Friday 15 September 2017

የኢትዮጲያ ከፍታችን፤ ያለመብሰል ምኞት ወይስ ከልብ የምንሻው እውነት?!



     Please read in PDF

    መጽሐፍ ቅዱስ ስለኢየሱስ ክርስቶስ ሲናገር እንዲህ ይላል፥ “ … በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለ ልክ ከፍ ከፍ አደረገው፥ ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው፤” (ፊልጵ.2፥9) በማለት ሲናገር ምክንያቱንም፣ “እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ የመኾኑ” ነገር ነው በማለት ይነግረናል፤ (ቁ.6-8)፡፡
   ጌታችን ኢየሱስ አንድ ባሪያን ይዞ ሳይሆን የባሪያን መልክ፣ የሰውን ትስብእት ይዞ፤ የማይሞተው እርሱ መዋረዱንና ሰው በመኾኑም ሞትን ሊቀምስ እንዳለው ያስተምረናል፡፡ ሰው ለመሆን ሲፈቅድ አገልጋይነትንና እስከሞት መታዘዝን መከራንና ስድብን ሁሉ መቀበልን(ማር.15፥29) ፍጹም ዝቅ ዝቅ ማለትን ያሳየናል፡፡ ሰማያዊ መብቱንም በፈቃዱ በመተው ፍጹም ዝቅታን መርጧል፡፡ በዚህ ክፍል ያለው ሃሳብ እጅግ ሰፊና ታላቅ ትምህርት ቢኾንም፣ ጌታችን ኢየሱስ በአብ ፊት አለልክ ከፍ ከፍ ለማለት ምክንያቱ ስለሰው ልጅ ማዳን አለልክ ዝቅ ዝቅ ማለቱን ከርእሳችን ጋር ተወራራሽ ነውና ልናነሣው ወደድን፡፡

    መዋረድን፣ አለልክ ዝቅ ዝቅ ማለትን፣ የሰውን ልጅ ሊያነሣ መውደቅን፣ ሰማያዊ መብቱን ፈጽሞ መተውን … ክርስቶስ እንደመቀማትና እንደመናቅ አልቆጠረውም፤ ይልቁን የተዋረደውና የወደቀው ሰው፣ በኃጢአት ምክንያት “ሰማያዊ መልኩን” ያጣው ሰው ያገኝና ይድን ዘንድ፣ በታላቅ መታዘዝ አደረገው እንጂ፡፡ ጌታ ኢየሱስ እጅግ አስደናቂ ሥራን መሥራት የተቻለው ራሱን እጅግ በማዋረድ ነው፤ ክርስቶስ ኢየሱስ እርሱ ዝቅ ብሎ እኛን ከፍ ሊያደርግ መምጣቱን የሚያስተምር ትምህርት በክርስትና ውስጥ መኖሩን ስናስብ እጅግ እንደነቃለን! አንድ ታላቅ ሥራን ለመሥራት በእውነተኛ ትህትና ራስን ዝቅ ማድረግ፤ በትክክል ማነስና በኋላ ላይ ግን ክብሩ የላቀና የተወደደ መኾኑን፣ ክርስቶስ እኛን ሲያድነንም ኾነ እንድንመስለው ባዘዘንም የጽድቅ ሕይወቱ በእውነት አስተምሮናል፡፡
     አሁንም ሌላ አብነት የሚኾነንን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ እናንሣ፤ የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር ፊት ነውርና በደልን በፈጸሙ ጊዜ ከእግዚአብሔር የሚመጣላቸው ድምጽ፣ “ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ለአባቶቻችሁም እንዳዘዝሁት፥ ባሪያዎቼ በነቢያት የላክሁላችሁን ትእዛዜንና ሥርዓቴን ሕጌንም ሁሉ ጠብቁ፤” (2ነገ.17፥13)፣ “ከዳተኛይቱ እስራኤል ሆይ፥ ተመለሽ፥ ይላል እግዚአብሔር መሐሪ ነኝና፥ ለዘላለምም አልቈጣምና በእናንተ ላይ ፊቴን አላደርግም፥” (ኤር.3፥12)፣ የሚል ሲሆን፣ ነቢያቱም በተመሳሳይ ቃል፣ “በሙሉ ልባችሁ ወደ እግዚአብሔር ከተመለሳችሁ እንግዶችን አማልክትና አስታሮትን ከመካከላችሁ አርቁ፥ ልባችሁንም ወደ እግዚአብሔር አቅኑ፥ እርሱንም ብቻ አምልኩ፤” (1ሳሙ.7፥3)፣ “ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እርሱ ሰብሮናልና፥ እርሱም ይፈውሰናል፤ እርሱ መትቶናል፥ እርሱም ይጠግነናል” (ሆሴ.6፥1)፣ “ሰዎችና እንስሶችም በማቅ ይከደኑ፥ ወደ እግዚአብሔርም በብርቱ ይጩኹ፤ ሰዎችም ሁሉ ከክፉ መንገዳቸውና በእጃቸው ካለው ግፍ ይመለሱ፡፡ እኛ እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ተመልሶ ይጸጸት እንደ ሆነ፥ ከጽኑ ቍጣውም ይመለስ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?” (ዮና.3፥8-9) የሚል መንፈሳዊ ጥማትና ረሃብ አዘል የተስፋ ቃልን ሳይፈሩ ይናገሩ ነበር፡፡
     በየትኛውም ዘመን የታላቅ ሥራ መጀመርያ ንስሐና ወደእግዚአብሔር መመለስ ነው፡፡ ንስሐ እውነተኛ መመለስን በውስጡ የያዘና በዋናነትም፣ “ … በልብህም ሁሉ በነፍስህም ሁሉ የፈለግኸው እንደ ሆነ ታገኘዋለህ” (ዘዳግ.4፥29) እንዲል ከልብ በመመለስ እግዚአብሔርን የመፈለግና በትክክል የማግኘት መንገድ ነው፡፡ በእርግጥ በእውነት ለተመለሱት ሁሉ እግዚአብሔር ቅርብና የሚገኝ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር በብዙ መንገድ ወደእርሱ እንዲመለሱ የንስሐን መንገድ እንዳዘጋጀ ሁሉ፣ ላልተመለሱ ልጆቹና ሊታዘዙት ላልወደዱት ደግሞ፣ “አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤ እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል” (ዮሐ.3፥10) የሚል ከባድ ማስጠንቀቂያ አለው፡፡
     2010 ዓ.ም “የኢትዮጲያ ከፍታ” እንደኾነ የሚያበስር መሪ ቃል ከቤተ መንግሥቱ ሰምተናል፤ ነገር ግን ይህን መሪ ቃል ለመቀበል ውስጤ በጣም ተቸግሮ አስተውዬዋለሁ፤ እንዳላየ ሰው ውስጤ ችላ ቢለው እንኳ፣ እረፍት ሊሰጠኝ አልቻለም፡፡ አዎን! “የኢትዮጲያ ከፍታ” ብለን ከማወጃችን በፊት ከከፍታችን የሚያስተጓጉሉ ነገሮቻችንን ልናስቀድማቸውና መፍትሔ ልናበጅላቸው ይገባናል ብዬ አሰላሰልሁ፤ እኒህንም የተከፈቱና ያልጠገጉ ቁስሎቻችን ናቸው ብዬ ገመትሁ፡፡
     ዝቅታንና ንስሐን እንጂ ከፍታን “የማይፈቅዱልን” ያልጠገጉና የተከፈቱ ቁስሎቻችን ከዚህ በታች የማቀርባቸው ናቸው፦
1.     የአገልጋዮችና የመሪዎች በዘረኝነት፣ በብሔርተኝነት፣ በሀብት፣ በሥልጣን ... መከፋፈላችን በአለም ሁሉ ፊት የታወቀ ነውራችን ሆኖ ከተገለጠ ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ አገልጋዮች “ወንጌልን ለመስበክ ከምንም ጊዜ ይልቅ ጨክነው የተነሡ ቢኾንም” የዚያኑ ያህል መከፋፈሉና አለመስማማቱ፣ ለመቀባበል አለመፈቃቀዱ፣ ጥቅምንና የግል ማህበርን፣ ግላዊነትን አስቀድሞ መንቀሳቀስ ... ጎልቶ ሲታይ ሃይ ባይ ያጣ ይመስላል፡፡
     የመጀመርያይቱ ቤተ ክርስቲያን ዋና መገለጫ የነበረው የመንፈስ አንድነትና የትምህርት ጥራት፣ በጸሎት የመትጋት አቅማቸው ነበር፡፡ “በሐዋርያትም ትምህርትና በኅብረት እንጀራውንም በመቍረስ በየጸሎቱም ይተጉ ነበር፤” (ሐዋ.2፥42)፡፡ ሥራቸውና ሕይወታቸው የክርስቶስ ወንጌል ስለነበርም የግል ዓላማዎቻቸውንና ድካሞቻቸውን ፈጽሞ አላዋጡም፤ ብርታታቸውን፣ አንድ የሚያደርጋቸውን፣ ወንጌሉን ለማሠራጨት የሚረዳቸውንና የመንፈስ አንድነታቸውን ብቻ እንጂ፡፡ ዛሬ ግን ተቃራኒውን እያየን ነው፣ ቆሮንቶሳዊው ጠባይ አይሎና ገንኖ፣ “እኔ የጳውሎስ ነኝ፥ እኔስ የአጵሎስ ነኝ፥ እኔ ግን የኬፋ ነኝ፥ እኔስ የክርስቶስ ነኝ” (1ቆሮ.1፥12) ማለት መንፈሳዊነት እስኪመስል ሠርጿል፡፡
     “የእገሌ ማኅበር ነኝ፣ ስለዚህ ከእነእገሌ ጋር አልተባበርም”፣ “እገሌ የሚባለው ማኅበር መናፍቅና ተሃድሶ ነው ያኛው ደግሞ ኦርቶክሳዊ ነው”፣ “ሰባኪ እገሌ እንትን ነው፤ ሰባኪ እገሌ ደግሞ …” የሚሉ ጸያፍና አስቀያሚ ክፍፍሎች በዘመናችን መታወቂያችን እስኪመስል አለልክ ገንኗል፤ ስለወንጌል የተሻለ ግንዛቤ አላቸው በሚባሉት አባቶች፣ ወንድሞች፣ እህቶችና ወንድሞች መካከልም መንጸባረቁን ስናይ ደግሞ የነገሩን አስፈሪነትና አስከፊነት የጎላ ይኾናል፡፡ ልንርቃቸውና ላንተባበራቸው የሚገቡን ግለሰቦች፣ ማኅበራትና ተቋማት ቢኖሩም፣ በወንጌል አንድ ነን፣ በዓላማችን ክርስቶስና ቤተ ክርስቲያንን እናስቀድም የምንል “ትምህርተ ኦርቶዶክሳውያን” አለመያያዛችንና ጨክነን በኅብረት አለመቆማችን ንስሐና እንባ የሚያስፈልገው ቀዳሚ ነገር ነው፡፡
    የኢትዮጲያ መሪዎችም አሁን ያሉበት ሁኔታ የሚሻል ነው ቢያስብልም፣ የዚያኑ ያህል አስፈሪና አስቀያሚ ነው፡፡ ዘረኝነታቸውና ጎጠኝነታቸው ድንበር የዘለለና ቅጡን ያጣ ነው፡፡ መናገር እስኪቀፍፍ መንደርተኝነታቸውና ወንዝነታቸው ሥር ሰዷል፡፡ ፖለቲካው የተቀመረበት ቀመር መርገምና በደል ነው፤ አለመያያዝና ዓመጽ ነው፡፡ ከዚህ በማይተናነስ መልኩ ለቁጥር የሚታክቱት መሪዎች “እንደመቃኞ በሬ” የሚነዱ እንጂ ግራና ቀኛቸውን አይተው የሚዳኙና የሚፈርዱ አይደሉም፡፡[1] የራሳቸውን ዙፋን ለማበጃጀትና ለመጠበቅ እውነትን ለመቅበር የማያቅማሙ፣ ሐሰትን የሚያገንኑ፣ ኀጥኡን የሚያጸድቁ፣ ቅዱሱን የሚያረክሱ … ናቸው፡፡
2.    ሁለታችን ወንድማማቾች የኾንነው ኢትዮጲያና ኤርትራ በገዛ ምድራችን ላይ ያወጅነው ጦርነትና ዘግናኝ ደም መፋሰስ ለእግዚአብሔር አለመኾናችንን፤ ለቅድስት ፈቃዱም አለመታዘዛችንን በአደባባይ ያስመሰከርንበት እውነት ነው፡፡ ይህን ጦርነት በተመለከተ ከአገራችንም ኾነ ከኤርትራ ምድር ባለመደገፍና በመቃወም ንስሐ እንድንገባበት፣ ቂምና ቅራኔያችንን እንድናርቅ ጨክኖ የተናገረን አባት ወይም እናት ለመኖሩ አላስታውስም፡፡[ካለ በይቅርታ ቃል ለመቀበልና ለመስማት ዝግጁ ነኝ!]፡፡
   ከምንም በላይ “የየትኛውንም ሐዋርያ ደም ሳናፈስስ ወንጌልን ተቀብለናል” ብለን በከንቱ ብንመካም፣ የራሳችንንና የወገናችንን ደም በማፍሰስ የሚተካከለን ያለ ግን አይመስለኝም፤ የታወቅንበት የጦርነት ገጽታችን በደም ተጨማለቀ ነው፡፡ በኢትዮጲያና በኤርትራ መካከል በተደረገው ጦርነት ብዙ መቶ ሺህዎች አልቀዋል፤ ነገር ግን አንድ ሰው የሞተ ያህል ተድበስብሶ ቀረ እንጂ ምንም የተሰማን አይመስልም፡፡ ከዚህ ጋር በተመሳሳይ መልኩ፣ የአጼ ኃይለ ሥላሴ ግድያና የስድሳዎቹ የንጉሡ መሪዎች በአንድ መቃብር መቀበራቸው፤ የቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር ጭፍጨፋን ማንሳትም ይቻላል፡፡ ከአርባ ዓመታት በላይ ምድሪቱን “በሞገስ” የመሩትን ንጉሥ ከአያያዛቸው እስከመገደላቸው ድረስ   የተፈጸመባቸው አስቀያሚና አስነዋሪ ነገር ይኸው ትውልድ የሚያውቀውና በደማቸው መፍሰስ፣ በመዋረዳቸው፣ በመናቅና በመገፋታቸው ሁሉ መንግሥትም ሕዝብም በመተባበር ያደረጉት ነውና የመረረ ክፋታችን፤ ነውራችንም ነው፡፡ ነገር ግን ምድሪቱ በሚበዛ ደም ተጨማልቃ ሳለ፣ ስለከፍታችን እንጂ ስለዝቅታ፣ ስለንስሐና ራሳችንን በማዋረድ ይቅርታ ስለመደራረግ የታደልን አይመስልም፡፡ 
   ኢትዮጲያ ከአርባ ዓመታት በላይ የመራት ንጉሥን የሚያህል በአደባባይ “ሌባ ሌባ” እያለች አዋርዳና አቅልላ፤ የመቃብሩን ደብዛ አጥፍታ ቀብራ ዛሬ ግን ስለከፍታ ስታወራ ምነው በጽድቅ በሚፈርደው ጌታ ላይ ዘበተች? የእነዚያ መሪዎች ውለታቸው ተክዶ [ምንም የተሳሳቱበት ነገር ቢኖርም፣ ቢበድሉም፣ ለአገር ምቹ ቢኾኑም ባይኾኑም] በአንድ መቃብር መቀበር፣ የቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር ጭፍጨፋ … በእውኑ ጌታ የማያውቀው ነውን? ወይስ ጊዜው ሲረዝም ጌታ የረሳው መሰለን? ምነው ንስሐ ሳንገባ እስከአሁን በመቆየታችን  እንኳ ቁጣው እንደነደደብን ማስተዋል ተሳነን? እግዚአብሔር የፊተኛው በደላችንን ልጁን በማመን ንስሐ እስካልገባንበት ድረስ ፈጽሞ ከበደል አያጠራንም፤ ይቅርታውንም አይሰጠንም!!! እርሱ እውነተኛ ዳኛ በጽድቅም ፈራጅ ነውና!!!
3.    የሁለቱ ሲኖዶሶች ክፍፍልና መወጋገዝ ሌላው የሚያዥና የተከፈተ ቁስላችን ነው፡፡ “ሕዝብ ጎንበስ ብሎ ጉልበታቸውን የሚስማቸው ጳጳሳትና ሊቃነ ጳጳሳት” “እንደደረስኩ ባይ ጎረምሳ” በአደባባይ ሲሰዳደቡና ሲወጋገዙ መስማት እጅግ አሳፋሪና ክፉ ምሳሌነት ነው፡፡ አንድ ቋንቋና አንዲት ሉዓላዊት አገርን “በመንፈሳዊ ነገር” ለማስተዳደርና “ለመምራት” መሽቀዳደምና መወጋገዝ መንፈሳዊ አባትነትን፣ እንኳን በቤተ ክርስቲያን መካከል ጌታን በማያውቁና መጽሐፍ ቅዱስን ባልጨበጡ ወገኖች መካከል እንኳ እጅግ ያስንቃል፡፡
    ለምን ነበር እስከአሁን እንደተወጋገዝን ያለነው? ለምን ነበር ያን ሁሉ የውግዘት እሩምታ ያወረድነው? እስከመች ነው በውግዘት ቂም ተዛዝለን የምንዘልቀው? መች ነው ለትውልድ ይቅርታና ምሕረት ለማውረስ እናንተ “ጳጳሳቱ” ከቂምና በቀል፤ ከከንቱ ውግዘታችሁ የምትፈታቱት? በእውኑ “የኢትዮጲያ ከፍታ” እናንተን ይመለከት ይኾን? ከተመለከታችሁስ በቂምና በቀል፤ በመወጋገዝና በመለያየት የትኛው ከፍታ ይኾን ለዚህች አገር የሚጠቅማትና ከሰቆቃ፣ ከችጋር፣ ከመቆሳሰል፣ ከዘረኝነት … የሚገላግላት? በእውኑ እናንተ ለወንጌል ጉዳይ ወይስ ለግል ክብራችሁ ይኾን የተወጋገዛችሁት? እውን ለቤተ ክርስቲያንና ለኢትዮጲያ ምድር ሰላምና ይቅርታን ስለማውረድ ይኾን የተወጋገዛችሁት? እናንተ “ታላላቅ ጳጳሳት ሆይ”! የመወጋገዛችሁ ዓላማ ከተሾማችሁለትና ከተሰጣችሁ የወንጌል አደራ ጋር ምን ዝምድና ኖሮት ይኾን? ደግሞ እስከመቼ ነው ንስሐ ለመግባት ልባችሁን እልኸኛ የምታደርጉት? መች ነው መለያየታችሁ አብቅቶ፤ በከንቱ መወጋገዛችሁ ተፈትቶ “ታራቂና አስታራቂ ሽማግሌነታችሁን” የምናየው? በእውኑ እናንተ እንዲህ ኾናችሁ የትኛው “የኢትዮጲያ ከፍታ” ይኾን የሚመጣው?
   ከዚህም በላይ አልፎ ተርፎ፣ ለቁጥር የሚታክቱ በየአገራቱ በውርደት፣ በጉስቁል፣ በዕርዛትና በእንባ ... በስደት የሚኖሩት የዚህች አገር ሕዝቦች ብዛት የእኛን ማንነት አይመሰክርብን ይኾን? የክፋታችን ማሳያ አይደሉምን? የኃጢአታችንን ውጤት አያመለክት ይኾን? መሪዎች ለሕዝባቸው ምድሪቱን ምቹ ሳያደርጉ በመቅረታቸው እጅግ ስግብግብ ባለሥልጣናት ራሳቸውን ሲያንደላቅቁ፤ ዱርዬዎቹ ሃብታሞች ደግሞ ምድሪቱን በሁዳድ ሁዳድ ተቀራምተው ከመያዛቸውና ድሃውን ከመግፋታቸው የመጣ እንደኾነ እንክደው ይኾንን? ፍትሕ ማጣት፣ መልካም አስተዳደር ስም ብቻ መኾኑ፣ ጉበኝነት ዓይን አውጥቶ መታየቱ፣ በድሃና በሃብታም መካከል ያለው ልዩነት የዝሆንና የጉንዳን ያህል መራራቁ፣ የንግዱ ወረት በማጭበርበር፣ በአታላይነት መከበቡ፣ መንፈሳዊ ነን ባዮቹ አገልጋዮች ዋሾዎችና ሞጭላፊዎች፣ ግብዞችና አስመሳዮች፣ ገንዘብ ወዳድና ሴሰኞች መኾናቸው … አስፈሪ ብቻ ያይደለ የእግዚአብሔርን ቁጣ ቀስቃሽ ናቸው፡፡
       ይህን ሁሉ ጉድና ነውር ተሸክመንም ግን አሁንም ከድፍረት በደላችን አልተመለስንም፤ ኢትዮጲያ ከፍ እንድትል መሻቴ፣ ምኞቴ፣ ናፍቆቴ፣ ጥማቴም … ጭምር ነው፡፡ ነገር ግን ዕዥ የሚያወጡ የበደል ቁስሎች አሉብን፤ የነውር መግሎች አሉብን፣ አንገት የሚያስደፉ የርኩሰት ስንጥቆችና ሽንቁሮች አሉብን፤ የሚከረፉና የሚሸቱ፤ ታጥበው ያልጠሩ እባጮች አሉብን፤ በእውነት ጤናማ ከፍታ፣ ትክክለኛ ከፍታ፣ እውነተኛ ከፍታ ከሻትን ንስሐ እንግባ፤ በደላችንን አስቀድመን እንጠብ፤ ብሔራዊ እርቅና ይቅርታን እናውርድ!!!
     የቀደመው ዘመን መበዳደልና መገፋፋትን በቃ ብለን እንመለስ፤ ለወገኖቻችንና ለሕዝባችን እውነተኛ አሳቢ አባትና መሪዎች እንሁን፤ ኢትዮጲያዊን ለመቀበል መስፈርታችን ኢትዮጲያዊ ብቻ መኾኑን እንመን፤ ሰው መኾንን ሁለተኛ ዘርና ጐሳን ቀዳሚ ከሚያደርግ ጋኔናዊ ምልከታ እንጥራ፡፡ ከኤርትራውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ትክክለኛ በኾነና እውነተኛ በኾነ መንገድ ይቅር እንባባል፤ እንታረቅ፤ የተለያዩ ወገኖችና ቤተሰቦች፣ ባለትዳሮችና ልጆች እንዲገናኙ ምድሪቱን የፍቅርና የመስማማት እናድርጋት፡፡ ከፍታውን ከማወጃችን በፊት በትክክል ንስሐ ለመግባትና ለመቀባበል ዝቅታችንን እናውጅ፤ አልያ የምናስበው ከፍታ ሕልም፤ የማንደርስበት ቅዠት መኾኑን ለመናገር “ነቢይ ነኝ ብሎ ልዩ መቀባት” አያሻውም፡፡
    ጌታ መንፈስ ቅዱስ ከእውነት ጋር መቆም እንድንችል ይርዳን፤ ክርስቶስን በማመን የሚገኘውን ዘላለማዊ ሕይወትና አዲስ ማንነት እንድንቀበል፤ እንድንለብስ፤ ክርስቶስን በልባችን እንድናከብረው መንፈስ ቅዱስ አምላካችን በጸጋው ይርዳን፤ አሜን፡፡





     [1]  2010 ዓ.ም በመግባቱ ዋዜማና ከገባ በኋላ ለአንድ ለራሴ ጉዳይ ወደሦስት የሚጠጉ “በአገሪቱ ስመጥር ወደኾኑ የቢሮ ዋና ኃላፊዎች” ጎራ ብዬ ነበር፤ እጅግ በሚያሳዝን መልኩ የሚያመናጭቁ፣ ፊታቸው እንደእሾኽ የሚጋረፍ፣ ፈጽሞ ትህትና የጎደላቸውና የሚሳደቡ ኃላፊዎች ገጥመውኝ እጅግ አዝኛለሁ፡፡ በነዚያ ሰዎች ውስጥ እነርሱን የሚመስሉ ስንት “አስቀያሚ ባለሥልጣናትንና ኃላፊዎችን” አይቼ “የኢትዮጲያን ከፍታ” ምናዊ እንደኾነ ማሰላሰል ጀመርኩ? በእርግጥም እነርሱ ብቻ ሳይኾኑ ዛሬ ብዙ ሃብትና ንብረት፣ የንግድ ወረቱን የተቆጣጠሩት “ኅሊና ቢስና አስተውሎት የጎደላቸው” ሃብታሞች መኾናቸውን ሳስብ የኢትዮጲያዬ ከፍታው ቁሳዊ እንጂ መንፈሳዊ፣ “ብልግና”[ግብረ ሰዶማዊነት፣ ዕርቃን ጭፈራ ቤቶችና የዝሙት ፊልሞች ከተደበቁበት ወደአደባባይ እየወጡ መኾናቸውን እንዳንዘነጋ] እንጂ ግብረ ገባዊ፣ መደዴነት እንጂ ሞራላዊ፣ ስግብግብነት እንጂ ቆርሶ መካፈልን እንደማያካትት አስተውያለሁ፡፡ ይህን ስል ግን ጥቂት ቢኾኑም አገራቸውን የሚወድዱና ከልባቸው በኹለንተናዋ የተዋበች አገር እንድትኾን የሚጥሩና የሚደክሙላት የሉም ማለቴ እንዳልኾነ ብዙዎች ይረዱኛል ብዬ አስባለሁ፡፡  

3 comments: