Wednesday 19 September 2018

“ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች” (መዝ. 42)

  የዳዊት መዝሙሮች፣ የብዙ ቅዱሳን ሰዎች ስብስብ መዝሙር ነው። ከእነዚህ አንዱ ደግሞ መዝ. 42ን በምሳሌነት መጥቀስ እንችላለን። መዝ. 42 ጠቅላላው በስደት ላይ ያለ አንድ ሌዋዊ የሚያለቅሰውን ልቅሶ የሚመለከት ነው። ከልቅሶው ውስጥ “ዋላ ወደ ውኃ ምንጭ እንደሚናፍቅ፥ አቤቱ፥ እንዲሁ ነፍሴ ወደ አንተ ትናፍቃለች። ነፍሴ ወደ ሕያው አምላክ ተጠማች፤ መቼ እደርሳለሁ? የአምላክንስ ፊት መቼ አያለሁ? ዘወትር፦ አምላክህ ወዴት ነው? ሲሉኝ እንባዬ በቀንና በሌሊት ምግብ ኾነኝ።” (ቁ. 1-3) የሚለው ክፍል እጅጉን ልብ የሚሰብር ክፍል ነው።

   መዝሙሩን የዘመረው ሌዋዊ ከቆሬ ወገን የኾነ፣ የቤተ መቅደስ አገልጋይና በቤተ መቅደሱ በታማኝነት እግዚአብሔርን የሚቀድስ፣ የሚወድስ፣ የሚባርክ የነበረ ነው። ሌዋዊው የመሰደዱና ከአገሩ የመነቀሉ ምክንያት የእርሱ ኀጢአት ይኹን የሕዝቡ ኀጢአት በግልጥ አልተገለጠም፤ ከምንም በላይ ግን ጠንካራ የኾነ የእንባ ዘለላና ስብራት ከብቦታል። ሌዋዊው በልቅሶው ውስጥ በጠንካራ ሃዘን ተከብቧል፤ ከፍ ባለው ሃዘኑ ውስጥ ደግሞ በቤተ መቅደሱ ውስጥ በእግዚአብሔር ፊት ለመኾን ያለውንም ጉጉት ያመለክታል። ይህን ታላቅ መሻትና ጉጉቱን ግን ኀጢአት ወይም የአስጨናቂዎቹ እገታ ገድቦታል።

  ይህ ስደተኛ ሌዋዊ በምን ምክንያት እንዲህ እንደኾነ ባናውቅም፣ ነገር ግን ከቤተ መቅደስ አምልኮ ፍጹም መለየቱንና ነፍሱ አምልኮ በማጣት፤ የአምላኩንም ፊት በመፈለግ የተከዘች፤ የታወከች መኾኑን ይነግረናል፤ “አምላኬ ሆይ፥ ነፍሴ በእኔ ውስጥ ታወከች፤” (መዝ. 42፥6)። ስለዚህም ሙሉ ኃይሉንና ናፍቆቱን “አምላክን”፣ ከዚያም “ሕያው አምላክን”፣ በመጨረሻም “የአምላክን ፊት” በመፈለግና ለማየትም በብርቱ እንደ ተመኘ እንመለከታለን፤ (ቁ. 1-2)። እግዚአብሔርን በሙሉ ክብሩ በመቅደሱ ማየትን አብዝቶ ናፈቀ። ከምንም በላይ ዋላ ውሃ የሚጠማውን ያህል አምላኩን እንደሚጠማ በመናፈቅ አሳየ።
   ሌዋዊው በውስጡ የጥያቄ ቱማታዎች ይዘበዝቡታል፤ ጠላቶቹ ደግሞ “አምላክህ የት አለ?” በሚል ፋታ አልባ ጥያቄ የነፍሱን ስቅየት ይጨምራሉ፤ ፍጹምም ያስጨንቁታል። የውስጡ ጥያቄ የበጠበጠው አገልጋይ፣ የጠላቶቹ ሙግትና የንቀት ጥያቄ ዕረፍት ይነሳውና፣ እርሱ ራሱ ደግሞ “አምላኬ ወዴት አለ?” በማለት ደግሞ ይጠይቃል። የፍለጋውንና የሐዘኑን ጥልቅና እጅግ ከባድነትም ለመግለጥም “እንባዬ በቀንና በሌሊት ምግብ ኾነኝ” ይላል፤ (ቁ. 3)። የሚሄድበት መጠጊያ የለውም፤ የሚያገለግልበት መቅደስም የለም፤ [ይህ ሌዋዊ በስደት፣ በእስር፣ ታግቶ ይኾንን?] ብቻ ግን ተስፋ መቁረጥ ዙርያውን ከብቦታል፤ ነገር ግን ተስፋ በቆረጠበት ነገር ኹሉ አምላኩ መልስ እንዲሰጠው የአምላኩን ፊት በብዙ መቃተት ይፈልጋል።
  ሌዋዊው በብርቱ ሃሳብና ናፍቆት ውስጥ ተውጧል፤ “ታላቅ ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር ቤት እየመራሁ፣ በእልልታና በምስጋና መዝሙር፣ በአእላፍ ሕዝብ መካከል፣ እንዴት ከሕዝቡ ጋር እሄድ እንደ ነበር ትዝ አለኝ።” (ዐመት ቁ. 4) እንዲል፣ የእግዚአብሔር ማዳን ለማስታወስና ለአምልኮ ሕዝቡ በቤተ መቅደሱ ውስጥና በአደባባዩ የሚያቀርቡትን ዝማሬና፣ መሥዋዕት፣ የበዓላቱን አከባበር ኹሉ በማስታወስ ነፍሱ ፈሰሰች፤ የትዝታው ስሜት መቆጣጠር የተሳነው እስኪመስል ተጋጋመ። እኒህ ነገሮችን በመከራ ውስጥ ማስታወስ እጅግ የጸና ሕመምን ቀስቃሽ ናቸው። “ታላቅ ሕዝብ ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመራ”  መኾኑን ስናይ ምን ያህል የከበረ አገልግሎት እንደ ነበረው እናስተውላለን፤ አኹን ግን እጅግ በመጠማት አለ!!
   ይህ ሌዋዊ አምላኩን፣ ሕያው አምላክን፣ የአምላኩን ፊት የመናፈቁንና የመጠማቱን፤ የመፈለጉንም ያህል በአምላኩ ላይ ፍጹም ተስፋ አለው፤ አምላኩንም ይታመናል፤ “ነፍሴ ሆይ፥ ለምን ታዝኛለሽ? ለምንስ ታውኪኛለሽ? የፊቴን መድኃኒት አምላኬን አመሰግነው ዘንድ በእግዚአብሔር ታመኚ። … አምላኬ ሆይ፥ ነፍሴ በእኔ ውስጥ ታወከች፤ ስለዚህ በዮርዳኖስ ምድር በአርሞንኤምም በታናሹ ተራራ አስብሃለሁ። … እግዚአብሔር በቀን ቸርነቱን ያዝዛል፥ በሌሊትም ዝማሬው በእኔ ዘንድ ይሆናል፤ የእኔ ስእለት ለሕይወቴ አምላክ ነው። …” (ቁ. 5-6፣ 8፣ 11) በማለት፣ በአምላኩ ላይ ያለውን መታመንና መተማመን ይገልጣል። በትካዜ ውስጥ ነው፣ ግን በአምላኩ ተስፋው ጽኑ ነው፤ ተስፋው ጽኑ ስለኾነም፣ ልክ እንደ ዋላ “በዮርዳኖስ ምድር በአርሞንኤምም በታናሹ ተራራ … በፍዋፍዋቴህ ድምፅ የቀላይ ቀላይን መጣራትን፤ የማዕበልና የሞገድ ነገርን ሁሉ” በማንሳት፣ በማስታወስ ፊቱን ወደ ተስፋይቱ ምድር ያቀናል። ተስፋ የቆረጠው ሌዋዊ፣ በአንዴ ተስፋንና መተማመንን ይሞላል።
  ብቻውን በመኖሩ ልቡ በብዙ እንዳልተፈተነ ወዲያው ደግሞ በመናፈቅ ውስጥ ባገኘው ኃይል ድል አደረገ፤ ተስፋውንም አጸና። አንድ አስደናቂ ነገር እናስተውላለን፤ እምነትና ጥርጣሬ የተጋመዱ መኾናቸውን፤ ሌዋዊው ድል የነሣ በመሰለው ጊዜ ወዲያው የእምነት ጥያቄዎችን ያሽጎደጉዳል፤ ነገር ግን ተስፋ እንዳይቆርጥና መንገዱን እንዳይስት እግዚአብሔር በተስፋው ደግፎት ይዞታል፤ በማናቸውም መንገድ ውስጥ ቢኾን እንኳ፣ የአምላኩን ማዳንና ድል መንሣቱን ፈጽሞ ያስበዋል፤ የአምላኩ ተስፋ ደግሞ ፈጽሞ እንደሚፈጸም እርግጠኛ ነውና ይተማመናል።
  በሌላ መንገድ ደግሞ ውስጡ የአምላክንም ፍርድ በማሰብ ይጨነቃል፤ እንዲያውም እንደ ዋላ በውሃ ከመርካት ይልቅ የአምላኩ ፍርድ ያስጨንቀዋል፤ አስተውሉ! ሌዋዊው ዘማሪ የአምላኩን ጥበቃ፣ እንክብካቤ፣ ጥበቃና ትድግና ያውቃል፤ አምላኩንም “የእኔ ስእለት ለሕይወቴ አምላክ ነው።” (ቁ. 8) በማለት፣ ከአምላኩ ጋር ጥብቅ ኅብረት እንዳለው አሳይቷል። መከራው፣ ብቻነቱ፣ ጥማቱ፣ ረሃቡ … ግን ምሕረቱን ያራቁበት፣ ደግሞ ተስፋውን ያሰለሉበት ይመስለውና እያመሰገነው ያለቅሳል፤ እያዘነ ይናፍቀዋል፤ ከመቅደሱና የያህዌን ማዳን ከሚያስታውሱ ነገሮች ኹሉ መለየቱ፣ ፊቱና ዓይኖቹ እስኪቀሉ ድረስ ለእንባ ዳርገውታል።
  ሌዋዊው የአምላኩን ዝምታና መሰወር በመጠራጠር ቢያሰላስልም ግን ደግሞ አምላኩን “አንተ መጠጊያዬ ነህ፤ ዐለቴ ነህ” ይለዋል፤ ጠላቶቹ እንደበረቱበት፤ ለጠላቶቹ ጉልበትም አምላኩ አሳልፎ እንደ ሰጠው ያስባል፤ እናም “ለምን ረሳኸኝ?] በማለት ደጋግሞ ይጠይቃል። ጠላቶቹ ይላገዱበታል፣ ውስጡ በጥያቄ ያስጨንቀዋል፤ እርሱ ምናልባትም እንደ ሞተ ሰው ኾኗል፤ መብቱን ኹሉ አጥቷል፤ ኹለንተናው ተጨንቋል፤ ተረብሿል፤ ነገር ግን ተስፋውን መልሶ ያለመልማል፤ ስንቁ እንባ፣ ቀለቡ ጭንቀት ቢኾንም እንደ ገና አምላኩን እንዲታመን፣ መቼም ሊያድነው የሚችለውን አምላኩን ተስፋ እንዲያደርግ መናፈቁና ሙግቱ፣ መሻትና ጥማቱ መርተውታል።
  ሌዋዊው አምላኩን ዘወትር ይጠማል፤ ከመከራው ባሻገር፣ ከተስፋ መቁረጡ በዘለለ፣ ከደረሰበት ጭንቀትና ምሬት በላይ አምላኩን እንደ ውሃ ይጠማል፤ ያለ ውሃ መኖር ከባድ እንደ ኾነ እንዲሁ፣ የእግዚአብሔርም ሃለወት ሕይወትን ለማርካትና የሕይወትን ተስፋ ለማስቀጠል እጅግ ወሳኝ ነገር ነው። እውነተኛ አማኝም በእርግጥ ጥማቱ፣ ፍላጎቱ፣ መሻቱ፣ የሁል ጊዜ ረሃቡ እግዚአብሔር ራሱን ፊቱን ወይም መገኘቱን፣ በረከቱንና ተአምራቱን የሚጠማ ነው። በመንፈሳዊ ሕይወት የማደጋችንና በትክክል የመጓዛችን አንዱ ማሳያ በእግዚአብሔር ላይ ያለን መጠማትና መራብ፣ መሻትና መናፈቅም ነው።
   እግዚአብሔርን አብዝቶ አለመጠማት በቀጥታ ወደ መንፈሳዊ ሞት ይመራል፤ ልባችንን የሚገዛው ልባችን ላይ የሚዘገየው ያው ነገር ነው። ብዙዎችን የብሔር ፖለቲካ፣ ዘረኝነት፣ ጥላቻ፣ ይቅር አለማለት፣ ዝሙት፣ ዘፈን፣ ከልክ ያለቸ ቸለተኝነት … የገዛቸው ልባቸው ላይ አብዝቶ ስለሚዘገይና ደጋግመው ስለሚያሰላስሉት ነው፤ ሌዋዊው በመከራና ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ ኾኖ ልቡን ያጸናውና ከክፉ የጠበቀው አምላኩን አጽንቶ መጠማቱ ነው። ለእግዚአብሔር ለራሱ ብቻ ያለንን መጠማት የሚቀንስብንና የሚወስድብንን ማናቸውንም ነገሮች ማስወገድና ፈጽመን መጥላት ይገባናል። “የዚህ ዓለም ዐሳብና የባለጠግነት ማታለል የሌላውም ነገር ምኞት ገብተው ቅዱስ ቃሉን እንዳያንቅ ከማፍራትም እንዳይከለክል” (ማቴ. 4፥19) ወደ እግዚአብሔር ከማይመሩ ማናቸውም ነገሮች አብዝተን መራቅ ይገባናል፤ ምክንያቱም እኒህ ነገሮች የእግዚአብሔርን ፊት በጸሎት ተግተን እንዳንጠብቅ ያደርጉናልና፤ ለእኛ ለአማኞች ትልቁ ነገራችን የነፍሳችን ወደ እግዚአብሔር መናፈቅ ብቻ ነውና።
 በአዲስ ኪዳን፣  “መንግሥትህ ትምጣ” የሚለው ትልቁ የመጠማትና የናፍቆቅ፣ የጸሎታችን የጩኸት ቃል ነው። በቀንና በሌሊት ትልቁ ጥማታችንም ይህ ብቻ ነው።  ማራናታ! ማንም በዚህ ምድር ቢመጣና ቢድ የማይበርደንና የማይሞቀን አንድ ጽኑዕ ተስፋ ስላለን ነው። የክርስቶስን መንግሥት ማየትና ጽድቁ ሙሉ ለሙሉ ተገልጣ ናፍቆታችን ተቆርጦ ማየት ትልቁ መሻታችን ነው። እርግጥ ነው፣ ጸሎታችን ወዲያው ላይመለስልን ይችላል፤ እጅግም ሊዘገይብን ይችላል፤ ነገር ግን ፍጹም በመታመን በጸሎት ልንጸና፣ ልንተጋ፣ ሳናቋርጥ ልናደርገው ይገባናል።
    በአገራችን፣ በቤተሰባችን፣ በመንፈሳዊ ሕይወታችን፣ በሥራችን፣ በትዳራችን … ጉዳይ እግዚአብሔር የዘገየ ሊመስል ይችላል፤ ዝም ያለም ሊመስለን ይችላል፤ ነገር ግን “ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናል እርሱም ይመፈውሰናል፤ እርሱ መትቶናል፥ እርሱም ይጠግነናል። … እንወቅ፤ እናውቀውም ዘንድ እግዚአብሔርን እንከተል፤ እንደ ወገግታም ተዘጋጅቶ እናገኘዋለን፤ እንደ ዝናብም ምድርንም እንደሚያጠጣ እንደ መጨረሻ ዝናብ ይመጣል።” (ሆሴ. 6፥1፤ 3)፣ “ንስሐ ግቡ፥ ኀጢአታችሁ ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ። የተስፋው ቃል ለእናንተና ለልጆቻችሁ ጌታ አምላካችንም ወደ እርሱ ለሚጠራቸው በሩቅ ላሉ ሁሉ ነውና” (ሐዋ. 2፥38-39)፣ “ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ።” (ኤፌ. 4፥12-13) የሚለው ቅዱስ ቃል ዘወትር ሊታወሰን ይገባል።
    እናም ከምን ጊዜውም በበለጠ እግዚአብሔርን ለማወቅና የመንፈስ ቅዱስን ሙላት ለማግኘት በተሰበረ ልብ መሻታችንን፣ መጠማታችንን፣ መራባችንን ሳናቋርጥ ልናደርገው ይገባናል። እግዚአብሔር አምላክን በሕይወታችን ሳናቋርጥ በፍቅሩና በማዳኑ፣ በተአምራቱና በድል አድራጊነቱ ልንተማመነው ይገባል። አዎን! እግዚአብሔር እርሱን በማመን ፍጹም በመተማመንም በማናቸውም የሕይወት ሰልፍ ውስጥ ኾነው በእርሱ በመደገፍ ሙሉ በረከቱን በመጠማት፣  ከምድራዊ መደላደልና መለዳለድ ራሳቸውን ጠብቀው፣ የእርሱን ጽድቅ የሚራቡትንና የሚጠሙትን አብዝቶ እንደሚባርክ ፍጹም ተስፋ ሰጥቷልና፤ (ማቴ. 5፥6)። ሌዋዊው እንደ ዋላ የተጠማህ፣ የናፈቀህ፣ የፈለገህ የሕይወታችን ስእለት ያህዌ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ ሆይ! የእኛም ነፍስ አብዝቶ ትናፍቅሃለችና ናልን! ፍለቅልን! ጠጥተንህም እንርካብህ! አሜን!


3 comments: