Tuesday 25 September 2018

የእግዚአብሔር ኃይል

Please read in PDF

“የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና።”
(1ቆሮ. 1፥18)
    ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የታወቀ አንድ ጠንካራ አባባል አለው፤ “እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ይልቅ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል” የሚል፤ ይህ ትምህርቱ እጅግ ጥልቅ ታላቅ መንፈስ ቅዱሳዊ ማስተዋልን የሚሻ አስደናቂ ትምህርት ነው። የትምህርቱ አስደናቂነት እግዚአብሔር ፍጥረትን እምሃበ አልቦ ሃበ ቦ (ካለ መኖር ወደ መኖር) እንዳመጣው፣ እንደ ቀድሞ ፍጥረትን ፈጥሮ በማስገኘት እንዳመጣበት አመጣጥ ያለ አይደለም። ይልቁን “ሕያው የኾነውን” የሰውን[አሮጌውን አዳም] በመስቀልና በመግደል አዲስና ልዩ ሕይወትን፣ ማለትም ለእርሱ ብቻ ሊኖር ያለውን ጠባይና ባሕርይ ገንዘብ ያደረገን አዲሱን ሰው በማስገኘት እጅግ አስደናቂ የማዳን ሥራን በመሥራት የኾነ እንጂ።

   ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ታላቅ እውነት በመንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ ተረድቷል፤ የተረዳ ብቻ ደግሞ አይደለም፤ ይህን እውነት ያምነዋል፤ ያውጀዋል፤ ይመሰክረዋልም፤ በዚህ መንገድ የሚመጣውን የትኛውንም መከራ ለመቀበል በነፍሱ እንኳ ሳይቀር ለመቀበል እጅግ ጨክኗል፤ ስለዚህም እጅግ ታላላቅ መከራዎቹን ኹሉ፣ የሌሉና ያልገጠመው እስኪመስለው የሚዘነጋው ለዚህ ታላቅና ዘላማዊ እውነት ራሱን እንደ ውኃ በማፍሰሱና በመስጠቱ ነው። በእርግጥም ይህ እውነት፣ በፍጹም የዋህነት ለሚያምኑና ለሚቀበሉ እንጂ ለአንዳንዶች መሰናክል፤ ለሌሎች ደግሞ ሞኝነት እንደ ኾነ ይነግረናል።
   ሐዋርያው ይህን መልእክት የጻፈው ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ነው፤ ለቆሮንቶስ መልእክቱን ከመጻፉ በፊት ደግሞ ወደ ቆሮንቶስ የመጣበት አመጣጥ የስጋትና የፍርሃት ነበር።ይህን የሐዋርያት ሥራን የዘገበልን ቅዱስ ሉቃስ ወደ ቆሮንቶስ የገባበትን ኹኔታ ይነግረናል።ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ቆሮንቶስ የመጣው በኹለተኛው ሐዋርያዊው ጉዞ ላይ ሳለ ነው፤ ይህ ኹለተኛው ጉዞው ደግሞ በደስታና በስጋት፣ በመወደድና በመጠላት የታጀበ አገልግሎት ነበር። ከቆሮንቶስ በፊት በነበሩት ከተሞች እንደነ ቤርያ ባሉት ደስታና መደነቅ ሲሞላው፣ እንደ ተሰሎንቄ ባሉት ሥራ ፈቶች፣ ልበ ደንዳኖችና ክፉዎች፣ እንደ አቴና ከልክ ያለፈ የቸለተኝነት ኀጢአት እጅግ መንፈሱ ሳይታወክና ሳይጨነቅ አይቀርም፤ በተለይም የተሰሎንቄው ጉዳይ ጢሞቴዎስና ሲላስ ምን ሊሉ እንዳላቸው በመጠበቅ ሳለ ነው (ሐዋ. 17፥16፤ 18፥1) ወደ ቆሮንቶስ የመጣው።
   ቆሮንቶስ ሲመጣ ያለው ነገር ምስቅልቅሉ፣ ርኩሰቱ አደባባይ የወጣ ነበር፤ በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን የጌታን ነገር ለመናገር ፈጽሞ መጨከኑን እናስተውላለን። በተለይም አገልግሎ ከሄደ በኋላ መልእክትን ሊጽፍላቸው ወደደ፤ ሊጽፍ የተነሣባቸው ምክንያቶቹ ብዙ ሊኾኑ ይችላሉ፤ በመካከላቸው ልዩነት እንዳለ ከቀሎዔ ቤተሰብ በመስማቱ (1ቆሮ. 1፥11)፣ በመካከላቸው ያለው ኅጢአት ከርቀት ጎልቶ ስለተሰማ (1ቆሮ. 5፥1)፣ ስለጻፉለት (1ቆሮ. 7፥1) እና ሌሎችም ምክንያቶች ይኖሩታል።
   ነገር ግን መሠረታዊውን ምክንያት ፈጽሞ አልዘነጋውም፤ እርሱም የተሰቀለውን ክርስቶስ። ቅዱስ ጳውሎስ የተላከበት ዋናው ነገሩ ይህ ነውና። ከዚህ ውጪ ሌላ ርእስ ፈጽሞ አልነበረውም፤ የለውምም። ምክንያቱም ይህ ጉዳይ ለብዙዎች የተስተዋለ ባይኾንም፣ እግዚአብሔር አምላክ ኃይሉን የገለጠበት መንገድ ነውና። ደግሞም በፍጥረት ታሪክ እጅግ አስደናቂውና አስደማሚው የያህዌ ሥራ ነውና። ይህ ነገር ለቆሮንቶሳውያንና ለግሪክ አሕዛብ ጭምር ሞኝነት፣ ለአይሁድ ደግሞ እጅግ አሰናካይ ነበር፤ እንዴት እንደ ኾነም ሦስት ምክንያቶችን ማቅረብ እንችላለን፦
1.      በአይሁድ ትምህርት የሚጠበቀውና የሚናፈቀው መሲሕ ፈጽሞ አይዋረድም፤ ሊዋረድም አይችልም፣ ድል አድራጊ ብቻ እንጂ። አይሁድ ብቻ ሳይኾኑ ሐዋርያት ጭምር መሲሑ ሲመጣ እስራኤላዊ መንግሥታቸውን እንደሚመልስላቸው ያምኑ ነበር፤ (ሐዋ. 1፥6-8)። ነገር ግን የመሲሑ ሥራና ዓላማ ከምድራዊ መንግሥት ጋር ሳይኾን ከእግዚአብሔር መንግሥት ጋር አንደ ኾነ አላስተዋሉም።
መሲሑ ግን ገና ከውልደቱ ጀምሮ በበረት ተገኘ፣ በድህነት ኖረ፣ ኀጢአተኞችን ተቀበለ፤ የተዋረዱትንና የተጠቁትን ወደ እግዚአብሐየር መንግሥት አፈለሰ፣ ሰው ለሌላቸው ሰው ኾኖ መጣ፣ እንደ ጠበቁት ሳይኾን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድና ሃሳብ ብቻ በትስጉት ዘመኑ ተመላለሰ፤ ይህ እርሱ የመጣበት መንገድ አይሁድን አሰናካይ ኾነ። ለንግሥና የጠበቁት ከድኾች መንደር ዋለ፣ ጦር ያደራጃል ያሉት እጅግ ደካሞች የኾኑ የገሊላ ሰዎችን ደቀ መዛሙርትን ሰበሰበ፤ እነርሱም የተናቁና ዓሳ አጥማጆች የሚበዙባቸው ነበሩ፤ ገሊላም የአላዋቂዎች የቀለምን ነገር ያልቀሰሙ “መሃይማን” መሰባሰቢያ ነበረች። ይህ ነገር ለአይሁድ ፈጽሞ አሰናካይ ኾነ።
2.     በአሕዛብም አንድ እጅግ የተከበረና የተወደደ ሰው እንዲህ ባለ መንገድ መከራ ሊቀበልና ሊንገላታ አይችልም።የክርስቶስ የሥጋ ሞት ለአንድ እጅግ መልካም ለኾነ ሰው መኾን ያልነበረበት ነው፤ ጻድቅና ቅዱስ የነበረው ብላቴና፣ በሰው እጅግ ተላልፎ በብርቱ መከራ ሞተ፣ ሞቱም አዳነን ማለት ለአንድ አሕዛባዊ የማይመስል የሞኝነት ትምህርትና የሞኝነት ስብከት ነው።
    ነገር ግን ደጉ ኢየሱስ ይህን ወድዶ በፈቃዱ ለሰው ልጆች ኀጢአት ሲል አደረገው፤ እንዲህ በማድረጉም ኃጢአተኞችንና በእርሱ ያመኑትን ኹሉ አዳነ።
3.     በኹለቱም ወገኖች [በመላው የሰው ልጅም ጭምር] ዘንድ ግን እንዲህ ባለ የሽንፈትና የመከራ መንገድ የእርሱ ማሸነፍና የሞትን መውጊያ መስበር፣ ሲኦልን ድል መንሣት፣ ገሃነምን ማፈራረስ ፈጽሞ በሰውኛ ዘይቤ የሚታሰብ አይደለም።ጌታ ኢየሱስ እየሞተ ድል ነሺ ነበር፤ ተይዞ እየተገረፈ ሰይጣንን እያሰረው ነበር፤ እየተሰቃየ የሰው ልጆችን ኹሉ፣ በሞቱና በትንሣኤው የሚያምኑትን ኹሉ ከስቃያቸው እያሳረፈ ነበር፤ እየተዋረደ ብዙዎችን ወደ ክብር መንግሥቱ እያፈለሰ ነበር።
   በውርደት መክበር፣ በመሸነፍ መርታት፣ በመሞት ሞትን መግደል፣ የሰዎችን ሸክም በመሸከም ደካሞችን ማሳረፍ፣ እኛ ከክርስቶስ ጋር ሞተን ሰዎች ሕይወት እንዲያገኙ ማድረግ፣ ሰዎች እንዲድኑ የራስን ክብርና ጥቅም መተው … ይህ በክርስቶስ መንፈስ ላልኾነ ፍጥረታዊ ሰው ሞኝነት፣ አላዋቂነት፣ መበለጥ፣ አለማስተዋል እንደሚኾን እውን ነው። ነገር ግን ክርስቶስ ይህን መንገድ አሳይቶናልና ልንጓዝበት ይገባናል።
    ክርስትና እጅግ ትሁትና የዋህ መኾን ይጠይቃል፤ ብልጣ ብልጥነት፣ ልወደድ ልወደድ፣ ልታይ ልታይ ባይነት፣ አቋራጭ መንገዶችን መጠቀም፣ ሰዋዊ ብልሃቶችን ማዳመቅ፣ ሰውን በራስ ጥበብ ለመማረክ መከጀል እጅግ ሞኝነትና ምስኪንነት ነው።ክርስቶስ ያለፈበት የቱም መንገድ ለእውነተኛ ክርስቲያኖች የእግዚአብሔር ኃይል እንጂ አይጎረብጥም፤ ክርስቶስ በዚህ መንገድ እንድናልፍ አስቸጋሪውን፣ ሸቃቃጩን፣ ፍጥረታዊውንና ለእግዚአብሔር ሊታዘዝ የማይፈቅደውን አዳምን በመግደል ያዳነን፣ ነጻ ያወጣን፣ የተቤዠን ውድ የእግዚአብሔር ኃይል አለ።
    በግሪኩ ይህ የእግዚአብሔር ኃይል “ዶናሚስ” ተብሎ ተጠርቷል፤ ይህም ለአሮጌውና ሊታዘዝ ለማይወድደው፣ እንዲኹም እኛን በማዳን ሊወርሰን የወደደው ጌታ “የተጠቀመው” ኃይል እጅግ አስደናቂ፣  ኹለንተናችንን አደባይቶ ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ እንድንቆም የሚያደርገን ኀይል ነው።ያንን ኃይል እግዚአብሔር የገለጠው በልጁ ሞት አማካይነት በመስቀል ላይ ነው። ይህ እውነት በልባቸውና በማንነታቸው ወይም ባላቸው ዕውቀትም ይኹን ሌላ ነገር ለሚመኩ ሞኝነት ወይም ማሰናከያ ነው፤ እግዚአብሔርን ለሚያምኑና ለሚድኑ ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው።
   ወገኖቼ! የተጠራነው በዚህ የእግዚአብሔር ኃይል በመዳን ለእርሱ ብቻ እንድንሆን ነው፤ እንኪያስ በዚህ ታላቅና ግሩም ኃይል እንጂ በራሳችሁ ለመዳንና ከኃጢአት፣ የኃጢአት ዝንባሌ ካለው ከፍጥረታዊው አዳም ለመዳንና ለማምለጥ ስለምን ትጥራላችሁ? ይህ ታላቅ ኃይል ስጦታነቱ ለሰው ልጅ ሁሉ ማዳኑ ደግሞ ለሚያምኑበት ኹሉ ነውና አምናችሁ ዳኑ፤ ድናችኹም ክብሩን ውረሱ። መስቀሉን ስናስብ እንዲህ ባለ መንገድ ብቻ ማሰብ ከእግዚአብሔርና ከቅዱስ ቃሉ መስማማትን ይጠይቃል፤ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ይህን የእግዚአብሔርንን ኃይል ትኩር ብለን በመንፈሱ እንድናየው ይርዳን፤ አሜን።



No comments:

Post a Comment