Sunday 9 September 2018

ዘመን - የእግዚአብሔር የቸርነት ስጦታ


 ስለበላን ወይም ስለጠጣን፣ ለብሰን ስላማረብን ወይም እናት አባት፣ ጉልበት ስላለን ወይም መውጣት መግባት ስለቻልን፣ የአገራችን መሪዎች ደግ ወይም ክፉ ስለ ኾኑ፣ ደመወዛችን ስለ ተደላደለ ወይም የንግድ ወረታችን ስላማረበት ወይም ስለ ተትረፈረፈ ከዚህ አልደረስንም፤ ደግሞም ይህ የኾነልን በአጋጣሚ ወይም ከሌሎች የተሻለ ጽድቅና መልካምነት ስላለን፣ እንዲሁ ደግሞ ሌሎች ክፉዎችና እጅግ አላስፈላጊዎች ስለ ነበሩ ተወግደው ለእኛ ዘመን የተጨመረልን፣ ዕድሜ የተሰጠን አይደለም። አዎን! በሕይወታችን ዕድል፣ ዕጣ ፈንታ፣ አጋጣሚ፣ ድንገት፣ የአርባና የሰማንያ ቀን ጽዋ የሚባል ነገር ተሳክቶልን ከዚህ አልደረስንም።

 በቸርነቱ ዓመትን የሚያቀዳጅ፥ ምድረ በዳውን ስብ የሚያጠግብ፣ የምድረ በዳ ተራሮችን የሚያረካ፥ ኮረብቶችንም በደስታ የሚያስታጥቅ፣ ማሰማርያዎች መንጎችን የሚለብሱት፥ ሸለቆችም በእህል የሚሸፈኑት፤ በደስታ ጮኸው የሚዘምሩት” (መዝ. 65፥11-13) ከእግዚአብሔር የተነሣ ብቻ ነው። ስለዚህም እንኳን እኛ፣ ግዕዛን ዓመታትን በዘላለም ዕቅዱ የሚያቀዳጀው ማን እንደ ኾነ “ያውቃሉ”፤ ከሰው ልጆችም ጋር ስለ በረከቱና ስለ ማዳኑ በዝማሬ  ሊወድሱት፣ ሊያሸበሽቡለት፣ ጮኸው ሊያመሰግኑ ይሰለፋሉ፤ እግዚአብሔር በአገዛዙ ቡሩክ ነውና፤ “ሰማያትና የዱር ዛፎች፣ ተራሮች ደስ እያላቸው፣ ምድርና በረሃው በሐሴት (መዝ. 96፥11-12)፣ ወንዞች በጭብጨባ (መዝ. 98፥8)፣ ሥራዎቹ፣ በግዛቱ ያሉ ፍጥረቶች ኹሉ በባርኮት (መዝ. 103፥22፣ 145፥10)፣ የአጥቢያ ኮከቦች በአንድነት ይዘምሩለታል (ኢዮብ 38፥7)፣ የምድር ጥልቅ በጩኸት፣ ተራራ፣ ዱሩና ዛፉ በእልልታ ይዘምሩለታል፣ (ኢሳ. 44፥23፤ 49፥13፤ 55፥12)።
   እግዚአብሔር አስቀድሞ የኪዳኑን በረከቶች በሙሉ ለእስራኤል ሕዝቡ ሰጥቷል፤ ከኪዳኖቹ አንዱ ደግሞ ውሃ ነው፤ ይህም የክረምት ዝናም። ክረምት ከመምጣቱ በፊት ማሳዎች ለእርሻ ይዘጋጃሉ፤ በተዘጋጁት እርሻዎች ላይ እግዚአብሔር የተዘራውን ዘር በውበት ያበቅላል፤ በመብቀሉ ደስ የተሰኙት ሕዝቡ፣ በጸደይ ወራት እህሉ ሲፋፋና ፍሬውንም ሲመለከቱ እጅግ ደስ ይሰኛሉ፤ በስብና በጥጋብ ይመላሉ፤ ሕዝቡ ብቻ ሳይኾን መላው ሥነ ፍጥረት ከበረከቱ ይካፈላል፤ በዚህም ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር በመኾን በአዳኙ ያህዌ እጅግ ደስ ይላቸዋል፤ ምስጋናም ያቀርባሉ።


  ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት፣ እስራኤል አኹን የአዳኙን ያህዌ ቸርነት እንዳላስተዋለች ይናገራል፤ አንዳንዴ እንደውም ሉዓላዊነቱንም ጭምር በመፈታተን ላለመገዛት የምትጥርበት ሂደት አለ፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ኹሉን ይገዛል። ድንቁን በማሳየት ኃይሉን ይገልጣል፤ ስለዚህም ሥራውን ልታከብረውና ልትፈራው ይገባት ነበር። አዎን! ከምንም በላይ ባደረገውና ባመጣው ልምላሜ፣ ጥጋብ፣ ሰላምና ፍትሕ እስራኤልና ሕዝቦቿ ኹሉ በደስታ እልል ብለው ሊያመሰግኑት፣ ሊያመልኩት ይገባቸዋል። በእውነት እግዚአብሔር አምላክና ፈጣሪ፣ አዳኝና በቸርነቱ ወደር የሌለው፣ በመጋቢነቱና በባርኮቱ አቻ የለውና።
የእግዚአብሔር በጎነትና ምሕረት እጅግ የተትረፈረፈ ነው፤ ቢመሻሽም፣ ለጊዜው እስራኤል ፈጥና ባትረዳውም፣ ኋላ ላይ ግን በጎነቱንና መልካምነቱን አስባ ለምስጋና ትነሣለች፤ ሥራዎቹ ድንቅ፣ ማዳኑም እጅግ ታላቅ፣ መልካምነቱም የተትረፈረፈ ነውና። እግዚአብሔር ይህን ያደረገው በዘመናት ዕቅዱ ምድርን እጅግ አድርጎ እየጠበቃትና ሁል ጊዜ ሳያቋርጥ ሲጠብቃት በሥራ ላይ መኾኑን በማሳየት ነው። እርሱ ሕዝቡንና ፍጥረቱን ኹሉ በማዳንና በመመገብ ኃይሉን የታጠቀ ነውና፤ ክብር ይኹንለት፤ አሜን። ይህንም እግዚአብሔር በመልካምነቱ አደረገ።
  ዘመን የእግዚአብሔር የመልካምነቱና የመጋቢነቱ ስጦታ ነው፤ ስጦታነቱም የተሰጠን ለአኹን ነው። ከአኹን በኋላ ምን እንደምንኾን አናውቀውም፤ የተጨመረልን ዓመት ማለትም 2011 ሙሉው አይደለም፤ የተጨመረልን አኹን ነው፤ “በተወደደ ሰዓት ሰማሁህ በመዳንም ቀን ረዳሁህ ይላልና፤ እነሆ፥ የተወደደው ሰዓት አኹን ነው፤ እነሆ፥ የመዳን ቀን አኹን ነው፤” (2ቆሮ. 6፥2) የሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንባብ የተጨመረልን አኹን እንደኾነ ነው የሚነግረን። አሁን የተባለው ሰዓት በተለይ በአዲስ ኪዳን በክርስቶስ ቀዳማይ ምጽአቱ በልደቱና በዳግም ምጽአቱ መካከል ያለው ጊዜ ነው ብለን መውሰድ እንችላለን፤ ከመጀመርያ መምጣቱ በፊት የነበሩት የብሉይ ኪዳን አማኞች ኹሉ፣ በክርስቶስ የተፈጸመውን ተስፋ አስቀድመው በመናፈቅ ተቀበሉ፤ ከሩቅ አይተውትም ልክ ተስፋው ሲፈጸም ገንዘባቸው አድርገውታል፤ (ዮሐ. 8፥56፤ ዕብ. 11፥13)።
  ዓመትን፣ ወርን፣ ቀንን፣ ሰዓትን፣ ሽርፍራፊ ሰከንድን ጭምር ሳይቀር ጌታ የሚጨምርልን በዘላለም ዕቅዱ ሊሠራ ያሰበውን የሰው ልጆችን ማዳን ለመፈጸም ነው። በተለይ በአዲስ ኪዳን የእግዚአብሔር ዘመን የመጨመር ዋና ዓላማው ከጥፋት ልጅ በቀር ኹሉ ይድኑ ዘንድ ነው፤ (ዮሐ. 17፥12)፤ ከእግዚአብሔር የተቀበልነው ትልቁ ስጦታችን ዘመን ወይም ዕድሜ ነው፤ ስለዚህም ለእግዚአብሔር ከዕድሜያችን ያነሰ ስጦታን ፈጽመን አንሰጠውም፤ እግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁ በመላ ዘመኑ እርሱንና እኛን በማገልገል ዘመኑን ለመዳናችን ሰዋው፤ ጌታችን ኢየሱስ ነፍሱን እንኳ ሳይቀር ለእና በመስጠቱ አልሳሳም፤ እኛም ከዕድሜያችን ያነሰ ስጦታ ለወደደንና ለሞተልን ጌታ ልንመኝ ወይም ልንሰጥ አይገባንም።
  የወራት መፈራረቅ፣ የዓመታት ሽክርክሮሽ፣ የሰዓታትና የሽርፍራፊ ሰከንዶች ፍጥነት፣ የምድር በጸደይና በክረምት መዋብና መደፍረስ፣ የበጋው ጥራት … በልተን፣ ጠጥተን፣ ደረት አቅልተን፣ ተደላድለን፣ ተለዳልደን እንድንቀመጥበት ብቻ የተሰጠን አይደለም፤ ዘመን ስጦታ ነውና፣ “እግዚአብሔር ያለማወቅን ወራት አሳልፎ አኹን በየቦታቸው ንስሐ ይገቡ ዘንድ ሰውን ሁሉ ያዛል፤ ቀን ቀጥሮአልና፥ በዚያም ቀን ባዘጋጀው ሰው እጅ በዓለሙ ላይ በጽድቅ ሊፈርድ አለው፤ ስለዚህም እርሱን ከሙታን በማስነሣቱ ሁሉን አረጋግጦአል።” (ሐዋ. 17፥30-31) እንዲል፣ እግዚአብሔር ጣዖት በማምለክ እርሱን ንቀው የነበሩ ግሪካውያንን እንኳ የታገሰውና ዘመን የሰጣቸው በንስሐ ወደ እርሱ እንዲመለሱ ነው።
   እግዚአብሔር ጥልቅ ድንቁርናን፣ አለማስተዋልን፣ ዓመጸኝነትን፣ ፍጹም አመንዝራነትን፣ የድፍረት ኀጢአትን፣ እርሱንና መንግሥቱን በመናቅ የሚፈጸመውን ኀጢአት ኹሉ ፈጽሞ የታገሰው ለንስሐ በመጠበቅ ነው፤ አዎን! ያለፈው ዘመን በደልና ኀጢአታችንን ቸል ብሎ አልፎታል፤ በልጁ ደምም ሊያጥበው ኪዳን ገብቷል፤ ከታላቅ ምሕረቱም የተነሣ ይቅር ሊለን ወድዷል፤ ነገር ግን ባንመለስ፣ ብናምጽ፣ በኀጢአታችን ብንደነድን እግዚአብሔር ይፈርዳል፤ የሰጠንንም የዘመን ወይም የዕድሜ ስጦታ መውሰድ ሥልጣን አለው፤ ይወስደዋልም፤ (ራእ. 2፥5)። ስለዚህ ንስሐ እንድንገባ ዘመን ሰጥቶ ያዘዘንን ጌታ፣ በማስተዋል ልንሰማው ደግሞም ልንታዘዘው ይገባናል፤ የተጨመረልን ድንቅ ዓመት ወይም አኹን የተባለው ጊዜ፣ ወድደን ለወደደን ጌታ በሚታዘዝ ልብ ልንሰጠው፤ ንስሐ በመግባትም መመለሳችንን በተግባር ልናሳይ ይገባናል።
  ብዙዎች በአዲስ ዓመት አዳዲስ ነገሮችን እንዲሁም መጥፎ ተግባሮቻቸውን ትተው፣ መልካሙን ለማድረግ ቃል ይገባሉ፤ ነገር ግን ሳይለወጡ ሌላ ዘመን ይመጣባቸዋል። አንድ የዘላለም እውነት እንንገራችኹ፤ ለክርስቶስ ወንጌል በመታዘዝ፣ ንስሐ በመግባት፣ ከኀጢአት ዝንባሌ ነጻ ለመውጣት በቅዱስ ቃሉና በመንፈስ ቅዱስ ብንታመን፣ በክርስቶስ በደሙም ብንታጠብ ከማናቸውም የክፋት ዝንባሌ ነጻ ሊያደርገን የሚቻለው የታመነ አምላክ አለን፤ ዘመናችንን ለእርሱ አደራ በመስጠት እንታመንለት፤ እርሱ በእኛ የወደደውን እንዲያደርግ እንገዛለት፤ የዚያኔ ጌታ እግዚአብሔር ነገርን ኹሉ ውብ አድርጎ በእኛ ይሠራል፤ አሜን። ጌታ ሆይ! የሰጠኸን ዘመን በፊትህ ስንጓደድ፣ ስናመልክህ፣ ስናገለግልህ ይለቅ፤ አሜን።

3 comments: