Saturday 30 September 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (የመጨረሻ ክፍል)

Please read in PDF 
4.   ስሐ እንግባ
    አማንያን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ብቻ በትክክል እንዲሰሙ፣ ክርስቶስን ሳይኾን ራሳቸውን የሚያገለግሉ አገልጋዮችን ከመስማት ተከልክለው ለቃሉና ለፈቃዱ እንዲታዘዙ ለማድረግ፣ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ጠባይ እንደቃሉ ማረቅና ዘወትር በቅዱስ ቃሉ መስታወትነት ራሷን መመልከት ይገባታል፡፡ ንስሐ ራስን ለእግዚአብሔር በትክክል ማቅረብና አራቁቶ ማቅረብ ብቸ ያይደለ፣ ድርጊታዊ ምላሽን ይሻል የምንለውም ከዚህ ተነሥተን ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሌሎችን ከክፋታቸው እንዲመለሱ ለመምከር ከመዘጋጀቷ በፊት፣ ከምትወቅስበት ወቀሳ ለራሷ ንጹህና በዚያም ነውርና ክፋት ያልተያዘች፤ ፈጽማም የጠራች ልትኾን ይገባታል፡፡
     የራሳችንን ክፉ ጠባይ ሳናስተካክል፣ ሌሎች ትክክለኛውን ነገር እንዲያደርጉና ወደትክክለኛው እውነት እንዲመጡ ጫና ከማድረግ መከልከል አለብን፡፡ ከዚህ ነገራችን ንስሐ ሳንገባ ይህንን የምናደርግ ከኾነ ግን ቅዱስ ቃሉ፦አንተ የምትፈርድ ሰው ሁሉ ሆይ፥ የምታመካኘው የለህም፤ በሌላው በምትፈርድበት ነገር ራስህን ትኰንናለህና፤ አንተው ፈራጁ እነዚያን ታደርጋለህና” (ሮሜ.2፥1) እንዲል፣ “በወንድምህም ዓይን ያለውን ጉድፍ ስለምን ታያለህ፥ በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለ ምን አትመለከትም?” (ማቴ.7፥3) በማለት በጽኑ ወቀሳ ሁላችንን ይወቅሰናል፡፡

    እውነተኛ ንስሐ፣ “ያልተገረዘ ልብን ማዋረድ” (ዘሌ.26፥41)፣ ዓይንን እንደጠቢብ በራስ ላይ ማድረግ”(መክ.2፥14)፣ “ … በሩቅ ቆሞ ዓይንን ወደ ሰማይ ማንሣት ሳይወዱ፥ ነገር ግን፦ አምላክ ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያሉ ደረት መድቃትን” (ሉቃ.18፥13)፣ “ራስንም በፍጹም መዋረድ እንደውኃ በፊቱ ማፍሰስና” (1ሳሙ.7፥6)፣ ከሐሰት መምህራን መራቅና ትምህርታቸውን መቃወም፤ ፈጽሞ አለመቀበል … ከዚህ ጋር ቀጥተኛ ዝምድና ያላቸውን መንፈሳዊ ሃሳብና ተግባራዊ ምላሽን በውስጡ ያካተተ ነው፡፡
    አገልጋይ ተኮር ምሪት አሁን በምድራችን ላይ እጅግ ተንሰራፍቷል፤ ቀስቶችና መንገዶች ሁሉ ወደክርስቶስ ከማመልከት ይልቅ፣ ወደሥጋ ለባሹ አገልጋይ ነቢይ፣ መጋቢ፣ ቄስና መምህር … እጅግ ሲከፋ ደግሞ፣ ወደሥጋዊ ተድላና፣ ብልጥግና፣ ምቾትና ቅምጥልነት … ቀስቶች ሁሉ ማማተራቸውን በግልጥ እያየን ነው፡፡ ከሰጪው ይልቅ የሰጪው ስጦታ ከገነነ እጅግ ከባድ ለኾነ ስህተት ተላልፈን ተሰጥተናል፡፡ ሥጦታው እጅግ እረፍት አልባ ከዳረገን ለመንፈሳዊ ጉስቁልና ተጋልጠናል፡፡ ከኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ዓይናችን ዝንጉ ከኾነ፣ “የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?” (ገላ.3፥1) የሚለው አምላካዊ ወቀሳ ፊት ለፊት ያገኘናል፡፡ ከዚህም ለመትረፍና ለመዳን ንስሐ መግባትና ፊታችንን ወደበደልነው ጌታ መልሰን መኖር፤ መጽናትም ይገባናል፡፡
    መጽሐፍ እንደሚልም፣ስለዚህ ውሸትን አስወግዳችሁ፥ እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ። ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ፤ በቁጣችሁ ላይ ፀሐይ አይግባ፥ ለዲያብሎስም ፈንታ አትስጡት። የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፥ ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም፡፡ ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፥ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል እንጂ ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ፤” (ኤፌ.4፥25-29)፡፡ 
     ለመምህራኑ አለልክ መፋነንና ከክርስቶስ ይልቅ ራሳቸውን ሲሰብኩና ሲያገንኑ በመቀበላችን እኛም የስህተታቸው ተጋሪ ነን፡፡ በዚህ ሳናበቃ፣ እንደወንድምና አገልጋይ ለቀረቡን ወንድሞችና አገልጋዮች ፊታችንን አጥቁረን፣ ደጃችንን ዘግተን፤ ለሐሰት መምህራን “ትክክለኛነት” ጥብቅና የቆምን፣  በማስመሰልና በግብዝነት ራሳቸውን የኢየሱስን ባሪያዎችን መልክ ይዘው ኪሳችንንና ልባችንን የሚበዘብዙትን፣ ለቁራሽ እንጀራና ለጭብጥ ገብስ ከኢየሱስ ጌታችን ይልቅ የሰው ፊት እያዩ ለሚያገለግሉት … “ … በክርስቶስም ትምህርት ለማይኖር ሰው አምላክ የለውም፤ በክርስቶስ ትምህርት ለሚኖር አብና ወልድ አሉት፡፡ ማንም ወደ እናንተ ቢመጣ ይህንም ትምህርት ባያመጣ በቤታችሁ አትቀበሉት ሰላምም አትበሉት፤ ሰላም የሚለው ሰው በክፉ ሥራው ይካፈላልና፤” (2ዮሐ.9-11) የሚለውን ቃል ቸል ብለን፣ በራችንን ከፍተን ከነስህተት ትምህርታቸው ተቀብለናቸዋል፡፡ ትምህርታቸውን መቀበል እነርሱን መቀበል፤ በቤታችንም እነርሱን መቀበል ትምህርታቸውን እንዲስፋፋ ዕድል መስጠታችንን ያሳያል፡፡ ለዚህም ደግሞ ንስሐ ልንገባ፤ እንዲህ ያለ ስህተታችንን ማረቅ ይገባናል፡፡
ጠቃለያ
   “ለቀባሁትም ሰው መብራትን አዘጋጃለሁ፤” (መዝ.132፥17) እንዲል፣ ምሪትንና የምሪትን ብርሃን ሰጪ ራሱ እግዚአብሔር እንደኾነ አስቀድሞ ተናግሯል፡፡ እንዲሁም “አንተ የእስራኤልን መብራት እንዳታጠፋ” (2ሳሙ.21፥17) እንደተባለም፣ አገልጋይ በእግዚአብሔር ዘወትር ሲያበራና እግዚአብሔርን ሲያሳይ ሊኖር ይገባዋል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም፣ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ”(ማቴ.5፥16) በማለት እንደተናገረውም፣ ከእርሱ የብርሃን ምንጭነት በሚወጣው የምስክርነታችን ሕይወት እግዚአብሔርን በሕይወታችን እንድናከብር ተጠርተናል፡፡
    በተጨማሪ አገልጋይም፣ ሯጭም፣ ወታደርም መንፈሳዊ ነገርን ሲጀምር ቀዳሚው መግቢያ በር ጸጋ ነው፤ ሕይወትንም፤ መዳንንም የተቀበልነው ከራሱ ከእግዚአብሔር እጅ ነው፡፡ የሚያድገው፣ የሚጸናው፣ የሚፋፋው ግን ደም እስከማፍሰስ ባለ ተጋድሎ ውስጥ ከማይታዩ ሰማያውያን የክፋት ሠራዊት ጋር በውጊያ ውስጥ ስናልፍ ነው፡፡ ያለሰልፍ የቆመ ክርስትና በዘመናት አልታየም፤ ከጌታ ጋር በውጊያው ጸንቶ የቆመም ወታደር ሁሌም አሸናፊና ድል ነሺ ነው፡፡
    ለክርስቶስ ባሪያ መኾንን በፍቅር የምናደርገው መንፈሳዊ ሥራ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለኤጳፍራ እንዲህ መሰከረለት፦ “ከተወደደ ከእኛም ጋር አብሮ ባሪያ ከሆነው ከኤጳፍራ እንዲህ ተማራችሁ፥ እርሱም ስለ እናንተ ታማኝ የክርስቶስ አገልጋይ ነው” (ቈላ.1፥7)፤ አዎን! ትኩረታችንና ልንከተለው የሚገባን አንድ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ሁላችን ግን ለእርሱ ባሪያ መኾናችንን ማሳየት አለብን፡፡
    የነገሩ እጅግ አባባሽና አሁንና ወደፊትን እጅግ አስፈሪ የሚያደርጉት እኒህ ራሳቸውን አግንነው ክርስቶስን የሚጋርዱ አገልጋዮች ዋናና ጫጩቶቻቸው መብዛታቸው ነው፡፡ ስጦታው ከሰጪው ያንሳል፤ የሥጦታው ባለቤት አንሶብን ጸጋውን እናዳናስበልጥና ሰጪውን ትኩረት እንዳንነፍገው አብዝተን እጅግ መጠንቀቅ አለብን፡፡ የሕይወት ዘመን ሩጫውን ስንሮጥ ከክርስቶስ ሌላ ላለማየት [የገዛ መልካምነታችንንና የሰዎችን ስጦታ እንኳ ቢኾን] ከልበ ዓይናችን ጋር ኪዳን መግባት ይኖርብናል፡፡ አነቃቅቶ ላነሣሣኝ፤ አነሣስቶ ላስጀመረኝ፤ አስጀምሮም ላስጨረሰኝ ለምወደውና ዘወትር በፊቴ ላለው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ምስጋና፤ አምልኮትና ስግደት ይኹንለት፤ አሜን፡፡
ተፈጸመ!!! 


1 comment:

  1. ለክርስቶስ ባሪያ መኾንን በፍቅር የምናደርገው መንፈሳዊ ሥራ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለኤጳፍራ እንዲህ መሰከረለት፦ “ከተወደደ ከእኛም ጋር አብሮ ባሪያ ከሆነው ከኤጳፍራ እንዲህ ተማራችሁ፥ እርሱም ስለ እናንተ ታማኝ የክርስቶስ አገልጋይ ነው” (ቈላ.1፥7)፤ አዎን! ትኩረታችንና ልንከተለው የሚገባን አንድ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ሁላችን ግን ለእርሱ ባሪያ መኾናችንን ማሳየት አለብን፡፡

    ReplyDelete