Friday 19 May 2017

ዘፈን - የወደቀው መልአክ እንጉርጉሮ (ክፍል 3)

Please read in PDF

ዘፈን ራሱ ኮሞስ ነው!

    ዘፈን የሚለውን ሃሳብ አስቀድመን ስንተረጉም፣
1.      በጥንት ግሪክ ለወይን አምላክ በሚደረግ ታላቅ ግብር ላይ ተሰልፎ መዞር፣ መፈንደቅ፣ መጨፈር፣ መጯጯኽ፣ መፈንጠዝ፣ ኢ ሥነ ምግባራዊና ገደብ የለሽ በኾነ የአልኮል መጠጥና ገደብ የለሽ በኾነ የአልኮል መጠጥና በምግባረ ብልሹነት እርካታ ለማግኘት የሚደረግ ወሲባዊ ጭፈራ( ... Drinking parties involving unrestrained indulgence in alcoholic beverages and accompanying immoral behaviour, - ‘orgy, revelling, carousing.)
2.     በአማልክት (በጣዖታት) ፊት በቡድንና በግል ሚደረግ ፈንጠዝያ፣ ዝሙትና መጠጥ ባካተተ መልኩ የሚደረግ ጭፈራ፣
3.     በቡድን በተደራጀ መልኩ በተለያየ ሁኔታ የሚደረግን አደባባያዊ ትርኢት መልክ ያለው የመንደር ክብር በዓል፣ ጭፈራ፣ ዘፈን፣ ግጥም፣ ዜማ፣ መሽከርከርን ... የሚያመለክት ትርጉም ያለው ነው፡፡”
ብለን በክፍል አንድ ላይ ማቅረባችንን መርሳት የለብንም፡፡
     እናም፣ ዘፈንን ኃጢአት ነው የምንለው “ዘፈን” የተባለውን “አንድ ቃል” አንጠልጥለን፤ እርሱኑ ደግሞ ለጥጠን አይደለም፡፡ ቀድሞ እንደተናገርነው የምንተረጉመውን ሁሉ የምንተረጉመው ለእግዚአብሔር ክብርና ለእኛ ጥቅም ነው፡፡ ከላይ በተለያየ ይዘት በትርጉም ከተጠቀሱት ውስጥ፣ ዝርዝር ሃሳብ እናውጣ ብንል፤ ዘፈን ማለት፦
1.     መንፈሳዊ አምልኮ ጋር መዛመድ የማይችል ርኩስ ጠባይን አመልካች ነው፡፡ በተለይም በጣዖታት ፊት የሚደረግ ማናቸውም የደስታ መግለጫ ሥርዓትን ማከናወን፣ “ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይሁኑልህ” (ዘጸ.20፥3) የሚለውን ሕግ ለማስቃረን አሳላጭ መንገድ ስለሆነ፣ ዘፈን አደገኛነቱ ምንም አያጠያይቅም፡፡

    “በነጋውም ማልደው ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕት ሠዉ፥ የደኅነትም መሥዋዕት አቀረቡ፤ ሕዝቡም ሊበሉና ሊጠጡ ተቀመጡ፥ ሊዘፍኑም ተነሡ፤” (ዘጸ.32፥6) በሚለው ቃል ውስጥ የተጠቀሰው የዘፋኝነት መንፈስ[1] ጥንስስ፣ ትንሽ እንቅስቃሴ ሊሆን እንደሚችል ማስተዋል አይሳነንም፡፡ ክፍሉን እንደምናነበው፣ እስራኤል አስቀድመው ዓይናቸውን ከግብጽ ካወጣቸው አምላክ ላይ በማንሳት፣ “ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሰው ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅም” በማለት በአመጽ ቃል ተናገሩ፡፡ ከሙሴ ደግሞ፣ ወደጣዖቱ ወረዱና፣ “እስራኤል ሆይ፥ እነዚህ ከግብፅ ምድር ያወጡህ አማልክትህ ናቸው” በማለት፣ ልክ እንደእግዚአብሔር በዓል ለጣዖታቱ ዘፈኑ፤ ስቀው፣ ተሳለቁ፡፡ ከዚሁ ጋር በማያያዝ ዘፋኝነት በእግዚአብሔር ያለመርካትና ያለመደሰት ስሜት እንዳለበት ማስተዋል እንችላለን፡፡
    ስለዚህም በፍጻሜ ድርጊታቸው በጣዖቱ ፊት እስከመዋረድና መፈንጠዝ ድረስ አደረሳቸው፤ ይህን እውነት ከዓይናችን መሰወሩ እጅግ አሳዛኙ ገጽታ ነው፤ ይህን እንድናስተውል ቅዱስ ጳውሎስ፣ “ሕዝብም ሊበሉ ሊጠጡም ተቀመጡ ሊዘፍኑም ተነሡ ተብሎ እንደ ተጻፈ ከእነርሱ አንዳንዶቹ እንዳደረጉት ጣዖትን የምታመልኩ አትሁኑ” በማለት ይመክረናል፤ (1ቆሮ.10፥7)፡፡
    ሰርጸ የዚህን ክፍል ትርጉም ያለምንም ማንገራገር የሚቀበል ይመስላል፡፡ እንዲያውም በአንዳንድ ጽሁፎቹ ውስጥ የዘፈን ጥንተ ሃሳቡ የጥንት ግሪክ አማልክትን የሚያገለግሉ አገልጋዮች ሃሳብ ስለመሆናቸው አይክድም፡፡
     “ዛሬ የምዕራቡን ዓለም አሸንፎ ያለው የሚዚቃ ዘዬ የተወረሰው ከጥንታውያን ግሪካውያን ነው፡፡ ግሪካውያኑ ለአፖሎ እና ለዲዮናስዮስ አምልክቶቻቸው የቀመሯቸው ሙዚቃዎች ለኋለኛው ዘመን የአውሮፓ ክላሲካል እና የሮማንቲክ ዘመን ቅማሬዎች መሠረት ኾነዋል፡፡ … በግሪክ የአምልኮ ሥርዐት ታላቅ የኾነው “ዚየስ” ለነበሩት ዘጠኝ ውብ ልጃገረዶች ያወጣላቸው ስም “ሚዩዝ” ወይም “አስደሳች” የተሰኘ ነበር፡፡ በግሪካውያኑ እምነት መሠረት “ሚዩዝ” ለጥበባት ሁሉ መፈጠር ምክንያት የኾኑ የዚየስ ውብ ልጃገረዶች ናቸው፡፡ ግሪካውያኑ የቆዩ ታሪኮቻቸውን ያሰፈሩባቸው መዛግብት መሠረት አድርገው የሚነግሩን የኪነ ጥበብ ታሪክ መጻሕፍት “የሥዕል፣ የቅኔ እና የዜማ ጥበባት እናት የነበረችው ከዘጠኙ “ሚውዝ” ውብ ልጃገረዶች አንዷ በልዩ መጠሪያ ስሟ “ኢዩቴርፒ” የተሰኘችዋ ናት፡፡ …”[2]
በማለት የ“ሚዩዚክ” መነሻ ስያሜና መገኛውን አስነብቦን ነበር፡፡
    ነገር ግን ሰርጸ፣ እንዲህ ብሎ የተናገረውን ሲደግመው አላስተዋልነውም፡፡ ዘፋኝነት ከመላው የጣዖት አለም ጋር ትስስር ካለው፣ አሁን ወደቅድስና ማጠጋጋቱ ምን አዲስ ነገር መጥቶ ይሆን?
2.   ሞስ መዘዘ ብዙ ነው!
   ብዙ ጊዜ የኃጢአትን ደስታ እንጂ የሚያመጣውን መዘዝና ኃላፊነቱን መቀበል አንፈልግም፡፡  ነገር ግን ለምናደርገው ለማናቸውም ነገራችን ኃላፊነቱን መውሰድ እንድንችል በሚያስችል “ልዩ የፍጥረት ችሎታ” ጌታ እግዚአብሔር ነጻ ፈቃድ፣ ዕውቀትና ስሜትን ሰጥቶናል፡፡ ከዚህ ተነስተን ብንመዝን ኮሞሳዊው ዘፈን መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ጥቂቱን ብናነሳ፦
2.1. ጣዖት “ያዘይራል”፦ በአጭር ቃል የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር ለተማሩትና በእጆቻቸው ለሠሩት ጣዖት ዘፍነዋል፤ ዘይረዋል፡፡ ሙሴ ያየውን ነገር መጽሐፍ ሲነግረን፣ “እንዲህም ሆነ፤ ወደ ሰፈሩ ሲቀርብ ጥጃውንም ዘፈኑንም አየ፤ የሙሴም ቍጣ ተቃጠለ፥” ይለናል፤ (ዘጸ.32፥19)፡፡ ነቢዩ ሙሴ ሕዝቡ ለጣዖቱ መዝፈኑንና ፍጹም መርከሱን አስተውሏል፡፡
    ይህንን በሚገባ ለማስተዋል የአገራችንን ቤተ ጣዖታትና ቃልቻ ቤት፤ ጠንቋይ ቤቶችን ማስተዋል በቂ ነው፡፡ በዚያ የርኩሰት ቦታ ሌሊቱን ከሚያረዝሙት ነገሮች አንዱ በዘፈን የሚካሄደው ዝየራ አንዱ ነው፡፡ ከዚያም ባለፈ የሰው[በተለይና በብዛት የሴቶችን] መልክ፣ ቅርጽ፣ ቁመና፣ ከሚመለክባቸው፣ ከሚወደስባቸው፣ ጾታዊ ፍቅር ደግሞ “አለልክ” ከፍ ከፍ ከሚደረግባቸው አንዱና ዋና ዘፈን ነው፡፡
  ይህም ብቻ ሳይሆን፣ ሰርጸ በሌላ እይታ ለዘፈኑ የሚሆኑ መሣርያዎችም ጭምር ከጣዖታቱ አማልክት እንደተሰጡ ስለበገና በጻፈበት አንድ አንቀጽ፣
   “እንደቀደምቶቹ ግሪካውያን አገላለጥ “ድራማንና ሙዚቃን አስተማሩን” ከሚሏቸው ከአፖሎና ከዲዮናስስ አማልክቶቻቸው “ተሰጡን” የሚሏቸው “ሊና” እና “ኪትሃራ” የተሰኙ የሚዚቃ መሣርያዎች ነው፡፡ እነዚህ የሙዚቃ መሣርያዎች ከበገና ወይም ከሐርፕ ሊቀድሙም፤ እኩያ እድሜ ሊኖራቸውም ይችላል፡፡ “ሊር” እና “ኪትሃራ” የአማልክት ውዳሴ የሚቀርብባቸው መሣርያዎች ብቻ አይደሉም፡፡ “ዓለማዊ” ለምንላቸው ጨዋታዎች ሁሉ ውለው የነበሩ በመሆናቸው በገና ወይም ሐርፕ ከተገለጹበት ባሕርይ ይለያሉ፡፡ …”[3]
በማለት የመሣርያውን የትመጣም ይነግረናል፡፡[4]
     መጽሐፍ ቅዱስ ለዘመናት በመናፍቃንና እርሱኑ ጨብጠው “እናምንበታለን” በሚሉ “ወገኖቹ” ሳይቀር፣ ትችትም ኾነ ነቀፌታንና ስድብን ሲያስተናግድ የኖረ መጽሐፍ ነው፡፡ ነገር ግን የተቹትንና የነቀፉትን ሁሉ በማይዝልና በማያረጅ ሕያው አምላካዊ ሥልጣኑ እየሻረና እያስረሳ ዘመናትን አልፎ አኹንም አለ፡፡ እግዚአብሔር ተናግሮታልና ለወደፊትም ሕያውና የሚኖርም ነው፡፡ አንድ ነገር በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ፤ ሰርጸ፣ ስለሙዚቃ አማልክት ሲተርክ “አድማጮቹን እስከማስጨብጨብ አፍ አስከፍቶ” መተረክ ይችልበታል፡፡ እንዲህ ያለው ሰው ግን ስለመጽሐፍ ቅዱስ ልምሾ ሆኖ ሲናገር ምንም አይደንቅም፡፡ ሰው በልቡ የመላውን እርሱን በአፉ ይናገረዋልና፡፡ አዎን! ስለአማልክት ብዙ በመናገር የሚውሉ ትክክለኛውን የክርስቶስን የጸጋና የማዳን ወንጌል እንዳይመሰክሩ እናምናለን፡፡ ጉዳዩ ተራ ልዩነት ሳይሆን፣ የሁለት መንግሥታት ጉዳይ ነውና፤ የእግዚአብሔርና የሰይጣን፡፡
    ሰርጸ፣ በዚሁ አንቀጽ በውስጥ ሃሳቡ ላይ አንድ መደምደሚያ መሥራት ይፈልጋል፡፡ “መንፈሳዊ ነገሮች ሁል ጊዜ ከቤተ ክርስቲያን ወደሕዝብ ብቻ ሳይሆን ከሕዝብ እና ከነገሥታቱ ወደቤተ ክርስቲያን በሥጦታነት እንደሚበረከቱ፤ ቤተ ክርስቲያንም አክብራ እንደምትቀበል የሚያሳይ አንድ የእውነት አስረጅ ነው፤” በማለትም በተጨማሪ ያትታል፡፡ በእርግጥ ይህን ሃሳብ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት በጥናት መልክ አንስቶ ብዙ እንዳከራከረ ራሱም በዚሁ ጽሁፍ ውስጥ ገልጧል፡፡
   ሰርጸ፣ የ“ዘፈን” ምንጩ የግሪክ አማልክት “ምሥጋና” እንደሆነና “የዘፈኑንም” መሣርያ “ሰጪዎቹ” አማልክቱ እንዲሆኑ ከመናገር አልፎ፤ ቤተ ክርስቲያን ሁል ጊዜ ለሕዝብ መስጠት ብቻ ሳይሆን ከሕዝብና ከነገሥታት የሚሰጧትን “በረከቶች” መቀበል እንዳለበት አስፍሯል፡፡ በዚህ ጭምቀ ሃሳብ ውስጥ ብዙ የተቀመሙ ስንግ መርዞች ይታዩኛል፡፤ ጥቂቱን ብናነሳ፦
§  የመጀመርያው “ዘፈንና መሣርያው” ከአማልክት ከተቀዳ፤ ዘፈንን ለመቀደስ መጽሐፍ ቅዱስን መታከክ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ሃሳብና የእግዚአብሔር ቅዱስ ዓላማ መጠምዘዝ ለምን አስፈለገ?
    “ዘፈን” ከርኩሳን አማልክት የተቀዳ መሆኑን እየታመነ ለምንድር ነው የዘፋን ዝሙታዊ ዓውድ ብቻ ትኩረት የሚሰጠው? እውነት ለመናገር ዘፈን ከዝሙታዊ ዓውድ ጋር ብቻ የሚያያዝ ከሆነ፣ ምሳሌነቱን ለምን ወደዳቪንቺ ኮድ አይነት ምሳሌ ማራቅ አስፈለገ? የአገራችን ዘፋኞችም ይሁኑ ከዚሁ ጋር በተያያዥነት የሚነሱት አካላት ከዳቪንቺ ኮድ ላለመተካከላቸው ወይም ላለመብለጣቸው ምን ማስረጃ አለን? እውነት ለመናገር የዘፈን ምንጩ አማልክት ከሆኑ ለምን በዝሙታዊ ድርጊቱ ብቻ ኃጢአትነቱ ይኮነናል? ሃሳቡስ ጤናማና ከቅድስና ምንጭነት የመጣ መች ሆነና?
§  ቤተ ክርስቲያን በደሙ በዋጃት በእግዚአብሔር የተጠራች ናት፤ (ሐዋ.20፥28)፡፡ መንፈሳዊ አምልኮን ሁሉ መቀበልና መስጠት ያለባት ከክርስቶስና ከክርስቶስ ብቻ ነው፡፡ ከእርሱ ያልተቀበለችውን ለእርሱ አትሰጥም፡፡ ከዓለማውያንና ከአሕዛብ የተለማመደችውን ደግሞ ለእግዚአብሔር ፈጽሞ ማቅረብ አትችልም፤ እንኳን በአዲስ ኪዳን በዚያኛው በአሮጌው ብሉይ ኪዳን እንኳ ለመሥዋዕት የሚሆነው እሳት የሚጫረው ከመሠዊያው እንጂ ከመንደር አልነበረም፤ ይህን ብርቱ ቃል የተላለፉት ቆሬ፣ ዳታንና አቤሮን ግን ምድር ተከፍታ ከነሕይወታቸው እንደዋጠቻቸው አስተውሉ! ቤተ ክርስቲያን ጋብቻዋ ከክርስቶስ ጋር ብቻ እንጂ ከሌላ ከማንም ጋር አይደለም፤ ከዚህ ውጪ ብታደርግ በክርስቶስ ላይ ታመነዝራች፡፡
    ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ለዓለሙ ሁሉ የምታበረክተው ሥጦታ ጌታ ኢየሱስ፣ “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ28፥19-20) ከሚለው አምላካዊ ምንጭ እንጂ ከራስዋ አቅንታና አፍልቃ አይደለም፡፡
§  ሌላው፣ በሰርጸ አተያይ ቤተ ክርስቲያን ማለትና ሕዝብ ማለት የተለያዩ ናቸው፤ ይህ ደግሞ በክርስቶስ ካመኑ ነፍሳት ቤተ ክርስቲያንነት ይልቅ የሕንጻውን ቤተ ክርስቲያንነት ያጸደቀ ይመስላል፡፡ ደግሜ እላለሁ፤ ቤተ ክርስቲያን ማለት ክርስቶስን በቃልና በሕይወታቸው አምነው የሚከተሉ ሁሉ ከሆኑ ቤተ ክርስቲያን የምትቀበለውና የምትሰጠው ሁሉ ከክርስቶስ እጅ የተቀበለችውን ብቻ ነው፡፡ እናም ቤተ ክርስቲያን አምልኮን በተመለከተ በማናቸውም መልኩ ከሦስተኛ ወገን ጋር ተሻርካ ለክርስቶስ የምታቀርበው ምንም ነገር የላትም፡፡ ዝማሬ ደግሞ ዘወትር ከአምልኮ ጋር የተዛመደ ነውና፡፡
     በእርግጥ፣ ሰርጸ አንዳንድ መንፈሳዊ “ነገሮችን” ባለማወቅም ይሁን በማወቅ መደባለቅ[ፈጽሞ የማይቻል ነገር ቢሆንም!] የሚፈልግበት ሁኔታ ወይም እንዲደባለቅ የሚሻበት ሁኔታ ወይም ከሆነ ነገር ተነስቶ ወደተሳሳተ መደምደሚያ ላይ መድረስን ይወዳል፡፡ እንዲያውም ሁለቱ ወይም ሦስቱ ጥቅሶች ላይ ብቻ[ሮሜ.13፥13 ፤ ገላ.5፥21 እና 1ጴጥ.4፥3] መንጠላጠሉና ለራሱ እንዲመች አድርጎ መተርጎሙ፣ ሌሎቹ ስለዘፈን የሚያወሱ ጥቅሶች እንደሚያፈርሱበት በግልጥ ስለተረዳ ይመስለኛል፡፡ በአንድ ሥፍራ “ዘፈንና መዝሙር ድንበር ያለው ይመስለኛል … አልያ ይደበላለቃል” ይልና፣ መልሶ ደግሞ የአማርኛ መተርጉማን “ኦርጂ ለሚለው ቃል አቻ ፍቺ ስላጡ ዘፈን አሉት” በማለት ሽምጥጥ አድርጎ ተቃራኒ ነገሮችን ያስቀምጣል፡፡
   ስለዚህም የእግዚአብሔርን የሆነውን ሁሉ ለፍጡር ማዋል፣ ያ ጣዖት አምልኮ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ እግዚአብሔርን በሙሉ ነፍሳችን፣ ኃይላችን፣ ስሜታችና መንፈሳችን በዜማ፣ በቅኔ፣ በዝማሬ፣ በሽብሸባ፣ በመንጓደድ፣ ከፍ ባለ ድምጽ ልናመልክ ተጠርተን ሳለን፣ ይህንን ወስደን በማናቸውም መንገድ ለፍጡር ማዋል እርሱ ርኩስ ነገር ነው፡፡  እንዲያውም እግዚአብሔርን ከሚያጋርድ ማናቸውም ጣዖት አጥብቀን ልንርቅ ይገባናል፡፡
 2.2.  ፈን የዝሙት መዳረሻ ድልድይ ነው፦ የ“ኢትዮጲያ” ዘፈኖች ሁሉም ሊያስብል በሚያስደፍር ቁጥር ተቀራኒ ጾታዊ ግንኙነትን አቀንቃኝ ዘፈኖች ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ በደፈናው ለመሸሽ ካልሆነ በቀር፣ ቀጥተኛ ግንኙነታቸው ከዝሙት ጋር ብቻ እንጂ ከሌላ ከምንም ጋር ሊሆን አይችልም፡፡  ሰርጸ እኒህን እውነታዎች በመሸሽና ሌላውን ለማጉላትና “ኦርጂን ብቻ” ዘፈን ለማለት፣ በዳቪንቺ ኮድና በሌሎች ሥፍራዎች የተጠቀሱትን ዓይነተኛ የዝሙትና የጣዖት ምሳሌዎችን ይጠቅሳል፡፡ ሰርጸ፣ በልቦለድ ውስጥ ያለ ምሳሌን ከመጥቀስ፣ የእኛን እውነተኛ ክፋታችንን ሊያነሳ የማያስችል ምን ምክንያት አለው? ለምሳሌ፦ “ሮዝ መጽሔት በቅጽ.4 ቁ.67 እና 68 ሰኔና ሐምሌ 2002 ዓ.ም ከገጽ 6-8  እትሙ “ ድብቆቹ የሸገር ጓዳዎች - ራቁት ዳንስ ቤቶች - የአደባባይ የወሲብ ገበያዎች” በሚል ርዕስ ዘፈንና ወሲብ፣ ዘፈንና ስካር፣ ዘፈንና መዳራት፣ ዘፈንና ርኩሰት፣ … እዚሁ አገራችን ላይ የደራና የአደባባይ እውነት መሆኑን አስቃኝቶናል፡፡ ሰርጸ ግን ይህን ምንም ሊለን አልፈለገም? አኹን ያለውም የዘፈንና የዝሙት ነገር የከፋ እንጂ የተሻለ እንደማይሆን ገምታለሁ፡፡
    ምናልባት ሰርጸ፣ ይህና መናገር አልደፈረ ይሆን? ለመሆኑ “የኢትዮጲያ”[እኔም ኢትዮጲያዊ ነኝ፤ ነገር ግን የቱም ዘፋኝ እኔን መወከል አይችልም፤ እንዲወክለኝም አልፈልግም] ዘፋኞች የበዛ አዳራቸው የት ነው? ከጭፈራና ከመዳራት ቤት ርቀው በስብሐተ እግዚአብሔርና በአርምሞ የሚያሳልፉ ናቸውን? ስንት ወጣት የሚረክሰውና ስንት ትዳር የሚፈርሰው፣ ስንት ተማሪ ከሁለተኛ ደረጃና ዩንቨርሲቲ ጠፍቶ የሚያነጋው ድሪያና ጭፈራን ሥራ ካደረጉ ዘፋኝና አዝማሪዎች ጋር አይደለምን? በአዲስ አበባው “ውቤ በረሃ” ምን ነበር ሲደረግ የተኖረው? …” ብዬ መጠየቅን ፈልጋለሁ፡፡
    ነገር ግን ሰርጸ ይህን ሁሉ በመተው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዘፈን የተናገረበትን ዓውድ ወደራሱ ሃሳብ በመጠምዘዝና መጽሐፉ ዘፈን የሚለው “ዳቪንቺ ኮድ” ላይ እንዳለው ድርጊት ሲፈጸም “ብቻ ነው” ብሎ፣ ነገር ግን ዝሙትን ማዕከል ካላደረገ ዘፈን ሊባል እንደማይገባ አፉን ሞልቶ ሲናገር ሰምተነዋል፡፡ በደፈናው ይህን ይበል እንጂ ትክክለኛ ማስረጃን ሲጠቅስ ግን አላየነውም፡፡
2.2. ንገትን ያስቀላል፦ ራስን መግዛትም ከመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች አንዱ ሆኖም ተጠቅሷልና፣ ክርስቲያ ራሱን በመግዛት ይታወቃል፤ (1ቆሮ.9፥25 ፤ ገላ.5፥23)፡፡ ዘፈን ራስን ወዳለመግዛት ይመራል፡፡ ዘፈን አቅልን ከሚያስቱና ኅሊናን ከሚያሳውሩ ነገሮች መካከል ግንባር ቀደሙ ነው፤ ለዚህ ደግሞ ዋና ማሳያችን በልደት ቀኑ “ስለተዘፈነለት” ሄሮድስ ማንሳት ብቻ በቂ ነው፤ በልደት ቀኑ ሄሮድያዳ በምቹ ሁኔታ በተቀነባበረ ሴራ[ዮሐንስ መጥምቅን ለማስገደል በተጠነሰሰ ሴራ] መጥታ፣ “በመካከላቸው ዘፈነች ሄሮድስንም ደስ አሰኘችው፤ ስለዚህም የምትለምነውን ሁሉ እንዲሰጣት በመሐላ ተስፋ አደረገላት፡፡ እርስዋም በእናትዋ ተመክራ፦ የመጥምቁን የዮሐንስን ራስ በዚህ በወጭት ስጠኝ አለችው፡፡ ንጉሡም አዘነ፥ ነገር ግን ስለ መሐላው ከእርሱም ጋር ተቀምጠው ስላሉት ሰዎች እንዲሰጡአት አዘዘ፤ ልኮም የዮሐንስን ራስ በወህኒ አስቆረጠው፣” (ማቴ.14፥6-10)፡፡
   ሄሮድስ አንዲት ሴት በፊቱ መጥታ በዘፈን ደስ ስላሰኘችው ያደረገውን አስተውሉ! የጻድቁን አንገት አስቆረጠው፤ ነፍስንም አጠፋ፡፡ እነሰርጸ እንዲህ ያለውን ነገር መጥቀስ የማይሆንላቸው ለምን ይሆን? ልክ እንደሄሮድስ በባለፉት ዘመናት ታሪክ ውስጥ፣ ስንቶች ዘፋኞች የስንቱን ባለጠጋና ባለሥልጣን ልብና ዓይን በማሳወር አስነዋሪ ነገር እንዳደረጉ ታሪክ በፊታችን  ታማኝ ምስክር ነው፡፡ በዩጋንዳው የሑቱ ቱትሲው [5]አሰቃቂ እልቂት ውስጥ፣ እልቂቱ እንዲጧጧፍ የተሳተፍ ዘፋኝ በአለም አቀፉ ጦር ወንጀለኛ ፍርድ ቤት መቅረቡ ከዓይናችን ሥር ያልተሰወረ እውነት፡፡ በአራችንስ ቢሆን “የጎበዝ እናት ታስታውቃለች፣ አፋፍ ላይ ቆማ በለው ትላለች” የሚለው “ስሜት ቀስቃሽ ዜማ” ከአስታራቂነት ወይም ከአቀራራቢነት ልንመድበው እንችል ይሆን? [ይህ ከዘፈን ሊቆጠር አይችልም ካልተባለ በቀር፡፡]
   በግልጥ ቃል ዘፈን ከመልካሙ ሥነ ምግባር እንድናፈነግጥ ጭምር ያደርገናልም፤ የተጠራነው በክርስቶስ ለክርስቶስ እንድንኖር ነው፤ ትላንት የነበርንበትን ዛሬ አይደለንም፤ ትላንት እንደሄሮድ ዘፋኞችና ዘፈንን የምንወድ የነበርን ብንሆን እንኳ፣ ዛሬ ግን ያንን ፈጽሞ አይደለንም፡፡ በአዲስ ልደት ለክርስቶስ ተወልደናል፡፡ ለእርሱም ሕያዋን ሆነን በጽድቅ እንኖራለን፡፡ ትላንት ኃጢአተኞች ነበርን፤ ዛሬ ግን ከክርስቶስ ደም፣ ከሞቱና ከትንሣኤው የተነሣ ተቀድሰናል፣ ጸድቀናል፣ ድነናልም፡፡ ይህንን እውነት ሊቀ ጉባኤ፦
“ክርስቲያን መሆን ማለት ከልዩ ከልዩ ዓለማዊና ሥጋዊ ነገሮች ተለይቶ በአንድ ልብ ተወስኖ ራስን ለክርስቶስ ብቻ አስገዝቶ በእርሱ ቅዱስ መንፈስ ተመርቶ ለቃሉ እየታዘዙ በመኖር በስሙ መከራውን በመታገሥ እስከመጨረሻው በታማኝነት መጽናት ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ነው ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና ምግባራችን በሌላ እንግዳ ሕግና መመሪያ ሳይን በራሱ በክርስቶስና በክርስቶስ ቅዱስ መንፈስ መሆን እንዳለበት የምንመሰክረው፡፡ እኛ ክርስቲያን መስለን በመታየት ሳይሆን ሆነን በመገኘትና መሆናችንንም በመንፈሳዊ ተጋድሎ በተግባር ስንገልጸው ነው፡፡ እንግዲህ ክርስቲያን መሆን ወይም አለመሆን እዚህ ላይ ነው ጥያቄው፡፡”[6]
በማለት በግልጥ ቃል ያስቀመጡት፡፡ አዎን! በክርስቶስ ያገኘነው ጽድቅ በኃጢአት እንድንኖር ፈጽሞ ነጻነትን አይሰጠንም፡፡ ስለዚህም በእርሱ እርሱን ብቻ ደስ ማሰኘት ይገባናል፡፡
2.3.                      ንግሥተ ሰማያትን አያስወርስም፦ ዘፋኝነትና ዘፈን ራስን፣ ሌላውን ሰውና ሰይጣንን ደስ የማሰኘት ሥራ ነው፡፡ እኛ ደግሞ የተጠራነውና የምንኖረው፣ ዘፋኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፡፡ ይህን የምንለው ቃለ እግዚአብሔርን ዋቢያችንና መሠረታችን አድርገን ነው፡፡ “የሥጋ ሥራም የተገለጠ ነው እርሱም ... ስካር፥ ዘፋኝነት፥ ይህንም የሚመስል ነው፡፡ አስቀድሜም እንዳልሁ፥ እንደዚህ ያሉትን የሚያደርጉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም፡፡” (ገላ.5፥19-21)፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ በተመሳሳይ የእግዚአብሔርን መንግሥት የማይወርሱትን ሌሎች ኃጢአተኞችንም ይገልጣል፤ (1ቆሮ.6፥9)፡፡
   ዘፈን ከሥጋ ፍሬዎች ውስጥ በዝርዝር የቀረበ ዋና ኃጢአት ነው፤ ስለዚህም ከመንፈስ ፍሬ በተቃራኒ የቆመ ነው ማለት ነው፡፡ ደግሜ እላለሁ፤ ዘፋኝነትና ዘፈን የሰይጣን መንግሥት ፍሬና መገለጫ ነው፤ ምክንያቱም በእግዚአብሔር መንግሥት ሊኖሩ ከሚገባቸው ከመንፈስ ፍሬዎች ውስጥ ፈጽሞ አልጠቀሰምና፡፡ ስለዚህ የሥጋ ፍሬን የሚያፈሩ ሁሉ፣ ከእግአብሔር መንግሥት በአፍአ ናቸው፡፡ የእግዚአብሔርን መንግሥት ፈጽሞ ሊያዩዋት አይቻላቸውም፡፡ በእርግጥም፣ በአልኮልና በፈንጠዝያ የሚያብዱና “አሸሼ ገዳሜ” የሚሉ፣ በሥጋዊ ተድላ ተቀማጥለው በዘፈን በክርስቶስ ላይ የሚቀማጠሉ፣ በዕጽና በዝሙት ታውረው “በመዳራት ሸጎዬ[7] የሚያስነኩቱ” እንደምን ሆነው ይሆን በክርስቶስ ቅድስና የምትወረሰውን የእግዚአብሔርን መንግሥት የሚያስቧት፡፡  
ጌታ መንፈስ ቅዱስ ሆይ ማስተዋልህን ለሕዝብህ አብዛ፤ አሜን፡፡
ይቀጥላል…




    [1] በዚህ ቦታ የተጠቀሰው ዘፈን ጻኻቅ ሳቅ፣ ስላቅ፣ ጨዋታ፣ ተብሎ ተጠቅሷል፡፡ እጅግ ፈንጠዚያ ቅጥ ያጣ ጩኸት መሆኑን “ኢያሱም እልል ሲሉ የሕዝቡን ድምፅ ሰምቶ ሙሴን፦ የሰልፍ ድምፅ በሰፈሩ ውስጥ አለ አለው፡፡ እርሱም፦ ይህ የድል ነሺዎች ወይም የድል ተነሺዎች ድምፅ አይደለም፥ ነገር ግን የዘፈን ድምፅ እሰማለሁ አለው፡፡ እንዲህም ሆነ፤ ወደ ሰፈሩ ሲቀርብ ጥጃውንም ዘፈኑንም አየ፤” (ዘጸ.32፥17-19) በሚለው ቃል በግልጥ ታውቋል፡፡ ይህ ድርጊት ዮሴፍ ከቀረበበት ክስና ሶምሶን “ልባቸውንም ደስ ባለው ጊዜ፦ በፊታችን እንዲጫወት ሶምሶንን ጥሩት አሉ” (መሳ.16፥25) ከሚለው ሃሳብ ጋር የሚዛመድና የሚመሳሰል ነው፡፡
[2]  አዲስ ነገር 2ኛ ዓመት ቁ.102 መስከረም 2002 ገጽ.6
[3] አዲስ ነገር 2ኛ ዓመት ቁ.075 መጋቢት 2001 ገጽ.4
    [4] ሰርጸ ለዚህ መከራከሪያው ከግሪካውያኑ አማልክት ትርክት በዘለለ ምን ማስረጃ እንዳለው አያቀርብም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከመጀመርያውም በገናንና ሌሎችንም የዜማ መሣርያዎች ከግሪክ የ“ጥበብና የአማልክት ትርክት” በፊት መጠቀሱና ለእግዚአብሔር ቅዱስ አምልኮ ይቀርብ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ዋና ምስክራችን ነው፡፡ “ዩባል በገናንና መለከትን ለሚይዙ አባት ነበረ” (ዘፍጥ.4፥21)፡፡ ይህ ቃል የተነገረውና የነበረው የግሪክ ሥልጣኔ ገና በምድሪቱ ላይ ሳይገን ነው፡፡ በተጨማሪም ላባ፣ ያዕቆብ ተሰውሮ ከእርሱ ዘንድ በሄደ ጊዜ፣ “ስለምን በስውር ሸሸህ? ከእኔም ከድተህ ስለምን ኮበለልህ? በደስታና በዘፈን በከበሮና በበገና እንድሰድድህ ለምን አልነገርኸኝም?” (ዘፍ.31፥27) በማለት በዚያ ዘመን በገና ለደስታና ለስንብት ጨዋታ መዝፈኛ እንደነበር ይነግረናል፡፡ እንዲህ እያልን ብዙ ማስረጃዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ መጥቀስ እንችላለን፡፡ ሰርጸ ግን እኒህን ሁሉ ማስረጃዎች “ክዶ”[ላለማንሳት ከልብ ፈልጎ]  የአማልክቱን ትርክት በማግነን ተጠምዷል፡፡
  በእርግጥ በእውነትና በፍቅር ክርስቶስንና የጸጋውን ወንጌል በትክክል ለማያምን ሰው ከክርስቶስ ያነሰ ነገር ቢመርጥና የአማልክትን ተረት አጥብቆ ቢሰብክ የሚደነቅ ነገር አይደለም፡፡ መጽሐፍ፣ “መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ፥ እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥ ለተጠሩት ግን፥ አይሁድ ቢሆኑ የግሪክ ሰዎችም ቢሆኑ፥ የእግዚአብሔር ኃይልና የእግዚአብሔር ጥበብ የሆነው ክርስቶስ ነው፤” (1ቆሮ.1፥22-24) የሚለው ቃል የሚገባቸው ዳግም ለተወለዱና በክርስቶስ ኢየሱስ ለሚያምኑ ብቻ ነው፡፡
   [5] በዚህ እልቂት አንድ ወር ባልሞላ ጊዜያት ውስጥ ወደአንድ ሚሊየን ገደማ ሰዎች በገጀራ፣ በመጥረቢያ፣ በፋስ፣ በሳንጃ … በአደባባይ ተራርደው በአሰቃቂ ሁኔታ ሕይወታቸው አልፏል፡፡
[6] አበራ በቀለ(ሊቀ ጉባኤ አባ)፡፡ ትምህርተ ሃይማኖት እና ክርስቲያናዊ ህይወት፡፡ 1996 ዓ.ም፤   አዲስ አበባ፡፡ ንግድ ማተሚያ ድርጅት(ማህበረ ቅዱሳን)፡፡ ገጽ.276
     [7] ሸጎዬ በሐረርጌ ኦሮሞ አከባቢ የታወቀ ጭፈራ ነው፤ በአብዛኛው ዘንጋዳ ሲደርስና በሠርግ ወራት የሚደረግ ጭፈራ ሲሆን፣ በተለይም ሌሊቱን ሙሉ የሚጨፈር ሲሆን ከጭፈራው መልስ ጥቂት የማይባሉ ሴቶችና ወንዶች ያመነዝራሉ፤ ልቅ ወሲብን ይፈጽማሉ፡፡ በዚህ ወራት በብዛት “የአስገድዶ መድፈር ክሶችም” ይበዛሉ፡፡[የዚህ ጽሁፍ ጸሐፊ ይህን እውነት ቦታው ድረስ በማየት የዓይን ምስክር ነው]፡፡

4 comments:

  1. amen Ewnet new

    ReplyDelete
  2. arif hasab new ... tebarek

    ReplyDelete
  3. አዎን! በክርስቶስ ያገኘነው ጽድቅ በኃጢአት እንድንኖር ፈጽሞ ነጻነትን አይሰጠንም፡፡ ስለዚህም በእርሱ እርሱን ብቻ ደስ ማሰኘት ይገባናል፡፡ amen yihun yidereeegln

    ReplyDelete
  4. በእርግጥ በእውነትና በፍቅር ክርስቶስንና የጸጋውን ወንጌል በትክክል ለማያምን ሰው ከክርስቶስ ያነሰ ነገር ቢመርጥና የአማልክትን ተረት አጥብቆ ቢሰብክ የሚደነቅ ነገር አይደለም፡፡ Yemigerm ababal new ....

    ReplyDelete