Please read in PDF
1. እንጸልይ፦ ጸሎት ሰባተኛው መሣርያ አይደለም፡፡ ከስድስቱም ጋር በአንድነት ዘወትር የምንታጠቀው ነው እንጂ፡፡ ስለዚህም እንደሰባተኛ ራሱን የቻለ መሣርያ አድርገን የምንቆጥረው አይደለም፡፡ ጸሎትን ዘወትር በትጋት መታጠቅ ይገባናል፡፡ ለክርስቲያን ጸሎት ዋና መንፈሳዊ መሣርያው ነው፡፡ ማናቸውንም መልካም ነገሮችን በጸሎት ልንጀምር፤ በጸሎትም ልንጨርሳቸው ይገባናል፡፡ “በጸሎትና በልመናም ሁሉ ዘወትር” የሚለው ቃል ስናጠቃም ኾነ ስንከላከል ጸሎት መሠረታዊና በማናቸውም ሰዓትና ሁኔታ ውስጥ ዘወትር መከናወን ያለበት ነገር እንደኾነ ያስገነዝበናል፡፡
አዎን! በመንፈስ ቅዱስ ማስተዋል
ልናደርገው የሚገባን ጸሎት፣ በአማናዊው ሰማያዊ ሥፍራ “ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም
ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር” ለሚደረገው ጦርነት አካል ኾኖ መቆጠር አለበት
እንጂ፣ ለራሳችንም ኾነ ለሌሎች ወንድሞቻችን ድል በተገኘልን ጊዜ ብቻ የምናቀርበው አንድ መሣርያ አይደለም፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር
አብረን በመሥራት ላይ ሳለን ሁሉንም መንፈሳዊያን መሣርያዎች ብንጠቀምም፣ ከምንም በላይ ግን ሁሉንም መሣርያዎች በጸሎት መልበስ ይገባናል፤ ጸሎት ከመሣርያዎቹ አንዱ ሳይኾን፣ ከሁሉም መንፈሳውያን ጋር የሚለበስ ነው፤
ስለዚህም ጸሎትን በመንፈስ ቅዱስ እውነትና ማስተዋል ለመጸለይ መታጠቅን መርሳት አይገባንም፡፡
ለእግዚአብሔር የመፈጠራችን መገለጫ ከኾኑት አንዱ
ወደእርሱ መጸለያችንና የመለኮትን እርዳታ መፈለጋችን ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት ጸሎት ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል፤ ለዚህም
ነው እግዚአብሔር ወደእርሱ እንድንጸልይ ያዘዘን፡፡ ወደእርሱ በምንጸልይበት ወቅት በመቃተት
እንድንጸልይ መንፈሱን ሳይሰስትም ይሰጠናል፡፡ “እንዲሁም ደግሞ መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥
ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤” (ሮሜ.8፥26)፡፡ መንፈስ ቅዱስ ክርስቶስን በሚያምነው አማኝ ሕይወት
ውስጥ ከሚሠራቸው ሥራዎች ትልቁ ሥራ፣ በነገር ሁሉ አብሮ መቃተቱ ነው፡፡ በማናቸውም ውጊያ ውስጥ የመንፈስ ቅዱስ መቃተት ከአማኙ
ጋር ከኾነ በመከራውና በውጊያው ሁሉ አማኙን ያጸናዋል፤ ያቆመዋል፡፡ አማኙ መከራውንና ሃዘኑን ሁሉ በመርሳት በፍጹም ደስታ የሚዋጠው በውስጡ ከሚቃትተው እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ነው፡፡
ጸሎትን በተመለከተ መንፈስ ቅዱስ አጋዥና ደጋፊ፣ አብሮን መከራችንንና
ሃዘናችንን በመጋራት አጽኚና አጽናኛችን ነው፡፡ ይህንን ቅዱስ ጳውሎስ በሚገባ በሕይወት ልምምድ ስለሚያውቀው፣ በየትኛውም የውጊያና
የመከራ መንገድ ውስጥ “በመንፈስ ጸልዩ፤ በዚህም አሳብ ስለ ቅዱሳን ሁሉ እየለመናችሁ በመጽናት ሁሉ ትጉ፤” በማለት ይመክረናል፡፡
በሚገጥመን መከራና ውጊያ ሁሉ እንዳናዝንና የልብ ስብራት እንዳይገጥመን ታላቁ ረዳታችንና አጋዣችን አብሮን ቃታቹ መንፈስ ቅዱስ
ነው፡፡
እግዚአብሔርም የምላሹን አጸፋ በመግቦቱ ውስጥ ያሳየናል፡፡ አንዳንድ ጸሎቶቻችን
ወዲያው መልስ ላይኖራቸው ይችላል፤ የዚህ ምክንያቱ ሁለት ሊኾን ይችላል፤ እግዚአብሔር የሚሰጠንን ነገር እጅግ አስፈላጊነቱን እንድናስተውል
አንደኛው ምክንያት ሊኾን ይችላል፤ አንዳንድ ጸሎታችን አሁን ቢደረግ ለመንፈሳዊ ነገራችን ምንም እርባና ላይኖረው ይችላል፤ ሁለተኛው
ሊሰጠን ያለው ጊዜው ገና መኾኑን ሊያሳየንና የሚበልጠው ክብሩን ሊያሳየን ሊኾን ይችላል፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔር በመዘግየት ውስጥ
ያለውን የመከራ መታገስ እንዲሁም የቆየና የበሰለ በረከትን እንድናጣጥም ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ ጸሎታችን ያልተመለሰበትን ምክንያት
እያሰብን ከመብሰክሰክ፣ ሰምቶ በእሳት የሚመልሰው አምላክ ለእኛ ጥቅም ለጊዜው እንዳልሰጠን ማስተዋል ታላቅ መንፈሳዊነት ነው፡፡
እኛ አማኞች
ዘወትር ማድረግ የሚገባን ተስፋ ሳንቆርጥ ተግተን መጸለይ ነው፡፡ አንዳንዴ ከመከራ ስለመውጣትና በሕይወታችን ያለው ሰልፍ ቶሎ እንዲጠናቀቅ
ልንጸልይ እንችላለን፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ፈቃዱ ጸሎታችንን ሰምቶ መልስ ከመስጠት ይልቅ እኛን በመደገፍ መከራውን ታግሰን
እንድናልፍና ድል በማድረግ ትእግስትን እንድንማር ማድረግ ሊኾን ይችላል፡፡ ስለዚህም ዘወትር ጸሎት እንዴት እንደሚሠራ ባናውቅም
“ከእኛ ይልቅ የእርሱ ፈቃድ እንዲሆን በመማለድ” ተግተን በፍቅርና በመንፈስ ኾነን መጸለይ አለብን፡፡
ጸሎት ልማዳዊ ድርጊት አይደለም፤ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል፣ በማንኛውም ጊዜና ዓይነት ዘወትር የምናደርገው ታላቅ መንፈሳዊ ተግባር ነው፡፡ “መጸለይን በመተው ቅዱስ እግዚአብሔርን መበደል”
አይገባም፤ (1ሳሙ.12፥23)፡፡ ደግሞም ስንጸልይ በውጊያው ውስጥ ላሉትና ቀስት ለተቀሰተባቸው ቅዱሳን[ክርስቶስን በማመን ለጸኑና
በምግባራቸውም ክርስቶስን ለሚገልጡና በንስሐ መንገድ ለሚመላሱ] ሁሉ መጸለይን መተው የለብንም፡፡ የምንጸልየውም በክርስቶስ በስሙና
በእርሱ መካከለኝነትና፣ እንዴት መጸለይ እንዳለብን በሚመራን በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት እንጂ እኛ ተዘልለን “ጸልዩልኝ” በሚል
የስንፍና ወንበር ላይ በመቀመጥ ሊሆን አይገባንም፡፡ ሌሎች እንዲጸልዩልን መጋበዝና “መለመን” ያለብን የአገልግሎታችን ጤናማነት
እንዲጠበቅ ነው እንጂ ፈጽሞ እኛን ተክተው ሁሉን ነገር እንዲያከናውኑ አይደለም፡፡
በመንፈሳዊው አለም አለመጸለይ ለጠላት ተመቻችቶ መገኘት ነው፤
ለራሳችንም ሆነ ለወንድሞቻችን በብዙ መጸለይ አለብን፤ መጸለይን ስንተው ግን እኛ ወይም እነርሱ ልንሸነፍ እንችላለን፤ ባለማቋረጥ
ስንጸልይ መከራዎችን ሁሉ ልንቋቋምና ድል ልንነሣ የሚያስችል አቅም እናገኛለን፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ “ሰው ሁሉ ለጸሎት በሚቆምበት”
በዚህ ዓለም ላይ በክርስቶስ አምኖ በስሙ አብን መለመንና መማለድ እጅግ ታላቅ ማስተዋልና ጥበብ ነው፡፡
2.
ከሐሰት መምህራን እንጠበቅ፤
አገልጋይ ለጌታው
እንጂ ለራሱ አይኖርም፤ የተገዛ ነውና የአገልጋዩ ሕይወትም ጭምር የጌታው እንጂ የእርሱ አይደለም፡፡ እጅግ መልካም አገልግሎትን
ቢያገለግል እንኳ አገልጋይ፤ አገልጋይ እንጂ ክብሩን ለራሱ የመውሰድ መብት የለውም፡፡ ሙሴና አሮን በመሪባ እንደባርያ ጌታን አልቀደሱትም፤ መታዘዝ ባለባቸው ልክ ስላልታዘዙ ጌታ እግዚአብሔር፣ “በእስራኤል ልጆች መካከል በጺን
ምድረ በዳ በቃዴስ ባለው በመሪባ ውኃ ስለ በደላችሁኝ፥ በእስራኤልም ልጆች መካከል ስላልቀደሳችሁኝ፥ … ” (ዘዳግ.32፥51) በማለት ፍጹም በማዘን ተናግሯቸዋል፡፡ የአገልግሎቱን ክብር መውሰድ የሚገባው ጌታ
እግዚአብሔር ኾኖ ሳለ እነርሱ ግን የጌታን ክብር ለራሳቸው ወሰዱ፡፡ ሙሴና አሮን ይህን ለጥቂት ጊዜ ቢያደርጉትም ይህን ክፍ
ተግባር የኑሯቸው ዘይቤ በማድረግ ነውራቸውን አልጨመሩም፡፡
በዚህ ዘመን ግን እንዲህ ያለውን አሮናዊና ሙሴያዊ ተግባርን[ከእግዚአብሔር
ይልቅ ራስን የመቀደስ መንገድ] እንደኑሮ ዘይቤ አጽንተው የያዙና ይኸው መገለጫቸው የኾኑ አያሌ የሐሰት መምህራን አሉ፡፡ እኒህ
ለቁጥር የሚታክቱ አገልጋዮች ኢየሱስን ከማሳየት ራሳቸውን፣ ክብሩንም “ለጌታቸው” ክርስቶስ ከማቅረብ ይልቅ ለራሳቸው
ሲያግበሰብሱት በአደባባይ እያየን ነው፡፡
አስተውሉ! ጌታችን ኢየሱስ ለሰውነታችን እጅግ
ስለሚጠነቀቅ ራሱን አሳልፎ ሰጥቶናል፤ ዋጅቶናልም፤ (1ቆሮ.6፥19)፡፡ ስለዚህም ኑሯችንም ኾነ ሕይወታችን ለእርሱ ክብር
የተሠዋ ነው፡፡ የሐሰት መምህራን ራሳቸውን ከሚያገኑበት መንገድ አንዱ ራሳቸውን ሕያውና ቋሚ አድርገው መሞገታቸውና መከራከራቸው
ነው፡፡ አማኝም ኾነ አገልጋይ በክርስቶስ ሲያምን ለዚህ ዓለም ነገር ሁሉ የሞተና ያልተገባ፤ ከክርስቶስም ጋር በመስቀል ላይ
ራሱን በመስቀል ራሱን ክዷል፡፡ የሐሰት መምህራን ይህን እውነት ማወቅም ሆነ መተግበር አይፈልጉም፡፡
ካልሞትን በቀር
ከክርስቶስ ጋር ለሕይወት አንነሳም፤ ከሞትን ደግሞ የሞተ ነገር ምንም ክብርና ሞገስ የለውምና ለራሱ የሚናገረው አንዳች ነገር
የለውም፡፡ ቆመን ለራሳችን የምንሟገት ከኾንን የክርስቶስን ስለእኛ መሞትና በሁሉ ነገር መናቁን መኮነናችን ነው፡፡ ከዚህ ርእስ
ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን በዚሁ ጡመራ መድረክ(ብሎግ) ላይ የቀረቡትን “ጌታ የማያውቃቸው የጌታ
አገልጋዮች” የሚለውንና “ክርስቶስን “በሚያባብል ቃል” … ለምን?!” እንድትመለከቱ በፍቅር እጋብዛችኋለሁ፡፡ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ሆይ! ልጆችህ በክርስቶስ መንገድ በማስተዋል
እንድንጓዝ እርዳን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል …
No comments:
Post a Comment