Wednesday 9 January 2019

ቤተ ክርስቲያን ተጐታችና ዘመነኛ ችግሮቿን አስተውላ ይኾንን!? (ክፍል 7)


Please read in PDF


1.5.      በፍርድ ቤት መክሰስና መካሰስ
     በታሪክ እስከ አኹን ያልተሰማ እንግዳ ሆኖ እየሰማን ካለው ነገር አንዱ፣ የቤተ ክርስቲያን የገዛ ልጆቿን ዓለማዊ ፍርድ ቤት አቁማ፤ ጠበቃ ቀጥራ የመክሰሷ ጉዳይ ነው። እንዲህ ያለ ነገር በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ተከስቶ እንደ ነበር “… ወንድም ወንድሙን ይከሳል፥ ይህም በማያምኑ ፊት ይደረጋልን? እንግዲህ ፈጽሞ የእርስ በርስ ሙግት እንዳለባችሁ በእናንተ ጉድለት ነው” (1ቆሮ. 6፥6-7) በማለት ሐዋርያው አስቀምጧል።

   በእኛ መካከል ያለው ግን፣ በሐዋርያው ዘመን እንዳሉት በአማኞች መካከል ያለ መካሰስና መወነጃጀል ያይደለ፣ በተደራጀ መዋቅር ውስጥ ያለችው ቤተ ክርስቲያን ጠበቃ አቁማ የገዛ ልጆቿን ትከሳለች፤ ያውም የክሱ ምንጭ፣ “ብዙ አገልግለው” በማገዷ ምክንያት የሠሩበትን ደመወዝ በመከልከሏ ምክንያት ነው። የዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ፣ በአንድ ሀገረ ስብከት በአንድ ዓመት ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ላይ በደመወዝ ክልከላ በተያያዘ የቀረቡ አሥራ አንድ ክሶችን የማየት ዕድል ገጥሞታል። የሚያሳዝነው በሁሉም ክሶች ላይ ቤተ ክርስቲያን እንድትከፍል መወሰኑን ስናይ ደግሞ ምን ያህል ሕግ “የማናከብር” መሆናችንን ያሳብቅብናል።
    ነገር ግን ቅዱስ ጳውሎስ “ብትበደሉ አይሻልምን? ብትታለሉስ አይሻልምን? ነገር ግን እናንተ ትበድላላችሁ ታታልሉማላችሁ፥ ያውም ወንድሞቻችሁን።” (1ቆሮ. 6፥7-8) ያለው ፍጹም መንፈሳዊ ምክር እኛንም ከእንዲህ ያለ ውርደት ብዙ በጠበቀን ነበር። ምናልባት የዚህን መፍትሔ አሳንሰው አስተዳደራዊ መፍትሔ ነው ብለው “መንፈሳዊ ፍርድ ቤቶችን እናቋቅም” የሚሉ ወገኖችን እሰማለሁ፤ ነገር ግን የቤተ ክርስቲያን ትልቁ ድርሻ በጎችን ሁሉ በአንድ መጠበቅና የታላቁ ጌታዋን ቃል ለአለም ሁሉ መናኘት እንጂ ተመርቆ የተከፈተውን አዲሱንና ሕያው የጽድቅን መንገድ ዘግታ፤ አዲስ ችሎት ሰይማ እንድታስሟግት አይደለም።
1.6.            ዝሙት
     መጽሐፍ ቅዱስ የዝሙትን መዘዝ በግልጥ ያስቀምጣል። በሥጋ ከሚያመጣው ደዌና በሽታ ባሻገር በግልጥ ቃል “… አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆን ወይም … አመንዝሮች … የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።” (1ቆሮ. 6፥9-10) በማለትም ይናገራል። ማምለጫውም አንድ መንገድ ብቻ፥ እርሱም መሸሽ ብቻ እንደ ኾነ ታላቁ መጽሐፍ ያስቀምጣል፤ (ዘፍ. 39፥12፤ 1ቆሮ. 6፥18)።
   አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ መዲናይቱ አዲስ አበባ ላይ ባሉት ማሳጅ ቤቶች ላይ፥ አቶ በላይነህ ዘለለውና አቶ ዮሴፍ አህመድ ከማክቤዝ ሚዲያ ኮሚኒኬሽንና ከአዲስ አበባ አስተዳደርና ኤች አይ ቪ መቆጣጠርያና መከላከያ ማስተባበርያ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር ባቀረቡት አንድ ጥናት፣ በአገራችን ያለው የዝሙት መንፈስ እጅግ አስፈሪ ከመኾኑም ባሻገር ለፍርድ እየሰባን መሆኑን የሚያሳይ ነው። በተለይ የ“ሴት እንተኛ” መሸታ ቤቶች ወደ ግለሰብ ቪላ ቤቶችና ወደ ማሳጅ ቤቶች መቀየራቸውን ላስተዋለው፣ ድርጊቱ በሕገ ወጥ መንገድ በንግዱ ዓለም ከተሳተፉ ግለሰቦች ያለፈና ሌሎችም እየተቻኮሉ የገቡበት መኾኑን ያሳያል።
   በሌላ አንድ ጥናት ደግሞ “ኢትዮጲያ የወሲብ ቱሪዝም ስበት(ማግኔታዊ መስህብ) ያላት አገር እየኾነች ነው” የሚል ዘገባም ቀርቧል። በዚህም ሆነ በዚያ እጅግ አጸያፊ የዝሙት ነውር በመካከላችን አለ። የዚህ ነውር ተካፋዮች ደግሞ በውጪ ያሉት አለማውያንና አሕዛብ ብቻ ሳይኾኑ “ከትንሽ እስከ ትልቅ የሃይማኖት መሪዎች፣ ሰባኪዎች፣ ዘማሪዎች፣ ዲያቆናት፣ ቀሳውስት፣ መነኮሳት፣ መነኮሳዪያት፣ ቆሞሳት፣ ጳጳሳት፣ ፓስተሮች ፣ መጋቢዎች ፣ የሃገር መሪዎችና ባዕለሥልጣናት … ጭምር” ናቸው።
    ከዚህ ባሻገር በየጊዜው በፍርድ ቤቶች እየበዛ ያለው የጋብቻ ፍቺ አስፈሪ ቁጥር፥ ነገ ትዳር ሊመሰርት በዝግጅት ላይ ላለው ወጣት ያለው አሉታዊ መልእክትም ቀላል አይደለም። ውበት መመለክ ከተጀመረ፣ ዘፋኝ ከበረከተ፣ ሽንጥና ዳሌ እንደ በሬ ሥጋ ረክሶ ለሽያጭ ከተገመተ … በእርግጥ አገር ለመቀጣቷ፤ የመቅሰፍትን ፍርድ በራሷ መጥራቷ ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዋቢ መጥቀስ ይቻላል (ዘፍ. 6፥2፤ 13፤ 2ሳሙ. 11፥2፤ 12፥10፤ ምሳ. 6፥26፤ 32፤ ኤር. 5፥7-9)፤ በሌላ መልኩ ፦
              “ከወደዱም አይቀር መውደድ ነው አቡን
               መስቀል እያሳመ የሚስመውን”፣
              “መታማት ካልቀረ ባንተማ ልታማ
               ከግብጽ የመጣኸው አቡነ ሰላማ”
               “እንጦንስና መቃርስ ምንኛ ተጐዱ
                የልጆቻቸውን ሰርግ ሳያዩ የሔዱ …”
የሚሉትና ሌሎች ሕዝባዊ ሥነ ቃሎች እንዲሁ እንደዋዛ አስፈግገው የሚያልፉ፤ የሚታለፉ አይደሉም። መነሾ ነገራቸው ምን እንደሆነ ያለትርጓሜ ያሳብቃልና። ይህንንም ዝሙት ግን ከግብጻውያን አቡኖች (እንደ አምልኮው ሥርዓት) ተዋርሶን ነው ለማለት ካላፈርን በቀር (ኢትዮጲያ ዛሬም ቅድስትና ምንም ነውር የለባትም የሚሉ ጥቂት አይደሉምና) መጠሪያችን ሊኾን አንድ ሐሙስ የቀረው ነው። እንደ መፍትሔ፦
1.6.1.   ጳጳስ ሚስት ቢኖረው ወይም በምሳሌነት ሚስት ያላቸውም ቢሾሙ፣
    መጽሐፍ ቅዱስ ከኤጲስ ቆጶስ ዋና ዋና ባህርያት አድርጎ ካስቀመጣቸው መስፈርቶች በተደጋጋሚ የጠቀሰው “የማይነቀፍና የአንዲት ሚስት ባል የሚሆን” የሚለውን ነው (1ጢሞ. 3፥2 ፤ ቲቶ. 1፥6[1])፣ ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስም የስድስተኛውን ጉባኤ ቀኖና አንቀጽ 12 በመጥቀስ “ኤጲስ ቆጶሳት ለመኾን መብት ያላቸው ግን በድንግልና የመነኮሱ የቅስናና የቁምስና ማዕረግ ያላቸው ናቸው” በማለት አስፍረዋል።[2] መጽሐፍ ቅዱስና የቤተ ክርስቲያናችን ፍትሐ ነገሥት አንዲት ሚስት ያለው ቢልም፣ ይህ መስፈርት ኾን ተብሎ ሲዘለል ያየንበት ጊዜም ደግሞ አለ።[3]
    መጽሐፍ ቅዱስ አንድን ኤጲስ ቆጶስ “የአንዲት ሚስት ባል የሚሆን” ካለ ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት መታዘዝ አጅግ የሚበልጥና መንፈሳዊ ብልኅነት ነው። ጥቂት ያይደሉ ጳጳሳት የመነቀፋቸውና በነውር የመያዛቸው ምክንያት ለዚሁ ቃል ካለመታዘዝ ጋር የሚያያዝ ነው። መጽሐፍ እንደሚል፣ “… ነገር ግን ስለ ዝሙት ጠንቅ ለእያንዳንዱ ለራሱ ሚስት ትኑረው ለእያንዳንዲቱ ደግሞ ለራስዋ ባል ይኑራት” (1ቆሮ. 7፥2) የሚለው ቃል መላውን አማኝ ክርስቲያን የሚመለከት ነው።
    ቤተ ክርስቲያን መነኮሳትን ብቻ በመሾም ሳይኾን የአንዲት ሚስት ባል የሚሆኑት፤ ቤተ ሰቦቻቸውንም በአግባቡ የሚያስተዳድሩትን ቅዱሳን ቀሳውስትም በመሾም “የአገልግሎቱን ቅድስና” ልትጠብቅ ይገባታል።

1.6.2.  ምንኩስና ከቅዱስ ጋብቻ በምንም እንደማይበልጥ ትምህርት ቢሰጥ፣

     ያለምንም ማስተባበያ በአብዛኛው ሰው ኅሊና “በትዳር ተሳስረው በዚህ ዓለም ከሚኖሩት ሰዎች ይልቅ በብህትውና ወይም በምናኔ ወይም በምንኩስና ተወስነው የሚኖሩ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር የመቅረብ ወይም ቅዱሳን መሆን እንደሚቻላቸው“ ያምናሉ።  እውነት ነው ከአገልግሎት አንጻር ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው፣ “ … ሰው ሁሉ እንደ እኔ ሊሆን እወዳለሁና … ሰው እንዲህ ሆኖ ቢኖር መልካም ነው። ነገር ግን ያለ አሳብ ልትኖሩ እወዳለሁ። ያላገባው ጌታን እንዴት ደስ እንዲያሰኘው የጌታን ነገር ያስባል፤ ያገባው ግን ሚስቱን እንዴት ደስ እንዲያሰኛት የዓለምን ነገር ያስባል፥ ልቡም ተከፍሎአል።” (1ቆሮ. 7፥7፤ 26፤ 32-33) እንዳለው እግዚአብሔርን የዘመናቸው ጌታ አድርገው ዕድሜያቸውን ሳይከፍሉ ለጌታ ብቻ መሥዋዕት አድርገው የሚያቀርቡ ከባዕለ ትዳሮች ይልቅ የተሻለ የአገልግሎት በር አላቸው።
   ይህን ብቻ ይዞ ግን መንኩሶ ፣ መንኖ ፣ በህትዎ … መኖርን ከቅዱስ ጋብቻ አብልጦ ማቅረብ  የተሳሳተ መንገድ ነው። ለሰው ሁሉ የተሰጠው የብርታትና የመተባበር መንገድ ቅዱስ ጋብቻ ነው (ዘፍ. 2፥18፤ መክ. 4፥12፤ ማቴ. 19፥5፤ 1ቆሮ. 7፥2)፤ ያለጋብቻም ሆነ በጋብቻ ጸንቶ መኖርን “ … ሳይናወጥ በልቡ የጸና ግን ግድ የለበትም፥ የወደደውን እንዲያደርግ ተፈቅዶለታል፤ ድንግልናውንም በልቡ ይጠብቅ ዘንድ ቢጸና፥ መልካም አደረገ። እንዲሁም ድንግልን ያገባ መልካም አደረገ ያላገባም የተሻለ አደረገ።” በማለት አስቀምጦታል (1ቆሮ. 7፥37-38)። ስለዚህም በድንግልና መኖር ከጋብቻ በምንም የሚበልጥ ነገር የለውም። ይህንን ማበላለጣችን ጵጵስናን ከድንግልና መኖር ጋር ብቻ አያይዘነው ጋብቻን አሳንሰነዋል። ይህ ግን በፍጹም ሊሆን አይገባውም ነበር።

1.6.3.  ወጣቶችን የሚመለከት ሥራ በሠፊው ቤተ ክርስቲያን ብትሠራ፣

   የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማህበር ሰኔ 16 2004 ዓ.ም በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ባዘጋጀው ሲምፖዚየም ላይ “የአብያተ ክርስቲያናት ትብብር ለሰላምና ለልማት” ሲል ባዘጋጀው አንድ መጽሔት በገጽ 53 ላይ የግሎባላይዜሽንን አሉታዊ ተጽዕኖዎች ሲያስቀምጥ፦
“ሀ. ዓለማዊነትን (securalism) ያስፋፋል ፤
ለ. በመጽሐፍ ቅዱስ ኅጢአት ለመኾናቸው የተረጋገጡ ተግባራትን እንደ መብት ሊሰብክ ይችላል።” ወዘተርፈ በማለት ያስቀምጣል።
     እ.ኤ.አ. በ2007 የተደረገው የሕዝብ ቈጠራ እንደሚያሳየው በኢትዮጲያ ውስጥ 63.2 ከመቶውን የሚሸፍኑት ከ24 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶችና ሕጻናት እንደ ኾኑ ያሳያል። ይህ ማለት በአገሪቱ በአብዛኛው “በሸመገለ ጊዜ ከእርሷ ፈቀቅ እንዳይል፥ በሚሄድበት መንገድ የሚመራው አባትና መሪ” (ምሳ. 22፥6) አብዝቶ ያስፈልጋል ማለት ነው። ምክንያቱም “በኃያል እጅ እንዳሉ ፍላጾች፥ የጐልማስነት ልጆች እንዲሁ ናቸው …  ና” (መዝ. 127፥3) በአግባቡ ሊገሩ፤ ሊመሩ ይገባቸዋል። በኃያል እጅ ያሉ ፍላጾች ኢላማ የማይስቱት ገታሪው በአገባቡ ስለሚገትረው ነው። ልጆችም ኢላማቸውን እንዳይስቱ ቤተ ክርስቲያን በምክርና በተግሳጽ ትውልድን የመንከባከብ አደራ ተረክባለችና (ኤፌ. 6፥4) የአንበሳውን ድርሻ ከማህበረሰቡ በሚበዛ መልኩ በመያዝ ይህን ልታደርገው ይገባታል።
    ከዚህ አንጻር ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች ላይ እየሠራች ያለው፥ እየደረሰ ካለው ጥፋት ጋር ሲመዛዘን ተካካይ ነው ብሎ አፍ መልቶ ለመናገር አያስደፍርም።  በየአጥቢያውና አድባራቱ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ቢኖሩም የተሰጣቸው ትኵረት እምብዛም ነው፤ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በአመራርነት በአብዛኛው የያዩዙት ሞገደኞችና ስሜታውያን ከመሆናቸውም ባሻገር የቤተ ክርስቲያኒቱ “ሙሉ ዕውቀት” የሌላቸው ናቸው። እጅግ የሚያስፈራውና የሚጨንቀው ነገር ደግሞ በአንድ ሰንበት ትምህርት ቤት ላይ ለዘመናት የአመራር ሥልጣንን ተቆናጠው፥ አዲስ ተማሪዎች ሲመጡ የራሳቸውን ዶግማና ቀኖና የሚያስጠኑ ደፋሮችም መኖራቸውን ስናስብ በእርግጥም ቤተ ክርስቲያን ወጣቶችን አብዝታ ችላ ማለቷን እናስተውላለን። በተጨማሪም “ዘመናዊነትንና መንፈሳዊነትን”  ከማደባለቅ አልፎ “እንደ ኅጢአት ሲቈጠሩ በግልጽ ያየናቸው ተግባሮች (ለምሳሌ፦ ዝሙት፣ ዘፈን፣ መዳራት፣ ርኩሰት፣ የዝሙት ፊልሞችን ማየት፣ አድመኝነት …) በአንዳንድ ሰንበት ትምህርት ቤቶችና ወጣቶች ዘንድ መታየቱን ልብ ይሏል!!!
     የእግዚአብሔር ቃል በሚሰበክበት ጉባኤ ላይ ተቀምጦ ቃሉን እየሰማ፣ ቅዳሴ ቆሞ እያስቀደሰ፤ ፌስ ቡክ፣ ጐጉል የሚጐለጉል ወጣት እየበዛ፤ ሥርዓተ አምልኮ መስመሩን ሲስት እያየን ነው። ቴክኖሎጂንና መንፈሳዊነትን አለማስታረቅ፤ ለዚህም የሚጠቅማቸውን ትምህርትና ከዝሙት እንዴት መሸሽ እንዳለባቸው ያለውን የሥነ ጾታ ትምህርት መንፈሳዊ ለዛውን ጠብቆ በግልጥ የሚሰጥበትን መንገድ ማደላደል እጅግ ሊታሰብበት የሚገባ ነገር ነው።  ይህ ግን አለመሥራቱ ብቻ ሳይኾን አለመታሰቡ ለምን? የሚል ጥያቄ ያጭራል።

1.6.4.  ሕገ ወጥ ደላሎችንና ነጋዴዎችን ቤተ ክርስቲያን በግልጥ መቃወም አለባት፣

   ትላንት ቤትና መኪና ለመሸጥ በድለላ ሥራ የተሰማሩ አብዛኛዎቹ ሰዎችና እጅግ በጣም አዳዲስ ደላሎች፥ ዛሬ የተሰማሩት በትምህርት ገበታ ላይ የተሰማሩትንና በየቤቱ ያሉትን ጨቅላ ወጣቶችንና ሕጻናትን ኅሊና ለሌላቸው ባዕለጠጎችና ባዕለ ሥልጣናት የሚደልሉ መኾናቸውን፤ ይህም ድርጊት ከዕለት ዕለት እየጨመረ እንጂ ምንም አለመቀነሱን እያስተዋልን ነው።
   ቤተ ክርስቲያን የማኅበረሰቡ አንዱ ገጽታ ናት፤ ማህበረሰቡ በሚጎዳበት በአንዱ ይሁን በብዙ ነገር እርሷም የችግሩ ተጎጂ፤ ተጋሪም ናትና ይህን ከባድ አደጋ ከማስወገድ አንጻር የእርሷም ድርሻ ጉልህ ነው። በሞቴላቸውና በሆቴላቸው ሕጻናትንና ወጣቶችን ለዝሙትና ለግብረ ሰዶም የሚያከማቹ፤ ሃብትን የሚያጋብሱ ነጋዴዎችና ደላሎች፥ በአንድም ይኹን በሌላም መንገድ ከቤተ ክርስቲያን ጋር የመገናኘት ዕድላቸው ሰፊ ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ግን እነዚህን ሰዎች በጉያዋ ባለመምከር፤ ባለመገሰጽ፣ ባለመቆጣት ዝም ብላ ተሸክማ የምትኖርበት አቅምም ሆነ ትዕግስት ፈጽሞ ሊኖራት አይገባም።
    እኒህ ሰዎች የሚያበላሹትና የሚመርዙት ግለሰቦችን ሳይሆን ትውልድን ነው። የትላንቱ “የውቤ በረሃ ትውልድ” ይነስም ይብዛም አሁን ባለው ትውልድ ላይ ያስቀመጠው የዝሙትና የስድነት ሕይወት እንዲሁ በቀላል የሚታለፍ አይደለም። የዚያ አሻራ ሳያገግም ሌላ ረመጥና እሳት በትውልዱ ላይ የሚጨምሩትን ግን በዝምታ ማለፍ ለቤተ ክርስቲያን “በእንቅርት ላይ … ” እንደሚባለው ጉዞዋን ጨለማና ከድጥ ወደማጥ ያደርግባታል።



[1]  ፍትሐ ነገሥት አን. 5 ቁጥር 83፤ 89
[2] ብጹዕ አቡነ ጎርጎርዮስ፤ ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን፤ 1993 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አሳታሚ ማህበረ ቅዱሳን፤ ገጽ 57
[3] ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ፤ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን፤ 1993 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፤ አሳታሚ ማኅበረ ቅዱሳን፤ ገጽ 113፤ እና ሐመር፤ ፲፫ዓመት ቁጥር ፭፤ መስከረም/ ጥቅምት ፲፱፻፺፰ ዓ.ም፤ ገጽ ፳፮

2 comments:

  1. papas mist binorew?

    ReplyDelete
  2. defar neh betaam. ante betekiristiyanachinn atawktm

    ReplyDelete