Tuesday 19 February 2019

“ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ” (ማቴ. 12፥41)

     Please read in PDF
    የአይሁድ መሪዎችና ሕዝቡም የክርስቶስን መሲሕነት ለማረጋገጥ ምልክትን [ተአምራትን] በተደጋጋሚ ጠይቀውታል። የጠየቁት መሲሕነቱን ለማመንና እርሱን ለመከተል አይደለም፣ ይልቁን መሲሕነቱን ለማወቅ የመጡበት መንገድ ጠማማና ያለማመን መንገድ ነው። በዚህ በማቴዎስ ወንጌል ምዕ. 12 ላይ ብቻ እንኳ ሊፈታተኑ በተደጋጋሚ ጥያቄ አቅርበዋል፤ (ቁ. 2፤ 14፤ 24፤ 38)፤ ፍጹምና ጻድቅ የኾነውን መሲሕ ሊፈትኑት እርሱ የሚያሳየውን ምልክት በተደጋጋሚ ጠይቀዋል። የፈለጉት ተአምራት በጉልህ የሚታይና አሁን በሰማያት ላይ የሚደረገውን ነበር፤ (ሉቃ. 11፥16)።
ምልክቱን የፈለጉት ራሳቸው እንደሚሹት ነው እንጂ ሊታነጹበትና እግዚአብሔርን የተአምራት ድንቅ አምላክ ብለው ለማመስገንና ለማምለክ አይደለም፤ ይልቁን ሊነቅፉት፣ ሊፈትኑት፣ በእርሱም ላይ ሊሳለቁ ነበር። በቀጥታ ንግግራቸውም ኢየሱስ ተአምራትን ያደርግ የነበረው በሰይጣን ኃይል እንደ ኾነ በግልጥ በመናገር ንቀታቸውን አሳይተዋል። በዚህ ንግግራቸው ይህን ብቻ የሚያደርጉ አይደሉም። እግዚአብሔር የዘለላም አምላክ መኾኑን የሚቃወሙ ናቸው። ምክንያቱም እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን የሠራቸው ሥራዎቹ፣ ተአምራቶቹ፣ ምልክቶቹ የሚያረጁና የሚያልፉ አይደሉምና። ይህን ባለማስተዋል በፍጹም ስተዋል።

ጌታችን ኢየሱስ ለእነዚህ ምልክት ፈላጊዎች አጽንቶ የተናገረው ነገር ቢኖር፣ “ክፉና አመንዝራ ትውልድ ምልክት ይሻል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም።” (ማቴ. 12፥39) የሚል ነው። ዮናስ የብሉይ ኪዳን ነቢይ ነው፤ በነቢይነቱም ክፉ ወደ ኾነችው ከተማ ተልኮ የነነዌን ሕዝብ እንዲያገለግልና የንስሐን ስብከት እንዲሰብክላቸው የተላከ ነቢይ ነበር፤ ነገር ግን ዓመጸኛ ኾኖ ሳይታዘዝ ቀረ፤ አለመታዘዙንም ለማሳየት እግዚአብሔር ወዳዘዘው ሳይኾን ወዳላዘዘው ወደ ነነዌ መሄድ ትቶ፣ ዋጋ ከፍሎ ወደ ተርሴስ ሊሄድ መርከብን ተሳፍሮ መንገድን ጀመረ፤ እግዚአብሔር አምላክ መታዘዝን እንቢ ያለውን ዮናስን ነፋስን፣ ማዕበልንና ሞገድን፣ መርከቡን፣ የመርከቢቱን ተጓዦች … በማዘዝ የዓመጸኛውን ነቢይ መንገድ እግዚአብሔር በቁጣው በማጠር በዓሳ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሌሊት እንዲኖር[እንዲጓጓዝ] በማድረግ ወደ ነነዌ እንዲመለስ አደረገው፤ ሕዝቡንም እንዲያስተምር እንደገና ላከው፣ ዮናስም በንስሐ ስብከቱ ሊመጣ ካለው ቁጣ እንዲርቁ ሕዝቡን አስጠነቀቀ፤ (ዮና. 1፥1-17)።
የዮናስ በዓሳ አንበሪ ሆድ ሦስት ቀንና ሌሊት ማደር፣ ለጌታችን ኢየሱስ ሥጋ ሞትና መቀበር ደግሞም ከተቀበረበት የምድር ልብ በሦስት ቀኑ ለመነሣቱ ምልክት ነው። ይህም ክርስቶስ ኢየሱስ እውነተኛ መሲሕ ለመኾኑ ለአይሁድ ምልክት ነው። እኒህ አይሁድ ተአምራትንና ድንቆችን ጌታ ኢየሱስ ሲያደርግ አይተዋል። ነገር ግን ባዩት ተአምራት ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ኾነ ማስረገጫ ናቸው ብለው አልተቀበሉአቸውም። ኃይሉን ከሰይጣን ያልተቀበለ መኾኑን በተአምራት እንዲያረጋግጥላቸው ምልክትን ፈለጉ።
የነነዌ ሕዝብ በመጨረሻው የፍርድ ቀን ይድናል፤ ምክንያቱም የንስሐ ስብከቱን ሰምተው ተመልሰዋልና። የነነዌ ሰዎች እንዲህ ታዛዥነታቸውና መልካምነታቸው የአይሁድን ክፋትና አመንዝራነት በትክክል ይገልጣሉ ወይም ያለንግግር ይዘልፋሉ። ነነዌ ከክፋቷ ስትመለስ አይሁድ ግን በብርሃኑ መሲሕ ፊት በክፋቷ ጸንታ በጨለማ ትመላለሳለችና። ነነዌ በግድ እንጂ በማይታዘዘው ነቢይ በዮናስ አማካይነት ተመልሳ ንስሐ ገብታለች፣ ዮናስ መጥቶ የንስሐ አዋጁን ባወጀ ጊዜ ነነዌ በፍጹም መዋረድ ንስሐ ገብታለች።
ኢየሱስ ግን ከዮናስ ይበልጣል፤ እነሆ እርሱ በትስጉት ተገልጦ በመካከላቸው ነው፤ አይሁድ ከዮናስ የሚበልጠው የዮናስ ጌታ በመካከላቸው ቆሞ ወይም ተገልጦ እየተመላለሰና እስተማራቸው ንስሐ መግባትና መመለስን አልፈለጉም። መሲሑ ገና በተገለጠ ጊዜ ለእስራኤል የተናገረው፣ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” (ማቴ. 4፥17) በማለት ነበር። በመካከላቸው ተገልጦ እጅግ በመደጋገም እንዲመለሱና እንዲድኑ አስተምሮአቸው ነበር። እነርሱ ግን ሊሰሙ አልወደዱም።
የዮናስን የአንድ ቀን ስብከት ነነዌ ሰምታ ተመለሰች፤ በተደጋጋሚ የሰበከውን የኢየሱስን ስብከቶች ግን ኢየሩሳሌም ልትሰማ፣ ልትቀበልም አልወደደችም። ኢየሱስ ከዮናስ ይበልጣል፣ ኢየሩሳሌም ግን ዮናስ በነነዌ ያገኘውን ተሰሚነት ያህል እንኳ ለኢየሱስ ልትሰጥ አልወደደችም። ስለዚህም የአይሁድ ጥፋት እጅግ፣ በደላቸውም ታላቅ ናት። የነቢይን ቃል አለመስማትና አለመታዘዝ ያስገድላል፤ (ዘዳ. 18፥19፤ ሐዋ. 3፥23)፤ በቀደመው ኪዳን የአንድን ነቢይ ቃል አለመስማት የሚያስገድል ከኾነ የኢየሱስን ቃል አለመስማት ፍርዱ ምን ይኾን?
ነነዌ የዮናስን ድምጽ ባትሰማ ትጠፋ ነበር፤ ሰምታ ግን ዳነች፤ ኢየሩሳሌም የነቢያትን ጌታ የኢየሱስን ቃል ልትሰማ አልወደደችም፣ ፈጽሞ አልፈለገችምም፣ ስለዚህ ፍርዷ እንዴት የከፋ ይኾን? ስለዚህም ነነዌ በኢየሩሳሌም ላይ ምስክር ትሆናለች፤ እንኳን ለላኪው ጌታ የተላከውን ነቢይ ቃል ሰምታ ተመልሳለችና፤ ኢየሩሳሌም ግን ነቢያትን የላከውን ጌታ ልትቀበል አልወደደችም፤ ዮናስ በእግዚአብሔር ስም ወደ ነነዌ ሄደ፣ ተቀበሉት፣ አካላዊ ቃል ወልድ፣ ኢየሱስ ግን ራሱ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ ፈጽሞ ተቀባይነትን አጣ።
እናም ምልክት ፈላጊዎቹን አይሁድ ጌታ ኢየሱስ ክፉና አመንዝራ ትውልድ በማለት ጠራቸው። ስለልባቸው ክፋትና ድንዛዜ ክፉዎች ተባሉ፤ ከእግዚአብሔር ይልቅ ሌሎችን በማምለካቸው ደግሞ አመንዝራዎች ተባሉ፤ ከእግዚአብሔር ውጪ ማምለክ አመንዝራነት ነውና። እንዲሁም የአመንዝራነት ጠባይ በአንድ ነገር አለመርካት ነው፤ የምልክት ወይም ተአምር ፈላጊ ትውልድም ጠባይ እድሜ ዘመኑን ከአንድ ተአምር ወደ ሌላ ተአምር ሲሸጋገር ይኖራል እንጂ ኢየሱስን በማመን ልቡ አርፎ አይረጋም።

በኢየሱስ ምልክቶች እረካለሁ ብሎ በኢየሱስ በራሱ አለመርካት ክፉና አመንዝራነት ነው። ዛሬ በአብያተ ክርስቲያናት የምናየው አስፈሪው ችግር ይህ ነው፤ ሰው በእግዚአብሔር መርካት፣ በልጁ በኢየሱስ ሐሴት ማድረግ አይፈልግም፤ ግን ስጦታዎቹን አብዝቶ ይፈልጋል፣ በዚያም ለመርካት ይጣጣራል፤ ኢየሱስ ከዮናስ ይበልጣል፣ ከነቢያትም ይበልጣል፣ የነቢያትና የሌሎችም ምልክቶችና ተአምራት ወደ ኢየሱስ ካልመራንና ካላሳረፈን አመንዝራና ክፉዎች ተብለን ብቻ የምንወቀስ አይደለንም፤ ያየናቸው ምልክቶች ኹሉ ምስክሮች ይኾኑብናል። ነነዌ በኢየሩሳሌም ላይ ምስክርናት፤ ምክንያቱም የዮናስ መጽሐፍ በብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ አለ፤ ታሪኩም የታወቀ ነውና፤ ኢየሱስ ደግሞ በእያንዳንዳችን ላይ ይፈርዳል፤ እርሱ ከዮናስ የሚበልጥ የሰማይና የምድር ኹሉ ጌታ ነውና፤ እንኪያስ ወገኖቼ! በማን መርካትና ማረፍ ትፈልጋላችሁ? በኢየሱስ በራሱ ወይስ እንደ ዮናስ ባሉ አገልጋይ በኾኑ ቅዱሳኑና ተአምራቶቹ? ወይስ በተአምራት አድራጊዎቹ? በማን መርካት ትፈልጋላችሁ? ከዮናስና ከኹሉ በሚበልጠው በኢየሱስ መርካትና መደሰት፣ ማረፍ ይኹንላችሁ፤ አሜን።  

3 comments:

  1. diakon,yemilwen,kel,atefaw,endaneta,ayentu,diakonen,ayewkelem,

    ReplyDelete
  2. AMEN BEHIYWOTACHIN YIMLALES YENAZRETU IYESUS TEBAREK

    ReplyDelete