Sunday 30 September 2018

ነገረ ኢሬቻና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አበው!

Please read in PDF

   ማሳሰቢያ፦ ማንኛውም ሰው የፈለገውን እምነት የመከተል መብት ከያህዌ ኤሎሂም ተችሮታል፤ የወደደውንም “አምላክ”[እግዚአብሔርንም ኾነ ሰይጣንን] መከተል ይችላል፤  ታድያ ካመለክነው ዋጋችንን መቀበል ሳንዘነጋ!!!! ይህ ጽሁፍ የኢሬቻን አምልኮአዊ ሥነ ሥርዐት ለሚከተሉና ዋቄፈታን ሃይማኖታቸው ላደረጉ አልተጻፈም፤ ነገር ግን በክርስትና ውስጥ መስገው፣ ኢሬቻንና ዋቄፈታን ወደ ክርስትና አሹልከው ለማስገባት የሚጥሩትን ሥራቸውን ዕቡይ፤ መንገዳቸውን እኩይ ለማለት የተጻፈ ክርስቲያናዊ የተግሳጽ ጽሁፍ ነው!
ምክንያተ ጽሑፌ
   ሰሞኑን ሚድያውን ከሸፈኑት ነገሮች መካከል አንዱ፣ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አበውና አንዳንድ “ክርስቲያኖች” [በክርስትና ስም ያሉትን ኹሉ ይመለከታል]፣ “ዕጣን ዕጣንነታቸውን፤ ክርስቶሳዊ ክርስቶሳዊነታቸውን” ትተው፣ “እሬቻ እሬቻ፤ ዋቄፈታ ዋቄፈታ” መሽተታቸው ነው። እናም ይህ ተግባራቸው እጅግ ቈጥቁጦኛል፣ ለምንስ እንዲህ መኾን አስፈለገው? ብዬ እንድሞግት አስገድዶኛል። በምን መሥፈርት አንዳንድ አባቶች “የኢሬቻ የክብር ተሸላሚ እንደ ኾኑና፣ ለምን ዓላማስ እንዲህ ሊሸለሙ እንደ ተፈለገ፣ ኢሬቻ “ባሕላዊ ወሃይማኖታዊ መልክ” ሊይዝ እንዳለው [እንደ ያዘና ዋቄፈታ በሚለው ዐውድ፣ እንደ ክርስትናና እስልምና ሃይማኖቶች “አምላኩን ጠርቶ” ሲባርክ እያየን ነውና] እየታወቀና እየተሄደበት፣ በግልጽ ሃይማኖታዊ ቀኖናና ዶክትሪን እየተዘጋጀለት ባለበት በአኹኑ ሰዓት፣ ክርስትናን በተለይም ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን መታከክ ለምን አስፈለገ?፣ ከክርስትናና የክርስቶስ ጌትነትና አዳኝነት፣ ቤዛነትና ብቸኛ ዋጂነት በማይሰበክበት መድረክ ላይ፣ እኒህ አባቶች የስማቸው መጠራት፣ በተጨማሪም ጥቂት የማይባሉ ክርስቲያኖች በማምለኪያው ሥፍራ[1] መገኘታቸው አልኮሰኮሳቸው፣ አልከነከናቸው፣ አልቆጠቆጣቸው ይኾንን?” … የሚልና ብዙ የጥያቄ ማዕበሎች ይህን ጽሁፍ ለመጻፍ ምክንያት ኾኖኛል።

  በተለይ ደግሞ “በቤተ ክርስቲያኒቱ ያገኘውን የሥልጣን ከፍተኛነት በመጠቀም፣ እሬቻን ከክርስትና ጋር ለመስፋት የሚጥር ሰው ቢኖር [ዕድሜ ልኩን አይሳካለትም እንጂ] “ቄስ በላይ መኮንን” ነው። ሰውየው ሥልጣኑን በዚህ መልክ የተጠቀመበትን ምክንያት ማንም ሰው ከማስተዋል ይዘነጋዋል ብዬ አላስብም። ለምንስ ዘወትር ይህን ሲያደርግ በዝምታ ይታለፋል? በቤተ ክርስቲያኒቱና በክርስትና ሽፋንስ ለምን እንዲህ ይሸቃቅጣል? … የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች አኹንም ወደ ልቤ ጎርፈዋል። በላይ[“ቄሱ”] በተለይ በኦሮሚኛ የሚያደርጋቸው ቃለ መጠይቆች ተለዋዋጭና የሰውን ፊት በማየት የሚያደሉ መኾናቸው ምንም መንፈሳዊነት የማይንጸባረቅበት ሰው፤ አፍነክናቂ [ያውም እጅግ አድሎዐዊ በኾነ መንገድ] መኾኑን አስተውዬበትአለሁ።
  ይህ ሰው በአንድ ወቅት OBS ከተባለ የኦሮሚኛ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ በ“harka fuune” (ቤት ለእንቦሳ) በሚለው ዝግጅት፣ ከጋዜጠኛ አብዲ ገዳ ጋር “ረዥም” ቃለ መጠይቅ አድርጎ ነበር። በዚያ ቃለ መጠይቅ ላይ የመጽሐፍ ቅዱስንና የኢሬቻን ወይም የዋቄፈታን “አንድ ዓይነትነት” እንዲህ ይናገራል፤
    “ … በዚህ ቤተ እምነት ወደ ወንዝ መውረድን ቀሳውስቱም ጳጳሳቱም ያወግዛሉ። ሥልጣን እስክይዝ እኔ ይህ ነገር ያመኛል፤ ሥልጣን አጊኝቼ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ስሆን መሄድ አለብኝ ብዬ የቤተ ክርስቲያኒቱን ልብስ ለብሼ ሄድኩኝ። ለምን? ሲሉኝ ለአቡነ ጳውሎስ በደንብ ነገርኳቸው። “አምላከ ባህር ወቀላያት”፤ ኦሮሞም የባህርና የገደል አምላክ ይላል፤ በግዕዝም እንዲሁ ነው የሚለው። ድሮ ክርስትና ሳይፈጠር በብሉይ ኪዳን የሚያመልኩ ሰዎች ወደ ወንዝ፤ ወደ አድባር ሄደው ይለምኑ ነበር። ለምሳሌ፦ አብርሃም ልጁን ለመስዋዕት ሲያቀርብ ወደ አድባር ወጥቶ ነበር፤ በዚያ አድባርም እግዚአብሔርን አነጋገረው ይላል፤ በእኛ ጊዜ ወንጀል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አድባር የሚለው ሙሴና አብርሃም እግዚአብሔርን ያነጋገሩበት ነው። በእኛ ጊዜ ወንጀል ያደርጉታል ፤ ወደ ወንዝ ስንሄድ ወንጀል ያደርጉታል። …”
   በትላንትናው ቀን ደግሞ፣ በLTV “ሰፊው ምህዳር” በሚል ፕሮግራም ላይ ተገኝቶ፣ “… መስቀል የክርስቲያን አይደለም፤ አስቀድሞ የኦሮሞ ዘመን መለወጫ ኾኖ ይከበር ነበርና” ይለናል “ቄሱ”፤ እንግዲህ አንድን ቡድን ለማስደሰት “ኹለንተናን አሳውሮ ማቅረብ”፣ አለማወቅን በአደባባይ ዓይንን በጨው አጥቦ እንዲህ ለማቅረብ ሃፍረት ይነሳል
   ለመኾኑ፣ አብርሃምና ሌሎች አበው ወደ አድባር፣ ወደ ወንዝ፣ ወደ ገደል ሄደው ይለምኑ ነበር የሚል ቃል በየትኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አለ? አብርሃም ልጁን ለመስዋዕት እንዲያቀርብ ወደ ሞሪያም ተራራ ይዘህ ሂድ ያለው እግዚአብሔር ነው፤ (ዘፍ. 22፥2) ይህ ግን እኛን አይመለከተንም፤ የታዘዘው የፈጸመውም አብርሃም ነው፤ ይመለከተናል ካልን ተራራውን ብቻ ለምን እንመርጣለን? እንደ አብርሃም እጅግ የምንወደው ልጃችንን ይዘን ለመሠዋት በየወንዙ በየተራራው በየገደላ ገደሉ መንከራተት አለብን፤ ይህን ደግሞ “ቄሱም ኾነ የትኛውም የእሬቻና የዋቄፈታ አማኝ” አያደርገውም። ደግሞ እኛ የአዲስ ኪዳን አምላኪዎች እንጂ ብሉያውያን አይደለንም፤ እንደ ብሉይ ኪዳን አማኞች ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደሱ ባለበት ካልሄድን ወይም እንደ እሬቻና ዋቄፈታዎች ወንዝ፣ ዛፍ ሥር፣ ተራራ ላይ … ካልሄድን እግዚአብሔር አይሰማንም የምንል አይደለንም፤ አምላካችን መንፈስ ነው፤ የትም፣ መቼም፣ በማናቸውም ኹኔታዎች ውስጥ ብንኾን ይሰማናል፤ እርሱ ቦታና ጊዜ፣ ኹኔታም አይገድበውምና፤ (መዝ. 138፥7-12፤ ዮሐ. 4፥24)፡፡ “ቄሲቻው” ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አላስተዋሏትም፤ ወይም አያውቋትም!
   ሌላ የፈጠጠ ውሸት ደግሞ እዩ! መስቀል ከክርስትና በፊት የኦሮሞ የዘመን መለወጫ ተደርጎ ይከበር ነበር ይለናል፤ ምን ማስረጃ አለ? በእውኑ መስቀል ከክርስትና በፊት በአምልኮ ምልክትነቱ ይታወቅ ነበር ወይ? የእርግማን ምልክት አልነበረምን? (ገላ. 3፥13)፤ አላዋቂ ሳሚ ንፍጥ ይለቀልቃል አለ የአገሬ ሰው!!!
መግቢያ
   ክርስትና ድሩም ማጉም፣ ጉልላቱም መሠረቱም፣ ጣርያውም ግድግዳውም፣ ማገርና ድምድማቱም የክርስቶስ ትምህርትና ሕይወት ብቻ ነው። ሕይወትንም ኾነ ትምህርትን፣ ልምምድንም ኾነ አምልኮን መለኪያ ቱንቢያችን፤ መመዘኛው ሚዛናችን ከክርስቶስ በቀር ማንም ምንም የለም። ማናቸውንም ነገር ለክርስቶስ ክብር ብቻ የምናደርግ ከኾነ፣ ለአንድ ጌታ ብቻ መገዛታችንን በግልጥ ማሳየት አለብን፤ (ማቴ. 6፥24)። ኹለት ጌታ ለማስደሰት መጣር ግብዝነትና ተላላነት ብቻ እንጂ ምንም መንፈሳዊ መልክ የለውም። እንዲያውም አንዱን በግልጥ አለመጥላት፣ ፊት ለፊትም አለመናቅ፣ “ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ኹለተኛውንም ይንቃል፤ …” የሚለውን የክርስቶስን ትምህርት እንደ መናቅና እንደ መሻር ይቈጠራል፤ ይህ ደግሞ ግልጥ አለመታዘዝ ነው።

   ብዙዎች በክርስቶስ ብቻ መርካት ስላልቻሉ፣ ሌላ የሚረኩበትን ፍለጋ ሲንከራተቱ እናያቸዋለን፤ ነገሩን መንፈሳዊና ምክንዩ ለማስመሰል ወደ ብሔራችን፣ ወደ አገርና ባህል ወዳድነታችን እናጠጋጋዋለን፤ “ክርስቶስን አያከብርምና ኃጢአት ነው” ስንላቸው፣ “አክራሪ፣ ጸረ ዘመድ፣ ጸረ ቤተሰብ፣ ጸረ ወንድም፣ ጸረ እህት፣ ጸረ ባህል፣ ጸረ አገር” የሚል ታርጋ ይለጥፉብንና ራሳቸውን ያለ ክርስቶስ የጽድቅ መምህራን አድርገው ይቀባሉ! ክርስቶስን ብቻ ለመያዝ የማንለቀው ነገር እርሱ ጣኦት ነው! ምንም ማንምም ቢኾን!
ለምን በመጻረር የማይቆመው “ክርስትና”
   በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዓለምን በመጻረር የቆመ ብርቱ ፓትርያርክ እንደ አትናቴዎስ የተነሣ ያለ አይመስልም። ዓለምን የናቀው ቅዱስ አትናቴዎስ ከመንበረ ፕትርርክናው ከአምስት ጊዜ በላይ ሲሰደድ፣ ከሠላሳ አምስት ዓመታት በላይም ስደትና እንግልት፣ ንቀትና እስርን የጠገበ ብርቅዬ የቤተ ክርስቲያን ልጅ ነው። “አትናቴዎስ - የአለሙ ተጻራሪ” የሚለውን ስም የያዘው፣ ዓለምንና በውስጧ ያለውን ክብር፣ ብእል፣ ሥልጣን፣ ሹመት፣ ሽልማት፣ አንቱታ፣ መወደስና መከበርን … ፈጽሞ በመናቁና በመጸየፉ ለክርስቶስና ለክርስቶስ ትምህርት ብቻ በመቅናቱ ነው።
   ቅዱስ አትናቴዎስ በክርስቶስ ወንጌል ላይ አልሸቃቀጠም፣ አልደበለም፣ በክርስቶስ ወንጌል ላይ የፋነኑትን አርዮሳውያንን በትምህርቱ ዝም፣ ጸጥ፣ ኩምሽሽ እንዲሉ በማድረግ አሳፍሯቸዋል፤ የነገሥታቱ ቁጣ አላስደነገጠውም፤ ነገሥታት ለእርሱ ከለላና ጥበቃ ባለማድረጋቸው አልተከፋም፤ ዓለምን ንቋልና፣ ዓለምም አልተገባችውምና (ዕብ. 11፥37) ቅንጣት ታህል አንዳች ቅር አልተሰኘም። ምክንያቱም እርሱ ከዓለሙ እንደ ተጻረረ፣ ዓለምም ያላትን ጥላቻዋን በሙሉ በእርሱ ላይ ገልጣለችና፣ በእርሷ ዘንድ ስንዝር የምታህል ሥፍራ የለውም። ዓለምም በእርሱ ዘንድ እንደ ጉድፍ የተጣለችና የተናቀች ነበረች።
   በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቤተ ክርስቲያንን የጎዳት፣ የቤተ ክርስቲያን የራስዋ ለዘብተኝነትና ከዓለማዊነት ጋር በዝምታ መስማማት ነው። ፓትርያኮቹ ለምን ይኾን በዝምታ ሽልማቱን የተቀበሉት? [በእርግጥ አውቃለሁ አኹን ያለው የፖለቲካ ጫና እንደማያፈናፍን፤ ግን የተጠራንለት ክርስቶስ ኹሉን አይበልጥምን? “ቄሱ” ለምን በቤተ ክርስቲያኒቱ ስምና ዝና እንደሚሸቃቅጡ ደግሞ አላውቅም፤ በእርግጥ ቄሱ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ይነግድ፣ ያጭበርብር፣ ያምታታ እንጂ “የዋቄፈታ አማኝነቱን” ካረጋገጠ፣ ለክርስትና ያለውንም ንቀት ካሳየ ውሎ አድሯል። አስተውሉ! በቤታችን መጽሐፍ ቅዱስን መስበክ መናፍቅ፣ ተሐድሶ፣ ኢ ኦርቶክሳዊ ያስብላል፤ ዋቄፈታና ኢሬቻን ሰባኪ ግን በክብር አሸልሞ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስምና ማዕረግ እንዲህ ያኮራል፤ ያዘባንናል። እንኪያስ እንዲህ ማለት አንችል ይኾን? ኦርቶዶክሳዊው ክርስትና ከወንጌል ውጪ ላሉ ተግባራት ዕውቅና ይሠጣልን? ወይም በዝምታ መስማማቱን ይገልጣልን? ወንጌል የሰበኩ ታርጋ ተለጥፎላቸው የሚሰደዱ ከኾነ ቄሱ የምን ወንጌል በመስበኩ ነው ዝም የተባለው?
  ከዓለሙ ጋር መስማማት ለክርስቶስ በተቃራኒነት ያስቆማል፤ ዓለምን እጅግ በጥቂቱ እንኳ መውደድ ሙሉ ለሙሉ የአባትን ፍቅር ያጠፋል፤ (1ዮሐ. 2፥15-16)። አለምንና በውስጧ ያለውን በተለይም በክርስቶስ ላይ ተቃዋሚ ኾኖ የቆመውን ማናቸውንም ነገር በግልጥ አለመቃወም በግልጥ መተባበር ነው፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለውን ነገር እንኳን መተባባር፣ በጥቂቱ እንድንታገሰው ፈጽሞ አልተባለልንምና፤ (2ቆሮ. 11፥4) አዎን! “የሰውንም አሳብ በእግዚአብሔርም እውቀት ላይ የሚነሣውን ከፍ ያለውን ነገር ሁሉ እናፈርሳለን ለክርስቶስም ለመታዘዝ አእምሮን ሁሉ እንማርካለን፥” (2ቆሮ. 10፥5) እንጂ፣ አንዳች አንራራም፤ ደግሞም አናመቻምችም፤ አንሸቃቅጥም። ዓለም አትናቴዎስን ከተቃረነች፣ አትናቴዎስ ዓለምን ተጻርሮ ይቆማል!!!
ከአበው  ልዩነት እንጂ መስማማትን እንዴት እንጠብቅ?
   አባቶች በወንጌል ጉዳይ መደራደር የለባቸውም፤ መንግሥትንም ኾነ ማናቸውንም አካል ደስ ለማሰኘት ቅንጣት ታህል መሥራት የለባቸውም። ይልቁን ኹል ጊዜ ከክርስቶስና ከወንጌሉ እውነት ጋር ብቻ በመቆም ሊመጣና ሊደርስባቸው ያለውን መከራ ኹሉ በመታገስ ሊቀበሉ ይገባቸዋል እንጂ። ቤተ ክርስቲያን ከተለሳለሰች የአለሙ መጫወቻ ነው የምትኾነው፤  ይህ ብቻ አይደለም በርኩሰትዋ ዓለምን በመተባበር እግዚአብሔር በዓለሙ ሊሠራ ያለውን ሥራውን በመዝጋት ፍርድን፣ ቁጣንና መቅሰፍትን አለልክ ታበዛለች።
   አባቶች በክርስቶስ ትምህርት ጸንተው መቆም ሲገባቸው፣ እንዲህ ባለ ኢ ክርስቲያናዊና ክርስቶስ በማይከብርበት ሥፍራ መቆማቸው፣ መጠራታቸው፣ መጠራታቸውንና ሽልማታቸውን አለመቃወማቸው … እግዚአብሔርንና ቤተ ክርስቲያንን ያስንቃሉ፤ ያስተቻሉ። እንዲህ ባለ ጉዳይ ቤተ ክርስቲያን በልዩነት እንጂ በመስማማት መቆም አይገባትም፤ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን አምባሳደርነቷ ለክርስቶስና ለእግዚአብሔር ክብር፣ ለሰው ልጆች መንፈሳዊ ጥቅም እንጂ ለሌላ ፋይዳ ፈጽሞ አይደለምና። አበው ሆይ! ክርስቶስን ከማያከብር ከማናቸውም ክፉ ነገር ተለያዩ!

ማጠቃለያ
የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ከመሲሁ የተቀበለችው አንድ ተልእኮ ብቻ ነው፤ ወንጌልን መናኘትና ሰዎችን ለክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ማድረግ፤ (ማቴ. 28፥18-20)፤ ከዚህ ውጪ ቤተ ክርስቲያን የሚበልጥባት ወይም ይዛው የምትሮጠው ደባል ተልእኮ የላትም። ከተልእኮዋ ጋር ለሚቃረን ማናቸውም ነገር ቅንጣት ታህል ዝምድና መፍጠርም የለባትም፤ ብርሃን ናትና ከጨለማ ጋር መተባበር አትችልም። ኢሬቻ ክርስቶስን አያውቅም፤ ዋቄፈታም ክርስቶስን አያከብርም፤ የመጽሐፍ ቅዱስንም ሥልጣን አይቀበልም፤ የክርስቶስን ጌትነት፣ አዳኝነት፣ መካከለኛነት፣ ቤዛነት፣ በኢየሱስ በደሙ መፍሰስም ዓለምን እንደዳነ አያምንም፤ ፈጽሞም አያውቅም። እንኪያስ እንዲህ ባለ የጸሎት ሥፍራ መቆም፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አምልኮውን ለማስማማት፣ ከክርስትናም በላይ እውነተኛ ትምህርት ለማድረግ መጣር እጅግ ክፉ ከኾነ ልብ የሚመነጭ አይደለምን? ደግሞስ፣ በዚህ በኩል የሚመጣን ሽልማትም ኾነ፣ አክብሮት ቤተ ክርስቲያን ለመቀበል ምን ሥልጣን አላት? ማንስ ፈቀደላት? ክርስቶስን የማያከብር እርሷን እንዴት ሊያከብራት ይችላል? ይልቁን እርሷን ያከበሩ በመምሰል የራሳቸውን እምነትና ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንደ ተቀበለች በማስመሰል ሊያስቱ፣ ሊያሳስቱ ይህን አድርገው ቢኾን ማን ያውቃል? ከትውልዱስ ማን አስተዋለ?! ጌታ መንፈስ ቅዱስ ሆይ! ለቤተ ክርስቲያን ማስተዋልን አብዛ፤ አሜን።



[1] በቦታው መገኘት ምን ችግር አለው?” ለምትሉ፦ ጴንጤው የኦርቶዶክስ፣ ኦርቶዶክሱ የካቶሊክ፣ ኦርቶዶክሱ የሙስሊሙ፣ ኦርቶዶክሱ የጴንጤው አምልኮ ላይ ተገኝቶ ወይም ጠንቋይ ቤትም ወጣ ገባ እያሉ ማሳየት እንደሚቀድም፣ “ምን ችግር አለው?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ሳይኾን አይቀርም።

9 comments:

  1. እጅግ በጣም የወደድሁት ወቅታዊና ፈጽሞ ለክርስቶስ ያደላ ጠንካራ መልዕክት ኾኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

    ReplyDelete
  2. ደግሞ ታሀድሶ ብለው እንዳያድዱህ እንጅ አስፈላጊ እና ወቅታዊ መልክት ነው። በኛ ቤት ውስጥ ግን አበውን መገሰፅ ተሀድሶ እያስባለ ነው።

    ReplyDelete
  3. Abenezer teklu Ye Aba አትናቴዎስ በረከታቸው ይደርብህ ለቄሱም አይነ ልቦናቸውን ያብራልን

    ReplyDelete
  4. Ye Addis kidan amagne kehonk lemin Tabor takebralek???

    ReplyDelete
  5. this is also one part of politics in our country individual right and freedom e should changed into politics by those not relay not know ayagebanim tohun selehen libohe nahuu inakahuwalen

    ReplyDelete
  6. yagazetenyohun sime beha yebekanale
    Manage

    ReplyDelete
  7. Sitamu inji sitamnu alayenim. E/r 1 nw . alsemam Irecha wuste new. 1000 ngr kemawerat 1 e/r amno beteseten maninet ena bahil menor.

    ReplyDelete
  8. ደግሞ ታሀድሶ ብለው እንዳያድዱህ እንጅ አስፈላጊ እና ወቅታዊ መልክት ነው። በኛ ቤት ውስጥ ግን አበውን መገሰፅ ተሀድሶ እያስባለ ነው።

    ReplyDelete
  9. ጅብን ሲወጉ በአህያ ከለላ የተደባለቀ እምነት የለም ክርስቶስን በእሬቻ ስም አይመለክም ብቻውን አምላአክ እና ጌታ ነው

    ReplyDelete