Thursday 21 September 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል ሃያ)


Please read in PDF
3. ጌታችን ጋር ጸንታችሁ ቁሙ፦ መጽናት፣ አለመናወጥን፣ መረጋጋትን፣ መቆምን፣ አለማወላወልን፣ ወደግራም ወደቀኝም አለማለትን፣ አንድን ነገር አጥብቆ መያዝንና ለዚያም ነገር ዋጋ መክፈልን ... የሚያሳይ ነው፡፡ መጽናት የብዙ መታገስ ውጤት[እጅግ ብዙ ትእግስት] ነው፡፡ ብዙ የማይታገስ የማይናወጠውን በመመልከት ሊጸናና ሊቆም አይችልም፡፡ በመከራ የሚታገሱ ሁሉ(ሮሜ.12፥12) በክርስቶስ መንግሥት የሚካፈሉት ሕይወትና ደስታ አላቸው፡፡ የማይጸኑና በክርስቶስ ትምህርት ታግሰው የማይኖሩ ግን እጅግ አስጨናቂ ነገር ይገጥማቸዋል፡፡
     መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድመን በክርስቶስ ኢየሱስ ባመንነው እምነታችን መጽናትና በዚያም ማወላወል እንደሌለብን በተደጋጋሚ ይነግረናል፤ ምክንያቱም ራሱ ክርስቶስ ኢየሱስ መከራን ሁሉ በቅድስናና ባለማጉረምረም በመጽናት የእውነተኛ ጽናት ዋና ተምሳሌት ነውና፣ (1ጴጥ.2፥21)፤ “ጽና፥ እጅግ በርታ፤ ባሪያዬ ሙሴ ያዘዘህን ሕግ ሁሉ ጠብቅ፥ አድርገውም፤ በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል፤” (ኢያ.1፥7)፤ “ንቁ፥ በሃይማኖት ቁሙ፥ ጎልምሱ ጠንክሩ” (1ቆሮ.16፥13)፤ “… ተመሥርታችሁና ተደላድላችሁ ከሰማችሁትም ከወንጌል ተስፋ ሳትናወጡ፥ በሃይማኖት ጸንታችሁ ብትኖሩ ይሆናል” (ቈላ.1፥23) “እናንተ በጌታ ጸንታችሁ ብትቆሙ፥ አሁን በሕይወት እንኖራለንና” (1ተሰ.3፥8)፤ “እንግዲያስ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ጸንታችሁ ቁሙ፥” (2ተሰ.2፥15)፤ “በነፍሳችሁ ዝላችሁ እንዳትደክሙ፥ ከኃጢአተኞች በደረሰበት እንዲህ ባለ መቃወም የጸናውን አስቡ” (ዕብ.12፥3) እንዲል፡፡

   መጽሐፍ ቅዱስ ስለመጽናት ሲናገር ስለቅዱሱ እግዚአብሔር ሕግ፣ ፈቃድና ሃሳብ መታዘዝ፣ እንቢ አለማለትና ከፈቃዱ ፈጽሞ አለመውጣትን በማመልከት ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ሃሳብና ፈቃድ አለመታዘዝ ማለት፣ ከእግዚአብሔር ጋር ለመጽናትና ለመቆም አለመፍቀድን ያሳያል፡፡ ከዚህ ቀደም እንደተናገርነው የክርስትና ሕይወት የተመሰለው እንደረጅም ሩጫ ነው፤ የክርስትና ሕይወት ሩጫውን ለመሮጥ ፍጹም መጽናትና አለመታከት ይገባል፤ ባሪያም ለጌታው ሲታዘዝ መብቱን ሁሉ በመተው በደስታና ባለመታከት ነው፤ ባሪያ እንደሎሌ መታዘዝን ሲሰለችና ሲታክት(ዮሐ.10፥12) ይሠራ የነበረውን ሁሉ ጥሎ የሚሄድ አይደለም፡፡ በማናቸውም ሁኔታ ውስጥ እንኳ የሚጸና እንጂ፡፡
     ከክርስትና ሕይወት ሩጫችን ለምን ትኩረታችን ዘወር ይላል? ብለን የመጀመርያውን ጥያቄ ብናነሣ፣ የምናገኘው መልስ፦ ከክርስቶስ ጋር አለመጽናታችን፣ ብድራቱን ትኩር ብለን አለማየታችንን ቀዳሚ ነገር አድርገን ልናየው እንችላለን፤ ቅዱስ ነቢይ ሙሴ፣ “… ለጊዜው በኃጢአት ከሚገኝ ደስታ ይልቅ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር መከራ መቀበልን መረጠ፤ ብድራቱን ትኵር ብሎ ተመልክቶአልና፡፡ የንጉሡን ቍጣ ሳይፈራ የግብፅን አገር የተወ በእምነት ነበር፤ የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ ጸንቶአልና፤” (ዕብ.11፥26-27) እንዲል፣ ሰማያዊውን ነገር ለመቀበልና በዚያም ነገር ለመርካት መወሰን ታላቅ ከጌታ ጋር የመኾን ጽናትን ይጠይቃል፡፡ ይህም ጽናት “ማየት ማመን ነው” የሚለውን ሽሮ፣ የማይታየውን እንደምናየው አድርገን የመቀበል መንፈሳዊ የእምነት አቅምን ይጠይቃል፡፡
    ብድራትን ትኩር ብሎ መመልከት እጅግ በጣም ጸንቶ ከመቆም ጋር ይያያዛል፤ ሙሴ ብድራቱን ትኩር ብሎ ለማየት ምክንያት የኾነው ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር በመኖር የሚገኘውን የእግዚአብሔርን ክብር ማስተዋሉ ነበር፡፡ ሙሴ የፈርዖንን ቁጣ መፍራቱን መጽሐፍ ቢናገርም (ዘጸ.2፥14)፣ የዕብራውያን ጸሐፊ ግን ሙሴ በእግዚአብሔር ታምኖ እንደነበርና በዚያም ያለምንም ፍርሃት በመከራ ሁሉ መጽናትን እንደወደደ ይነግረናል፡፡ ከሚኖርበት የቤተ መንግሥት ኑሮው ዝቅ ብሎ እረኛ ቢኾንም፣ በዚያም መከራና ስደት ቢያገኘው፣ ከፈርዖን የልጅ ልጅነት ወደምድረ በዳ ወርዶ ከዚህ ስም ቢሻርም … ያጸናውና ከአቋሙ ሳይወላውል እንዲቆም ያደረገው ብድራቱን ትኩር ብሎ መመልከቱ ነው፡፡
   ብዙዎቻችን ብድራታችንን ትኩር ብለን ከማየት የሳትነው፣ ከባዕለውለታችን ከጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምሪት ይልቅ፣ ሳይኾኑ የ“እርሱ አገልጋዮች ነን” የሚሉትን ሰዎች ምሪት መከተልን ስለፈቀድን ነው፡፡ ዋናው ነገራችንን ክርስቶስን ትክ ብሎ ዘወትር መመልከትና የእርሱን አገልጋዮች በመመልከት መካከል እጅግ የሰፋ ልዩነት አለ፡፡ ጠላት ተግቶ የሚሠራው ክፉ ነገሩ ቢኖር፣ “ማስተዋላችንን በመውሰድ በዓይናችን ፊት እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ የነበረውን ክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችንን እንዳንታዘዝ በሚያደርግ አዚም መክበብና መንፈሳዊ ዓይንን ማሳወር ነው፤ (ገላ.3፥1)፡፡ የተሰቀለውን ኢየሱስን በትክክል ትክ ብሎ መመልከት ሕይወትና መዳን ያለበት የዘላለም ደስታ ነው፤ እርሱን አለመመልከትና ከእርሱ ዓይናችንን ፈቀቅ ማድረግ ታላቅ ኪሳራና ከሁሉ ይልቅ የሚያንስ ምስኪንነት ነው፡፡
     የሚሮጥ ሰው ሲሮጥ ያልበው፣ ይደክመው፣ እጅጉን ይዝል ይኾናል፤ ይሁንና ግን ለአክሊል ስለሚሮጥ ሊታዘንለት፤ ሊራራለት አይገባም፡፡ ምን ከባድ ድካምና ጥረት ውስጥ ቢኾንም፣ ከሩጫው አቁም ወይም እስኪ ትንሽ እረፍ አይባልም፡፡ “በርታ፤ ጽና፤ እስክትፈጽመው እንዳታቆም፤ በርትተህ ፈጽመው!” ነው የሚባለው፡፡ ከጌታ ጋርም ጸንተን ስንቆም ወደኋላ የሚስቡ፣ የሚያደክሙ፣ ወደሥጋ ለባሽ ፊታችንን ዘወር እንድናደርግ የሚያደርጉ … ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ግን መታገስና ከጌታ ጋር ጸንቶ መቆም የዘላለም የድል አክሊልን ያሰጣል፡፡
    ብዙዎቻችን ከማን ጋር ይኾን የቆምነው? ትላንትና ከወደቅሁባቸው ስህተቶቼ አንዱ፣ “የጌታ ለምላቸው አገልጋዮች አፌን ሞልቼ ብዙ መናገሬ ነው፤” የተከራከርኩላቸው ብዙ አገልጋዮች ወድቀው፣ ከውድቀታቸው በንስሐ አልመለስ ብለው፣ ልበ ደንዳና ሲኾኑና ለበደሏቸው ሰዎች ምንም ዓይነት የይቅርታ ርኅራኄ አለማሳየታቸውን ሳይ፣ ስለእነርሱ በተናገርኩት ነገርና በእነርሱ ሥራ እጅጉን አፍሬያለሁ፡፡ በእርግጥም እንደዛ በማድረጌም በመጸጸት ንስሐ ገብቻለሁ፡፡ አዎን! ብዙዎቻችን ከክርስቶስ ይልቅ ከመካከላችን “አገልጋይና [ለእግዚአብሔር ይቀርባሉ] ለምንላቸው ሰዎች” የመታዘዝና የእነርሱን ቃሎች ትኩር ብሎ የመመልከት፣ የማመን፣ የመታዘዝ … አዚም ወድቆብናል፡፡ ይህ ብዙ ጊዜ ከክርስቶስ ከራሱ ይለየናል እንጂ፣ በምንም ሊያቀርበን አይችልም፡፡ ይህንን ስል ግን የታመኑ የጌታ እውነተኛ አገልጋዮችን ስለመመልከት እየተቃወምኹ አለመኾኔን እንዲስተዋልልኝ እሻለሁ፡፡
    ቅዱስ ይሁዳ፣ “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስደውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ” በማለት ይመክረናል፡፡ በክርስቶስ ጌታችን ወደዘላለም ሕይወት የወሰደንና የሰጠን ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ የሰጠን ብቻም አይደለም፣ ደግሞም የሰጠንን የዘላለም ሕይወትን በፍቅሩ ራሳችንን እንድንጠብቅ የሚያስችለንን አቅምም ይሰጠናል፡፡ ከሐሰተኞች መምህራን አንዱ መከላከያው መንገድ ራስን በእግዚአብሔር ፍቅር መጠበቅ፤ ከእርሱም ጋር ፍጹም መጽናት ነው፡፡ በሌላ ንግግር ሐሰት በሚፋንንባት ዓለም ላይ ተዘልለን መቀመጥ አልተባለልንም፤ የሚገጥመንን ማናቸውንም መሥዋዕትነት በመክፈል ከጌታችን ኢየሱስ ጋር አብሮ መጽናት ይገባናል፡፡ መንፈስ ቅዱስ አጽናኝና አጽኚያችን ብርታትና ጸጋውን ያድለን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል …


1 comment:

  1. Yetewededke wendeme hoy, Egzabher Kantega yehun dengel Tetebekeh.Libe mechem betam yaznal I don't Antem Yen Begashaw group khonk.Alwekem men Endeml Balachubet Krstose Ereft Yehunlachu Eyesus Besega Endeteglet Erasum Amlake Endehon kalamnen.Sebketachen hulu kentu.Mastewal yeseten Amen.Begeziabher selam Enwedehalen.Dengel Maryam Lantem Enatehe nat.Geta Amlak Bebetu Yasenah Wendeme.

    ReplyDelete