Thursday 24 August 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል አሥራ ሰባት)


   “ሌሊቱ አልፎአል፥ ቀኑም ቀርቦአል፡፡ እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ፤” (ሮሜ.13፥12) ሌሊቱ ተብሎ የተጠቀሰው አሁን ያለው ክፉ ዘመን ነው፡፡ ጊዜውም ክርስቶስ ከሙታን ከተነሣበት ጊዜ ጀምሮ ያለውን የሚያካትት ነው፡፡ ቀጥሎም ሐዋርያው የክርስቶስን መምጣት አጽንቶ ይናገራል፡፡ “ቀኑም ቀርቦአል” ሲልም፣ በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች፣ “ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ” (ማቴ.24፥33)፣ “ዘመኑ አጭር ሆኖአል፤”(1ቆሮ.7፥29)፣ “ዳሩ ግን የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል”(1ጴጥ.4፥7)፣ “የእግዚአብሔርን ቀን መምጣት እየጠበቃችሁና እያስቸኰላችሁ” (2ጴጥ.3፥11)፣ “ልጆች ሆይ፥ መጨረሻው ሰዓት ነው፥ … ስለዚህም መጨረሻው ሰዓት እንደ ሆነ እናውቃለን” (1ዮሐ.2፥18) “ጌታ እስኪመጣ ድረስ ታገሡ” (ያዕ.5፥7)፣ “ዘመኑ ቀርቦአል” (ራእ.1፥3) ተብለው ከተገለጡት ምንባባት ጋር በመስማማት የዘመኑን  ከፊት ይልቅ ወደእኛ መቅረብና ክርስቶስ ሊመጣ በደጅ መኾኑን ይገልጥልናል፡፡

   በአዲስ ኪዳን መግቢያ ያሉት የጥንት አማንያን፣ የዘመኑን መቅረብ “ደርሷል ብለው” ካበሠሩን እኛ እንዴት ይበልጥ አንዘጋጅ ይኾን? ምክንያቱም የክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ የመጨረሻው ዘመን የጀመረበት ወሳኝ የታሪክ ክንውን እንደኾነ በትክክል ስላስተዋሉ የዘመኑን መቅረብ ደጋግመው ሲያውጁ አይተናልና፡፡ መዘንጋት የሌለብን ነገር የዘመኑን መቅረብ መናገር ብቻውን እርባና አይሰጥም፣ ይልቁን፦ “እንግዲህ የጨለማውን ሥራ አውጥተን የብርሃንን ጋሻ ጦር እንልበስ” እንደተባለ ክርስቲያኖች በኑኖአቸው ሁሉ የክርስቶስን በጎነት እንዲገልጡ በመናገሩ፣ እኛም ይህን ማድረግ አንዳለብን ይበልጥ ያሳስበናልና፡፡
    ብርሃን፣ ለክርስቶስ ካለን የምስክርነት ሕይወት ጋር በትክክል እንደሚያያዝ ጌታችን በተራራው ትምህርቱ በምሳሌ አስተምሮናል፤ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፡፡ በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም” (ማቴ.5፥14)፡፡ ብርሃናችን በሰዎች ፊት በትክክል መብራትና ክርስቶስን ማሳየት አለበት፡፡ በተለይም በዚህ በዘመን መጨረሻና በአመጸኛ ትውልድ መካከል እኛ የዚህ ዘመን የክርስቶስ ምስክሮች፣ ምስክርነታችን የበራና የፈካ፤ መሰወርም የማይችል ኾኖ በቤተሰባችን፣ በጓደኞቻችን፣ ከትዳር አጋራችን ጋር ስንኖር፣ በልጆቻችን ፊት፣ በማኅበረሰባችን መካከል … ለሰው ሁሉ ሊታይ ይገባዋል፡፡
    እምነታችንንና ምስክርነታችንን በክፉ ፍላጻዎቹ ሊዋጋ ሰይጣን ዘወትር በፊታችን አለ፡፡ የሰይጣን ማጥቂያዎቹ ፍላጻዎች ናቸው፡፡ የሚወረውረው ፍላጻዎቹ ማንነታችንን የሚጎዱ ናቸው፤ ስለዚህም ይህን ለመከላከል የእምነትና የምስክርነት ጋሻችንን ልናነሳ ይገባናል፡፡ ያለእምነት ጋሻና ያለምስክርነታችን ወይም በቅድስና በክርስቶስና በሰው ሁሉ ፊት አለመመላለሳችን የሚንበለበሉትን ፍላጻዎች ማጥፋት አይቻለንም፡፡  ይህንንም ለማድረግ ጽኑ እምነትና የጠራ ምስክርነት የሚገኘው የእግዚአብሔርን ቃል በመስማትና በልብም በመሰወር ነው፡፡ ስለዚህ ሰይጣን ለሚወረውራቸው የትኛውም የክፋት ፍላጻዎቹ በክርስቶስና በሰው ፊት የበረታና ታላቅ የኾነ የእምነትና በቅድስና የታጠረ የምስክርነት ሕይወት ሊኖረን ይገባናል፡፡
5.   መዳንንም ራስ ቁር ያዙ፦ “በራሱም ላይ የማዳንን ራስ ቍር አደረገ፤” (ኢሳ.59፥17) የሚለው ሃሳብ ከዚህ ክፍል ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ የራስ ቍር፣ “ከናስ ወይም ከቆዳ ወይም ከብረት የተሠራ በራስ ላይ የሚደፋ የጦር መሣርያ መከላከያ”[1] ነው፡፡ ዋናውን የሰውነታችን ክፍል ራሳችንን የሚከላከልንን መሣርያ ነው፡፡ ይኸውም ለራስ መተማመኛ፣ አደጋም እንዳይደርስበት ሙሉ ለሙሉ በመሸፈን የሚታወቅ ነው፡፡ ቍሩ እስካለ ድረስ በዋናው የሰውነቱ አካል ላይ የሚደርሰውን ማናቸውን አደጋ ይከላከላል፡፡
    በመጽሐፍ ቅዱስ ራስ፣ ለሰው አካል የክብር ምልክት መሆኑን፣ እንዲሁም የዋና ነገር ምሳሌ መገለጫ ሆኖ መጠቀሱን እናገኘዋለን፡፡ የራስ ቍር የመዳን ምሳሌ ነው፡፡ ራስ ዋና ነገር እንደሆነ እንዲሁ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ በስሙ የምናምን ሁላችን የዘላለም ሕይወት እንዳለንም ማረጋገጫ ነው፡፡ መዳናችንም ዋና ነገራችንና የእግዚአብሔር ልጅን የሥጋ ሞትን የጠየቀ እጅግ የከበረ ነገር ነው፡፡ ከተናገርነውና ከምንናገረው ዋና ነገር በክርስቶስና በክርስቶስ ብቻ መዳናችን ነው፡፡ እርሱ ለእኛ የሰጠን መዳን ወይም በሥጋ ሞቱ የከፈለልን ነገር ዋናና በማንም የማናስነካውና የማንኛውም ቅዱስም ኾነ መልአክ እጅ ያለበት ወይም የገባበት አይደለም፡፡
    የቍር ዋና ተግባሩም ራስን መከላከል የመሆኑን ያህል፣ መዳናችን ዋና ተግባሩ የራሳችንን ወይም የአእምሮአችንን ክፍል መፈወስና ኹለንተናችንን ማዳኑ ነው፡፡ ስለዚህም የሰውነታችንን ዋና ክፍል ማጥቃት ደግሞ የዲያብሎስ ተግባር ነው፡፡ ነገር ግን አማኙ የራስን ቍር በመድፋቱ ምክንያት ጠላት ዲያብሎስ ሊገድለው አይችልም፡፡ በክርስቶስ መዳናችንና የደኅንነታችን ራስ ቍር በመልበሳችን፣ ሰይጣን መንፈሳዊ ነገራችንን እንዳይገድል ፍጹም መከላከያችን ነው፡፡ ስለዚህም የክርስቶስ ማዳን ከምንም በላይ የምንመካበት ዋስትናችን ነው፡፡ በእርሱ ማመናችንና ከእርሱ ጋር በቅድስና መኖራችንም የዘላለም ሕይወት እንዳለን ዋና ማረጋገጫችን ነው፡፡
    በተለይም ዲያብሎስ አእምሮን ወይም ዋናውን ነገራችንን የሚያጠፋውና የሚያጎድለው “በግልሙትናና በወይን ጠጅ ስካር” (ሆሴ.4፥11)፣ “ከሴት ጋር ስናመነዝር” (ምሳ.6፥32 ፤ 7፥7 ፤ 9፥4)፣ ከክርስቶስ ይልቅ “ከንቱ በኾነውና ማዳን በማይችሉ በሰው ልጆችና በአለቆች ስንታመን” (መዝ.60፥11 ፤ 146፥3) እንደሆነ ቅዱስ ቃሉ በግልጥ ይናገራል፡፡ ይልቁን “በጥቂትም በብዙም የሚያድን” (2ነገ.5፥7 ፤ 2ዜና.14፥11)፣ “የማዳንን ደስታ ሰጪ” (መዝ.9፥14 ፤ 51፥12)፣ ማዳን ለእርሱ ብቻ የኾነለት (ዘዳግ.32፥39 ፤ 1ሳሙ.14፥34 ፤ መዝ.3፥8 ፤ 50፥22 ፤ 85፥4 ፤ ኢሳ.43፥11 ፤ ቲቶ.2፥11-14 ፤ 3፥4 ፤ ይሁ.25) ስንመካ በእርግጥ የመዳን ራስ ቍራችንን እንጥላለን፡፡ አዎን! መዳንን ስናስብ ከእርሱ በቀር ማንም የለም፡፡ ሁልጊዜም ትምክህታችንና ቍርጥ ውሳኔያችን ከእርሱ ጋር መኾንና እርሱን ብቻ መስማት ነው፡፡
    ስለዚህም ዲያብሎስ አእምሮአች በክፋት እንዳያጠቃ በእግዚአብሔር ተስፋ ልባችንን መሙላት ይገባናል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የራስ ቍራችንን መዳናችንን በክርስቶስ ካረጋገጥንና በክርስቶስ በትክክል በጽድቅ ኑሮው ከእርሱ ጋር ከኖርን ሰይጣን የዘላለም ሕይወታችንን አይወስድብንም፡፡ ከምንም በላይ በክርስቶስ ያገኘነውን መዳናችንን ወደፍጡር በማውረድ[በራሱ በክርስቶስ ሎሌዎችና አገልጋዮች ቢኾን እንኳ] ክርስቶስን ማስቀናት መጀመር የለብንም፡፡ እርሱ ከቀድሞም፣ “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ፡፡ በላይ በሰማይ ካለው፥ በታችም በምድር ካለው፥ ከምድርም በታች በውኃ ካለው ነገር የማናቸውንም ምሳሌ፥ የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ፤” (ዘጸ.20፥3) በማለት በግልጥ ተናግሯልና፤ በቅዱሳን ብቻ ሳይኾን በራሱ በእግዚአብሔር ምንም ምስልና ምሳሌ እንዳናደርግ በማስጠንቀቂያ ነግሮናል፤ (ዘጸ.22፥20 ፤ ዘዳግ.5፥4)፡፡ ስለዚህም መዳንን በተመለከተ ጌታችን ኢየሱስ ዋና ነገራችን ስለኾነልን፣ ዲያብሎስ ይህን እንዳይወስድብን በብርቱ ልንጠነቀቅና ልባችንን ወደፍጡር በማስዘንበል የዘላለም ሕይወታችንን እንዳያሳጣን ማስተዋል ይገባናል፡፡
    በሌላ መልኩ ቅዱስ ጳውሎስ ይህን ሃሳብ፣ “እኛ ግን ከቀን ስለ ሆንን፥ የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እየለበስን በመጠን እንኑር፤” (1ተሰ.5፥8) በማለት ስለመዳናችን እርግጠኞችና በቂ ግንዛቤ እንዲኖረን በማድረግና አጥብቀን መያዝ እንዳለብን አስረግጦ ይናገራል፡፡ ጌታ መንፈስ ቅዱስ ጸጋና ማስተዋሉን ያብዛልን፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል …




   [1]  የኢትዮጲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፣ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፣ ገጽ.67

No comments:

Post a Comment