6.
የመንፈስንም ሰይፍ
ያዙ፦
ሰይፍ፣ “ከብረት የሚሠራ የጦር መሣርያ፤ (1ሳሙ.13፥19 ፤ 22)፡፡ አንዳንዱ ሰይፍ ባለሁለት አፍ ነው፤ (መዝ.149፥6)፡፡”[1] ሰይፍ ከማይታዩ
ከክፉ ኃይላት ጋር አማኙ ለሚያደርገው ጦርነት በዋናነት የሚጠቀምበትና ከማጥቂያ መሣርያዎች የሚካተት ነው፡፡ ወታደር ዘወትር ከሚይዛቸው
መሣርያዎችና ጥብቅ ስልጠና ከሚወስድበት አንዱ ስለሰይፍና አጠቃቀሙ ነው፡፡ በዚህ ክፍል በሰይፍ ምሳሌነት የቀረበው “እርሱም የእግዚአብሔር
ቃል ነው” ተብሎ የተነገረው ነው፡፡
ሰይጣን ከምንም በላይ በእግዚአብሔር ቃል
ላይ ያለንን መታመን ዋጋ ለማሳጣት ወይም ለማጥፋት በኹለንተናው የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል፤ “እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን
ቃል በልብህ ያዝ፡፡ ለልጆችህም አስተምረው፥ በቤትህም ስትቀመጥ፥ በመንገድም ስትሄድ፥ ስትተኛም፥ ስትነሣም ተጫወተው፡፡
በእጅህም ምልክት አድርገህ እሰረው፤ በዓይኖችህም መካከል እንደክታብ ይሁንልህ፡፡ በቤትህም መቃኖች በደጃፍህም በሮች ላይ ጻፈው፤”
(ዘዳግ.6፥6-9)፣ “በልብህ ጽላት ጻፋቸው” (ምሳ.3፥3 ፤ ኤር.31፥33)፣ “እንድንሰውራቸውም” (መዝ.119፥11)
የታዘዝነውን የእግዚአብሔር ቃል ሰይጣን እንድንጥለው ብርቱ ጥረት ያደርጋል፡፡ ቃሉን በመጣል ውስጥ ያለውን ቀላልና አስቀያሚ ሽንፈት
ዲያብሎስ በሚገባ ያውቀዋል፡፡
ሰይጣን ቃሉን በልባችን እንዳንሰውረው ብቻ ሳይኾን፣ እንዳናነበውም ልባችንን
በማባከን፤ ተላላም በማድረግ በብዙ ይተጋል፡፡ ሰዎች ቃለ እግዚአብሔርን ከማንበብና ከማጥናት ይልቅ በሌሎች ነገር ሲባክኑ ውጊያና
የሰይጣን ተንኮል እንደኾነ አያስተውሉም፡፡ ቃሉን ዕለት ዕለት አለመመገብ ለመንፈሳዊ እድገት መቀንጨር ዋና ምክንያት ነው፡፡
ይህን ግን በትክክል የሚያስተውሉት ከቃሉ ጋር ቀጥተኛ ትስስር ያላቸውና ከቃሉ የሚገኘውን በረከት ቀምሰው የተረዱ ብቻ ናቸው፡፡
ከምንም በላይ ደግሞ
በዚህ ዘመን፣ የእግዚአብሔር ቃል “የእግዚአብሔር እስትንፋስ አይደለም” ከሚለው ከንቱ ሃሳብ ካላቸው ሰዎች መከልከል አለብን፡፡
ከወትሮው በተለየ መጽሐፍ ቅዱስን እንደአንድ መጽሐፍ እንዲታይ ለማድረግ ብዙ ጥረት ሲደረግ እያየን ነው፤ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ
የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ የእግዚአብሔር እስትንፋስ ስላለበትም(2ጢሞ.3፥16) እያንዳንዱ የውጣ ቃል ሕጸጽ አልባ፣ እንከን አልባና
ፈጽሞ እውነት ነው፡፡ መዳናችንንና ሐለወተ እግዚአብሔርን በመናገሩ ብቻ ሳይኾን፣ ታሪክንና ዓለማትን በተመለከተም የዘገበው ሁሉ
እውነትና ፍጹም ትክክል ነው፡፡
የመለኮት እስትንፋስ ያለበትና ዘመን ተሸጋሪ ስለኾነም በእርሱ ላይ በየዘመኑ
የተነሡትን ተቃዋሚዎች ሁሉ ድል እየነሣ፤ እያሳፈረ እስከጌታ ዳግመኛ መምጣት ለዘላለም ይኖራል፡፡ እንግዲህ “ያዙ” የተባልነው፣
መቼም መች የማይለወጠውንና ከቃሉ መካከል አንዲት ቃል እንኳ የማታልፈውን ይህን ቅዱስ ቃል ነው፤(ማቴ.5፥18 ፤ 24፥35)፡፡
ጌታ ኢየሱስ እና ሐዋርያት እስትንፋሰ እግዚአብሔር ላለው ለእግዚአብሔር
ቃል ሲናገሩትና በተግባር ሲተረጉሙት ፍጹም ታማኝነትን አልተውም፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትና በክርስቶስ የሚያምኑ ቅዱሳን ሁሉ በትክክል
በሕይወታቸው ለውጥ እንዲያመጣ በመፍቀድና በመታዘዝ ታማኝነታቸውን አሳይተዋል፡፡ ይህም ማለት ቃሉ ለመገሰጽ፣
ለማስተካከል(ለመምከርና ለመገሰጽ)፣ ለመቤዠት፣ ለመፈወስ፣ አጋንንትን ለማስወጣትና ክፋትን ሁሉ ለማሸነፍ ያለውን ኀይል አላሳጡም
ማለት ነው፡፡ ብዙዎች የኢየሱስን ስም በመጥራት ለሚያስተምሩት “ሰባኪያን ሁሉ” ለትምህርቶቻቸውና ለትእዛዞቻቸው ሁሉ ከእግዚአብሔር
ቃል ይልቅ ሲታዘዙና ሲያደርጉ እናያለን፤ ይህ ግን ለቃሉ ባለመታዘዝ ለእግዚአብሔር ታማኝነታችንን ማጉደላችንን የሚያሳይ ነው፡፡
ወንጌል አገልጋዩን አገልጋይ ልክ እንደኢየሱስ አልታዘዝንም፤ የሚናገረውን ቃል ሁሉ ግን ከጌታችን ቃልና ትምህርቶች ጋር በመመርመር
አንድ ኾኖ ስናገኘው ልንቀበለው ይገባናል እንጂ፡፡
ዘወትር መዘንጋት የሌለብን ነገር፣ መጽሐፍ ቅዱስ
ለሚሰጠው ትምህርት ሁሉ ፍጹም ትክክል መኾኑን መካድ ማለት፣ ራሳችንን ለሰይጣን ክንድ አሳልፈን መስጠት ማለት ነው፡፡ ቃሉ ፈጣሪና
አስገኚ፣ በምድር ላይ ካሉ ማናቸውም ኃይላት ይልቅ የሚበልጥና ተካካይ የሌለው፣ ፍጹም ትክክልና ለእውነተኛ ሕይወት
መንገድ የኾነ ነው፡፡ ይህንን አለመቀበል ለክፉውና ለአስጨናቂው፤ ወደርኩሰት ሁሉ ለሚመራው ሰይጣንና መልእክተኞቹ ንግግሮችና ትምህርቶች
በገዛ ፈቃዳችን ልባችንንና ፈቃዳችንን አሳልፈን መስጠታችንን ያሳያል፡፡ ለሰይጣን ላለመመቻቸትና ባገኘን ጊዜም ሁሉ ድል እንዳይነሣን
ቃሉን መታጠቅና መያዝ ምንም አማራጭ የሌለው ነገር ነው፤ ምክንያቱም የቅዱስ ቃሉን ሰይፍ ከያዝን በማንኛውም ጊዜ የማሸነፍ ኃይል
ሁሉ ከእኛ ጋር ነው፡፡
ለዚህ ደግሞ፣
ዘወትር መንፈስ ቅዱስ ቃሉን ለልባችንና ለመንፈሳችን ያስታውሰናል፤ ደግሞም ልክ የዚያኔ ክርስቶስ እንደተናገረው ዛሬም
ያስተምረናል፤ (ዮሐ.6፥45 ፤ 14፥26)፡፡ ይህንንም ዘወትር ተግተን በመጸለይ፣ ቅዱስ ቃሉን በማንበብ፣ በማሰላለሰል ከመንፈስ
ቅዱስ ልንማር፤ ልናስተውልም ይገባናል፡፡ ይህን በማድረግና ቃሉን በመያዝ እንድናሸንፍ የእግዚአብሔር ዕቅድ ነው፤ ጌታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ቃሉን በመያዝ ሰይጣንን ድል በመንሣት ታላቅ ምሳሌ ኾነን፤ (ማቴ.4፥1-11)፡፡
የእኛን
ሁለንተና ማንነት ያለአድልዎ የሚፈትሸውና መንፈሳዊ እንሁን አንሁን በትክክል የሚናገረን ቅዱስ ቃሉ እንደኾነ ቅዱስ ጳውሎስ፦
“የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና
ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ ይወጋል፥” (ዕብ.4፥12) በማለት ተናግሯል፡፡ ስለዚህም የእግዚአብሔር ቃል፦
1.
ቅዱሳን ነቢያት፣ የጌታችን ኢየሱስ ንግግሮችና ሐዋርያትና ሌሎችም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጻፉት
ሁሉ የእግዚአብሔር ቃል ናቸው፡፡ የማይበላለጡና ሁሉም በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ገላጭነት የተጻፉና እኩል ክብር ያላቸው ናቸው፡፡
የትኛውም መንፈሳዊ ክፍል ከየትኛውም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በእውነትነቱ አይበልጥም፤ ደግሞም አያንስም፡፡
2.
እኛ በክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችን የምናምን ሁላችን፣ “ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፥
በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ፤” (1ጴጥ.1፥23) እንዲል በአዲስ ልደትና ሕይወት፤ የሕይወት
ቃል ከኾነው ከክርስቶስ ተወልደናል፤ (1ዮሐ.1፥1)፡፡
3.
ስለዚህም ዘወትር ከዲያብሎስ ጋር ስንዋጋ እንደጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ “ተጽፎአል” በማለት ልንመልስለት፣
ልንዋጋውና ድል ልንነሣው ይገባናል፡፡ ጌታችን “ተጽፎአል” በማለት ለዲያብሎስ የመለሰው ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት የተነገረውንና
የተጻፈውን ቃል ነው፤ ይኸውም የቃሉን ዘመን አይሽሬነት በትክክል ይገልጣል፡፡
4.
በመንገዳችን ሁሉም፣ ቃሉን ለመስማት የምንጓጓ (ኢሳ.1፥10)፣ ለመረዳት በብዙ የምንጥር (ማቴ.13፥23)፣
ቃሉን ልንወደው (መዝ.119፥16)፣ ቃሉ የሚለንን ሁሉ በፍጹም ልባችን ልንቀበል (ማር.4፥20 ፤ 1ተሰ.2፥13)፣ የሚለንን ሁሉ
ልንታዘዘው(መዝ.119፥17፤ ማቴ.5፥17 ፤ ዮሐ.14፥21 ፤ ያዕ.1፥22) … ይገባናል፡፡
5.
ቅዱስ መጽሐፍ የሚለንን በትክክል ለመረዳት ደግሞ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የጠበቀና በንስሐ የቀና ግንኙነት
ሲኖረን ብቻ ነው፡፡ ቃሉን ሊያበራልን፣ ፍቺውን ሊገልጥልን፣ የቃሉ ሙሉ ሥልጣንነት እንድንቀበል የሚያደርገንና ሕይወታችን እንደቅዱስ
ቃሉ ሃሳብ ለክርስቶስ የሚገርዘው መንፈስ ቅዱስ አምላካችን ነው፡፡
ስለዚህ ከምንም
በላይ ቃሉን ከማናቸውም ነገር በላይ ልንከብረውና እንዳለንም ልንታዘዘው ይገባናል፡፡ ደግሜ እላለሁ፦ ቃሉን ከነቢያት፣
ከሰባክያን፣ ከትንታኔዎች፣ ከማብራሪያዎች፣ ከትርጉሞች …. በላይ ልናከብረው እኒህንም ሁሉ በቃሉ ሚዛንነት ልንመዝናቸው ይገባናል፡፡
አልያ ግን “ያዙ” የተባልነው ቃሉን በትክክል ያልያዝን መኾናችንን መዘንጋት የለብንም፡፡ ከማናቸውም ማብራሪያዎችና ስብከቶች ይልቅ
ከቃሉ ጋር ቀጥተኛ የኾነ ዝምድና ሊኖረን ይገባናል፡፡
በተለይም “መንፈሳዊ
ቻናሎችንና ስብከቶችን” ስንሰማ ሁሉንም መስማት ያይደለ፣ የምንሰማውን ልንመርጥ፣ ማንን እንደምንሰማ መጠንቀቅ ይገባናል፡፡
ስንሰማም ሰባኪውን፣ መምህሩን …ዝም ብሎ ከመስማት ይልቅ የተናጋሪውን ቃሎች ሁሉ እንደመጽሐፉ መኾኑንና አለመኾኑን፤ በትክክል መባሉንና
አለመባሉን ከመጽሐፉ ቃሎች ጋር የማስተያየትና ገልጦ የማየት ልማድ ቢኖረን እጅግ መልካም ነው፤
ይህን ስናደርግ ከአገልጋዩ ይልቅ ለተናጋሪው ጌታ በትክክል ክብርን እንሰጣለን፡፡ ጌታ መንፈስ ቅዱስ በነገር ሁሉ ማስተዋልን ያብዛልን፤
አሜን፡፡
ይቀጥላል
…
No comments:
Post a Comment