Friday 4 January 2019

ቤተክርስቲያን ተጐታችና ዘመነኛ ችግሮቿን አስተውላ ይኾንን!? (ክፍል 6)

Please read in PDF
1.4.     ዐይን ያወጣ ጉበኝነት
·        ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል።
·        ሹም ሲቆጣ ማር ይዞ እደጁ፥ ደስ ሲለው ማር ይዞ እደጁ።
    በምሳሌነት ይህን ተረት አነሳን እንጂ ከዚህ ተመሳሳይነት ያላቸው ተረቶችና ምሳሌያዊ ንግግሮች በተወሰነ መልኩ በባህላችን ውስጥ ተሰንቅረው ለጉበኝነትና ለመታያ ስጦታ የሚሰጡት ኢ ሥነ ምግባራዊና ሞራላዊ ድጋፍ አለ።
    የእግዚአብሔር ቃል በግልጥ፦ “ፍርድን አታጣምም ፊት አይተህም አታድላ ጉቦ የጥበበኞችን ዓይን ያሳውራልና፥ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና ጉቦ አትቀበል” (ዘዳግ. 16፥19) በማለት ይናገራል። አንድ ሹም ጉቦ ወይም መማለጃን የሚቀበለው እውነቱን ሐሰት፤ ሐሰቱን እውነት ለማለት ወይም ለማድረግ ነው። እውነቱን ሐሰት ስንል ጻድቁን ወይም እውነተኛውን እንበድላለን፤ ሐሰቱን ደግሞ እውነት ነው ስልን ኅጢአተኛውን በጻድቁ ላይ እናሰለጥናለን።

    በእስራኤል ፊት ያለነውር በሞገስና በመወደድ፤ ያለምንም መማለጃ ይመላለስ የነበረው (1ሳሙ. 12፥3) ታላቁ ነቢይ ሳሙኤል፣ ልጆቹ እንደ እርሱ የተባረኩ አልነበሩም። ስለልጆቹ ታላቁ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ልጆቹም በመንገዱ አልሄዱም፥ ነገር ግን ረብ ለማግኘት ፈቀቅ አሉ፥ ጉቦም እየተቀበሉ ፍርድን ያጣምሙ ነበር” (1ሳሙ. 8፥3) ይላል። ይህ ማለት በሳሙኤል እጅ ትፈረድ የነበረችው የእግዚአብሔር ቅን ፍርድ፣ የሳሙኤል ልጆች መማለጃን በቀኝ እጃቸው እየተቀበሉ (መዝ. 26፥10) ጠማማ ፍርድን በመፍረድ ያፈርሱ ነበር ማለት ነው።
   ያለምንም ማባበያ ቃል ዛሬ ቤተ ክርስቲያን በጉበኞችና መማለጃን በሚወድዱ፥ ንብ የማር ቀፎን እንዲከብብ ተከብባለች። አምስትና ሐምሳ ሺህ ለመጠየቅ አምስቱን አዕማድ፣ ሰባት ሺህ ለመጠየቅ ሰባቱን ምስጢራት፣ አስር ሺህ ለመጠየቅ አስሩን ሕግጋት በኰድ የሚጠቀሙ ፌዘኛና አታላዮች፣ ቤተ ክርስቲያን ከተከበበች ውላ አድራለች። ዛሬ የተመረጡ አድባራት ላይ ከድቁና እስከ ቁምስና  ለመመደብ ጉቦው ራሱ በልዩ ጨረታና በእሽቅድምድም ነው የሚሰጠው። ከተመደቡ በኋላ ደግሞ ለመቆየትና ላለመነሳት ምጽዋተ ሙዳይ እየሰበሩና ካላቸውና ከወዛቸው እየቆረሱ መማለጃ የሚሠጡትን ስንሰማ ጆሮ ጭው ያደርጋል።
    ከብሔርተኝነት በማይተናነስ፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የምናየው አስጨናቂ ነውር ጉበኝነትና መማለጃን መውደድ ነው። ነገር ግን ጉቦን በመቀበል የችጋረኛውን ፍርድ የሚያጣምሙትን እግዚአብሔር ኃጢአታቸው የጸና እንደ ኾነ ይናገራል፤ (አሞ. 5፥12)። “መማለጃን ከመጨበጥ እጁን የሚያራግፍ … እርሱ ከፍ ባለ ስፍራ ይቀመጣል፤ ጠንካራ አምባ መጠጊያው ይሆናል እንጀራም ይሰጠዋል፥ ውኃውም የታመነች ትሆናለች” (ኢሳ. 33፥15-16)።
    ፍትሐ ነገሥቱም፦ “ሳይገባው ገንዘብ ተቀብሎ የሚሾም ኤጲስቆጶስ ቢኖር ይለይ። …” (አን. 5 ቁ.177) እንዲል።
ምን እናድርግ?
1.4.1.   በልክ መኖር
     ኑሮዬ ይበቃኛል አለማለትና ባለጠግነትን አብዝቶ መሻት፣ “በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም እንደሚጥል” (1ጢሞ. 6፥9) የእግዚአብር ቃል በግልጥ ያስቀምጣል። ይልቁን የእግዚአብሔር አገልጋዮች “ምግብና ልብስ ከኖረን ግን፥ እርሱ ይበቃናል” (ምሳ. 30፥8፤ 1ጢሞ. 6፥8)፣ ሊሉ ይገባቸዋል እንጂ ወይም ፍትሐ ነገሥቱ እንደሚለው “ኤጲስቆጶስ ከምግብና ከልብስ የሚበቃውን ያህል የሚወስድ ይሁን ለሚያገለግል ዋጋው ይገባዋልና። ልብሱን አያሳምር ሥጋውን ለመሸፈን የሚበቃውን ያህል ይውሰድ እንጂ። ሌላ ጌጥ የሚያስፈልግ አይደለም”[1] እንደሚለው ራሳቸውን ልከኞች አድርገው ሊኖሩ ይገባቸዋል።
   መጥምቁ መለኮት የጌታን መንገድ ለመጥረግ ይመላለስ  በነበረበት ዘመኑ ልብሱ የግመል ጠጉር፣ ወገቡ ጠፍር የታጠቀ፣ ምግቡ አንበጣና የበረሃ ማር፣ ቤቱ ምድረ በዳ መሆኑ ምን ይሆን የሚያስተምረን? እንደ ዛሬው አገልጋዮች ሽቶ የተቀቡና ውድ የሆኑ ቀሚሶችን፣ የእጅ፣ የአንገት መስቀልን መልበስና መያዝ ይኾን? ወይስ በኹለትና በሦስት ከተማ ያማሩ ቤቶችን መገንባት? ወይስ ቤተ ክርስቲያን የሰጠቻቸውን ቤት ትተው የራሳቸውን በከተማው መካከል ቪላ መገንባት ነውን? ወይስ ጰጵሶ ብዙ ሚሊየን ብር በባንክ አስቀምጦ ወለዱን ቁጭ ብሎ መብላት ነውን? ወይስ መንኩሶ ሳይሠሩ ቁጭ ብሎ ፍትፍት እያማረጡ መብላት ነውን?
  በእውኑ፣ “ለቀበሮዎች ጕድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም” (ሉቃ. 9፥58) ያለው ጌታ ምንን ይኾን የሚያስተምረን? ኹሉን እያለው ድሃ የሆነው ጌታ ሕይወቱ አይዘልፈንንምን? አዎ! “ኑሮዬ ይበቃኛል ለሚለው ግን እግዚአብሔርን መምሰል እጅግ ማትረፊያ ነውና” በኑሯችን ልከኞች እንሁንና በኑሯችን ጌታችንን እናክብረው፤ ከጉበኝነትም እንራቅ።
1.4.2.  ከክፉ መጎምጀት መራቅ
  “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለምና ተጠንቀቁ፥ ከመጐምጀትም ሁሉ ተጠበቁ” (ሉቃ.12፥15)
 “… አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ …” (1ጢሞ. 6፥10-11)
      በልክ ለመኖር መሠረቱ ልብን ከሚከፍለው ክፉ መጎምጀትና ራስን በክፉ ከሚወጋ ምኞት መጠበቅ፤ መጠበቅና መሸሽ ያስፈልጋል። ዛሬ ላይ በምንኩስናና በተለያየ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ዘርፍ መሳተፍ ለቅዱስ አገልግሎት ከመሠማራት ይልቅ ምድራዊ ሀብትን ማግኛ አጭር መንገድ ሆኗል ብንል ምንም ግነት የለበትም። ክፉ መጎምጀት ወይም ስግብግብነት ወደ ዘላለም ጥፋት የሚመራ ኃጢአት ነው።
   በአንድ ወቅት በእስራኤል ልጆች የበረሃ ጉዞ ታሪክ “በመካከላቸውም የነበሩ ልዩ ልዩ ሕዝብ እጅግ ጐመጁ … ” (ዘኁል. 11፥4) ይለናል ታላቁ መጽሐፍ። የእነዚህ ሕዝቦች ፍጻሜ ግን “የእግዚአብሔር ቍጣ በሕዝቡ ላይ ነደደ እግዚአብሔርም ሕዝቡን በታላቅ መቅሠፍት እጅግ መታ። የጐመጁ ሕዝብ በዚያ ተቀብረዋልና የዚያ ስፍራ ስም የምኞት መቃብር ተብሎ ተጠራ።” (ቁ. 33-34) በማለት በአጭሩ ያስቀምጥልናል። እንኪያስ የዛሬዎቹም አገልጋዮች ለጉበኝነትና የሌላውን ቤት የሚያሳያቸው አንዱ ነገር ክፉ መጎምጀት ወይም ስግብግብነት ወይም ራስ ወዳድነት ነውና ከዚህ መራቅ ይገባል።
1.4.3.  የሰዎችን ችግር በመካከላቸው ተገኝቶ ማየት
     ታች በድህነት ያለው ሕዝብ በምን አይነት ድህነት ውስጥ እንደሚኖር ብናስተውልና ያሉበት ድረስ በመሄድ ችግሮቻቸው ምን እንደሚመስል ብናስተውል እጅግ መልካም ነው። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የአገር መሪዎች በገጠር የሚኖረውን እረኛ “ምን ብሏል ዛሬ” ይሉ እንደ ነበር እንሰማለን። ምክንያቱም እረኛው አገሪቱ ያለችበትን ሁኔታ በሥነ ቃል አዋዝቶ ያስቀምጠዋልና ነው። በእርግጥም ሕዝብ ያለውን እየሰሙ እንጂ ሕዝብ ባለው እየተመሩ አገርን መምራት ማስተዋልን ይሻል።
    ይሁንና ራስን ባዶ አድርጎ (ፊሊ. 2፥7) የታችኛውን ሕዝብ ማየት ራስን ለቅምጥለትና ለስግብግብነት አይጋብዝም። ማንም ባለአዕምሮ የሆነ ሰው በረሃብ የታጠፈ አንጀት አይቶ ምግብ ስለማማረጥ አያስብም፣ የትኛውም የሚያስብ ህሊና ያለው ሰው በአልጋው ላይ እንደ ትኋን የተጣበቀ ሰውን አይቶ ገንዘብ ስለማከማቸት አያምረውም፣ ከንፈሩና እግሮቹ ተሰንጥቀው፤ ልጆቹን እቤት አስርቦ ከሚመጣ ገበሬ ላይ ውድ ጫማ መግዣና ያማረ የእጅ መስቀል ወይም መስቀል መግዣ የሚጠይቅ ይኖራል ብሎ መገመት እጅግ የሚዘገንን ነው። ግን ሕዝቡ ያለበትን አለማየታችን እንዲህ ያለውን ናር በማድረግ ልበ ደንዳናነታችንን አሳይተናል፤ መለስ ብለን ያለንበትንና የምኖርበትን ማህበረሰብ ብናይ ከጭካኔያችን ምናልባት እንራራ ይሆናል። (ማን ያውቃል?)
ጌታ መንፈስ ቅዱስ ይርዳን፤ አሜን።
ይቀጥላል ...




[1] ፍትሐ ነገሥት አን. 5 ቁ.127

3 comments:

  1. betekristiyann lemewkes ante maneh? mejemeriya temar ante rasu

    ReplyDelete
  2. betekristiyann lemewkes ante maneh? mejemeriya temar ante rasu

    ReplyDelete
  3. geta Yesus libona yisten

    ReplyDelete