Tuesday 29 January 2019

ቤተ ክርስቲያን ተጐታችና ዘመነኛ ችግሮቿን አስተውላ ይኾንን!? (ክፍል 9)

1.8.      ግብረ ሰዶማዊነት

“ሴቶቻቸውም ለባሕርያቸው የሚገባውን ሥራ ለባሕርያቸው በማይገባው ለወጡ፤ እንዲሁም ወንዶች ደግሞ ለባሕርያቸው የሚገባውን ሴቶችን መገናኘት ትተው እርስ በርሳቸው በፍትወታቸው ተቃጠሉ፤ …” (ሮሜ 1፥26-27)
“… ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ … የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።”   (1ቆሮ. 6፥9-10)
  ኀጢአትን አዘውትረው ለሚሠሩ ሰዎች ሁሉ (ክርስቲያኖችን ጭምር) መንፈሳዊ ሞት የሚያገኛቸው መኾኑን ታላቁ መጽሐፍ ደጋግሞ ተናግሯል (ሮሜ 6፥16፤ 8፥13፤ ገላ. 5፥21፤ ኤፌ. 5፥5-6፤ 1ዮሐ.2፥4፤ 3፥9፤ ያዕ. 1፥15)። ኀጢአትን በተመለከተ ምንም መታለል አይገባም፤ ብዙ ሰዎች በክርስቶስ ሞት ያገኙትን ነጻነት ለራሳቸው የኃጢአት ሥራ በነጻነት ለመፈጸም እንዲያመቻቸው ሲጠቀሙበት እናያለን። ይህንንም በተመለከተ ታላቁ መጽሐፍ፦ “ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ ለአርነት ተጠርታችኋልና፤ ብቻ አርነታችሁ ለሥጋ ምክንያትን አይስጥ፥ … ” (ገላ. 5፥13) እንዲሁም “አርነት ወጥታችሁ እንደ እግዚአብሔር ባሪያዎች ሁኑ እንጂ ያ አርነት ለክፋት መሸፈኛ እንዲሆን አታድርጉ” (1ጴጥ. 2፥16) በማለት በግልጥ ያለምንም ማወላወል አርነታችንን ኀጢአትን ለመፈጸም እንደ መሸፈኛ ማቅረብ እንደማንችል ያስቀምጣል።

   ግብረ ሰዶማዊነት አስነዋሪ ምኞት በመኾኑ (ሮሜ 1፥26) ፍጹም ኀጢአት ነው። ከምንም ነገር በላይ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ኀጢአት በቀጥታም ይኹን በተዘዋዋሪ ፈጽሞ ልትተባበር አይገባትም። ነገር ግን ዛሬ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ይህን ለመቃወም አቅም እያጣች የመጣች ይመስለኛል፤ የምዕራቡ አለም አብያተ ክርስቲያናት ዛሬ ላይ በግልጽ ተቀብለው በየአብያተ ክርስቲያናቱ እንደ መብት ቆጥረውት እየፈጸሙት ነውና የዚያ ተጽዕኖ አሻራና በዋናነት የእኛም ኀጢአተኝነት ታክሎበት በአስፈሪ ፍጥነት እየተስፋፋ መኾኑን እያየን ነው። [የአሜሪካው ፕረዘዳንት በዚህ በነዲድ እሳት ወቅት በተሻለ ድፍረት ግብረ ሰዶማዊነትን “የሰይጣን ጋብቻ” ማለቱ እጅግ አስደናቂ ሳይኾን አይቀርም!]
   ቤተ ክርስቲያን ከመቃወም ዝምታን መምረጧ ብቻ ሳይኾን፣ በዚህ ጉዳይ የሚሳተፉና የተሳተፉትን አገልጋዮችና አባላቶቿን ዝም ብላ በጉያዋ ሸሽጋ ማስቀመጧ የቅድስና ቀሚሷን በፈቃዷ ለማውለቅና ለእግዚአብሔር ፍርድና ቁጣ ራስዋን እያዘጋጀች ይመስላል። በአንድ ወቅት አንድ አገልጋይ በዚህ ነውር በግልጽ ተይዞ በንስሐ ለመመለስ ጥረት ሲያደርጉ ከአንዲት “የቤተ ክርስቲያን ሴት አዛውንት” አንደበት የተሰማው መልስ ምት እጅግ አስደንጋጭ ነበር። “እናንተ በእርሱ እንትን … (በስም ነው የጠሩት) እናንተ ምን አገባችሁ? … እርሱ የፈለገውን ቢያደርግበትስ?” እንዲህ በቤተ እግዚአብሔር ተቀምጠው ኀጢአተኞችን የሚያበረታቱ “ቀላል አዛውንቶች” ቤተ ክርስቲያን አክብራ፤ አንከብክባ መያዟ እጅግ ለልብ የማይሽር ቁስል ሕመም ነው።

1.9.      ትላንት በግልጽ ዛሬ ደግሞ “በመንፈስ የግብጻውያን” ተጽዕኖ አለመቅረቱ

   ከአንድ ሺህ አምስት መቶ አመት በላይ፣ ከአንድ መቶ አስራ አንድ አባቶች የማያንሱ ጳጳሳት የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከግብጽ እልፍ አዕላፍ ወርቅ፣ ዕንቁ፣ የዝሆን ጥርስ፣ አልማዝ፣ የከበረ ድንጋይ፣ ብር፣ የተለያዩ ውድ አልባሳትና ሌሎች ብዙ እጅ መንሻዎችንና ገጸ በረከቶችን በማቅረብ (ልዋጭ በመስጠት) ታስመጣ ነበር። የማስመጣቷ ምክንያት ደግሞ እስከዛሬ ከፍትሐ ነገስታችን ላይ ጉብ ብሎ እስካልተነሳው ስርዋጽ አንቀጽ የተነሳ ነው፤[በባለፈው ሲኖዶስ ውሳኔ አንቀጹ እንዲነሣ ቢታዘዝም አኹንም ከነ ግርማ ሞገሱ አብሮት አለ!]
“ … የኢትዮጲያ ሰዎች ከዐዋቂዎቻቸው ወገን በራሳቸውም ፈቃድ ሊቀ ጳጳሳትን ለራሳቸው አይሹሙ። ጳጳሳቸው ከእስክንድርያው በዓለ መንበር ሥልጣን በታች ነውና።”[1]
   ይህ አንቀጽ ለምን ይኾን ዛሬስ ከፍትሐ ነገሥቱ ላይ ያልተነሳውና ወደ ሙዝየም ያልገባው? ነው ወይስ ለዳግመኛ ባርነት ሌላ የሚጠብቀው ትውልድ አለ? በጣም የሚያሳዝነው ሌላው ታሪክ ደግሞ በአንድ ወቅት ኢትዮጲያውያን ጳጳስ ይሾምልን ብለው ግብጻዊውን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤልን እነአጼ ሐርቤ ስለጠየቁ “ንጉሡ ኢትዮጲያውያን ኤጲስ ቆጶሳት እንዲሾሙ በመጠየቁ እግዚአብሔር ተቆጥቶ በአገሩ በኢትዮጲያ ላይ መቅሰፍት አወረደ” ይላል በሚያዝያ ፲ ቀን የሚነበበው “ስንክሳራችን”። እንዴት በገዛ እጃችን በራሳችን ላይ ተሳልቀናል?! እንዴት ባለ ትብታብና ድንዛዜ ነው የተያዝነው?
    ከግብጽ ከሚመጡት ጳጳሳት ከእጅግ በጣም በጣም ጥቂቶቹ በቀር አብዛኛዎቹ እንደ“አቡነ” ዳንኤል ያሉት ገንዘብ አፍቃሪዎች፣ እንደ“አቡነ” ሳዊሮስ ያሉት መስጊድ የሚያሠሩ የሙስሊም ኢማሞች … ሌሎቹ ደግሞ አመንዝሮችና ቅጥ ያጡ ጥቅመኞች ነበሩ። ሌሎቹ  እንደ አቡነ ሚካኤል ያሉት ደግሞ ከእርጅና የተነሳ ምንም መሥራት የማይቻላቸው ነበሩ።[2]
     የግብጽ ቤተ ክርስቲያን ትላንት “ከጠቀመችን ጥቅም” ይልቅ በጉዳት ያጠቃችን ጥቃት እጅግ ይበልጣል። በታሪካችንና በአምልኮአችን ውስጥ ረጅም እጇን ሰድዳ ወደአሻት አቅጣጫ ስትመራን ኖራለች ማለት ይቻላል።የኢትዮጲያ ቤተ ክርስቲያን በግብጽ ቤተ ክርስቲያን የደረሰባትን በደል አባ ጎርጎርዮስ ሲያስረዱ፦
“ … በነዚህ አያሌ አመታት ውስጥ ውስጥ ለመላው ኢትዮጵያ ሚላከው አንድ ጳጳስ ብቻ ነበር ፤ እሱውም የሕዝቡን ቋንቋ ስለማያውቅ ለማስተማርም ሆነ ለማስተዳደር በስማ በለው ነበር። የሚቀመጠውም ንጉሡ ባለበት ቦታ በከተማ ብቻ ስለነበር ፤ በገጠሩ የሚኖረው ሕዝብ ቤተ  ክርስቲያኑ እንዳይዘጋበት ሕጻናቱን በጀርባው አዝሎ በትከሻው ተሸክሞ ጳጳሱ ወዳለበት የወር የሁለት ወር ጐዳና ተጉዞ ይመጣል። ከዚያም ገንዘቡን ከፍሎ ካኑልኝ ሲል ጳጳሱ ገንዘቡን ተቀብሎ ከሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውጪ ዕድሜው ለክህነት ሳይደርስ ፤ ለክህነት የሚያበቃ ሙያ ሳይኖረው እየካነ ይልከዋል። ልጁም ተክኖ በቂ ትምህርት ሳያገኝ በቤተ ክርስቲያን በድምጫ የሰማውን ብቻ ይዞ … ያገልግላል።” [3]
ይህን ተንተን አድርገን ብናየው፦
1.      ለድፍን ኢትዮጲያ አንድ ጳጳስ ብቻ ነው ያለው።
2.     ጳጳሱ የሕዝቡን ቋንቋ አያውቅም ፤ ስለዚህም ማስተማርም ሆነ ማስተዳደር አይችልም።
3.     የሚቀመጠው ንጉሡ ባለበት በዋናው ከተማ እንጂ ወደሕዝቡ አይወርድም።
4.     የገጠሩ ሕዝብ ማንም፤ ምንም አስታዋሽ የለውም። ስለዚህ ጳጳሱን ለማግኘት ወደከተማ በብዙ ድካም ይመጣል።
5.     ክህነት ለመቀበል ለጳጳሱ የሚሰጥ ክፍያ አለው። ጳጳሱም በመቀበል ክህነትን ይሰጣል።
6.    የተካነውም ዲያቆንም ሆነ ቄስ ትምህርት ሳይማር ክህነት ይሰጠዋል። ከዚያም በስማ በለው ሲያገለግል ይኖራል።
     ይህ በግብጻውያን ጳጳሳት ዘመን የነበረውን “ትንሽ” ችግር ይዘን ወደ ዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ብንመለስ፥ ያው ችግር አድጎ፤ ሰፍቶ፤ ሥር ሰዶ ተንዠርግጎ በእጅ አዙር ይታያል።
  የሰው ኃይል ሳያጥር ኹለት ሀገረ ስብከት ዛሬም በአንድ ሊቀ ጳጳስ ሲመራ ከማየታችን ባሻገር አመዳደቡ እንኳ ፍጹም የሚያሳዝን ነው። የማይገናኙ ሀገረ ስብከቶችን ለአንድ ሊቀ ጳጳስ ሲሰጡ እናያለን።
·        ሁሉም ማለት ይቻላል ሊቃነ ጳጳሳቶቻችን የሚችሉት መደበኛ ቋንቋ አማርኛ ነው። አልፎ አልፎ ደግሞ ትግርኛና ኦሮሚኛ። ከሰማንያ በላይ ቋንቋ በሚነገርባት ኢትዮጵያችን ውስጥ በሌሎች ሕዝቦች ቋንቋ የሚናገሩ ጳጳሳት ማየት እጅግ ብርቃችን ነው። በቅርቡ ኦሮሚኛ ተናጋሪዎች ጳጳሳት ያየን ቢኾንም ግና አኹንም ያልተነካ ነው። ይህን ስለብሔርተኝነት አንልም፤ ቅዱሳን ሐዋርያት በኹሉም ዓለም የሚነገረው ቋንቋ ለወንጌል አገልግሎት ከመንፈስ ቅዱስ የተነሳ ተገልጦላቸዋል (ሐዋ. 2፥6)። ዛሬ ለአንድ ጳጳስ ወይም የወንጌል ሰባኪ በአለም ላይ ያለው ቋንቋ ይገለጥ አንልም ወይም ብለን አንጸልይም። ምክንያቱም በኹሉም አለም ባሉ አገራትና ብሔራት ቋንቋ ተናጋሪ አማኝ ክርስቲያኖች አሉና። ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ሆና በውስጧ ግን ብዙ ብልቶች አላትና ጸጋ ተጠቅልሎ ለአንድ ሰው የሚሰጥበት ሁኔታ የለም።
     መንፈስ ቅዱስ ለአንድ ሐዋርያ ከሰባ ቋንቋ በላይ የገለጠበት ምክንያቱ ክርስትና ገና ያልተሰበከና የአስተምህሮ መሠረቱ ያልተጣለበት ዘመን ስለነበር፥ ሐዋርያት መሠረቱን ሊያንጹ (ኤፌ. 2፥20) ወደ ኹሉም አገሮች በመንፈስ ቅዱስ ጉልበት ሄደዋል። ዛሬ የኢትዮጲያ ቤተ ክርስቲያን በአለም ላይ ካሉ አብዛኛዎቹ ቋንቋዎችን ተናጋሪ አማኞች አላት፤ በቋንቋቸውና በባህላቸው የሚያስተምራቸው፣ የሚያጠምቃቸውና ደቀ መዝሙር የሚያደርጋቸው አገልጋይና አባት ግድ ያስፈልጋቸዋልና ቤተ ክርስቲያን አብዝታ ልታስብለት ትችላለች።
·        ጳጳሳቱ ዛሬም የሚኖሩት በ“ሀገረ ገዢው” ከተማ ውስጥ ነው። ከእነርሱ ያዩ ሰባኪዎችና ዘማሪዎቹም ጉባኤ በደመቀበት ከተማ እንጂ ወደ ገጠር መሄድና ማገልገል አይመቻቸውም። ከማን ይኾን የተማሩት? “እርሱም መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ … ” (ሐዋ. 10፥38) ከተባለው ከኢየሱስ ነውን? … ወይስ ስለወንጌል “… ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ። ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፤ … በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፥ በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም፥ በብርድና በራቁትነት ነበርሁ።” (2ቆሮ. 11፥25-27) ካለው የተወደደ ሐዋርያ ነውን? ከማን ይኾን የተማሩት?
   ታዲያ የገጠሩ ሕዝብ በጥንቈላና በሌላ ነገር ቢያዝ ምን ይደንቃል? እኛ ያልራራንለት ሕዝብ ጠላት ሰይጣን ቢጨክንበት ምን ይደንቃል? አዎ! ተበትኖ ሳለ ላልራራንለት፤ ግራና ቀኙን ያልለየውን ሕዝብ ነፍስ ደም፥ እግዚአብሔር ከእኛ ይፈልጋል።
·        እንዲሁ አገልግሎት ከገጠር ብዙ ኪሎሜትሮችን አቋርጦ የሚመጣ ሕዝብ ዛሬም ቁጥሩ ትንሽ አይደለም። የገጠር አብያተ ክርስቲያናት አገልጋይ አጥተው መዘጋት ከጀመሩ ቆይተዋል፤ ስለዚህም በገጠሩ ያሉት ሕዝቦች ወይ ወደ እስልምና ወይ ደግሞ ሃይማኖት የለሽ ከመሆን የሚተርፉት ጨክነው አገልግሎት ወዳለበት ከተማ መምጣት ከቻሉ ብቻ ነው።
·        ዓይኖቻችን አይተው አብዝተው ከተጠየፉት ነገር አንዱ ክህነትና የቤ ክህነት የሥራ ዝውውር በገንዘብ መሆኑ ነው። ይኸው ከእነዚያ ባዕዳን ግብጻውያን በምን ነው የምንለየው? እነርሱም ይዘርፉ ነበር፤ እኛም ይኸው ከመዝረፍ ማን ከልክሎን? የክፋትን ውርስ ወራሽ ከእኛ በቀር ማን አለ?
·        ወንጌልን በወንጌል ዓውድና በወንጌላዊ ባህርይ ሳይሆን፥ በስማ በለው የሚሰብከው ቁጥሩ ስንት ይሆን? እውነቱን ብናወራ ወንጌል ዛሬ በየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚሸቀጠውንና በስማ በለው የሚሰበከውን ያህል በሌላ ጊዜ አልሆነም ብል ግነት ያለበት አይመስለኝም።
     እንኪያስ፥  እኛ ከእነዚያ በምን ይሆን የምንለየው? ቤተ ክርስቲያን ከባዕዳን አስተዳደር ተገላገለች እንጂ ከግፈኞች፣ ለሕዝብ ምንም ከማይገዳቸው፣ ከሙሰኞች፣ ከአመንዝሮችና በአለማዊነት ከሚቀማጠሉት መሪዎች ገና መች ተላቀቀች? አምልኮው ሲጠነዛ፣ አስተዳደሩ እንደ መርገም ጨርቅ ክብሩን ሲያጣ፣ በሥነ ምግባር ብልሹነት ከልጅ እስከ አዛውንቱ እኩል ሲወድቁ፣ አገልግሎት ንግድ፣ መዝሙርና ስብከት ችርቻሮ ሲሆን ምን አሉ ይሆን “የእኛ ተወላጅ” ሊቃነ ጳጳሳትና ጳጳሳት? ኤጲስ ቆጶሳትና ቆሞሳትስ ቢሆኑ የት ያሉት? የነገረ መለኮት ተማሪዎችም ብንሆን ትልቅ ሥራ ከእናንተ ብዙ ይጠበቅ ነበር … እናንተስ የት ነው ያላችሁት? ዲያቆናቱስ የት ነው ያለነው? በእውኑ ይህ ሕዝብ እንዲህ እንደጎበጠ ፤ ቀና ሳይል ይኖር ዘንድ መልካም ነውን?
ይቀጥላል


[1] ፍትሐ ነገስት.አን.፬ ቁ.፶፤ ገጽ 30
[2]አባ ጎርጎርዮስ (M.A)፤ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ፤ 1991 ዓ.ም 3 ዕትም፤ አዲስ አበባ፤ ትንሳኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት፤ ገጽ 34-35
[3]ዝኒ ከማኹ ገጽ 75

No comments:

Post a Comment