ እንዲሆን የዘወትር መቃተታችንና ጸሎታችን እንዲሆን ፥በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ የምታምኑ አማኞችን ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን ትንሳኤ በጸሎት እንድትተጉ በመስቀሉ ርኅራሄ እለምናችኋለሁ።
   ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ባለመጥፋት ከሚወዱ ሁሉ ጋር ጸጋ ይሁን፤ አሜን። (ኤፌ.6፥24)
ተፈጸመ።
ይህ ጽሑፍ ከሦስት ዓመታት በፊት በአንድ ሌላ ጡመራ መድረክ ላይ ወጥቶ ነበር!


ዋቢ መጻህፍት

v የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር(1962)መጽሐፍ ቅዱስ።አዲስ አበባ፣ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት።
v ሃይማኖተ አበው። ፤1982 ፤ አዲስ አበባ ፤ ተስፋ ማተሚያ ቤት።
v ፍትሐ ነገሥት ሥጋዊ ወመንፈሳዊ የሕግ ምንጭ በግዕዝና በአማርኛ።1992 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ተስፋ ማተሚያ ድርጅት።
v ኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር(2002)።የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት 9ኛ እትም፣አዲስ አበባ።ንግድ ማተሚያ ድርጅት።
v ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ፤ ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፤ 1993 ዓ.ም፤አዲስ አበባ፤ አሳታሚ ማህበረ ቅዱሳን።
v አበራ በቀለ(ሊቀ ጉባኤ አባ)፡፡ ትምህርተ ሃይማኖት እና ክርስቲያናዊ ሕይወት፡፡ 1996 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ ንግድ ማተሚያ ድርጅት (ማኅበረ ቅዱሳን)፡፡
v አባ ጎርጎርዮስ (M.A) ፤ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ  1991 3ኛ ዕትም ፤ አዲስ አበባ ፤ ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት።
v ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ፤ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ፤ 1993 ፤ አዲስ አበባ ፤ አሳታሚ ማህበረ ቅዱሳን ።
v ዲበኩሉ ዘውዴ(ዶ/ር)፤ ፍትሐ ነገሥት ፡ ብሔረ ህግ ወቀኖና ፤ 1986፤ አዲስ አበባ።
v አማርኛ መዝገበ ቃላት ፤ የኢትዮጲያ ቋንቋዎች ጥናትና ማርምር ማዕከል ፤ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ፤ የካቲት 1993 ፤ አርቲስቲክ ማተሚያ ድርጅት።
v የማርክሲዝም ሌኒኒዝም መዝገበ ቃላት፤ አዲስ አበባ ፤ 1978 ፤ ኩራዝ ማተሚያ ድርጅት።
v ደራሲው ያልተጠቀሰ ፤ ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ ፤ ቅጽ አምስት ፤ 1993 ፤ አዲስ አበባ ፤ሜጋ አሳታሚ ድርጅት።
v የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ፤ ሰኔ 16 2004 ዓ.ም. ፤ በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ባዘጋጀው “የአብያተ ክርስቲያናት ትብብር ለሰላምና ለልማት” ሲል ያዘጋጀው መጽሔት።
v ዲ.ን ዳንኤል ክብረት ፤ ስማችሁ የለም ፤ ነሐሴ 2006 ፤ አግዮስ ኅትመትና ጠቅላላ ንግድ ሥራ ሐላ.የተ.የግል ማኅበር።
v ሐመረ ተዋህዶ ዘዕሥራ ምእት፤ ማህበረ ቅዱሳን ፤ ሐምሌ 2000፤ አዲስ አበባ።
v ሐመር ፤ ፲፫ዓመት ቁጥር ፭ ፤ መስከረም/ ጥቅምት ፲፱፻፺፰ ዓ.ም ፤ ገጽ ፳፮።
v ጥር 30 1999 በአሜሪካ ሬድዮ የአማርኛው ፕሮግራም ላይ የቀረበ ዜናና መግለጫ።
v ጥር 25 1999 ዓ.ም ከምሽት ዜና በኋላ በኢትዮጲያ ሬድዮ አገልግሎት የቀረበ ዜናና መግለጫ።


[1]ደራሲው ያልተጠቀሰ፤ ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ፤ ቅጽ አምስት፤ 1993 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ሜጋ አሳታሚ ድርጅት፤ ገጽ21።

1 comment:

  1. ትልቁ መሻታችን ቤተ ክርስቲያን በቅድስናና በንጽዕና ለምልማ፤ በመንፈሳዊ ፍሬ ጎምርታ ማየት እንጂ ድካምን በማውራት ብቻ ዘመንን መቁጠር አይደለም። ይህ እንዲሆን የዘወትር መቃተታችንና ጸሎታችን እንዲሆን ፥በክርስቶስ ሞትና ትንሳኤ የምታምኑ አማኞችን ሁሉ ለቤተ ክርስቲያን ትንሳኤ በጸሎት እንድትተጉ በመስቀሉ ርኅራሄ እለምናችኋለሁ።

    ReplyDelete