Tuesday 15 January 2019

ቤተ ክርስቲያን ተጐታችና ዘመነኛ ችግሮቿን አስተውላ ይኾንን!? (ክፍል 8)

Please read in PDF
1.7.   እንደ ወንጌሉ ታላቅ መርሖ አለመኖር
1.7.1.   መርሖ አንድ፦ “ሂዱ”
       ከወንጌል ትውፊትና ዋና መርሖ አንዱ ሂዱ የሚለው ነው። የቤተ ክርስቲያን የዕድሜ ልክ ታላቁ ተልዕኮዋም “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ …” (ማቴ. 28፥19) የሚለው ነው። ቤተ ክርስቲያን ተዘልላ ተቀምጣ የሚመጡትን ብቻ መጠበቅ የለባትም። ውኃ በአንድ ቦታ ሲቀመጥ ይሸታል፤ አማኞችም አንድ ቦታ ሰፍረው እንዲቀመጡ አልተባለላቸውም። እንደ ዘር እንዲበተኑና እየዞሩ ወንጌሉን እንዲሰብኩ እንጂ  (ሉቃ. 10፥1፤ ሐዋ. 8፥4 ፤ 13፥1-4)።

   ቤተ ክርስቲያን ሐዋርያት በትምህርታቸው የገለጡትን የክርስቶስን የማዳን እውነትና የገለጡትን አዲስ ኪዳን መሠረት አድርጋ በዓለም ሁሉ በመሔድ ወንጌልን መናገር ይገባታል። በእርግጥም የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአፍሪካ ወንድሞችና እህቶቿ ከተወቀሰችው አንዱ ነገር፥ ይህን የታላቁን ጌታ ታላቅ ተልዕኮ ይዛ ጎረቤቷ ያሉትን አፍሪካዊ ወንድሞችና እህቶቿን እንኳ እንደታዘዘችው ሄዳ ማገልግል ሳትችል ቀርታ ምዕራባውያን ከሩቅ አህጉር መጥተው ሰብከው እንደ ወሰዷቸው በቁጭት ሲናገሩ ተሰምቷል (እንዴት ልብ የሚነካ ቁጭት ነው!!!)፤ እንኳን በሩቅ ላሉት በቅርባችን ላሉት መድረስ አለመቻላችን እንዴት ያለ ከባድ ድንዛዜ ያዘን የሚያስብል የቁጭት ጥያቄ ያጭራል (በእርግጥ ዛሬም አልመሸም። ለአፍሪካ ስደት፣ ዘረኝነት፣ ጦርነት፣ እርስ በእርስ አለመተያየት፣ ሙስና  … መፍትሔ ለማምጣትና ለማሳየትና እንዲጠቀሙበት እንደጌታ በጸሎት ማሰብና ፍሬውን ማየት … አዎን! አልመሸም። ቤተ ክርስቲያን ሆይ! ተነሺና ሂጂ!!!)
   ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን ያዘዘው ለእርሱ ደቀ መዛሙርትን እንድታፈራ ነው። ይህም ማለት ቤተ ክርስቲያን የአባላትን ቁጥር በማብዛት ላይ ብዙ መሥራት አለባት ሳይሆን የዚህንዓለም ክፉ ኃጢአትና ርኩሰት ተጠይፈው የተለዩ፥ ከበጎ ነገር ጋር የሚተባበሩትን (ሮሜ 12፥9)፤ “የጨለማውን ሥራ አውጥተው የብርሃንን ጋሻ ጦር የለበሱትን” (ሮሜ 13፥12)፤ “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ የማይጠመዱትን” (2ቆሮ. 6፥14)፤ “በክርስቶስ ፍርሃት የሚገዙትን” (ኤፌ. 5፥21)፤ “ከማናቸውም ዓይነት ክፉ ነገር የሚርቁትን” (1ተሰ. 5፥22)፤ “በእውነት ቃሉ የሚኖሩትን” (ዮሐ. 8፥31) ደቀ መዛሙርትን ማፍራት ይገባታል ማለት ነው። ለዚህ ማስፈጸሚያው ዋናው መርሖ ደግሞ ሂጂ ተብላለችና ፈጽሞ መቀመጥ አይገባትም።
1.7.2.  መርሖ ሁለት፦ “ወንድማማች ነን”
   ለመመካከርም፣ ለመወቃቀስም፣ ለመገሳሰጽም፣ ለመቆጣጣትም … ድፍረት የሚሆነን ወንድማማችነት ነው። በክርስቶስ መንግሥት “አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው” እንጂ መለያየት፣ መበላለጥ፣ አንዱ ሎሌ ሌላው ጌታ፣ አንዱ ምንዝር ሌላው አለቃ፣ አንዱ ትንሽ ሌላው ትልቅ፣ አንዱ ታዛዥ ሌላው በበላይነት አዛዥ የሚሆንበት የሥልጣንና የሹመት ተዋረድ ሳይሆን የተጠራነው በወንድማማችነት እንድንዋደድ (ሮሜ 12፥9)፤ በወንድማማችነት እንድናገለግል (ማቴ. 23፥8)፤ በብዙ ወንድሞች መካከል በኵር ሆኖ እንደ ተመላለሰው ጌታ (ሮሜ 8፥29) በትሁት መንፈስ እኛም ልንመላለስ ይገባናል።
   ዛሬ ታላላቅ እንደሆኑ የሚያስቡትን ወይም የሚመስሉትን (ገላ. 2፥6፤ 9) ባጠፉና በስህተት በተያዙ ጊዜ እንደጳውሎስ በግልጥ መቃወም ያልተቻለን (ገላ. 2፥11) በእርግጥም የአለቅነትና የአዛዥነት ሠንሠለት በመካከላችን ተዘርግቶ የወንድማማችነት መንፈስ ከመካከላችን ፈጽሞ ስለጠፋ ነው። ስለዚህም “… ለእውነት እየታዘዝን ግብዝነት ለሌለበት ለወንድማማች መዋደድ ነፍሳችንን አንጽተን እርስ በርሳችን ከልባችን አጥብቀን ልንዋደድ ይገባናል።” (1ጴጥ. 1፥22)
1.7.3.  መርሖ ሦስት፦ “ወንጌሉ መሸቃቀጥ አይሻም”
  “የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት እንደ ብዙዎቹ አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደ ተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ኾነን እንናገራለን።” (2ቆሮ. 2፥17)
“የእርሱን ግርማ አይተን እንጂ በብልሃት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችሁ።” (2ጴጥ. 1፥16)
          ወንጌል በብልጣ ብልጥ አቀራረብ ፈጽሞ አይገለግልም፤ ወይም ሀብትን፣ ተቀባይነትንና ስኬትን፣ መወደድን፣ ዝናንና ክብርን፣ የዕለት እንጀራቸውን ለማግኘት ሲሉ ወንጌል መስበክ የሚጠይቀውን ዋጋ (መስዋዕትነት) ችላ በማለት ለማገልገል የወንጌልን ክብር የሚቀንሱትን ሐዋርያው በቁርጥ ቃል ሲናገራቸው እናያለን። ወንጌልን በመሸቃቀጥ የሚያገለግሉ ሰዎች ሰዎችን የመግባባት “ችሎታ” (ብልጣ ብልጥነት) ያላቸውና በራሳቸው የሚመኩ ሰዎች ናቸው። ትልቁ ትኩረታቸው የወንጌል ምስክርነት ሳይሆን በወንጌል ካባነት ሀብትን ማጋበስ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ወንጌልን ይሰብክ የነበረው ከማንም ቀለብ ሳይሰፈርለት በራሱ ወዝ ጥሪት ሲያገለግል (ሐዋ. 18፥3፤ 1ቆሮ. 9፥12፤ 2ቆሮ. 11፥7) እንዲያውም ስለሌሎች መዳን “ያላቸውን ሳይሆን … ገንዘቡንም ፥ ራሱንም በመክፈል ያገለገለ ነው፤ (2ቆሮ. 12፥14)። ወንጌሉን በመሸቃቀጥ የሚያገለግሉቱ ግን አንዳንዶች “መጥፎውን ረብ በመመኘት” (1ጴጥ. 5፥2) ሌሎች ደግሞ “ለወገናቸው ወይም ለግል ምኞታቸው [ጥቅም] ከቅንነት ጎድለው” ወንጌልን ይሰብካሉ፤ (ፊሊ. 1፥17)።
      በዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ወንጌሉ የሚሸቃቀጠውና ሥፍራውን ያጣው ስለሆድ መብል ነው፤ በተለይ እንጀራቸውን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ የመሰረቱት (ከእጅግ እጅግ በጣም ጥቂቶቹ በቀር) “ወንጌሉን በወንጌሉ ክብር” ሳይሆን ጳጳስ፣ የደብር (የገዳም) አለቃ (አበምኔት) ለማስደሰት ብቻ አስበው እንጂ ስለእግዚአብሔር ክብር ፍጹም ተጨንቀው አይደለም። ለዚህ ደግሞ በየስብከቱ መሐል ዘወር እያሉ ከኋላ ላለው አለቃና ጳጳስ እየሰገዱና እጅ እየነሱ አበላቸውንና ደመወዛቸውን ያበስላሉ እንጂ የበላዩንና የተጠሩለትን ትልቁን ጌታ ትዝ ብሏቸው ሲያገለግሉ ብዙም አይስተዋልም።
   የስብከት ማዕከል የሆነውን የክርስቶስን ነገረ ድኅነት ዘንግተው እልፍ ዕላፍ ቦታ ዘባርቀው ከመድረክ የሚወርዱ ለቁጥር የሚታክቱ ናቸው። በእርግጥም ወንጌል የጨከነና የማይደራደር አገልጋይ እንጂ በየመሐሉ ገንዘብና ዝና አሳዳጅን አትሻም። ክርስቶስን በእውነተኛ ግርማው እንደሐዋርያው ጴጥሮስ  ያየው ሰው በዚህ ዓለም ያለው ነገር ያንስበታል እንጂ ከክርስቶስ ወንጌል ይልቅ ተረታ ተረትን አያስቀድምም። በእርግጥም ክርስቶስን በግርማው ያላዩ ሰዎች ብልሃታዊ ተረትን ፈጥረው ሕዝብን ከወንጌል ለይተው ቢያስቱት የሚደንቅ ነገር አይደለም! 
ይቀጥላል …

No comments:

Post a Comment