Tuesday 23 May 2017

ከኢየሱስ ተኮር - ወደ “አገልጋይ[ስጦታ]” ተኮር ሩጫ (ክፍል ዘጠኝ)

Please read in PDF
3.     ከራን ተቀባይ ነው“እንደ ኢየሱስ ክርስቶስ በጎ ወታደር ሆነህ፥ አብረኸኝ መከራ ተቀበል” (2ጢሞ.2፥3)፡፡ የእውነተኛ አማኝም ሆነ አገልጋይ ዋና መገለጫው፣ ከጠላት ዘንድ የሚመጣበት ብርቱ ሰልፍና ዋና ተቃውሞ ነው፡፡ ክርስቲያንን ከዓለም ጋር የሚያስማማው ምንም የሕይወት ዘይቤ ወይም ሥርዓት የለውም፡፡ ጌታ ራሱም፣ “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ” (ዮሐ.16፥32) በማለት መከራው የማይቀርና ነገር ግን አሸናፊው ቀድሞ መከራውን ስላሸነፈው ፍርሃት እንደማይገባ አስረግጦ ነግሮናል፡፡ ዓለም ስለእኛ የምትመሰክረው “በጎ ነገር” ካላት፣ ክርስትናችንን ቆም ብለን መፈተሽ ይገባናል፡፡
    ቅዱስ ጢሞቴዎስ በኋለኛው ዘመኑ በመከራው ጽናትና እየሆነ ባለው ነገር ፈጽሞ በፍርሃት ተውጦ ነበር፡፡ ስለዚህም ከመከራው ጽናት የተነሣ መንፈሳዊ ድፍረትን አጥቶ ነበር፤ (2ጢሞ.1፥7)፡፡  በመፍራትም ወደኋላ እንዳይል አበክሮ ቅዱስ ጳውሎስ ያበረታታዋል፡፡ እምነታችንም፤ አገልግሎታችንም በክርስቶስ ጸጋ ላይ የተመሠረተ ነው፤ ደግሞም ይህን ብርቱ ሥራ መከራ በመቀበል ልናምነውና ልናገለግለው ይገባናል፡፡ ውጊያችንም ሁሉ ታላቅ ወታደራዊ ጽናትን በሚጠይቅ ማንነት ውስጥ ማለፍ ይገባናል፡፡

   መከራን እንድንቀበልም ጥሪ ተደርጎልናል፤ (1፥8 ፤ 2፥9) ወታደሮች በሥልጠናው ወቅት እንኳ በብዙ ስቃይና መከራ ውስጥ ያልፋሉ፡፡ በጦርነት ሜዳም ብርቱ ትጋትና ጥብቅ ሥርዓትንና መመሪያዎችን መከተል ይገባናል፡፡ እንደሯጭ መሥዋዕትነትን መክፈል፤ እንደገበሬም ለረጅም ሰዓት አገልግሎት መስጠትንና አለመታከትን ማሳየት አለብን፡፡ ስለዚህ ወታደር ራሱን ለመከራ እንዲያዘጋጅ እንዲሁ፣ በክርስቶስ ጌታችን የሚያምኑ ሁሉ ለዚህ ነገር ራሳቸውን ዘወትር ሊያዘጋጁ ይገባቸዋል፡፡
    ለኢየሱስ ያልሆኑ የራስ ደቀ መዛሙርትን ለማፍራት፣ የመስቀሉ ኢየሱስን አለመስበክና መከራን ከእግዚአብሔር ጋር እንዳለመስማማት መቁጠር የዚህ ዘመን ጤናማ ያልሆነው አደገኛው ስብከት ነው፡፡ ጥረትን ሁሉ ከራስ ስኬትና ምንጭነት ጋር ማቆራኘት በክርስቶስ የተሰጠንን ድል መናቅ ነው፡፡ እውነተኛ አማኝ አሸናፊ የሆነው ከራሱ ብቃት አይደለም፤ በመስቀል ላይ በሥጋ የሞተውና ሞትንና መቃብርን ድል በነሣው ጌታ ተረጋግጦለታል፡፡
   ሁላችን አማኞች አሸናፊዎች የሆንነው ከራሱ ከክርስቶስ ጌታችን ታማኝነት የተነሳ ብቻ ነው፡፡ እርሱ ክርስቶስ ጌታችን፣ ኃይለኛውን ሞትና ዲያብሎስን በማሰር ምርኮን በዝብዟል (ማቴ.12፥29)፣ ጠላታችንም ላይጎዳን ኃይሉን አጥቷል (ሉቃ.10፥18)፣ ተሸንፎ ወደውጭ ተጥሎሏል (ዮሐ.12፥31)፣ ክርስቶስ አማኞች ሁሉ  ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሰይጣንም ሥልጣን ወደ እግዚአብሔር ዘወር እንዲሉ ዓይናቸውን ከፍቷል (ሐዋ.26፥18)፣ ደግሞም … በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደምስሷል፤ እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል፤ አለቅነትንና ሥልጣናትን ገፏል፥ ድል በመንሣት በእርሱ እያዞራቸው በግልጥ አሳይቷል” (ቈላ.2፥14-15)፡፡
     በየትኛውም ጽኑና ከባድ መከራ ውስጥ ብናልፍ እንኳ የምንዋጋው ከተሸነፈ ጠላት ጋር ነው፡፡ ጠላታችንን እኛ እንዳላሸነፍነው መዘንጋት የለብንም፡፡ ያሸነፈው ጌታችን ኢየሱስ ነው፡፡ እኛም ከእርሱ ጋር መከራውን በመካፈል ድል ነሺዎች፤ አሸናፊዎች ነን፡፡ ከእርሱ ጋር በስሙ መከራውን አብረው እየተካፈልን ይሆን? አገልጋይ ስለመደገፍና ስላለመደገፍ እየተነቀፋችሁና መከራ እያገኛችሁ ነው ወይም በጌታችን ኢየሱስ ስምና ስለእርሱ ባላችሁ ፍቅርና ምስክርነት መከራን እየተቀበላችሁ ይሆን?
    ባርያውን በማድነቅና ጸጋውን ብቻ በማየት ልባችሁን በማዘንበል በሕይወታችሁ ሙሉ እዳትከስሩና ደመወዛችሁን እንዳታጡ ተጠንቀቁ! መከራውን ለመቀበልና ከእርሱ ጋር ለመቆጠር ክርስቲያን ወታደርነትን እንድትወዱ እማልዳችኋለሁ!
4.    ውነተኛ ወታደር ጌታችን ኢየሱስን ከፍ ያደርገዋል፦ “በወንጌል እንደምሰብከው፥ ከሙታን የተነሣውን፥ ከዳዊት ዘርም የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስብ” (2ጢሞ.2፥8)፡፡ የወታደር ትልቅ ሕልሙ የበላይ አለቃውን ወይም አገሩን ወይም ባንዲራውን ከፍ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህም መከፈል ያለበትን ማናቸውንም መሥዋዕትነት መክፈል ካለበት እንኳ ከማድረግ ወደኋላ ፈጽሞ አይመለስም፡፡ ጢሞቴዎስ ይህን ዋጋ ከመክፈል ችላ ብሎ ነበር፤ (1ጢሞ.4፥14)፡፡
     ወታደር በየትኛውም ተልእኮው ውስጥ የአዝማቹን ትእዛዝ ሳይረሳ በታማኝነት ስሙን ከፍ በማድረግ እንዲተጋ፣ እንዲሁ እውነተኛ አማኝም ሆነ አገልጋይ የክርስቶስን ትእዛዝና የተናገረውን ቃሉን ቸል ባለማለት ክርስቶስን ከፍ በማድረግ በዘመኑ ላይ ክርስቶስን ይሾማል፡፡ ወታደር በማናቸውም መከራ ውስጥ ቢሆን እንኳ፣ የአዝማቹን ትእዛዝና ስም ባስታወሰ ጊዜ እንዲበረታ፣ ከፍ ለማድረግም እንዲጥር፣ እንዲሁ እውነተኛ ክርስቲያንም በታላቅ መከራ ውስጥ ቢሆን እንኳ የክርስቶስ ስምና ቃሎቹ ሁሉ መጽናኛውና ሁሉን ድል መንሻ ብርታቱ ነው፡፡
   ዘመናችንን ሁሉ መኖር ቢገባን የምንኖረው፣ ክርስቶስንና ስሙን ከፍ ለማድረግ ነው፡፡ ስሙ፣ “ንስሐና የኃጢአት ስርየት ከኢየሩሳሌም ጀምሮ በአሕዛብ ሁሉ መስበኪያ”(ሉቃ.24፥47) ብቻ፣ ሳይሆን ለእውነተኛ ክርስቲያን ፍጹም መታመኛና ግርማ ሞገሱም ነው፡፡
ጌታ መንፈስ ቅዱስ በነገር ሁሉ ማስተዋልን ይስጠን አሜን፡፡

ይቀጥላል …

1 comment:

  1. ለኢየሱስ ያልሆኑ የራስ ደቀ መዛሙርትን ለማፍራት፣ የመስቀሉ ኢየሱስን አለመስበክና መከራን ከእግዚአብሔር ጋር እንዳለመስማማት መቁጠር የዚህ ዘመን ጤናማ ያልሆነው አደገኛው ስብከት ነው፡፡ Geta tsega yabzalh.... amen.

    ReplyDelete