Saturday 5 January 2019

ሕጻኑና እናቱ


Please read in PDF
    የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከቅድስት ድንግል የመወለዱን ነገር ከጻፉልን ወንጌላውያን አንዱ ቅዱስ ማቴዎስ ነው፤ መሲሑ ተናፋቂው ማስያስ፣ በነቢያት ትንቢትና በአበው ምሳሌ የተነገረለትና የዘመናት ናፍቆት የነበረው ሕጻንና ጌታ፣ አባትና ልዑል ምጡቅ ከኾነው ከአባቱ ከሰማይ ወጥቶ ወደ ሰው ልጆች ኹሉ[ወደ እኛ] በመምጣቱ ተገለጠ፤ ቅዱስ ማቴዎስ ይህን እውነታ የመሲሑን ነገረ ልደት ከአይሁድና ከአሕዛብ የትውልድ ሐረግ ቈጥሮ በመምዘዝ፣ በመዘርዘርም መሲሑን ዘላለማዊ ነገር ግን በሥጋ ዕድሜ የተወሰነ ጊዜ ሊቈጠርለት እንዳለው (1ጢሞ. 2፥6) በመንፈስ ቅዱስ ተነድቶ ጻፈልን።  
   ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ስለሕጻኑና እናቱ ሲናገር፣ ሕጻኑን ቀዳሚና አቻ የሌለው በማድረግ ኹል ጊዜ ያቀርበዋል። በምዕራፍ ኹለት ላይ ብቻ ይህን እውነታ በጕልህ መመልከት እንችላለን፤ “ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት”፣ “ሕፃኑንና እናቱንም ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ”፣ “እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና …”፣ “ሕፃኑንና እናቱን ያዘና ወደ እስራኤል አገር ገባ”፣ (ማቴ. 2፥11፣ 13፣ 14፣ 21) በማለት በማናቸውም ስፍራ ላይ ከእናቱ በፊት ሕጻኑን በማስቀደም፣ ፊተኛ በማድረግ፣ በማግነን፣ በማላቅ ያስቀምጠዋል[በእርግጥስ ሕጻኑ ያልላቀ ማን ሊልቅ፣ መሲሑ ያልገነነ ማን ሊገንን፣ ኢየሱስ ፊተኛ ያልኾነ ማን ሊቀድም …?]።

  በሰው አተያይ መቅደም ያለባት እናቱ ናት፤ ነገር ግን በመንፈስ ቅዱስም ኾነ በወንጌላውያን እይታ ኹል ጊዜ ቀዳሚውና ብቸኛው፣ ክብርን ጠቅላዩ በሥጋ ዕድሜ የተቈጠረለት ሕጻኑ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ሕጻኑ “አወጣጡ ከቀድሞ[ከጥንት] ጀምሮ ከዘላለም የኾነ ነውና ማንም የሚቀድመው የለም። ደግሞም ለዘመኑ ጥንት ለዘመኑ ፍጻሜ [ኅልፈት] የለበትምና ከቶ እርሱን ይቀድመው ዘንድ፣ ማንም ከእርሱ በፊት አልነበረም። ድንግል ማርያም ሕጻኑን በሥጋ ወልዳዋለችና የኢየሱስ እናት ተብላ ትጠራለች፤ (ዮሐ. 2፥1፤ 19፥26፤ ሐዋ. 1፥14) ነገር ግን ለሕጻን ኢየሱስ ልጅዋ እርሷ ፍጡሩ እንጂ ቀድማው የነበረች አይደለችም።
   ሕጻኑ ኢየሱስ በሥጋ የተወለደው ከፈጠራትና በእጁ ካበጃጃት ድንግል ማርያም ነው፤ እርሱ የፍጥረት ኹሉ ፈጣሪና አስገኚ ነው፤ በቃሉ ዓለማትንና ፍጡራንን ያስገኘ ሕጻን ግን ጌታና ኤሎሂም፣ የፍጥረት ፈጣሪና ተቈጣጣሪ፣ ፍጥረቱም በኀጢአት በወደቀ ጊዜ ሊፈልገው የመጣ ቅዱስ አምላክ ያህዌ ነው (ዘፍጥ. 3፥10)። ይህ ታላቅና ገናና አምላክ ከፈጠራት እናቱ በገዛ ፈቃዱ፣ ራሱን በማዋረድ የእኛን ሥጋ ለብሶ ተወለደ።
    ወንጌላዊው ማቴዎስ ሕጻኑን በማግነን እናቱን ያስከትላል፤ ሕጻኑን ያልቃል፣ ከፍ ከፍ ያደርጋል፣ አቻ እንደሌለው አጕልቶ ያሳያል፤ ይህንም በወንጌሉ ምዕራፍ ኹለት ላይ ብቻ እንኳ፣ የሕጻኑን ስም ከአሥራ አንድ ጊዜ ሳያሳንስ ደግሞ ደጋግሞ ይጠራዋል። ሕጻኑ የአዲስ ኪዳን ዋነኛና ማዕከል ነው፤ ያለ ሕጻኑ አዲስ ኪዳን ፈጽሞ ሊኖር አይችልም፤ አንዳንድ ሰነፎች፣ “ያለድንግል ማርያም ክርስቶስ፣ ያለ ክርስቶስ ክርስትና የለም” እንደሚሉት አይደለም፤ ሕጻኑ ኹሉን የፈጠረ ኹሉም ደግሞ በሕይወት ይኖር ዘንድ አጋጥሞ፣ ደግፎ የያዘ ነው፤ (ቈላ. 1፥17፤ ዕብ. 1፥3) ።
   ያለ ክርስቶስ ድንግል ማርያም ትኖር ዘንድ አይቻላትም፤ ያለድንግል ማርያም ግን ክርስቶስ ነበረ፣ ኗሪ ነው፤ ይኖራልም። የድንግል ማርያም ክብርና መወደድ ከሕጻኑ የተነሣ እንጂ በራሷ አይደለም። ድንግል ማርያምን ብንወዳት፣ በወንጌል እንደ ተነገረላት ብጽዕት[ምስጉን] ብንላት ከሕጻኑ የተነሣ ነው፤ ክርስትና የቆመውና መሠረቱን የዘረጋው ተቀዳሚ ተከታይ በሌለው አንድያ ሕጻን ኢየሱስ ላይ እንጂ በማናቸውም በፍጡር መተማመኛ ሰነድ ላይ አይደለም።
  በክርስትና ቀዳሚውንና የመጀመርያውን ስፍራ ሊወስድ የሚገባው አንዱ ሕጻን ኢየሱስ ብቻ ነው። ደፍረን ቅንጣት ታህል ሳንጠራጠር ልንናገር የምንችለው እውነት፣ ያለክርስቶስ ክርስትና ፈጽሞ ሊኖር አለ መቻሉን ነው፤ ክርስቶስም ያለማንም ብቻውን ኅልውና ዘላለማዊ፣ ኗሪና “እኔ” ብሎ መናገር የሚቻለው ነው። ለዚህም ሕጻኑና እናቱ በተጠሩበት ቦታ ኹሉ ሕጻኑ ሁል ጊዜ ቀዳሚና የመጀመርያ ነው። በምንም ዐይነት ኹኔታ እናቱ ቀድማ የተጠራችበት ሥፍራም የለም፤ ሊኖርም አይችልም። ሕጻኑ ለዘላለም አልፋ ነውና።
የመንፈስ ቅዱስና የእግዚአብሔር ዋነኛ ዐላማ ሕጻኑ በሰው ልጆች ኹሉ ዘንድ ልቆ፣ ገንኖ፣ ጐልቶ፣ ደምቆ እንዲታይ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ፣ ወልድ ወደ ሰማያት ባረገ ጊዜ ለሰው ልጆች ኹሉ ኢየሱስ የተናገረውን ያስታውሳል፤ ያስተምራል፣ ያከብረዋልም (ዮሐ. 16፥14)፤ እግዚአብሔር አብም ልጁን ለዓለሙ ኹሉ እንዲሁ የሰጠበት ዋነኛ ዓላማው (ዮሐ. 3፥16) ከማንኛቸውምና ከማንኛውም ነገር ይልቅ ሰዎች በአንድያ ልጁ እንዲታመኑና እንዲድኑ ነው። አዎን! ሕጻኑ የመቅደሙና መጀመርያ የመኾኑ ዋና ምክንያት ሰዎች ኹሉ እንዲያዩትና በእርሱ አምነው እንዲቀሩ ነው (ዮሐ. 20፥31)።
   ወንጌላዊው ከእናቱ ይልቅ ሕጻኑን እንድናየው እጅግ ይፈልጋል፤ አንዳንዶች እንዲህ ሲባል፣ ድንግል ማርያም የተገፋች ያህል ይከፋቸዋል፤ ድንግል ማርያም እንኳ ልጅዋ እንጂ እርስዋ መታየትን እንደማትሻና ልጅዋንና ራስዋን ባሰበች ጊዜም፣ ራስዋን እንደ ባርያና ምስኪን መመልከቷን ፈጽመው ይዘነጋለሁ፤ (ሉቃ. 1፥48)። ሕጻኑ በሰማይና በምድር ብቻውን ክብርን ሊቀበል የሚገባው አምላክና መድኀኒት ነው። በመታረዱና በመስቀል ላይ በተቀበለው በሥጋ መከራው ሰዎችን ኹሉ ያዳነና በዚህም በሰማይና በምድር “ይገባሃል” የተባለለት ብቸኛ ልዑል ነው፤ (ራእ. 4፥11፤ 5፥12፤ 7፥10)።
    እናቱ ሕጻኑን ታመልከዋለች፣ ትሰግድለታለችም፣ ትንበረከክለታለች፣ ይገባሃል እያለችም በሰማይና በምድር ከሚያመሰግኑ የበጉ ዘማርያን ጋር ትዘምራለች፤ እንዲሁም ከቅዱሳን ሐዋርያት ጋር በአንድነትም ኾና በትጋት ትጸልያለች፣ (ሐዋ. 1፥14) ታመሰግናለችም፤ ለሕጻኑ ትታዘዛለችም። እናም ሕጻኑ መቼም መች ቀዳሚና ፊተኛ ነው፣ የሚቀድመው የሚመስለውም የለም። ከሕጻኑ ይልቅ ወደ ሌላው እንድንመለከት የሚያደርግ ማናቸውም ትምህርትና መንገድ እርሱ ከሰማይ ወይም ወንጌሉን ካጻፈው ከመንፈስ ቅዱስ አይደለም፤ ሕጻኑ ለዘመን አዝማናት፣ ለዘላለምም ፊተኛና ቀዳሚ፣ ዋና ርእስ ነው፤ ታመኑበት፤ ተማመኑበትም፣ ፈጽሞ ተደገፉት፣ ተዘልላችሁ በሕይወት ትኖሩበታላችሁ።
    ሕጻኑን ኢየሱስን ከማናቸውም ነገር ይልቅ በማላቅና በማግነን ልደቱን ታስቡ ዘንድ በመስቀሉ ርኅራኄ ለመንኳችሁ፤ ጸጋና ሰላም በሕጻኑ ኢየሱስ ይብዛላችሁ፤ አሜን።

3 comments:

  1. ተባረክ ወንድሜ። ፀጋ አሁንም ይብዛልህ።

    ReplyDelete
  2. abeni tebarek tebarek tru iyita naw

    ReplyDelete