Tuesday 22 January 2019

“ከ“መጋቢ”ው የተሻለ መናፍቅ፣ በዚህ ዘመን ይገኝ ይኾንን?”


Please read in PDF

   “ … መጽሐፍ ቅዱስ ማኑዋል አይኾንም ወይ? መጽሐፍ ቅዱስ እኮ፣ የኃጢአታችን ውጤት እንጂ የጽድቃችን ውጤት አይደለም፣ አርፈን ገነት ብንቀመጥ አንድ ሺህ ገጽ መጽሐፍ አይጫንብንም ነበር፣ አዳምና ሔዋን ተንቀዥቅዠው ከገነት ከወጡ በኋላ ነው፣ አንድ ሺህ ገጽ ጉዳችንን የሚዘረዝር ኀጢአት ተዘርዝሮ፤ እርሱማ የጉዳችን ማኑዋል ነው፣ ጠባያችንን አይገልጥም፤ ለዚህ ነው እኔ የኀጢአት ውጤት ነው፣ በነገራችን ላይ ብሉይ ኪዳንም ኾነ አዲስ ኪዳን፣ ቁርአንም ኾኑ ሌሎቹም መጻሕፍት በጠቅላላ ከገነት ከተባረርን በኋላ ለስደተኛ የተጻፉ መጻሕፍት ናቸው፤ ስደተኛውን ለማረጋጋት የተጻፉ መጻሕፍት ናቸው እንጂ፣ ማኑዋልማ ሊኾን አይችልም፤ በግል ልታወራኝ ትችላለህ፣ እኔ የገባኝ ይህ ነው፤”(ጫጫታና ሳቅ፣ ጭብጨባ ከሕዝቡ)

   “መጋቢ” [አ]ዲስ ይህን ንግግር የተናገሩት፣ ዶክተር ምሕረት ደበበ በሚያዘጋጀው፣ “mindset” እየተባለ በሚጠራ መደበኛ ፕርግራም ላይ፣ “ህሊናና ስብዕና” በሚል ርእስ ተዘጋጅቶ በነበረው የውይይት መድረክ  ነው። በውይይቱ ላይ ማናቸውም ሰው መሳተፍ እንደሚችልና “አእምሮን ለመገንባት” በሚል “ዒላማም”፣ የተለያዩ ዝግጅቶች ጭምር እንደሚቀርቡበት ይታመናል። ለዚህም ይመስላል የተለያየ ግንዛቤና ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች በፕሮግራሙ ላይ በመጋበዝ ሃሳብ ይሰነዝራሉ፣ የውይይት መነሻ ሃሳቦችን ያቀርባሉ፣ ጥናቶችን ያስደምጣሉ፣ ውይይቶች ይደረጋሉ። ከሚቀርቡት ሰዎች መካከል ደግሞ መጋቢ” አዲስ አንዱ ናቸው።

   “መጋቢ” አዲስ ያሻቸውን ለማውራት እንዲመቻቸው “እንደ ስድስት ኪሎ አንበሳ ታጥሮ መኖር አልፈልግም” ይላሉ፤ እንግዲህ ሰውየው “ዐውድ” የሚባል ነገር አይወዱም ማለት ነው፤ ዐውድ አለመጠበቅ ደግሞ ቅጥር እንደሌላት ከተማ፣ እንደ ፈለግን ገብተን እንደ ፈለግን ልንወጣ የምንችልበት “መብት” ይሰጠናል፣ ከዚያም ባለፈ አንድ ፍሬ ነገር ያለው ጭብጥ መናገር አንችልም ማለት ነው። “ዐውድ ንጉሥ ነው” በሚባልበት የነገረ መለኮት ዓለም፣ በተቃራኒው “ዐውድ” አይመቸኝም የሚል “የቤተ ክርስቲያን መምህር” መገኘቱ ሳይደንቅ አይቀርም። መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስተምር ሰው ያለዐውድ ማሰብ እንደማይችል ገና የተረዱም አይመስሉም።
   “መጋቢ”ው ከተናገሩት ንግግር የምናስተውለው አንድ እውነት፣ መጽሐፍ ቅዱስንና ጠባያቱን ፈጽመው ሲሽሩና ሲክዱ ነው። ስለመጽሐፍ ቅዱስ ምን አሉ? ቢያንስ ኹለት መሠረታዊ ነገሮችን ሲክዱ እንመለከታለን፤ ይኸውም፦
1.      መጽሐፍ ቅዱስ የሕይወት ማኑዋል(መመሪያ) አይደለም፣
2.      ብሉይ ኪዳንም ኾነ አዲስ ኪዳን፣ ቁርአንም ኾኑ ሌሎቹም መጻሕፍት በጠቅላላ ለስደተኛ የተጻፉ መጻሕፍት ናቸው ይላሉ።
    በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕግና ሥርዓት ሳይጨመር ሳይቀነስ በሕይወት ዘመን ኹሉ፣ ሊጠብቁትና ሊታዘዙ እንደሚገባ ጌታ እግዚአብሔር ተናግሯል፤ ከዚያም ባሻገር መጽሐፍ ቅዱስ ለእውነተኛ አማኞች የሕይወት መመሪያነትና ሕይወትነት መሰጠቱን በግልጥ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ በዘዳግም መጽሐፍ ብቻ ደጋግሞ ይናገራል፦
ü  አሁንም፥ እስራኤል ሆይ፥ እንድታደርጉአቸው በሕይወትም እንድትኖሩ፥ የአባቶቻችሁም አምላክ እግዚአብሔር ወደሚሰጣችሁ ምድር ገብታችሁ እንድትወርሱ፥ የማስተምራችሁን ሥርዓትና ፍርድ ስሙ። እኔ ያዘዝኋችሁን የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትጠብቃላችሁ እንጂ ባዘዝኋችሁ ቃል ላይ አትጨምሩም፥ ከእርሱም አታጎድሉም።” (ዘዳግ. 4፥1-2)
ü  “እስራኤል ሆይ፥ አሁንስ አምላክህን እግዚአብሔርን ትፈራ ዘንድ፥ በመንገዱም ሁሉ ትሄድ ዘንድ፥ አምላክህንም እግዚአብሔርን ትወድድ ዘንድ፥ በፍጹምም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ ታመልከው ዘንድ፥ መልካምም እንዲሆንልህ ዛሬ ለአንተ የማዝዘውን የእግዚአብሔርን ትእዛዝና ሥርዓት ትጠብቅ ዘንድ ነው እንጂ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ የሚፈልገው ምንድር ነው? …” (ዘዳግ. 10፥12-13)
ü  “እኔ የማዝዝህን ነገር ሁሉ ታደርገው ዘንድ ጠብቅ፤ ምንም በእርሱ ላይ አትጨምር፥ ከእርሱም ምንም አታጕድል።” (ዘዳግ. 12፥32)
   መጽሐፍ ቅዱስ በማናቸውም የሕይወት ዘይቤ ለሚኖሩም ኾነ፣ ለመንፈሳዊ ተግባራቸው የሚመሩበት መመሪያ፣ ከመንፈስ ቅዱስ የኾነና በቅዱሳን ሰዎች በኩል የተሰጠ ቅዱስ ቃል ነው፤ (2ጴጥ. 1፥20-21)። ምክንያቱም ሰው በኃጢአት ከወደቀ በኋላ ዝንባሌው ኹሉ በኃጢአት የተበከለ ኾነ፣ ለዚህም ጌታ እግዚአብሔር ሰዎች በፊቱ በመልካምነት ይመላለስ ዘንድ፣ “ … እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው። በእጅህም ምልክት አድርገህ እሰረው፤ በዓይኖችህም መካከል እንደክታብ ይሁንልህ። በቤትህም መቃኖች በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው።” (ዘዳግ. 6፥6-9፤ ምሳ. 6፥21) በማለት በግልጥ የተናገረው፤ ነገር ግን ከመመሪያ ባለፈ የሕይወት ቃል ባይኾን ኖሮ፣ ቅዱስ ቃሉ እንዲህ ሊነገር ይችላልን?!
   ጌታችን ኢየሱስም ሲናገር እንዲህ አለ፤ “እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ቃሌን የሚሰማ የላከኝንም የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው፥ ከሞትም ወደ ሕይወት ተሻገረ እንጂ ወደ ፍርድ አይመጣም።” (ዮሐ. 5፥24) ቅዱስ ቃሉ መመሪያችን ብቻ ያይደለ፣ ሕይወታችንም ጭምር ነው። ቅዱስ ቃሉ የዘለዓለም ሕይወት ለማግኘት አለኝታችን ነው። ጌታችን ኢየሱስ አይሁድን የጠየቀውን ጥያቄ መልሰን “መጋቢው”ን እንጠይቃቸዋለን፤ በእርግጥ “መጻሕፍትን ካላመኑ ግን የኢየሱስን ቃሉን እንዴት ያምናሉ?” (ዮሐ. 5፥47)። ጭብጨባና አጉል ሙገሳ ለማግኘት፣ በሰው ፊትም አዋቂ ለመባል የእግዚአብሔርን ቃል ከሕይወትነት አልፎ ከመመሪያነት እንኳ ማውረድ፣ ሥልጣኑን መካድና አለመቀበልም ጭምር ነው።
   መጽሐፍ ቅዱስ በግልጥ ቃል፦ “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።” (2ጢሞ. 3፥16) በማለት መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው ለበጎ ሥራ የሚዘጋጅበት፣ ደግሞም የእግዚአብሔር መንፈስ ስላለበት ለትምህርት፣ ለተግሳጽ፣ ልብን ለማቅናትና ለጽድቅ ምክር እጅግ አስፈላጊውና ዋናው መጽሐፍ እንደኾነ፣ ከመመሪያነትም ያለፈ መጽሐፍ መኾኑን በጽኑ ቃል ይነግረናል፤ እናም “መጋቢ”ው ከመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትና ምሪት መውጣት ከሕይወት መሰናበት መኾኑን ፈጽመው ዘንግተዋል፣ ስተዋልም።
    ኹለተኛውና መጽሐፍ ቅዱስንና ዘላለማዊ ቅድስናውን እንዲሁም፣ ልዩትነቱን ፍጹም በመካድ ይናገራሉ፤ መጽሐፍ ቅዱስ በዓለም ላይ ካሉት የትኞቹም መጻሕፍት ቢኾን ልዩና ተካካይ የሌለው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ ነው ስንል፣ ቅዱስ ነው ማለታችን ነው፤ እግዚአብሔር ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ ሃሳቡን የገለጠበት፣ ፈቃዱን የተናገረበት፣ ራሱን ለእኛ የተረከበት ሌላ መጽሐፍ ፈጽሞ የለውም። የየትኛውም ቤተ እምነት መጽሐፍ፣ የየትኛውም ሰባኪና ነቢይ ቃል፣ ትምህርት፣ ስብከት፣ ተግሳጽ … በመጽሐፍ ቅዱስ ሲዳኝ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ግን በማንም በማን አይዳኝም፤ እርሱ የእግዚአብሔር ቃልና እስትንፋስ ነውና።
  ለዚህ ነው ጌታ ኢየሱስ፣ “እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ።” (ማቴ. 5፥18) በማለት አምላካዊ ቃሉ ምንም ያህል ትንሽና የውጣ ያህል ብትኾንም ሥራን ትሠራለች፤ ከመፈጸምም የሚያግዳት ኃይል እንደሌለ የሚነግረን። ቃሉ በማናቸውም መንገድ ከሌሎች መጻሕፍት ጋር በደባልነት የሚጠቀስ አይደለም፤ ብቻውንና አቻ በማይገኝለት ልዕልና ከፍ ያለ፣ ቅዱስና ልዩ ነውና።
    “መጋቢ”ው በማያምኑና የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን በሕይወታቸው በማይገልጡ ሰዎች መካከል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ አፍረው፣ ተሸማቅቀው፣ በይሉኝታ ተጠፍረው … መጽሐፍ ቅዱስን ከሌሎች መጽሐፍ ተርታ በመመደባቸው፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ቃል በማፈራቸው የሚደርስባቸውን የኩነኔ ድምጽ አላስተዋሉም፤ እንዲህ የሚለውን፦ “በዚህም በዘማዊና በኃጢአተኛ ትውልድ መካከል በእኔና በቃሌ የሚያፍር ሁሉ፥ የሰው ልጅ ደግሞ በአባቱ ክብር ከቅዱሳን መላእክት ጋር በመጣ ጊዜ በእርሱ ያፍርበታል” (ማር. 8፥38)። ጌታ ኢየሱስ ከሚያፍርብን ዓለም ኹሉ ቢያፍርብን እንደሚሻል ማን በነገራቸው?
   “መጋቢ”ውን ደፍሬ እንዲህ ማለት ይቻለኛል፤ በሰዎች ዘንድ ለመወደድ በጌታ ቃል መሸቀጥ አለማዊነት ነው፤ እኖርበታለሁ የሚለውን ቃል እንዲህ ከካደ ለምንስ ጠቅሶ ያስተምረዋል? ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያሉትን “መምህር” ነው፣ የአዲስ ኪዳን መምህር ብላ በኮሌጇ ላይ የሾመቻቸው? ለሕይወታቸው መመሪያነት እንኳ የማይጠቀሙትን መጽሐፍ ቅዱስ፣ እንዴት ለሰዎች ሕይወት ይኾናል ብለውስ ያስተምሩታል? ከዚህ የከፋ ግብዝነትና ዓለማዊነት፣ መናፍቅነትስ ከወዴት አለ? በእውኑ “መጋቢ” የተባሉት መጽሐፍ ቅዱስን እንዲመግቡ አልነበረምን? እንግዲህ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲህ የሚያዋርዱትንና በጠራራ ፀሐይ የሚክዱትን ሰው “መጋቢ” ማለት ሊታፈርበት የሚገባ አይደለምን? የመጽሐፍ ቅዱስና የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትን ልናፈራና አምጠን ልንወልድ ባልቃተትን መጠን እንዲህ አንገት ሰባሪዎችን ማፍራታችን አይቀርልንም፤ መጋቢው መጽሐፍ ቅዱስን ባዋረዱበት ግልጥ አደባባይ፣ መልሰው ንስሐ ገብተው ተጸጽተው ቃላቸውን ይሽሩ ዘንድ ይቻላቸው ይኾንን? መንፈስ ቅዱስ ይርዳቸው፤ አሜን። እኛ ግን መጽሐፍ ቅዱስን እናከብራለን፣ ሕይወትና አለኝታችን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ማለትም የራሱ የአግዚአብሔር ሥልጣን እንደ እናምናለን፤ እንታመናለንም፤ አሜን።

13 comments:

  1. ማነዎት መጀመሪያ ከፃፉት ጽሑፍ ጋር ይታረቁ በርግብ አምሳል ማለት ርግብ መስሎ ታዬ የሚሉት እኮ ነው እርሰዎ ሌላው ደግሞ የትም ሳንሄድ እዚሁ ጽሑፍ ከፅንሰቱ ጀምሮ ፍፁም አምላክ ፍፁም ሰው አሉን እርሰዎ(ባያምኑበትም) ታዳ ምን ጎሎ ነው እሚያዘጋጀው? እሚሾመው(ፍፁም አምላክ ነው ብለውን አልነበር?) አዘጋጁስ ማነው? ነው ፍፁም እና አምላክ እሚሉት ቃላት ትርጉሙ ጭንቅ ነው?

    ReplyDelete
  2. ወንድሜ እግዚአብሔር አብዝቶ ይባርክህ። አንዳንድ ሰዎች ዝና ሲፈልጉ ፍልስፍናና የተሳሳተ አስተምሮ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፣ ተሳስተው ብዙዎችን ባያሳስቱ መልካም ነው። እግዚአብሔር ሁሌም ምሕረቱ ብዙ ነውና ንስሃ ቢገቡ።

    ReplyDelete
  3. አቤነዘር ሰዉ ሊሳሳት ይችላል አንተ ግን የዉኃዉንና የመንፈሱን የደሙን የምስራቹን ወንጌል ብቻ መስክር ሌላዉ ስለማይጠቅም!!!

    ReplyDelete
  4. ወቸ ጉድ እና መፅሀፍ ያስፈለገው እኮ ከሀጥአት በኋላ አይደለምን ደግሞ ሙሉ የተናገሩት እንጂ አታሳጥር

    ReplyDelete
  5. አዎ አዳም ሳይበድል በፊት መጽሐፍ ቅዱስን መመሪያህ ነው ብሎ አልሰጠውም ለሐጥያቱ የተጫነበት ነው

    ReplyDelete
  6. ለዚህ ነው ጌታ ኢየሱስ፣ “እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይና ምድር እስኪያልፍ ድረስ፥ ከሕግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ ከቶ አታልፍም፥ ሁሉ እስኪፈጸም ድረስ።” (ማቴ. 5፥18) በማለት አምላካዊ ቃሉ ምንም ያህል ትንሽና የውጣ ያህል ብትኾንም ሥራን ትሠራለች፤ ከመፈጸምም የሚያግዳት ኃይል እንደሌለ የሚነግረን። ቃሉ በማናቸውም መንገድ ከሌሎች መጻሕፍት ጋር በደባልነት የሚጠቀስ አይደለም፤ ብቻውንና አቻ በማይገኝለት ልዕልና ከፍ ያለ፣ ቅዱስና ልዩ ነውና። Abeni Tebarek

    ReplyDelete
  7. the law before the written law given through Moses =Hige libuna:: this is believable wiz strong truth. this law covered the time from Adam to Moses. it is clear that the canonization of Holly Bible took place 4th century onwards. we are talking the written laws and commandments! i.e after moses. even what you are mentioning is from the book of moses and new testament, . after the fall of Adam, this all is given in written form. do you think the laws and commandments of this much chapters and verses are given to Adam before his fall, even if the commandments are the breath of God!!! is that possible to say what is in the mind and heart of God is fully given to Adam before his fall!?

    ReplyDelete
  8. define 1.breath of God 2. revealation of the words of God to man!

    ReplyDelete
  9. Geta yibarkih wendmachin.

    ReplyDelete
  10. እኛ ግን መጽሐፍ ቅዱስን እናከብራለን፣ ሕይወትና አለኝታችን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ማለትም የራሱ የአግዚአብሔር ሥልጣን እንደ እናምናለን፤ እንታመናለንም፤ አሜን።

    ReplyDelete
  11. አቶ አቤኔዘር ተክሉ በዚህ ዘመን ከአንተ የከፋ መናፍቅና የሉተር ዲቃላ የት ይገኝ ይሆን!??? እግዚአብሔር ልብ ይስጥህ ለንስሐ ሕይወት ያብቃህ።

    ReplyDelete
  12. ስለ እሳቸው እንጂ ስለ ስህተታቸው አንድም ነገር አልተናገርክም።እባክህ ወንድሜ ዝም ብለህ ውዝግብ ከመፍጠርህ በፊት ይሄን ይሄን ብለዋል ብለህ በማስረጃ ወንጅል።ከዚህ ውጪ ግን ወይ ለሐይማኖትቱ ወይ ለእሳቸው ቀና አለመሆንህን ከመግለፅ ውጪ ጥቅም የለውም!!!!

    ReplyDelete