Tuesday 5 February 2019

ዘመነኛ “አገልጋዮችን” ሳስብ ትዝ የሚለኝ እንዲህ ነው!


  ጌታ አትረፍርፎ ባርኮኛል፣ ዲታና ቱጃር አድርጐ¡ እንዴ ጌታ ቢባርከኝ አይደል እንዴ የ10 ሚሊየን ብር መኪና ለራሴ፣ የ12 ሚሊየን ብር መኪና ለባለቤቴ መግዛቴ?¡ ጌታማ ልዩነት ያደርጋል፣ እንኳን በማያምኑትና በእኔ፣ በሚያምኑትና በእኔ መካከል ራሱ ልዩነት ያደርጋል፣ አዎን ያደርጋል፣ ስለሚያደርግም ነው፣ የ200 ሚሊየን ብር መኖሪያ ቤት የሰጠኝ፤ ደግሞ ባርኮቱ እጅግ በጣም ስለተትረፈረፈልኝ፣ ከሰሞኑ ደግሞ የ600 ሚሊዮን ብር ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ላሠራ ነው፤ ገና ደግሞ በእስቴዲየም ደረጃ የወንጌል ማገልገያ አዳራሽ እናሠራለን፤ ለወንጌልማ ሰማይ ጠቀስ ሕንጻ ሊገነባለት ይገባል¡¡¡  ለምን ብለን በየመንደሩ፣ ለምን ብለን በየቀዬው፣ ለምን በየገበያው፣ ለምን በየወንዛ ወንዙ እየሄድን እንደ ኢየሱስና ጳውሎስ እንደ ቀደሙት ደቀ መዛሙርት ለምን “ሳይመቸን እየተንዘላዘልን” እንሰብካለን?¡ ኢየሱስ ራሱ፣ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ …” ማለቱ ትክክል አይደለም፤ እርሱ ዞሮ ያልሰበሰበውን ሕዝብ እኮ እኛ ይኸው ተቀምጠን በቀላሉ ሰብስበን አይደለም ወይ? የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ባይኾኑም የእኛ ምርጥ ደቀ መዛሙርት ናቸውና ደስ ይለናል?

   ኮሰስ ያለ አለባበስም አይመጥነንም፤ ቀሚሱ ከኢየሩሳሌም፣ ሱፉ ደግሞ ከዱባይ፣ ከርቤና ዕጣኑ ከቴላቪቭ፣ ወንጌሉና አስኬማው ደግሞ ከግሪክ ሊመጣልን ይገባል፣ አገልጋዮች አይደለን እንዴ? ለየት ያለ ነገር ይገባናል¡ አገልጋይማ ቀብረር ሲል ነው የሚያምርበት¡ የምን እንደ ኢየሱስ ከአንዲት ሳምራዊት ሴት ጋር ቀን ሙሉ መለፍለፍ ነው? በርጠሚዎስ ከሚባል ለማኝ ጋር ቆሞ ማውጋትም ክብር ይነካል? ከድሆች ጋር መዋልም ትክክል አይደለም፤ “አሪፍ አሪፎቹን፣ ምርጥ ምርጦቹን፣ ሸጋ ሸጋዎቹን፣ ሎጋ ሎጋዎቹን፣ ረብጣ ረብጣ ያላቸውን” መርጦ መጠጋት ነው እንጂ ... ኢየሱስን ይመስል “ራሴን የማስጠጋበት የለኝም” ብሎ መመለስና ድሃ ኾኖ መኖር አግባብ አይደለም¡
   ኢየሱስ እኮ ሃብታም ነው፤ ሰማይና ምድር የእርሱ አይደል? ታዲያ ድሃ ለምን እንኾናለን? ጳውሎስ ድንኳን እየሠፋ መኖሩ፣ “ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነው፤ ወደ ዓለም ምንም እንኳ አላመጣንምና፣ አንዳችንም ልንወስድ አይቻለንም፤ ምግብና ልብስ ከኖረን ግን እርሱ ይበቃናል” ማለቱም፣ የእኛን ክፍለ ዘመን ያገናዘበ ንግግር አይደለም¡¡¡ እኛ ምርጥ አዳራሽ፣ ምርጥ ቸርች፣ ምርጥ ሕንጻ፣ ምርጥ ቀሚስ፣ ምርጥ ሱፍ፣ ምርጥ አስኬማ፣ ምርጥ የዕንቁ ወይም የወርቅ የብር ወይም የእጅና የአንገት መስቀል፣ እንደ እጅ የሚመች ፑልፒት፣ የ5 ሚሊየን ብር ታቦተ መንበር፣ የፕላቲንየም ጉልላት፣ ጌጠኛና የተንቆጠቆጠ ላንቃ፣ የወርቅ ጻህል ... ለቸርቻችን ያስፈልገናል
  በተለይ ደግሞ አገልጋይ ከምዕመናን ለየት ያለ ወንበር ይገባዋል፤ እንደ ምዕመናንማ ተመሳሳይ ወንበር ላይ መቀመጥ “ያስፎግረዋል”¡ ነቢያችን፣ ሐዋርያችን፣ ጳጳሳችን፣ ሰባኪያችን፣ የደብራችን አለቃ፣ የማኅበራችን መሪ ... ልዩ ወንበር ሊዘጋጅለት ይገባል፤ እንጂማ እንዴት ከኀጢአተኞች ጋር እንደ ተቀመጠው ኢየሱስ፣ ከምዕመናን ጋር በአንድነት መቀመጥ የለበትም፤ ኢየሱስ ግን ለምን ነው ከኀጢአተኞች ጋር መቀመጡ አግባብ ነው? የእኛን አገልግሎት ለማሳጣት ማድረግ አልነበረበትም¡¡¡
   ኢየሱስ ዝቅ ዝቅ ማለቱም አግባብ አይደለም፤ የደቀ መዛሙርቱን እግር ማጠቡ እንዴት ኾኖ ነው አግባብ የሚኾነው? ለአገልግሎት ይህን ያህል ራስን ማዋረድ ለምን? እግራችንን የሚያጥቡ ሌሎች እንጂ እኛ ታላላቅ አገልጋዮች እንዴት ዝቅ ብለን፤ አደግድገን የሰዎችን እግር እናጥባለን? ከኾነም እንኳ ለመታሰቢያነት በዓመት እንዴ ማድረግ እንጂ፣ ለምን ብለን ዘወትር እግር በማጠብ በዝቅታ እንጠመዳለን? በሥነ ልቡና እኮ ራስን ብቁ ማድረግ እንጂ ኹሌ በዝቅታ መኖር አግባብ አይደለም? ኢየሱስ ዘወትር “ትሁት” ኹኑ ያለው ነገር የምር ሰውን ይጎዳል¡¡
    ደግሞ ዘወትር ኢኮኖሚያችን የተስተካከለ መኾን አለበት፤ ለዚህ ደግሞ የባንክ አካውንታችን በደንብ መደለብ አለበት፤ ከጐረቤታችን ያሉትም ቸርቾች በግል አካውንት ከፍተው ማጠራቀም አለባቸው፤ ለምን ይህን ሁሉ አስቀመጣችሁ? እንዳይሉን የብሩ መጠን ለምዕመናን/ለአማኞች መናገር አይገባም? እና ደሞዛችንም ከፍ ማለት አለበት፣ ምነው የአንድ እግር ኳስ ተጨዋች ደመወዙ በሳምንት አይደለም ወይ የሚሸለገው? ታድያ እኛ በየቀኑ እያገለገልን በየቀኑ ደመወዝ ሊከፈለን አይገባም?¡
   ይህ ጳውሎስ ግን ምን ኾኖ ነው “ብዙ ጊዜም በራብና በጥም ብዙ ጊዜ በመጦም፣ በብርድና በራቁትነት በመካከላችሁ ነበርሁ” ያለው ልክ አይደለም፤ ለምን ብሎ ነው በዚያ ሁሉ አማኝ መካከል የሚራበው? የተራበው የተጠማው በብርድና በራቁትነት የተቸገረው ሰውን መጠጋት ስለማይችልበት ነው፤ ከአንዱ ንጥጥ ቱጃር ተጠግቶ ቀለቡን ዝም ብሎ አይሰፍርም? በዚህ እንኳ ጳውሎስ ጥበብ ይጐድለዋል።
    ደጋግሞ ደጋግሞ “ኢየሱስ ኢየሱስ፣ ኢየሱስ ለኀጢአተኞች ተሰቀለ፣ ሞተ፣ በሦስተኛው ቀን ከሙታን ተነሣ፣ አርጎ በግርማው ቀኝ ተቀመጠ” የሚለውን ሰባኪ በቀስታ ወይም በቀጥታ ከአገልግሎት ውጪ ማድረግ መልካም ነው፤ የደብሩን አለቃ፣ የአገረ ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ፣ የቸርቹን መጋቢ፣ የቤተ ክርስቲያኑን መሥራችና ባለራዕይ፣ ነቢዩን … የሚያሞጋግሰውን፣ የሚያቆላምጠውን፣ የሚያንቆለጳጵሰውን ግን ዕድገት መስጠት፣ ደመወዝ መጨመር፣ በየቀኑ ዓውደ ምሕረት ላይ እንዲቆም፣ ፑልፒቱን ተደግፎ ፕሮግራም እንዲመራ ማድረግ በጣም ጥሩ ነው፤ ምክንያቱም የኢየሱስን ትምህርትና ሕይወት ደጋግሞ ስለማያነሳ አያሸማቅቀንም¡
    ስለኀጢአትና ኀጢአተኝነት፣ ስለክርስቶስ ቤዛነትና አዳኝነት መነገርም ትክክል አይደለም፤ ኹላችንም ኃጢአተኞች ነን፣ ስለዚህ ማንም ከማንም አይሻልም፤ የተገለጠ ኀጢአት ቢኖርም ዝም ብሎ መሸፋፈን እንጂ መገሰጽ አይቻልም። “አንተ ማን ነህና ነው እንዲህ ነህና ተመለስ፣ ተው፣ ትክክል አይደለም የምትለው? እያንዳንድሽ ትላንት ምን እንደ ነበርሽ፣ ጉድሽን ደብቀሽ የሰው ኀጢአት የምትጎረጉሪ እንደኾንሽ እናውቅሻለን¡ እና ስለ ኀጢአት ደጋግማችሁ አትጨቅጭቁን! ደጋግሞችሁ ወደ ንስሐ አትምሩን፣ ፈታ፣ ዘና፣ ልቅቅ፣ ዝርግት፣ ፍስስ፣ ብትን እንበልበት!!! አታጨናንቁን፣ እንድናለቅስ አታድርጉን¡¡¡ …  
እንደሚሉ እርግጠኛ ነኝ!
   ግና ኢየሱስ እርሱ ጻድቅና እውነተኛ ነው፤ ብዙዎቻችን የኢየሱስን ትምህርት አድናቂዎች እንጂ ሕይወቱን ወዳዶች አይደለንም፤ ሕይወቱ አይጣፍጠንም፤ ከድሃ ሴት እንደ ተወለደ፣ እየተዘዋወረ እንዳስተማረ፣ ከድሆችና ከኀጢአተኞች ጋር እንደ ነበር መናገርና መስበክ አንፈልግም፣ የትምህርቱ ያህል ሕይወቱ አይጣፍጠንም፤ ካመንን ግን ኢየሱስን በኹለንተናችን ማመንና መቀበል ያስፈልገናል!!! ጌታ መንፈስ ቅዱስ በእውነት ይርዳን፤ አሜን።

No comments:

Post a Comment